Friday, January 3, 2014

ኢትዮጵያ የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን ማቋቋም የሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ ናት (ገለታው ዘለቀ)

/www.zehabesha.com


   ገለታው ዘለቀ  
reconciliatioባለፉት ጥቂት ተከታታይ ጽሁፎች ላይ እንደተወያየነው በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ውስጥ መግባት ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ ኣማራጭ መፍትሄ ይሆናል። ታዲያ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ላሉብን ውስብስብ ሁለንተናዊ ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ይሆናል ማለት ሳይሆን ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊፈቱ የሚገባቸውን ባህላዊ ማህበራዊ ችግሮች መስመር በማስያዝ በሂደት እየተፈቱ እንዲሄዱ ከማድረጉም በላይ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ደግሞ ቀጥተኛ ያልሆነ ኣስተዋጾ ስላለው ነው።   በችግር ኣፈታት ጊዜ ከሚመጡት መፍትሄዎች መካከል የትኛውን ብናስቀድም ነው ሌላውን ችግርም ኣብሮ ሊፈታልን የሚችለው ብለንም እንጠይቃለንና በዚህ ረገድ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ውስጥ መግባት ሌሎች መጋቢና ተለጣጣቂ ችግሮችን ለመፍታት ይጠቅማል ከሚል ነው።
ባለፉት ዘመናችን ያሉብንን ሃገራዊ ችግሮች ሁሉ ስንዘረዝር ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ምናምን እያልን ለያይተን እንዘርዝራቸው እንጂ ሁሉንም ችግሮች ለመፍታት የምንሄድበት መንገድ ግን ፖለቲካዊ ይዘት ባለው መንገድ ነው። ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን ፖለቲካዊ ይዘት ባለው መንገድ፣ ማህበራዊውን ደግሞ ማህበራዊ በሆነ መንገድ፣ ኢኮኖሚውንና ሌሎቹንም እንደ ተፈጥሯቸው ከመፍታት ይልቅ ለሁሉም ችግር ፖለቲካን የችግር መፍቻ ቁልፍ ኣድርገን መውሰዳችንና የፖለቲካው ጣልቃ ገብነት በማየሉ ችግሮቻችን መፍትሄ ሳያገኙ እንዲቆዩ ያደረገ ይመስላል። ለማህበራዊ ችግሮቻችን ሁሉ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ባህላዊና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዩችን ከባህርያቸው ኣንጻር ለመፍታት ብንጥር ችግሮቻችን ኣሁን ያሉትን ያህል ኣይበዙም ነበር። በኣሁኑ ሰዓት ፖለቲካው ማህበራዊውን ህይወታችንን የነካበት ምክንያት የማያገባው ውስጥ ገብቶ በመገኘቱ ነው።
በዛሬው ውይይታችን የምናነሳው ጉዳይ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ስንል ኣንድ ቁልፍ ቃል በዚህ የመወያያ ርእስ ውስጥ ይሰመርበታል። ይህም  ስምምነት የሚለው ነው። ስምምነት ስንል ወይም እንዴት ኣድርገን ነው ወደ ስምምነት የምንመጣው ስንል  በዚህ ኣገባብ ሶስት ጉዳዩችን ይዳስሳል።
1. ያለፈውን ታሪካችንን እንዴት ኣድርገን ነው ወደ ስምምነት የምንመጣው? ታሪካዊ ግድፈቶችን እንዴት እንፍታቸው? እንዴትስ እንያቸው? በሚለው ዙሪያ ያጠነጥናል::
2. ችግሮቻችን ታሪካዊ ብቻ ሳይሆኑ ኣሁን ድረስ ስላሉ እነዚህን ችግሮች እንዴት እንያቸው?  እንዴትስ እንዳይቀጥሉ ማድረግ እንችላለን? የሚለውን ይይዛል
3. ሁላችን የምንፈልጋትን የወደፊት ኢትዮጵያን እንዴት ኣድርገን ነው በጋራ ጥሩ መሰረት ጥለን መጻኢ እድሏን የምናበጀው? የሚለውንም ይይዛል።
እንግዲህ በነዚህ ከፍ ብለን በዘረዘርናቸው ኣሳቦች ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ስንል በምን መንገድ ነው የምንወያየውና የምንስማማው? የትና በማን ኣማካኝነት ይፈጸማል? የሚሉ በጣም ተግባር የናፈቃቸው ጥያቄዎች መነሳታቸው ኣይቀርም። ምክንያቱም ሃገራችን ውስጥ ላሉት ችግሮች የመፍትሄ ኣሳብ ኣይደለም የጠፋው:: በየጊዜው በቡድንም በግልም ጠቃሚና የሃገርን ችግር ሊያቃልል የሚችል ኣሳብ ይመጣል:: ነገር ግን እነዚህን የመፍትሄ ኣሳቦች የሚያደራጅና መልክ የሚያስይዝ ባለመኖሩ እንዲሁ ኣንዱን እያነሳን ኣንዱን እየጣልን እንኖራለን።
በዛሬው ውይይታችን ስምምነት የሚለውን ኣሳብ እንዴት ልናመጣው እንደምንችል ተግባራዊ ሃሳቦችን እናነሳለን። እንግዲህ ወደ ነጥባችን እንውረድና ስምምነትን ልናመጣበት ከምንችልባቸው ዘዴዎች ኣንዱ የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽንን ኣቋቁሞ በመስራት ነው። ይህ ኮሚሽን ኣሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ቢደግፈውና ኣብሮ ቢሳተፍ እሰየው ካልሆነም ግን ከመንግስት እውቅና ውጭ መቋቋም ይችላል። መንግስት ደገፈው ኣልደገፈው የሚያመጣው ችግር ኣይኖርም። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ሁዋላ እንወያያለን። ለኣሁኑ ስለ ብሄራዊ እርቅ መሰረታዊ ጉዳዮችን ኣንስተን እንወያይ።
ስለ ብሄራዊ እርቅ ምንነትና ይዘት እንዲሁም ኣፈጻጸም ስንወያይ ብሄራዊ እርቅን የምናየው  ባለፈው በተወያየንበት በስምምነት ላይ በተመሰረተ የባህል ውህደት ጽንሰ ሃሳብ ማእቀፍ (framework) ውስጥ ነው።

የብሄራዊእርቅምንነት ይዘትና ኣፈጻጸም
ከሁሉ ኣስቀድመን ብሄራዊ እርቅ የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ሁኔታ ምን ማለት እንደሆነ ልንበይነው ይገባል። ብሄራዊ እርቅ በኣለማችን ታሪክ ውስጥ በብዙ ኣገሮች የተፈጸመ ሲሆን የእርቁ ትርጓሜና ኣፈጻጸም እንዲሁም ግቦች ሁሉ ሊለያዩ ይችላሉ። እኛ ኢትዮጵያዊያን ወደ ብሄራዊ እርቅ ለመግባት መጀመሪያ ብሄራዊ እርቅ በኢትዮጵያ ሁኔታ (context) ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ካልተረዳን ብሄራዊ እርቁ ግቡን ላይመታ ይችላል። በመሆኑም ብሄራዊ እርቅ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ጉዳይ ኣንስተን በሚገባ እንወያይ። ሃሳባችንን ለማፋፋት ብሄራዊ እርቅን ከኣንዳንድ ሃገሮች ታሪክ ኣንጻር በመጀመሪያ እንመልከት። ለምሳሌ  ያህል በኣውስትራሊያ ውስጥ የብሄራዊ እርቅ ጉዳይ ተነስቷል። እንደሚታወቀው ከታላቋ ብሪታኒያ የኣስራ ስምንተኛው ክፍለዘመን ሰፈራ ፕሮግራም በፊት ኣውስትራሊያ በነባር(indiginious) ህዝቦች የተያዘች ኣገር እንደነበረች ይታወቃል። በሰፈራው ጊዜ በነባሮቹ ህዝቦች ላይ የመፈናቀል፣ የማንገላታት ወንጀሎች ተፈጽመዋል። ዛሬ የኣውስትራሊያ መንግስት ያን የተፈጸመ ታሪካዊ  ስህተት ኣመርቅዞ እንዳይቆይ የወሰደው ርምጃ ብሄራዊ እርቅ ማድረግ ሲሆን ከ 1998 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት የብሄራዊ እርቅ ወይም (National sorry day) ኣውጆ በየዓመቱ እየታሰበ ይገኛል። የዚህ የይቅርታ ቀን ኣዋጅ የሚያሳየው ነገር ላለፉት ስህተቶች ሃላፊነት የሚወስድ ኣካል መገኘቱንና የነበረውን ግፍ እውቅና መስጠት መቻላቸውን ለወደፊቱም እንደዚያ ኣይነት ግፍ እንዳይፈጸም ዋስትና መስጠታቸውን ነው። የኣውስትራሊያ ችግር እንደኛ በሶስት መንገድ ላይታይ ይችላል። ይቅርታው ግን ለስንት ኣመት እንደሚደረግ ኣይታወቅም። ዋናው ግን በነባሩ ህዝብ ዘንድ የነፍስ ጽዳት ለማምጣት የታሰበ በመሆኑ ብሄራዊ እርቁ ለኣውስትራሊያውያን ከፍተኛ ጠቀሜታ ኣለው። የነበረውን ታሪካዊ ችግር እውቅና ሰጥቶ ይቅርታ ማወጁ የኣውስትራሊያን ህዝብና መንግስት ልበሰፊነትና ኣርቆ ኣሳቢነት ያሳያል። ነባር ህዝቦችም በዚህ የሚረኩ ይመስለኛል። ከዛ ውጭ ኣፈታሪክ እንደሚናገረው ራሳቸው ነባር ህዝቦችም ከሌላ ክፍለ ዓለም መጥተው የሰፈሩ ናቸው። ዋናው ጥያቄያቸው በሰፈራው ወቅት የነበረው ግፍና በደል ሲሆን እነሆ ዛሬ ተባብረው ዴሞክራሲያዊ መንግስት  በመመስረታቸው ታሪክን ወደ ሁዋላ ኣይቶ ለችግሮች እውቅና ለመስጠት ችለዋል።
ደቡብ ኣፍሪካን ደግሞ እንይ። በደቡብ ኣፍሪካም እንደዚሁ ታሪካዊ የሆነ ብሄራዊ እርቅ የተካሄደባት ኣገር ስትሆን ከኣፓርታይድ ኣገዛዝ ለመላቀቅም ሆነ ከተላቀቀች በሁዋላ ደቡብ ኣፍሪካን በከፍተኛ የመንፈስ ልእልና ሲመራ የነበረው የብሄራዊ እርቅ ስሜት ነው። በደቡብ ኣፍሪካ ብሄራዊ እርቅ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት መካከል Nelson Mandela ኣውራ ናቸው። በኔልሰን ማንዴላ የተመራው ደቡብ ኣፍሪካን እንደገና የማነጽ ስራ ሲጀመር ኣገሪቱ ያለፈችበትን መራራ ችግር ለመፍታት የተጠቀመችው ዘዴ በሪስቶሬቲቭ  ጀስቲስ (Restorative justice) እና ቀስ እያለ በሚያድግ ዴሞክራሲ ቁስልን ማከምና የወደፊቷን የሁሉም የምትሆንን ደቡብ ኣፍሪካን መገንባት ይመስላል።
ደቡብ ኣፍሪካ ከኣፓርታይድ እንደተላቀቀች ወደ ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ (Retributive juctice) ኣተኩራ ቢሆን ምናልባትም ውጤታማ ኣትሆንም ነበር። ዋናው ጉዳይ ግን ደቡብ ኣፍሪካ ውስጥ የኣፓርታይድ ገዢዎች ለነበረው ችግር ሃላፊነት የመውሰድና ብሄራዊ እርቅን በሪስቶሬቲቭ ጀስቲስና በዝግ እያለ በሚያድግ ዴሞክራሲ ለመፍታት ፈቃደኛ በመሆናቸው የጥፋትና የሞት መላእክን ከደቡብ ኣፍሪካ ሊያባርሩት ችለዋል። ታላቁ የብሄራዊ እርቅ መሪ ኔልሰን ማንዴላም በዚህ ረገድ የተጫወቱት ሚና ታሪክ ሁሌ ሲዘክረው ይኖራል።
የሩዋንዳን ጉዳይም እናንሳ። ሩዋንዳ በዚህኛው ክፍለ ዘመን የዓለምን ህዝብ ያስደነገጠ ወንጀልን ካስተናገደች በሁዋላ ወንጀሉ ጋብ ሲል የወደፊት ኣቅጣጫዋ ግራ ያጋባት ኣገር ነበረች። ለኣንድ መቶ ቀናት በየቀኑ ስምንት ሺህ ሰዎች፣ በየሰዓቱ ከሶስ መቶ ሰላሳ ሰዎች በላይ ያለቁባት ሃገር የወደፊት እጣ ፈንታዋን ለማሰብ በርግጥም እጅግ ከባድ ስራ ነበር።  በርግጥ ሩዋንዳ ያ ወንጀል ጋብ ሲል ለወደፊት እጣፈንታዋ ወዲያው ኣዋጭ መስመር መስሎ የታያት ብሄራዊ እርቅ ማውረድ ቢሆንም ብሄራዊ እርቁ በሩዋንዳ ሁኔታ ምን መልክ ይያዝ? በምን መልኩ ይፈጸም? የሚሉት ጥያቄዎች ግን በጣም ሊከብዷት የሚችሉ ጉዳዩች ነበሩ። በኣንዳንዶች ዘንድ ኣጥብቆ ይቀነቀን የነበረው ጉዳይ ብሄራዊ እርቁ በሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ኣማካኝነት ሊፈጸም ይገባዋል የሚል ነበር። ሁላችን እንደምናውቀው ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ማለት ለወንጀለኛው ተገቢውን ቅጣት በመስጠት የተበዳይን ነፍስ ማጽዳት ወይም ማርካት ማለት ሲሆን ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ደግሞ የሚያተኩረው ወንጀለኛውን በመቅጣት ላይ ሳይሆን ተበዳዩን በመካስ ላይ ያተኮረ የፍትህና የእርቅ ማውረጃ ዘዴ ነው። ታዲያ ኣንዳንድ  ሩዋንዳዊያን ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ነው ፈውስ የሚያመጣልን ሲሉ በርግጥ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኙ ኣልቀሩም። ምክንያቱም ወንጀሉ የተፈጸመው በኣጭር ጊዜ በመሆኑ፣ ወንጀሉ ግድያ በመሆኑ፣ ገዳይና የሟች ቤተሰብ ጎረቤት በመሆናቸው፣ ኣሰቃቂ ወንጀል በመሆኑ ሪትሪቢዮቲቭ ጀስቲስ ተገቢነው እንዲሉ የገፋፋቸው ይመስላል። ይሁን እንጂ በኣንድ መቶ ቀናት ላለቀው ስምንት መቶ ሺህ ህዝብ ገዳዩችና ለገዳዩቹ ተባባሪዎች ፍርድ ለመስጠት ሩዋንዳ ኣቅም ኣልነበራትም። ሩዋንዳ በዚያን ወቅት ላለቁት ስምንት መቶ ሺህ ቱትሲዎችና ለዘብተኞች ወደ ኣንድ መቶ ሺህ ወንጀለኞችን ለፍርድ ኣቅርባ መቅጣት ከፈለገች ኣጠቃላይ የፍርዱ ሂደት ወደ  ኣንድ መቶ ኣመት ይፈጅባት ነበር የሚሉ ወገኖች ኣሉ።  ሪስቶረቲቭ ጀስቲስን ተጠቅማ ችግሯን ለመፍታት ብትሞክር ደግሞ ገዳይና ሟች ጎረቤታም በመሆናቸው፣ የሟች ደም ገና ስላልደረቀ በርግጥ የሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሌላ ችግር ውስጥ መውደቁ ሌላ ኣሳብን ያመጣባት ትመስላለች። ሩዋንዳ የነበረችበት መስቀለኛ መንገድ ኣስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የጣላት በመሆኑ ሁለቱንም የፍትህ ኣሰጣጥ ዘዴዎች ኣደባልቃ እንድትሄድ ሳያስገድዳት ኣልቀረም። በመሆኑም ባህላዊ የጋካካ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም የተወሰነውን ችግር በዚህ በሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ የተወሰነውን ደግሞ ዝግ እያለ በሚያድግ ዴሞክራሲና በሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ይፈታል እያለች እየደለለች ማርገብ ችላለች። ከሁሉ በላይ ግን ሩዋንዳ ወደ ዘጠና በመቶ የሚሆነው ህዝብ ክርስቲያን በመሆኑና ኣብያተ ክርስቲያናት የሚሰብኩት የይቅርታና የምህረት ትምህርት የሩዋንዳን ችግር በሪስቶሬቲቭ ፍትህ ለመፍታት ከፍተኛ ኣስተዋጾ ሳያደርግ ኣልቀረም። በኣጠቃላይ የሩዋንዳ ችግር ውስብስብና ኣስቸጋሪ በመሆኑ ሁለቱም የፍትህ ኣሰጣጥ ዘዴዎች ተግባር ላይ የዋሉ ይመስላሉ።
