Friday, January 17, 2014

ቅዱስ ጦርነት (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
teddy n jawarሰሞኑን ከያኔ (አርቲስት) ቴዎድሮስ ካሳሁን ለዕንቁ መጽሔት የሰጠውን ቃለ ምልልስ ተንተርሶ በተለይ በማኅበራዊው የብዙኃን መገናኛ ልክና ገደብ ያለፈ መራኮት ተፈጥሮ ነበር ፡፡ አጋጣሚው የሀገር ጠላቶች ኢትዮጵያን እንዳልነበረች ለማድረግ ያላቸውን ዝግጅትና አቅም ያሳየ ሆኗል ፡፡ ክርስቶስ አደቡን ማስተዋሉን ይስጥልን ከማለት ውጪ ዓላማ ብለው ለያዙት የጥፋት ልጆች ለጊዜው ምንም የምለው ነገር የለኝም ፡፡ በእነዚህ የጥፋት መልእክተኞች እየተወናበዱ ላሉ የዋሀን ዜጎች ግን በአጭሩ የምለው ነገር አለኝ ፡፡ እባካቹህን አስተውሉ ይሄንን የተሳሳተ አስተሳሰብ የፈጠረው መርዘኛው የወያኔ የዘር ፖለቲካ እንደሆነ ልብ በሉ ፡፡ በእርግጥ እውነት ነው ዐፄ ምኒልክ 2ኛ ከዐፄ ቴዎድሮስ የተረከቡትን አደራ ኢትዮጵያን እንደገና የመሰብሰብና አንድ የማድረግ ተልእኮ ለመፈጸም ሲሉ እዚህም እዛም የገደሏቸው የፈጇቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ አሉም፡፡
በእርግጠኝነት ልንናገር የምንችለው ነገር ቢኖር ዐፄ ምኒልክ የኦሮሞም ይሁን የሌላ ተወላጆችን የዚያ ብሔረሰብ አባል ስለሆኑ ብቻ አላጠፉም አልፈጁም አልገደሉም ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን ክፍለ አካላት ለመሰብሰብ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት  መንገዳቸው ላይ የቆሙ ወይም እንቅፋት የሆኑ የኢትዮጵያን መሰባሰብ አንድ መሆንና እንደገና ተጠናክሮ መውጣት የማይፈልጉ የባዕዳንና የጠላት ቅጥረኞች የሆኑ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ግን ፈጽሞ ለመመከርና ለመማር ፈቃደኞች ሆነው ባለመገኘታቸው ጨርሰዋል ፈጅተዋል ፡፡ ይሄንን ከማድረግ ውጭም ሌላ አማራጭ አልነበረምና ትክክል ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ህልውና በሽታ የሆነባቸው ደናቁርት ጠባቦችና የኢትዮጵያ ጠላቶች (ወያኔ) ለጥፋት ተልእኳቸው ይመቻቸው ዘንድ የፈጠራ ታሪኮችን በመፈብረክና አንድና ሁለት ብሔረሰቦችን ነጥለው በመጥቀስ እነዚሁ ብሔረሰቦች ብቻ በዚህ ዘመቻ እንደተጨፈጨፉ አድርገው በማናፈስ የሕዝቡንና የሀገሪቱን አንድነት ለማፈራረስ ከፍተኛ ጥረት ላይ ናቸው ፡፡ ብዙ የዋሀንንም ማጥመድና ማታለል ችለዋል ፡፡ ይሄንን የወያኔን መርዘኛ ስብከት አምነው ለተቀበሉት ወገኖች ላነሣው የምፈልገው ጥያቄ ዐፄ ምኒልክ በዚህ ዘመቻቸው የፈጇቸው እንቢተኛ የኦሮሞና የወላይታ ተወላጆችን ብቻ ነው ወይ ? በዚሁ ዓላማ ምክንያት (ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ወይም አሐዳዊ መንግሥት ሥርዓት የመመሥረት) በየ መሳፍንቱ የተደለሉና የተከፋፈሉ እንቢተኛ የአማራ ተወላጆችስ አላለቁምን ? ዐፄ ምኒልክ ጎጃም ንጉሥ ተክለሃይማኖትን ድል ለመምታትና ጎጃምን የዚሁ አሐዳዊ መንግሥት ወይም የኢትዮጵያ አካል ለማድረግ በላኩት ጦር የአማራ ተወላጆች አላለቁምን ? የኋላ ኋላ ግን ዐፄ ምኒልክ የማረኳቸውን ንጉሥ ተክለሃይማኖትም ሆነ ንጉሥ ጦናን በዚህ ዓላማ ማመናቸውን ዓላማውን መቀበላቸው ሲያረጋግጡ  ግዛቶቻቸውን መልሰውላቸው እስከ ህልፈታቸው ድረስ በጋራ ለአንዲት ሀገር በየፊናቸው ይሠሩ እንደነበር ይታወቃል ፡፡ አስቀድሞም ዐፄ ቴዎድሮስ ይሄንን ዓላማ ለማስፈጸም በመሳፍንት ተከፋፍላ የነበረችውንና ህልውናዋ አደጋ ላይ ወድቆ የነበረችውን ሀገር አንድ ለማድረግ ባደረጉት ዘመቻ ከማንም በላይ ያለቀው የተፈጀው በየመሳፍንቱ ተይዞ የየመሳፍንቱን ጥቅም ለማስከበር ተገዶ እርስ በእርሱ ይዋጋ የነበረው የአማራ ሕዝብ አይደለምን?
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
እናም መሆኑን ባንወደውም አማራጭ ያልነበረው እርምጃ በመሆኑ ድርጊቱን ፈጽሞ ልንኮንን ልናወግዝ አንችልም አይገባምም የተለየ ዓላማ ካልያዝን በስተቀር ፡፡ አይ የሚል ወገን ቢኖር ኢትዮጵያን አንድ የማድረጊያው ሌላኛውንና ነገሥታቱ ያልተጠቀሙበትን አማራጭ ማቅረብ ይኖርበታል ቢያንስ ለወደፊቱ ይጠቅመናልና፡፡ እነሱ እንደሚመኙት ይህች ሀገር የተበጣጠሰችና ያልተሰበሰበች እንደሆነች ወደ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጥታ ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት የከፋ ውጥንቅጥ ውስጥ ልንገባ እንደምንችል እንኳን መገመት የሚችሉ አይደሉም፡፡ ተሰባስበን በአንድ ቆመን ያለቻልነውን ሁለንተናዊ ፈተና እንዴት ተበጣጥሰን እንችለዋለን የተሻለም ነው ብለው እንደሚያስቡ አይገባኝም፡፡ የትኛውም የኢትዮጵያ አካል አሁን ያለችው ኢትዮጵያ አካል ሳይሆን የቀረ ቢሆን ኖሮ ከብዙ አቅጣጫ ሲታይ ሀገር ሆኖ እንደሀገር የመቀጠል የመኖር አቅምና ዕድል ማግኘት የሚችል የለምና፡፡ ተለነገሩ እነዚህ ሰዎች ይሄንን ያህል ርቀው ማሰብ የሚችሉ ስላልሆኑ ያለው አደጋ ጨርሶ አይታያቸውም በመሆኑም ነው ፈጽሞ ኃላፊነት የጎደለውን ተግባር በድፍረት እየፈጸሙ የምናያቸው፡፡ እናም የነበረውንና ሳንጠቀምበት የቀረነውን አማራጭ ሳናቀርብ እንዲሁ በደፈናው መወንጀል መኮነን ማውገዝ ከሆነ ይህ ከባድ ድንቁርናና ከውስጥ ከተደበቀ የሀገር ጠላትነት ከአባቶቻቸው በደም የወረሱት የባንዳነት ስሜት የሚመነጭ ነውና አድማጭ ሆይ ልብ በል         ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው ) 
መስማት ማዳመጥ ያለብህን ለይተህ ስማ ፡፡ይሄንን እያራገቡ ያሉ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ማንነት ብታጤነው በእርግጠኝነት ለዚህች ሀገርና ለሕዝቧ ጠላቶች የሆኑ ሆነው ታገኛቸዋለህ ፡፡ ወደፊትም ቢሆን በተመሳሳይ አቋምና እርምጃ መንቀሳቀስ እስካልቻልን ጊዜ ድረስ የዚህችን ሀገርና ሕዝብ አንድነትና ህልውና ማስጠበቅ ፈጽሞ አይቻለንም ፡፡ እዚህ ላይ ልብ እንድትሉልኝ የምፈልገው ነገር ቢኖር የአሥተዳደር በደልንና ኢትዮጵያዊነትን ለይታቹህ እንድታዩ ነው ፡፡ ችግሩ እየተፈጠረ ያለው እነኝህን ነገሮች እየቀላቀሉ ከመመልከት ነው ፡፡ የሰው ፍጹም ይኖራል ተብሎ ባይገመትም ያለ ሀገራዊ ወይም ብሔራዊ ምክንያት ማለትም ለሀገርና ለሕዝቧ ሲባል ከሚወሰድ ምክንያታዊ እርምጃ ውጪ ለግል ጥቅሙ ብቻ ሲሉ ግፍና በደል የፈጸሙ ግለሸቦች ካሉ ሊጠሉ ሊወገዙ ይገባል ፡፡ ነገር ግን ሊጠሉ ሊወገዙ የሚገባቸው የአሥተዳደር በደሉን ያደረሱት ግለሰቦች እንጅ ሀገርና የወጡበት ብሔረሰብ አይደለም ሊሆንም አይችልም፡፡ ነው ካልን ግን ከዚህ ድንቁርናችን የተነሣ ገና ካሳለፍነውም የሚከባብዱ ፈተናዎችን እየጋበዝን ነውና በእጅጉ ልንጠነቀቅ ይገባናል ፡፡
ይህ አቋምም ማንንና እንዴትም ሊጠቅም እንደሚችል ለሕሊናችን እንመልስ ፡፡ እናም በእነዚህ እኩያንና አጋንንት እነሱ ብቻ ወደሚያውቁት እኛ ወደማናውቀው መታረጃ ከመነዳታችን በፊት ይህ ድንቁርና ለሀገር፣ ለሕዝብ፣ ለራስም ለማንም እንደማይጠቅም ተገንዝበን የሰው ደም ጥማት ያንቃቃቸውን አጋንንት እንቢ በማለትና በማሳፈር ህልውናችንን የማረጋገጥና አስተማማኝ የማድረግ ግዴታ በሁሉም ዜጋ ጫንቃ ላይ ነው ፡፡

No comments:

Post a Comment