Saturday, December 14, 2013

የሕገመንግስት የትርጉም ጥያቄ ያስነሳው የአቶ መላኩ ጉዳይ ዛሬም አልተቋጨም


ታህሳስ ፫(ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ክሳቸው በየትኛው ፍርድ ቤት ይታይ በሚለው ጉዳይ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔውን እንዲያሳውቅ ሲል የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ትእዛዝ በመስጠት ለታህሳስ 22 ቀን 2006 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

ፍ/ቤቱ ቀደም ሲል በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ጉዳዩን የመረመረው የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የውሳኔ ኀሳቡን ዛሬ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት አቶ መላኩ ፈንታ የተሾምኩትና ስሰራ የቆየሁት በሚኒስትር ማዕረግ ነው፣የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ነበርኩኝ ፤ስለዚህም በፍርድ ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅ 25/88 መሰረት እኔ በሚኒስትር ማእረግ የተሾምኩ ስለሆንኩኝ የቀረበብኝ ክስ መታየት ያለበት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሳይሆን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው በማለት ያቀረቡትን መከራከሪያ ፍ/ቤቱ በማጤን ጉዳዩ የህገመንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በሚል ለሕገመንግስት አጣሪ ጉባዔ እንዲመራ ህዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት መወሰኑ ይታወሳል።

የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ በበኩሉ አቶ መላኩ በሚኒስትር ማዕረግ መሾማቸው ጥቅማ ጥቅማጥቅሞችን በሚኒስትር ደረጃ እንዲያገኙ እንጂ ሚኒስትር ስለነበሩ አይደለም ሲል የአቶ መላኩን መከራከሪያ ተቃውሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአቶ ካሳ ተ/ብርሃን የሚመራው የፌዴሬሽን ም/ቤት ከሕገመንግስት አጣሪ ጉባዔ የደረሰውን የውሳኔ ሃሳቡ በ30 ቀናት ውስጥ ምላሽ መስጠት እንዳለበት በሕግ የተደነገገ ቢሆንም፥ ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት የሚገኙ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ምክር ቤቱ በቀጣይ 18 ቀናት ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔውን እንዲያሳውቅ ሲል ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment