Wednesday, January 1, 2014

ቴዲ አፍሮና የቢራው ፖለቲካ (ክንፉ አሰፋ)

January1/2014


በጋዜጠኛ ስህተት የወጣች አንዲት ጽሁፍ ምክንያት 18 ሺህ ፊርማ በኢንተርኔት መሰበሰቡን ሰማን። ጽሁፉን ያሳተመው መጽሄት ስህተቱን አረመ። ይቅርታም ጠየቀ። ዘመቻው ግን እንደቀጠለ ነው። ቴዲ አፍሮ ይንን እንዳልተናገረ መግለጫ ቢሰጥም ጉዳዩ እልባት ሊያገኝ አልቻለም።   ከቶውንም አንድነታችንን የማይፈልጉ ምእራባውያን ጭምር ይህችን ምክንያት በመያዝ ጉዳዩን ማረገብ ጀመሩ። አንድ የዳች ጋዜጣ አጼ ምኒሊክን ከሂትለር ጋር አመሳስሎ በመጻፍ ጋዜጣውን በዚህ ሳምንት አሰራጭቷል! ያለ አንዳች መረጃ። “ለነጮች እጄን አልሰጥም!” ብሎ አድዋ ላይ ስላዋረዳቸው ምኒሊክን ለማንቋሸሽ ምንም መረጃ አያስፈልጋቸውም።

እልፍነሽ ቀኖ የተባለች የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ በአንድ ወቅት በለቀቀችው ነጠላ ዜማ ምክንያት ማእከላዊ እስር ቤት ታስራ ነበር። ምርመራውን የሚያካሂዱት ሰዎች በመጀመርያ የዘፈኑ ግጥም ወደ አማርኛ እንዲተረጎም አደረጉ። በግጥሙ ምንም አይነት የወንጀል ነገር ሲያጡ ግጥሙ “የህግ ትርጉም ይደረግለት” ሲሉ አዘዙ። የህግ ትርጉሙም ብዙ ስላላስኬዳቸው ለግጥሙ የፖለቲካ ትርጉም እንዲሰጠው አደረጉና ሙዚቀኛዋን “ጥፋተኛ ነሽ” ሲሉ ከሰሱ።  የፖለቲካ ትርጉሙ “ይህን ያለችው እንዲህ ለማለት ነው…”  ከማለት ተነስቶ አቀንቃኝዋ በልቧ አስባው ይሆናል የሚለውንም ያካተተ ነበር። በኢትዮጵያ “የፍትህ ሰዎች” የምናስበውንም ያውቁ ኖሯል።

የበደሌ ቢራ አድማ ጠሪዎች ቴዲ አፍሮ በልቡ ያሰበውን የማንበብ ሃይል እንዳላቸው አናውቅም። እሱ ግን የተባለውን ነገር እንዳልተናገረ ገልጾላቸዋል።

አጼ ምኒሊክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ያከሄዱት ጦርነት “ቅዱስ ጦርነት ነው” ወይንም “አይደለም” የሚለውን ሙግት ለግዜው ወደጎን እንተወው። ምክንያቱም የዚህ ውይይት ውጤጥ የኦሮሞ ህዝብ አሁን ላለበት ችግር የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም። የህሊና አይኖቹን ክፍት አድርጎ ለሚመለከት ሁሉ፤ የዛሬው የኦሮሞ ህዝብ ችግር የበዴሌ ቢራን ከመጠጣት እና ካለመጠጣት የላቀ ነው። ለነገሩ እንጂ 90 በመቶ የሚሆነው የኦሮሞ ህዝብ የሚተዳደረው በግብርና፤ ኑሮውም ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ የበደሌ ቢራን የመጠጣት አቅሙም ሆነ እድሉ የለውም። የዚህ ዘመቻ መሪ ተዋንያን የሆነው ጃዋር መሃመድ እንደነገረን ከሆነ ደግሞ 90 በመቶው የኦሮሞ ህዝብ የሙስሊም እምነት ተከታይ ነው። በሙስሊም አልኮል “ሃራም” ነው።

“እስር ቤቱ ሁሉ ኦሮምኛን ይናገራል!” ያለው ማን ነበር? አዎ! የስርዓቱ ቁንጮ የነበረው ስዬ አብርሃ ነው። ስዬ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከርቸሌ ታስረን የነበርን ጋዜጠኞች የእነ ኦቦ ባይራን ጉዳይ እያነሳን በኦነግ ስም በግፍ ለታሰሩት ስንጮህ የዝሆን ጆሮ ነበር የሰጠን።  አቶ ስዬ አብርሃ አይኑ የተከፈተውና ጆሮው ኦሮምኛን መስማት የጀመረው እጆቹ  የኋሊት ታስረው ቃሊቲ ሲወርድ ነበር። በእርግጥ ማየት ማመን ነው። ያየውንና የሰማውን በመመስከሩ ሊመሰገን ይገባዋል። ልብ በሉ። እስረኛው ሳይሆን እስር ቤቱ ነው ኦሮምኛ እየተናገረ ያለው።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ሰሞኑን በለቀቀው ዘገባ፤ በኦሮሞ ወገናችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን አስከፊ ስቃይ በድምጽና በምስል ጭምር አሰራጭቷል። ይህንን ስቃይ ለማስቆም የፌስቡክ ታጋዮቹ ስንት ሺህ ፊርማ እንዳሰባሰቡ አልነገሩንም። የበዴሌ ቢራን የኦሮሞ ህዝብ እንዳይጠጣ በ24 ሰዓታት ውስጥ 18 ሺ ፊርማ ተሰብስቧል ብለውናል።

እርግጥ ነው። “ሰብአዊ መብት ይከበር!” የሚል ዘመቻ ከመጀመር ይልቅ “ቢራ አትጠጡ!” ማለቱ ቀላል ሊሆን ይችላል።  በምእራቡ አለም የሚመረተውን ሄነከን ቢራ ራሳቸው እየተጎነጩ  ይህንን ቀጭን ትእዛዝ ሲያስተላልፉ ግን በዚያ ትልቅ ህዝብ ላይ እያሾፉበት መሆኑን የዘነጉት ይመስላል።

የኦሮሞ ልሂቃን ግራ ያጋቡኛል። ይህን ስል ያለምክንያት አይደለም።  በአባ ጅፋር ግዛት ተወልጄ በኦሮሞ ባህል ታንጼ ነው ያደግኩት።  በደሙ ብቻ ‘ኦሮሞ ነኝ’  እያለ ከሚመጻደቀው ይልቅ የኦሮሞን ህዝብ ማንነት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። ቋንቋው፣ ባህሉና ስነልቦናው ውስጡ ሰርጎ ሳይገባ በደሙ ብቻ ራሱን እየለካ ከህልም እና ከቅዠት አለም ውስጥ ገብቶ የኋሊት ከሚራመደው በተሻለ መንገድ።  …    እናም አንድ የኦሮሞ ህዝብ አውቃለሁ።  በቋንቋው፣ በባህሉና በታሪኩ የሚኮራ ህዝብ።  ታታሪና ሰራተኛ ህዝብ።  ከሌላው ጋር ተዋልዶና ተከባብሮ በፍቅር አብሮ የሚኖር ህዝብ።   የኦሮሞ ህዝብ  ከሌላው ወገኑ ጋር በደም ተሳስሯል። ሃቁ ይህ ነው። ግና ፖለቲከኞቹ ከዚህ ህዝብ በሁለት ሺህ ማይልስ ርቀው በምእራቡ አለም በሚሰሩት ስራ ይህንን ትልቅ ህዝብ እጅግ ትንሽ የሚያደርግ መሆኑን ያስተዋሉት አይመስለኝም።

