Friday, January 17, 2014

የሩዋ ፈለግ ቀበሌ ነዋሪዎች ለሁለተኛ ቀን ከፖሊሶች ጋር ተፋጠዋልጥር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ በሩሃ ቀበሌ ከመስኖ ግድብ ጋር በተያያዘ ሃሙስ እለት የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ እስከ አርብ ምሽት የቆየ ሲሆን፣ የወረዳው የአስተዳደር ሰራተኞች እና የደህንነት ሀይሎች አመጹን የቀሰቀሱት እነማን ናቸው አውጡ በማለት ከህዝቡ ጋር እየተወዛገቡ ነው። ህዝቡ በበኩሉ ጥያቄው የህዝብ እንጅ የተወሰኑ ግለሰቦች ባለመሆኑ በግፍ የታሰሩት ሰዎች ይፈቱና ለጥያቄው መንግስት አፋጣኝ ምላሽ ይስጥ በማለት መልሶ እየጠየቀ ነው።

ግጭቱ የተነሳው ለመስኖ ስራ በሚል ለተወሰደው መሬት የቀበሌው አርሶአደሮች ተገቢውን ካሳ ባለማግኘታቸው ነው። አርሶ አደሮቹ ለ ዓመታት ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም እስካሁን የረባ መልስ አለማግኘታቸውን ይገልጻሉ።

በቅርቡ ከሳውድ አረቢያ ተባረው ወደ ሀገራቸው የተመለሱና ወደ ቀበሌያቸው እንዲሄዱ የተደረጉት የአካባቢው ተወላጆች “ከአባቶቻችን ላይ ለተወሰደው መሬት ተገቢውን ካሳ ይከፈለንና ወደ ስራ እንግባ” በማለት ጥያቄ ማንሳታቸው ለአመታት ታፍኖ የቆየው ጥያቄ እንደገና እንዲነሳ አድርጎታል።

ሀሙስ ሌሊቱን ሙሉ ጥይት ሲተኮስ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎች፣ አርብ ደግሞ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የጸጥታ ሃይሎች ህዝቡን ከበው ጥያቄውን ያነሱት አሸባሪ የሆኑት የተቃዋሚ ሃይሎች ናቸው በማለት ሰላማዊውን ጥያቄ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየወሰዱት መሆኑን ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

የቀበሌ ሚሊሺያዎች ከህዝብ ጎብ በመቆማቸው ከሌሎች አካባቢዎች ታጣቂዎች እንዲመጡ መደረጉን ከስፍራው ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል።

አቶ በረከት ስምዖን አርሶአደሩ በአገዛዙ በመርካቱ ” ተኛ ብንለው ይተኛል፣ ዝም ብንለው ዝም ይላል” በማለት ተናግረዋል፣ የትግራይ አርሶ አደር ሁኔታስ ምን ይመስላል ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ አንድ የሩሃ ፈለግ ቀበሌ ነዋሪ ሲመልስ፣ በትግራይ ውስጥ ያለው የህዝብ ተቃውሞ እየተሰራጨ መምጣቱንና የአገዛዙን ፕሮፓጋንዳ መስማት ማቆሙን ገልጿል ።

No comments:

Post a Comment