ለኣብነት በየሃገሩ የተፈጸመውን ወንጀል እያነሳን የተወያየነው ችግር በየቤቱ ኣለ፣ ይሁን እንጂ ሁሉም ሃገር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው ኣገር የቆመው ለማለት ነው። ወደኛው ኣገር እንመለስና ብሄራዊ እርቅ በኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖር የሚችለውን የብሄራዊ እርቅ ይዘት ለማየት መጀመሪያ ስለ ኣለፈው ታሪካዊ ግድፈቶች ማንሳት ተገቢ ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው በኣውስትራሊያ ውስጥ ለነበረው ግፍ ሃላፊነት የሚወስድ እውቅና የሚሰጥ ኣካል ተገኝቱዋል። ወደኛ ሃገር ስንመጣ ላለፉት በደሎች እውቅና ለመስጠትም ሆነ ኣንድ ኣካል ለጥፋቱ ሃላፊነት ለመውሰድ የምንችልበት ሁኔታ ጠፍቷል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሁሉም የባህል ቡድን በየፊናው ባለፉት ስርዓቶች ተጎድቻለሁ ባይ በመሆኑ ነው።
በኣጼ ምኒልክ ጊዜ የጠፉ ጥፋቶች ካሉ ለነዚያ ጥፋቶች የኣማራውን ህዝብ ሃላፊነት ውሰድና ይቅርታ በል የሚል ኣካል ቢነሳ ኣማራው ለራሱ ተበድያለሁ ባይ ነው። በፊውዳሉ ስርዓት በጭሰኝነት፣ በባርነት መከራየን ኣይቻለሁ:: በወቅቱ የተጠቀሙት ጥቂት ፊውዳሎች ናቸው:: ተውኝ እባካችሁ ይላል። በኣጼ ሃይለስላሴ ዘመንም ቢሆን የወሎ ርሃብ ሲመጣ ሃይለስላሴ ዓለም እንዳይሰማ ኣድርገው በዚያ ደረጃ ጨክነው ኣስጨርሰውኝ የለም ወይ? ደርግ ኣማራ ነው ካላችሁ ደግሞ የጎንደርንና የወሎን ወላድ እምባ ኣታዩም ወይ? ወዘተ. እያለ እያነባ ባለፉት ስርዓቶች የተጎዳውን ይቆጥራል። ኦሮሞው በበኩሉ በዚህኛውም ባለፈውም መንግስት ተነጥየ ተጎዳሁ፣ ባህሌ፣  ማንነቴ ተጎዳ ብሎ እያነባ ይናገራል፣ ትግሬው በበኩሉ ባለፈውም ሆነ ኣሁን የተመቸኝ ነገር የለም፣ የውስጥ ችግሬን እኔ ነኝ የማውቀው ተለይቼ ተበድያለሁ እያለ ያነባል፣ የደቡብ ህዝቡ ተበድያለሁ የኔን መከራ ማን ባየው እያለ እያነባ ይናገራል፣ ሱማሌው የኔ መከራ መቼ ነው የሚያቆመው? መከራየን እያየሁ ነው እያለ ያነባል። ጋምቤላው፣ ኣፋሩ ሁሉም በተናጠልም በቡድንም ተጎድቻለሁ እያለ ያነባል። ታዲያ እንዲህ በሆነባት ኣገር ብሄራዊ እርቅ ምን መልክ ይኖረዋል የሚለው ጥያቄ ላይ ነው መወያየት ያለብን።
በመጀመሪያ ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለፉ ታሪካዊ ችግሮች ኣጥንተን መፍትሄ ለመስጠት የታሪክ ተዓማኒነትም ችግር ኣለብን። በተለይ በኣሁነ ወቅት ፖለቲካው ከፋፍሎ የመግዛት ዘዴን የሚጠቀም በመሆኑ ኣንዳንድ በፈጠራ የሚጻፉ ታሪኮች ያለፈውን ታሪካችንን በሚገባ ኣይተን ብሄራዊ እርቅ ለማምጣት እንቅፋት ነው። የሆነ ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፈውም ሆነ ኣሁን ላለው ግፍና በደል ኣንድ ቡድን እንደ ቡድን ሃላፊነት ወስዶ ይቅርታ የሚልበት ሁኔታ የለም። በደቡብ ኣፍሪካም ሆነ በኣውስትራሊያ ወይም በሌሎች ኣገሮች እንደተፈጠረው ኣይነት ሃላፊነት ወስዶ የቡድኖችን እንባ የሚያብስ ጠፋ። በመሆኑም የኢትዮጵያ ምሁራን በዚህ ኣስቸጋሪ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄራዊ እርቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነና ሁላችንን የሚፈውስ ኣሳብ በግድ ኣምጠው ሊወልዱ ይገባል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው ቡድኖች እንደቡድንም በጅምላም ባለፈው ጊዜ ለደረሰባቸው በደል ሁሉ ያለፈውንና ኣሁን ያለውን ስርዓት የታሪክ ተጠያቂ ማድረጉ ኣንዱ የስምምነቱ ኣሳብ ወለል ቢሆን መልካም ነው። ይሁን እንጂ ላለፉት ችግሮቻችን ቡድኖች እንደ ቡድን ተጎዳሁ የሚሉት ካለ ለዚያ ቡድን ጉዳት እውቅና መስጠት ኣንዱ የስምምነቱ ኣካል ሊሆን ይገባል። ኣንድ ቡድን ተጎዳሁ ተጎድቼ ነበር ሲል የለም ያንተ ጉዳት ትንሽ ነው የኔ ይበልጣል ማለቱ ብሄራዊ ፈውስን ኣያመጣም።ሰው ህመሙን የሚያውቀው ራሱ ነው። በመሆኑም ቡድኖች  የተጎዳነው ኣለ ሲሉ ማዳመጥና ሃዘንን መጋራት ለችግር እውቅና መስጠት ነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ መሰረቱ።  ኦሮሞው ኣጼ ምኒሊክ ጎድተውኛል ካለ ሌላው ብሄር ልክ ኣይደለም ኣልጎዱህም ማለቱ ለብሄራዊ እርቁ ኣይጠቅመንም። ኣንዱ ዜጋ ኣጼ ምኒሊክ  ካጠፉት ጥፋት ይልቅ የሰሩት ጀብዱ በተለይም ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ ለመመከት ያደረጉት ተጋድሎ ከበለጠበት ቢወዳቸው ቢፎክርላቸው ሌላው ኢትዮጵያዊ መበሳጨትና ጥል ውስጥ መግባት የለበትም። ኣንድ መሪ ለኣንዱ ኢትዮጵያዊ ተወዶ ለሌላው የሚጠላ ቢሆንም ከዚህ ልዩነታችን ጋር ኣብረን መኖር እንችላለን። ኢትዮጵያዊ ለመሆን ሁሉ ሰው ኣጼ ምኒሊክን መውደድ ኣለበት ማለት ኣይደላም።ፕሬዚደንት ኦባማንና ፕሬዚደንት ቡሽን የሚወድም የሚጠላም በሰላም እንደሚኖረው እኛም ከልዩነት ጋር መኖርን መልመድ ያስፈልገናል።
ኣሁን እኛ ጋር ያለው የኮሙኒኬሽን ችግር ይመስላል። የኮሙኒኬሽን ችግሮች ምንጫቸው የእውነት መዛነፍ (distortion of truth) እንዲሁም የማንነት ፖለቲካ ውጤቶች ስለሆኑ ለነዚህ ችግሮች ራስን ሰለባ ኣለማድረግ ነው።በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ ዋናው መሰረት እርስ በርስ መረዳዳት(understanding eachother) ነው ማለት ነው። ያለፈውን ህመማችንን በመደማመጥ ነው ልንፈታው የምንችለው። ችግራችንን ስንገልጥ የለም ያንተ ቁስል ትንሽ ነው የኔ ነው ትልቁና ኣንተ ስለ ብሶትህ ኣታንሳ ኣይባልም። ቢሆን ቢሆን ራስን ከውጭ ወደ ውስጥ ከውስጥ ወደ ውጭ የማየት ልብ ቢኖረን እሱ ነው ያለፈውንና ኣሁን ድረስ የቀጠለውን ችግራችንን የሚፈታው። በኣሁኑ ሰዓት እኔ ኦሮሞ መሆኔ ቀርቶ ትግራይ ሆኘ ብፈጠር ምን ይሰማኝ ነበር? ምን እሆን ነበር? ብሎ ቢያስብ በኣንጻሩ የትግራይ ህዝብ ኦሮሞው ኣማራው ተለይቼ ተጎዳሁ ሲል  በኣሁኑ ሰዓት እኔ ኦሮሞ ሆኘ ተፈጥሬ ቢሆን ምን ይሰማኝ ነበር? የሚል ከፍ ያለ መረዳት (understanding eachother’s pain and understanding each other’s feelings) በተለይ በሌሂቁ በኩል ቢታይ ነው የብሄራዊ እርቁ መሰረቱ የሚጠብቀው። ኣንድ ሰው ጉዳቴ ከፍተኛ ነው ሲል የለም ያንተ ትንሽ ነው የኔ ነው ትልቁ ጉዳት ወደ ማለት ማዘንበላችን የኮሙኒኬሽን ችግር ያመጣብናል። እውነቱን እንነጋግር ከተባለ እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለፈውን ችግር  በብሄራዊ ይቅርታ ለመዝጋት የገጠመን ችግር ይሄው የኮሙኒኬሽን ችግር ነው። ያለመደማመጥና ህመምን ለመካፈል መድረክ ማጣት ትልቅ ችግሮች ሆነዋል። ሌላው ደግሞ ቅድም እንዳልኩት ያለፈውን ችግራችንን በብሄራዊ እርቅ ለመፍታት የነበሩትን በደሎች ወደ መድረክ ኣምጥቶ እውነትን ለመግለጥ ኣሁን ያለው መንግስት ታሪክን ስላቆራፈደውና ብርታትንም ሆነ ድካምን ከቡድን ማንነት ጋር እንድናያይዝ የሚገፋ ነገር በመኖሩ በከፍተኛ ሁኔታ እውነትን የማግኘትና የመዋጥ ችግር ይገጥመናል። በተጨማሪም  ኢትዮጵያዊያን ኣዳዲስ በሚወለዱ ታሪኮች ሳንደነብር ከስሜት በላይ ሆነን እርስ በርስ በመረዳዳትና ኣለ ለተባለው ችግር እውቅና በመስጠት ነገሩን ማርገብ ይጠበቅብናል።ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያ ያለፈውን ችግር ልታይበት የምትችልበት ኣንድ ሌላ ትልቅ ነገር የዛሬው ይዞታዋ ነው። በፊት የነበሩ ማህበራዊና ፓለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ኣሁን ድረስ እየተንከባለሉ መጥተው ስለሚገኙ ኣሁን ያለውን በቡድኖች መካከል ያለውን ክፍተት በሪስቶሬቲቭ ፍትህ ልትፈታው ይገባታል።  በትምህርት፣ በፖለቲካ ተሳትፎ በባህልና በቋንቋ ኣካባቢ ያለውን ችግር ኢትዩጵያ ለመፍታት ስምምነት ውስጥ መግባት ኣለባት። ይህ ስምምነት ነው ኣንዱ የብሄራዊ እርቁ ይዘት።  ሪስቶሬቲቭ  ፍትህ ስንል በማህበራዊ ተቋማት ግንባታ ይሁን ከፍ ሲል በገለጽናቸው ሁኔታዎች የተጎዱ ኣካባቢዎችን በኣፌርማቲቭ ኣክሽን ዘዴዎች ለመፍታት ስምምነት ላይ መጀመሪያ መድረስ ኣለብን። ይህ የብሄራዊ እርቁ ሰነድ የሚይዘው ኣንዱ ጉዳይ መሆን ኣለበት።