በቅርቡ ሳውዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ የጸመችውን ግፍ ለመቃወም በአለም ዙርያ ያለ ኢትዮጵያዊ በጋራ በሚጮህበት ወቅት አንድ እንግዳ ክስተት በኢንተርኔት ላይ ወጥቶ አየን። “ሳውዲ አረቢያ ኦሮሞን አትግደሉ፣ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለም፣ ኦሮሞ ወንጀለኛ አይደለም።” የሚል መፈክር የሚያሰሙ ሰዎች ለብቻቸው ሰልፍ ወጡ። እነዚህ ሰዎች የተሰለፉት “ኦሮሞን አትንኩ። ሌሎቹ ግን ወንጀለኞች ስለሆኑ ይገባቸዋል” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ነበር።  መቼም ከማንም ሰብአዊ ፍጡር እንዲህ አይነት ኢ-ሰብአዊ አባባል አይጠበቅም። ድርጊታቸው ያሳፍራል። አንገትም ያስደፋል። ይህ አሳፋሪ ድርጊት እኔን እንዲህ ካሸማቀቀኝ፤  አፈር ስንፈጭ ያደግነው በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሮ የኦሮሞ ልጆች ቢያዩት ምን ሊሉ እንደሚችሉ በምናቤ እስል ነበር።  በዚያ ትልቅ ሕዝብ ስም አደባባይ ወጥተው፣ ተግባራቸው ግን ማስተዋል የተሳነው ትንሽ ህዝብ ነበር።  ያንን ኩሩ ህዝብ እንዲህ … እንዲህ እያሉ ሊያሳንሱት አየን።

እ.ኤ.አ. በ1998 ገደማ አቶ ዳዊት ዮሃንስ በሆላንድ ውስጥ ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቶ ነበር። ከስብሰባው መሃል አንድ ሰው ከመቅጽበት ተነስቶ ‘ለኦቦ ነጋሶ ጊዳዳ የሚያደርሱልኝ ጥብቅ መልእክት አለኝ’ አለ። ስብሰባውን የሚመራው አቶ ዳዊት ዮሃንስም ሰውዬው ተነስቶ መልእክቱን እንዲናገር ፈቀደለት። ሰውየው ከመቀመጫው ተበሳ።

“ፊንፊኔ መሃል ላይ ያለው የምኒሊክ ሃውልት በአስቸኳይ እንዲነሳ ይንገሩልን!” አለ ፊቱን ቅጭም አድርጎ በኩራት እየተናገረ።  በስብሰባው የነበርን ሰዎች ግን ለተናጋሪው አፈርን። ያሳፈረን ይህንን መልእክት ማስተላለፉ አልነበረም። ሰውየው ሊናገር ከመቀመጫው ሲነሳ ሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ያነሳል ብለን ገምተን ስለነበር እንጂ።  ‘ሰዎች በዘራቸው (በኦሮሞንታቸው) ብቻ የሚታሰሩት፣ የሚሰቃዩትና የሚገደሉት እስከመቼ ነው?’ የሚል መልእክት ነበር የጠበቅነው። ምክንያቱም ወቅቱ በቁጥር 20 ሺህ የሚደርስ የኦሮሞ ተወላጆች የጦር ካምፕ እስረኛ እንዲሆን ካደረጉ በኋላ፤ የኦነግ መሪዎች በባሌ ሳይሆን በቦሌ እየተሸኙ የወጡበት ሰሞን ነበር።  የኦነግ መሪዎች ከህወሃት ጋር በጋራ መስርተውት የነበረውን ቻርተር ረግጠው በመውጣታቸው ምክንያት ኦሮሞው ወገናችን የህይወት መስዋእትነት ጭምር ይከፍል የነበረበት ወቅት።

ዳዊት ዮሃንስም አግባብ ያለው ጥያቄ መሆኑን ከተናገረ በኋላ መልእክቱን ለርእሰ-ብሄሩ እንደሚያደርስ ቃል ገብቶ ሄደ።  መልእክቱን ለዶ/ር ነጋሶ ያድርስ፤ አያድርስ የታወቀ ነገር የለም። ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በዚያን ወቅት የሃገሪቱ ርዕሰ-ብሄር ነበሩ። እንኳንና የተባለውን መልእክት ሊያስፈጽሙ፤  እሳቸውም የዛ ስርዓት ሰለባ ሆነው አየን።

