Friday, January 17, 2014

ለ1.6 ቢሊዮን ዶላር የቴሌ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አማካሪ ድርጅት ሊቀጠር ነው

ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች ሁዋዌና ዜድቲኢ ለሚያከናወኑት የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አማካሪ ድርጅት ለመቅጠር ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቷል፡፡
ጨረታውን ያወጣው የፕሮጀክቱ ባለቤት ኢትዮ ቴሌኮም ነው፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አማካሪ ድርጅቱን ለመቅጠር የወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም. በይፋ ይከፈታል፡፡ 
ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች እያንዳንዳቸው በ800 ሚሊዮን ዶላር የሚያከናውኗቸውን የሞባይል ኔትወርክና የኢንፎርሜሽን ሲስተም ማስፋፊያ ሥራዎች የጥራት ደረጃ ለማረጋገጥ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ገለልተኛ አማካሪ ድርጅት ስለሚያስፈልግ ጨረታው መውጣቱ የግድ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ይህ ገለልተኛ አማካሪ ድርጅት በዋነኝነት የሚሠራው ፕሮጀክቱ በኮንትራት ስምምነቱ ሰነድ መሠረትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ መከናወኑን ይቆጣጠራል፤›› ያሉት አቶ አብዱራሂም፣ አማካሪ ድርጅቱ ከኩባንያዎቹና ከኢትዮ ቴሌኮም የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር በመሆን የዕለት ተዕለት ሥራዎችን እንደሚከታተል አስረድተዋል፡፡
አማካሪ ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃና በኮንትራት ስምምነቱ መሠረት እያንዳንዱን ሥራ በሚገባ ከመከታተሉም በላይ፣ የጥራት መጓደል በሚኖርበት ወቅት በፍጥነት ለመንግሥት ሪፖርት ያቀርባል ብለው፣ ከዚህ በተጨማሪም ቅድመ ኦዲት ሥራዎችን እየሠራ ክፍተቶችን እየነቀሰ በማውጣት የመንግሥት ዓይን እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት የአማካሪ ድርጅቱ የቅጥር እንቅስቃሴ መጀመር አልነበረበትም ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ሒደቱ እኩል መጀመሩን ነገር ግን የቅደም ተከተል ጉዳይ በመሆኑ እንጂ የዘገየ ነገር የለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ኩባንያዎቹ የሰርቬይ ሥራ ላይ ስለሆኑ ፕሮጀክቱ ሲጀመር የቁጥጥሩ ሥራም ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ የአማካሪ ድርጅቱ መረጣ ተከናውኖ ሲያበቃ ኩባንያዎቹ ዋናውን ሥራ ስለሚጀምሩ ችግር የለውም፡፡ ዋናው ነገር ይህ አማካሪ ድርጅት በሚገባ ታይቶ ከተመረጠ በኋላ እያንዳንዱ ኩባንያ በዝርዝር በተቀመጠለት መሠረት ሥራውን መሥራቱን ቁጥጥር በማድረግ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ በጥራት መጠናቀቁ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች በመካከላቸው ጤናማ የሆነ ግንኙነት ባለመኖሩ ምክንያት በፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ላይ ችግር አይፈጠርም ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ሁለቱም ኩባንያዎች እዚህ የመጡት ለሥራ ነው፡፡ በኮንትራት ስምምነቱ መሠረት ይሠራሉ፡፡ አማካሪ ድርጅቱም ይህንን በጥንቃቄና በትኩረት ይከታተላል፡፡ ዋናው ነገር ፉክክር መኖሩ ያለ ነው፡፡ እኛም ፉክክር መኖሩን እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ የአገሪቱን ጥቅም ከማስከበር አንፃር እያንዳንዷን ዕርምጃ እንከታተላለን፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም አማካሪ ድርጅት ለመቅጠር ጨረታ ማውጣቱ ሁለቱን ኩባንያዎች ደስ አያሰኛቸውም ተብሎ ቢታሰብም እንኳን፣ ለአገሪቱ ግን ጠቃሚ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች የቁጥጥር ሥራውን ቢያካሂዱ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በሚገባ ስለሚያውቁት አገሪቱ ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ትሆናለች ብለው፣ ጥራት ያለው ሥራ እንዲሠራ ከተፈለገ እንዲህ ዓይነት አማካሪ ድርጅት የግድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስመራሪ እየሆነ የመጣውን ኔትወርክ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አብዱራሂም፣ የሞባይል አገልግሎት ጥራት ትልቁ ችግር መሆኑን አውስተው ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ዕርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል ብለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚደርሰውን የአገልግሎት አቅርቦት ችግር ለማስተካከል 315 ጄኔሬተሮች ተገዝተው አገር ውስጥ መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
‹‹በመላ አገሪቱ ከአራት ሺሕ በላይ አንቴናዎች ለሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ተተክለዋል፡፡ አንዳንድ በሥራቸው ላሉ አንቴናዎች 27 ያህል ለሚሆኑ አነስተኛ አንቴናዎች ያቀባብላሉ፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የኃይል መቆራረጥ ሲገጥመን አገልግሎት ማቅረብ ያዳግተናል፡፡ አነስተኛ አንቴናዎች የሚሸፍኑት አንድ ወረዳ ወይም ዞን ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉም ቦታ ችግር አለ ባይባልም፣ አሁን ግን ችግሩን ለመቅረፍ ጄነሬተሮችን ገዝተን ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት ስለተጀመረ ችግሩ በአብዛኛው ይቀረፋል፤›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን የሞባይል ኔትወርክ ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀረፋል ተብሎ የሚጠበቀው የ1.6 ቢሊዮን ዶላሩ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በጥራት ተጠናቆ አገልግሎት ሲጀምር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ለጊዜው በኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚያጋጥመው ችግር እስኪፈታ ድረስ ደንበኞች እንዲታገሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

No comments:

Post a Comment