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በስምምነቱዋ ወቅት የምታካትታቸው ጉዳዩች በግልጽ መጀመሪያ መቀመጥ ኣለባቸው። ቡድኖች እንደ ቡድን ሁሉም ተበድለዋልና ብሄራዊ እርቁ  ሁሉንም ሊክስ የሚችልና ኮሙኒኬሽንን የሚያዳብር መሆን ኣለበት። በዓለማችን የሚነሱ ጦርነቶች ኣብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል ምክንያታዊነት ያላቸው ኣይደሉም ኣብዛኛዎቹ ከኮሙኒኬሽን ችግር ጋር የተያያዙ ናቸው። ኣንዳንዴ ቡድኖች የተጣሉበትን ሁኔታ በውል ሳያውቁት ብዙ ይዋጉና ብዙ ሰው ካለቀ በሁዋላ ይታረቃሉ። የሚገርመው ሲታረቁና ስሜታቸው ሲረጋ የከፈሉት ዋጋ እንዲሁ ሜዳ ላይ ሆኖ የሚያገኙበት ጊዜ ይኖራል። በመሆኑም ብሄራዊ እርቁ በቡድኖች መካከል ያለን ኮሙኒኬሽን ለማስተካከል መላ ሊወልድ ይገባዋል።
ከፍ ሲል እንዳልነው ብሄራዊ እርቅ በኢትዮጵያ የሚኖረው መልክ ሁሉንም በመካስ ላይ ሁሉንም ችግሮች እውቅና በመስጠት ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል። በተለይ ያለፈውን ችግራችንን ለመፍታት ችግሩ ከኮሙኒኬሽንና ከስሜት ሃያልነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በረጋና በሰከነ መንፈስ ዜጎች ያለፈውን ችጋራቸውን በጋራ እውቅና ሰጥተው ሲንከባለል ለመጣው ችግር ደግሞ ኣፈርማቲቭ ኣክሽንስና ሌሎች የርስበርስ የመካካሻ ዘዴ ተጠቅመው  ፈውስን ማውረድ ኣለባቸው። እንዲህ ስናደርግ ብሄራዊ እርቁ ሁለቱን ርምጃዎች የሚራመድ ሲሆን ሌላ ሶስተኛ ጉዳይ ደግሞ በውስጡ ሊያቅፍ ይገባዋል :: ይህ ሌላው የእርቁ ፓኬጅ የሚይዘው ደግሞ ኣዲሲቷን  ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ እንዴት ኣብረን እንውጣ? እንዴት የጋራ ቤታችንን ኣብረን እናጥብቅ የሚለውን ያካትታል:: በመሰረቱ ይሄ ጉዳይ ቀላልም ከባድም ነው። ቀላል የሆነበት መንገድ በኣብዛኛው ፖለቲከኛና ሌሂቅ ዘንድ ቅንነቱ ካለ መፍትሄው ቀላል ስለሆነ ሲሆን ጠማምነቱ ካለ ደግሞ   ፈተና ነው።
በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ብሄራዊ እርቅን በኢትዮጵያ የሚያየው እንደዚህ ነው። በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ብሄራዊ እርቁ ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስን መሰረት ያደረገና  በሚያድግ ዴሞክራሲ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ስምምነት ማለት ነው። ይህ ማለት ግን ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ቦታ የለውም ማለት ኣይደለም። በኣሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ሙስናና ከፍተኛ ወንጀል እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች ይህንን ኣሳባችንን እያዩ እንደ ጅልነት ኣይተው ከስልጣን እስኪወርዱ በግፋቸው እንዲቀጥሉ በር ኣይከፍትም።
የብሄራዊ እርቅ ሰነዱ እንደነዚህ ኣይነት ሰዎችን በቡድን እያየ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ወደ ፍርድ ሊያመጣቸው መቻሉ ኣያጠያይቅም። እንደ ቡድን እንደ ሃገር ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን ዝግ እያለ ሊሰራጭ በሚችል የሪዲስትሪቢዩሽን ዘዴ ተመጣጣኝ እድገት ለማምጣት መስማማት፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎን ከባህላዊ ውህደት ስምምነት ኣንጻር ኣይቶ ከብሄር ፖለቲካ ኣውጥቶ በኣንድ ብሄራዊ ማንነት ስር ለመገንባት መስማማት፣ ዋና የሃገሪቱን ቋንቋዎችን ቁጥር  መጨመር ኣጠቃላይ ፈውስን ለማምጣት ይጠቅማል።
ኢትዮጵያ ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ላይ እንድታተኩር የሚያደርጋት ለዘላቂ ሰላምና ልማት ኣንድነት የሚረዳት ሲሆን ይህ የፍትህ  ኣሰጣጥ ዘዴ በኢትዮጵያ ቡድኖች ዘንድ የተባረከና የሚበረታታ ነው። የኦሮሞ ስርዓትን ብናይ ለሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ትልቅ ቦታ ኣለው። ይቅር ማለትን፣ በዳዩን ከመቅጣት ይልቅ ተበዳዩን መካስን ያበረታታል። ኣማራው ኣካባቢ ያለውን የሽምግልና ስርዓት ስናይ በኣብዛኛው ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ የሚበረታታበት ሁኔታ ኣለ። በደቡብ፣ በምስራቅ በተለይም በሶማሌ ክልል ይህ የፍትህ ስርዓት ከፍተኛ ተጽእኖ ኣለው።
የሃይማኖት ዳራችንም ቢሆን ወደ መቶ ፐርሰንት የሚጠጋው ህዝብ ሃይማኖተኛ በሆነበት ኣገርም ይህ የፍትህ ስርዓት ሊሸከመው የሚችል በተፈጥሮው የተደራጀ ተቋም በመኖሩ ተመራጭ እንዲሆን ያደርገዋል።
ሌላው ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ባለፈው ጊዜ በግድ በሆነ ኣሲምሌሽን ጠፉ የሚባሉ ባህሎች ካሉ እነሱን የማስመለስ (Restoration and revival) ስራ ለመስራት መስማማቱ ነው ኣንዱ የእርቁ ሰንድ የሚይዘው ጉዳይ። የጠፉና በመጥፋት ላይ ያሉ ጠቃሚ ባህሎች ካሉና ቡድኖች የሚቆጩባቸው ከሆነ የማስመለስ ፖሊሲ ኣውጥቶ ቡድኖችን ሁሉ ተባብሮ ለመካስ ኪዳን መግባት። ቡድኖች ኣጣናቸው የሚሉዋቸውን በሙሉ ለማስመለስ ባይቻልም ኣብዛኛውን በመመለስ የቡድኖችን ልብ ማሳረፍ ይቻላል።
ሌላው የብሄራዊ እርቁ ሰነድ ሊይዘው የሚገባው ጉዳይ ለወደፊቱዋ ኢትዮጵያ የሚሆን ኣስተዳደራዊ ባህልን የመገንባት ስምምነት ሲሆን ይህም ዴሞክራሲ ነው። ቡድኖች በመጀመሪያ ዴሞክራሲ ከኣሁን በሁዋላ ያስተዳድረን  መንግስታት ቢቀያየሩም ዴሞክራሲ ግን የጋራ ባህላችን ይሁን የሚል ስምምነት ውስጥ ሊገቡ ይገባል። ይህ ኣስተዳደራዊ ባህል የጋራ የሁላቸው በመሆኑ ወደፊት ለህይወታቸው መሪ ይሆናል ማለት ነው።
ሌላው መሰመር ያለበትና የስምምነቱ ኣንዱ ኣካል ሊሆን የሚገባው ለመልካም ታሪኮቻችንም እውቅና መስጠት ነው። ኢትዮጵያን የመከራ ቤት ብቻ ኣድርጎ ከማየት የኣፍሪካ መቀመጫ ያደረጋትን የነጻነት ታጋይነቱዋን ማስታወስና ለነዚህ ታሪኮቻችን ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ኣስተዋጾ በማድረጋቸው እውቅና ሊሰጡት ይገባል። ይህ ኣይነቱ ስሜት ሚዛናዊ የሆነ ስሜትን ከመፍጠሩም በላይ ኣገር ኣለን ስንል የምንመካባቸው ብዙ ኣኩሪ ታሪኮች እንዳሉንም ስለሚያደርግ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የስምምነታቸን ሰነድ ኣንዱ ሊይዘው የሚገባው ነገር የማትከፋፈል ኢትዮጵያን ለትውልድ ማሳለፍ ነው። መንግስት መጥቶ መንግስት ሲሄድ ቋሚ ዶግማ የሆነ ስምምነት ሆኖ ሊቀመጥ የሚገባው ጉዳይ ነው። የወደፊቷን ኢትዮጵያን እንደገና ማነጽ ማለት ይሄው ነው።

ማጠቃለያ
በቅርቡ ከኔልሰን ማንዴላ ሞት ጋር በተያያዘ ዓለም ያሳየችውን ስሜት ስናይ ያስደንቃል።በኔልሰን ማንዴላ ሞት ምክንያት የዛሬይቱ ዓለማችን በሚያስደንቅ መልኩ መነቃነቋ፣ ያ ሁሉ መሪ ወደ ደቡብ ኣፍሪካ መጉረፉ የሚያሳየው የሃያ ኣንደኛዋ ክፍለ ዘመን ዓለም ለብሄራዊ እርቅና ይቅርታ የሰጠችውን ታላቅ ክብርና ቦታ ነው።ኢትዮጵያዊያንም ከዚህ የምንማረው ኣለ:: ኢትዮጵያ ብህዙ በመሆኑዋ ይህ ተፈጥሮዋ በስምምነት ላይ የተመሰረተች  ኣገር እንድትሆን ያስገድዳታል:: በመሆኑም በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ያስፈልገናል የምንለው ኣንዱ መነሻ ይሄ ነው። እንዴት ወደ ስምምነት እንገባለን? በምን መንገድ ነው ወደዚያ መስመር የምንገባው? ተግባራዊ ሂደቱ ምንድነው? ካልን ኣንዱ መንገድ ብሄራዊ እርቅ ማምጣት ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው ብሄራዊ እርቅ ማለት በኢትዮጵያ ኣንዱ በዳይ ሌላው ካሳ የሚሰጥ ሳይሆን ርስበርስ የሚረዳዱበትና ሁሉም የሚካሱበት የእርቅ ኣሳብ ነው። በዋናነት ብሄራዊ እርቁ ያለፈውን ችግር መፍታት ኣሁን የዘለቀውን ችግር ማቆም ሆኖ ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ የስምምነት ነጥቦችን ኣውጥቶ በነዚያ ስምምነቶች ዙሪያ መስማማት ነው። እነዚህ የስምምነት ኣጀንዳዎች የሃገሪቱ ዶግማዎች ይሆኑና ዘላለማዊ ኪዳን ይሆናሉ። ይህ ኪዳን ከህገ መንግስቷም በላይ ሆኖ የሚኖር ይሆናል።። ህገ መንግስት የሚያረቁ መንግስታትም ከነዚህ ዶግማዎች ኣንጻር ህጎችን ሊያወጡ ይገባል። ይህ የእርቅ ሰነድ በሃይማኖት መሪዎች፣ በባህል መሪዎች በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሲቪክ ማህበራት ዘንድ ሁሉ የሚቀመጥ የሚከበር ትልቅ ኪዳን መሆን ኣለበት።ኢትዮጵያ በእንደዚህ ኣይነት ለየት ባለ ቅርጽ ብትተዳደርስ? ከህገ-መንግስቷም በላይ ሌላ ዶግማ የሆነ ኣዲስ ኪዳን ቢኖራት ጥሩ ኣይሆንም ?