የአጼውን ሃውልት ግን ዛሬ በባቡር ሃዲድ ስራ ምክንያት ከነበረበት ስፍራ እንዲነሳ አድርገውታል።
የተዛባ ታሪክ ይዘን፣  ጥላቻን ብቻ በምናባችን አርግዘን የት እንደምንደርስ አላውቅም። አሁንም በመፍትሄው ላይ ሳይሆን በችግሮቹ ላይ ተወጥረናል።  የምኒሊክ ሃውልት ተነሳም አልተነሳ እንደ እንስሳ ለሚታደነው የኦሮሞ ህዝብ ምን ፋይዳ አለው?  “በእስር ያሉ ወገኖቼ ይፈቱ!” ለማለት እንኳን ሞራል ሳይኖረን አእምሯችንን በአፈ-ታሪክ ብቻ ወጥረን አንዲት ኢንች እንኳን ወደፊት መራመድ እንዳልቻልን ለምን አናስተውልም?
አጼ ምኒሊክ ኢትዮጵያን ግዛት አንድነት ለማስፋፋት ባደረጉት ጦርነት ወንጀል ፈጽመው ከሆነ አጽማቸው ወጥቶ ለፍርድ ይቅረብ ነው የምትሉት?  ወይንስ ይህ ትውልድ የዚያ ወንጀል ውርስ አለበት? ውርስ ካለበትስ ማን ነው ወራሹ? አማራው? ጉራጌው ወይንስ ኦሮሞው?  እንደ ዘረኞች፣ ደም መለካት ካለብን እኚህ መሪ ከአማራም፣ ከኦሮሞም፣ ከጉራጌም ይወለዳሉ። ጠለቅ ብለን ከሄድን ደግሞ ራስ ጎበና ዳጬን በዚያ ስእል ውስጥ እናያለን። ምእራብ እና ደቡብ ኢትዮጵያን በሃይል የያዙና ያስገበሩ የአጼው የጦር መሪ። ራስ ጎበናን ልንጠላቸው እንችል ይሆናል። ኦሮሞነታቸውን ግን ልንክደው አንችልም።   የወንጀል ውርስ በተዋረድ (guilt by association)  ውስጥ ከገባን የኦሮሞን ህዝብም በአእምሯችን ለፈጠርነው ወንጀል ወራሽ ልናደርገው ነው።

የቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” አልበም  የሚያሞግሰው ኢትዮጵያን ከወራሪ ጠላት የታደጉትን ጀግኖች ነው። እነ ፊታውራሪ ሃብተጎርጊስ ዲነግዴን እና እነ ባልቻ አባ ነፍሶ። ቴዲ አፍሮ ለነዚህ ጀግኖች ባያቀነቅንላቸውም ከታሪክ መዝገብ ላይ ልንፍቃቸው አንችልም። የታሪክ ተመራማሪዎች ስለነዚህ ጀግኖች የጻፉት አፈ-ታሪክ ወይንም ድርሰት አይደለም። በጀግኖቹ የምንኮራው በዘራቸው ሳይሆን የሰሩት ገድል ነው። በ’ጥቁሩ ሰው’ የተመራው ይህ የጸረ-ቅኝ ግዛት ገድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው አፍሪካና ለጥቁር ህዝቦች ነጻነት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ሊዋጥላችሁ የሚገባ እውነታ ነው። በዚያ ገድል የሚያፍሩ ካሉ የራሳቸው ጉዳይ። መላው የአፍሪካ ህዝብ ግን ይኮራበታል። የአለም ጥቁር ህዝብም ሲያስታውሳቸው ይኖራል።
ዘር እየቆጠርን ከሄድን ብዙ የሚጎረብጡ ነገሮችን ልናነሳ ነው። በግዛት ማስፋፋቱ ሂደት ግን አንድ ሃቅ አለ።  ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ህልቀ መሳፍርት ኢትዮጵያዊ አልቋል። ይህ ደግሞ የድንበር መስፋፋት፤ እድገት እና ስልጣኔ ይዞት የሚመጣው ችግር እንጂ አንድን ህዝብ ለመጨረስ ጥናት ተደርጎ የተሰራ እንዳልሆነ ታሪኩን ከስር መሰረቱ ማየቱ ይበጃል። ችግሩ በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በአያሌ ሃገሮች እንደተከሰተ የታሪክ መዛግብት ይነግሩናል። በ17ኛው ክፍለዘመን የተከሰተው የኢንዱስትሪ አብዮት ሳብያ እንኳን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት የማይተናነስ እልቂት ነበር።

አጼ ምኒሊክን ከጀርመኑ ኦቶ ቮን ቢስማርክ ጋር የሚያመሳስሉ ምሁራንም አሉ። እርግጥ ነው ጀርመን  አሁን የያዘችውን ግዛት ቅርጽ እንድትይዝ ያደረገው ፕሩሲያዊው ቢስማርክ ነው። ቢስማርክ የጀርመንን አንድ ታላቅ ኤምፓየር ለመፍጠር አንባገነን፣ ሃይለኛና ጦረኛ መሆን ነበረበት። ታዲያ ይህችን ሃያል ሃገር በመመስረቱ ጀርመኖች አልጠሉትም። ይልቁንም የጀግንነት ስያሜ ለግሰውታል። አያሌ የመታሰቢያ ሃውልቶችንም አቁመውለታል።

ቢስማርክ የህግ ምሁር ነበር። አጼ ምኒሊክ ግን መደበኛም ሆነ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ ሰው አልነበሩም። ከታሪክ እንደምንረዳው በአጼ ልብነድንግል ዘመነ መንግስት፤ የግራኝ አህመድ ወረራን ተከትሎ የነበረውን መከፋፈልና መተላለቅ ለማስቆም መሪዎች ተነሱ።  ሃገርን አንድ የማድረጉን ትግል አጼ ዮሃንስ ጀመሩት፣ አጼ ቴዎድሮስ ቀጠሉበት ከዚያም እምዬ ምኒሊክ ተረከቡት።


አጼ ምኒሊክ ለአመታት በኦነግ ሰዎች ተወግዘዋል። ውግዘቱ አሁንም እታገልለታለው የሚሉትን ህዝብ ችግር ሲፈታው አለየንም። በ1991 ከህወሃት ጋር ጋብቻ ፈጽመው የምኒሊክ ቤተ-መንግስት ሲገቡ ይናገሩት የነበረውን ሁሉ ረሱት። ከቶውንም ያነሱት የነበረው የኦሮሞ ህዝብ የመብት ጉዳይ ሳይሆን የስልጣን ጥያቄ ለመሆኑን አረጋገጡልን።  የሽግግር መንግስቱን ቻርተር ሲያጸድቁ “ኢትዮጵያዊ አይደለንም” የሚለውንም ሳያውቁ ዘንግተውት ነበር። ከገዢው ፓርቲ ጋር የጀመሩት ግዚያዊ ጋብቻ በፍቺ ሲጠናቅቅ የምኒሊክ ጠላትነት መፈክራቸውን እንደገና አነሱት።
የዘር ፖለቲካው ስካር ሞቅ ብሎ በነበረበት በዚያን ወቅት እንደቀልድ ይነገር የነበረ አንድ ቁም ነገር አለ። አንድ የምግብ ቤት በር ላይ በላቲን ፊደል “አማራ መግባት ክልክል ነው!” የሚል ጽሁፍ ሰፍሯል። የጽሁፉ ትርጉም ያልገባው አንድ የአማራ ተወላጅ ጎራ ብሎ ምግብ አዘዘ። አስተናጋጆቹ የሰውየው ድፍረት አስደነገጣቸው። ባለስልጣን ስለመሰላቸው አስተናገደዱት። ዳግም እንዳይመለስም እጥፍ ዋጋ አስከፈሉት። ሰውየው በድጋሚ ሲመጣ ሶስት እጥፍ አስከፈሉት። በሌላ ግዜ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር መጥቶ ምግብ አዘዘ። ከተስተናገደ በኋላም አራት እጥፍ ቢል አቀረቡለት።  በዚህ ግዜ ቲፕም ጨምሮ ሰጣቸው።  የሆቴሉ ባለቤት በነጋታው “አማራ መግባት ክልክል ነው!” የሚለውን ጽሁፍ አንስቶ “ኦሮሞ መግባት ክልክል ነው!” በሚል ቀየረው።