መቼም ይሄ ተግባር የናፈቀው ህሊናችን ጥያቄ ማንሳቱ ኣይቀርም። ይህ ብሄራዊ እርቅ የሚባለው ነገር መቼ ነው መካሄድ ያለበት? ተዋንያኑስ እነማን ይሆናሉ? የሚል ተግባራዊ ጉዳዮች ይመጣሉ። በኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ ማለት የተጣሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መታረቅ፣ ወይም ውህደት ማድረግ ማለት ኣይደለም። በርግጥ የነዚህ ፓርቲዎች ውህደትና ስምምነት ለብሄራዊ እርቁ ከፍተኛ ኣስተዋጾ ኣለው። ኣሁን የምናወራውን ሰፊ ኪዳን ለመፈጸም ነው። ዓለምን የሚያስደምም ስምምነት ተስማምተን ኢትዮጵያን እንደገና ልናቆም ነው። ተዋንያን የሚሆኑት የተለያዩ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ቡድኖች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ባህላዊ ቡድኖች ዜጎች ሁሉ ናቸው። ከኣለማቀፉ ማህበረሰብም ታዛቢ ኣስገብታ ይህንን ስምምነቱዋን ለኣለም ማሳየት ኣለባት። ከዚያ በሁዋላ ኢትዮጵያ ታላቅ ድግስ ደግሳ ያን የተስማማችበትን ቀን ዘወትር የምታከብረው የኢትዮጵያ ዳግም ምስረታ (Foundation day) ቀን ብላ ያን ቀን ዘወትር በየዓመቱ ታከብረዋለች።ይሄ መሆን የሚችል ነው።
ኢትዮጵያ ይህን የእርቅ ኪዳን የምትገባው ኣሁን ያለው መንግስት ወደ እርቅ ከመጣ ብቻ ኣይደለም። ይህ መንግስት ለዚህ እርቅ ሁኔታዎችን ቢያመቻችና ኣብሮ ቢሳተፍ ታሪክ ያመሰግነዋል። ነገር ግን በነውጥም ሆነ በጠመንጃ ይህ መንግስት ከወደቀ በሁዋላም ኢትዮጵያ የግድ ወደዚህ ኪዳን ውስጥ መግባት ስላለባት ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ባለፈው ታሪካችን የጠፋው ይሄ ነው። ለውጦች ሲመጡ ብሄራዊ እርቅ ሳይደረግ ኣሸናፊው ተሽናፊውን እየረገመ የተሻልኩ ነኝ እያለ ስለመጣን ብሄራዊ ችግሮቻችን እየባሱ መጥተዋል። ኣሁን ግን በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን ኢትዮጵያ በዚህ የእርቅ ኣሳብ ውስጥ ማለፍ ኣለባት። ይሄ የግድ ነው።የብሄራዊ እርቁን የሚመራውና የእርቅ ኣሳቦችን የሚያመጣውን ኮሚሽን ኣገር ወዳድ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ሚዲያዎችና ኮሚኒቲዎች ከፊታቸው ያለውን የልዩነት ተራራ በጎን በኩል ዞረው ኣልፈው ይህን ሰነድ የሚያዘጋጁና መላ የሚፈጥሩ ኣካላትን ሊፈጥሩ ይገባል።ይሄ ሰው የሚሰራው ኢትዮጵያዊያን ልንሸከመው የምችለው ሃላፊነት ነው። ኣሁን ባለው የፖለቲካ ኣሰላለፍ ኢትዮጵያ የጎደላት ይሄ ነው። ኣልፎ ኣልፎ የተለያዩ ፓርቲዎችን ኣገናኝቶ በማነጋገር የእርቅ ኣሳብን ለማዳበር የሚሰራ የለም ማለት ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በየጊዜው የሚመጡ ለችግራችን የሚሆኑ የመፍትሄ  ኣሳቦችን የሚያጠናና የሚያደራጅ ባለመኖሩ ወርቅ የሆኑ ኣሳቦች ሁሉ ባከኑ። ለዚህም ኣንድ ጠርናፊ እውነትን የሚያፈላልግ የእርቅ ኣሳቦችን የሚያዳብር ተቋም ያስፈልገናልና በዚህ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትኩረት ሰጥቶ መላ ሊለው መስሎኝ ነው።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

No comments:

Post a Comment