በአሁኑ ዘመን ከበድ አለ እንጂ፣ ሰዎችን በጎሳ አደራጅቶ ከማሳደም የቀለለ ትግል የለም። ደም ከውሃ ይወፍራል እንዲሉ፤ ሰዎች በጋራ የሚጋሩትን ነገር እያነሱ ስነልቦናዊ ዘመቻ ማድረግ ስኬት ሊኖረው ይችላል። ዘለቄታ ግን አይኖረውም። የዘር ፖለቲካ ልክ እንደ ስካር ነው። ይሞቃል ከዚያም ይበርዳል። በርግጥ በሞቅታ ግዜ የሚፈጠረው አደጋ ቀላል ላይሆን ይችላል። እ.ኤ.አ. በ1993 በምስራቅና በምእራብ ኢትዮጵያ የተፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል ለዚህ ዋቢ ነው። የኦነግ ልሂቃን የ19ኛውን ክፍለ ዘመን ጉዳይ እየደጋገሙ ያነሱልናል።  በ21ኛው ክፍለ ዘመን በራሳቸው እጅ የተፈጸመው ግድያ ግን በብሄራዊ ቴሌቭዥን ጭምር እንድናየው ተደርጓል።  ነብሰ-ጡር ሴቶች በጩቤ ሆዳቸውን እየተሰነጠቁ ሲገደሉ አየን። ነብስ ያላወቁ ሕጻናትና የ90 አመት አዛውንት ጭምር ከተራራ ላይ እየተወረወሩ ሲጣሉም የአይን ምስክሮች ነን። እነዚህ ሰዎች የምናስታውሰው ይህን በመሰለ ወንጀል ብቻ አይደለም። ድርጊቱ የቂምና የቁርሾ አሻራ ጥሎ አልፏል።

ይህ ሁሉ በደል በዘመናችን ተፈጸመ። በዳዮቹ ግን አሁንም በቀልን አርግዘው ይጓዛሉ።

የበደሌ ቢራን አለመጠጣት የኦሮሞን ችግር የሚፈታ ከሆነ፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቢራውን መጠጣት ያቁም። የአኖሌን ሃውልት መሰራት ለኦሮሞ ህዝብ ፍትህ የሚያመጣ ከሆነ ደግሞ፤ ሃውልቱ በየከተማው ይገንባ። ግና ይህ ሃውልት ለመጭው ትውልድ ጥሎት የሚያልፈው ቂምና በቀልን እንጂ፤  ለሚታገሉለት ህዝብ የፍትህ ጥያቄ ዋስትናው ምን እንደሆነ ልንረዳው አልቻልንም።  አሁን ያለው ትውልድ ያልፋል። ከዚህ ትውልድ በኋላ ለሚወለዱት ልጆች ጥለንላቸው የምናልፈው ቅርስ ጥላቻ፣ ቂም እና በቀል ብቻ ይሆናል።

ከዘመናችን ታላቅ ሰው ከኔልሰን ማንዴላ አንድ ነገር እንማር። ማንዴላ የደቡብ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን የአለምን ፖለቲካ የለወጠ የፖለቲካ ነብይ ነው። ይህንን ሲያደርግ የፖለቲካ ፎርሙላ አልነበረውም። ክፉን ነገር በበጎ ለማሸነፍ ወሰነ። ጥላቻን በፍቅር ለወጠ። ልክ እንደ ክርስቶስ፣ የበደሉትን ሁሉ ይቅር ብሎ በፍቅር አሸነፋቸው። ታሪክ ሰርቶ አለፈ። ስሙም ከመቃብር በላይ ለዘልአለሙ ይኖራል።

No comments:

Post a Comment