Saturday, December 7, 2013

የዋለልኝ መኰንን የሕይወት ታሪክ ዋለልኝ



የዋለልኝ መኰንን የሕይወት ታሪክ ዋለልኝ መኰንን በድሮው አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት በደብረሲና ወረዳ ከአባቱ ከአቶ መኰንን ካሣና ከእናቱ ከወይዘሮ ዘነበች ግዛው መጋቢት 11 ቀን 1938 ዓመተ ምህረት ተወለደ። በ50ዎቹ ወስጥ አባቱ አቶ መኰንን ካሣ ወደ ደሴ ከተማ በመምጣት ኑሮአቸውን ከመሰረቱ በኋላ በንግድ ሥራ ሕይወታቸውን መምራት ጀመሩ። ዋለልኝ መኰንንም በዚሁ በደሴ ከተማ በሚገኘው የንጉሥ ሚካኤል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ቀጠለ። በስድስት ዓመቱ አካባቢ የመደበኛ ትምህርቱን ጨረሰ። በመቀጠልም የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዚሁ በንጉሥ ሚካኤል የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ክፍል አጠናቀቀ።ከዚህም በመቀጠል መስከረም /1954 ዓመተ ምህረት የደሴውን የወይዘሮ ስሕን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ተምህርት ቤት ተቀላቀለ። የዘጠነኛና የአስረኛ ትምህረቱን የተከታተለው በዚሁ ትምህርት ቤት ነበር። በዚህ ትምህርት ቤት ቆይታው በተለያዩ የትምህርት ቤቱ ክበባት ውስጥ አገልግሏል። በክርክር ክበብ ወስጥ ተሳትፎ አድርጓል። በትያትር ክበብ ውስጥ አጼ ቴውድሮስን በመሆን ሁለት ጊዜ የተለያዩ ድራማዎችን ሠርቷል። ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ እንደ አጼ ቴወድሮስ ሆኖ የሰራው ክፍል በጊዜው አድናቆት አትርፎለታል። ዋለልኝ መኰነን በወይዘሮ ስሕን ቆይታው ሁለት ገጠመኞች አሉት። በ50ዎቹ ውስጥ ሆነ አሁንም ብዙ ስዎችን የሚያማልለው ሎተሪ ለዋለልኝ መኰንን አሥር ሽህ የኢትዮጵያ ብር ደርሶት ገንዘቡን ለራሱና የተቸገሩ ስዎችን በመርዳት ተጠቅሞበታል። ሁለተኛው ገጠመኝ፣ የአባቱን ላንድ ሮበር መኪና አስነስቶ ሲያሽከረክር ዳውዶ ከሚባል አካባቢ ከባሕር ዛፍ ግንድ ጋር ተጋጭቶ ከፍተኛ አደጋ ደርሶበት ሞትን አምልጧታል። ዋለልኝ መኰንን ከልጅነቱ ጀምሮ ይሉኝታ የሚባለውን ጐታች ባሕል ከላዩ ላይ አሽቀንጥሮ የጣለ ደፋር ወጣት ነበር። ስህተት ካዬ የማያልፍ ፤ መተቸት መተቸት የሚወድ፤ ላመነበት ጉዳይ ወደኋላ የማይል ንቁ ልጅ ነበር። ዋለልኝ የ12ኛ ደረጃ ትምሕርቱን ያጠናቀቀው በ 1958 በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ስር ይተዳደር በነበርው በልዑል በዕደማርያም ቅድመ ዝግጅት ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። በዚህ ትምህርት ቤት ቆይታው በሥነ ፅሁፍ ዝግጅት የላቀ ሚና ተጫውቷል። የክርክር ክበብ ምክትልና ዋና ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግሏል። በዚሁ ክበብ አማካኝነት በተለይም የሥነ አመክኗዊ /Logic / ውይይት አካሄድን ልቅም አድርጐ እንደተማረ ይነገርለታል። ትምህርት ቤቱ ዋለልኝን ተከራካሪ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ፀሃፊም እንዲሆን ረድቶታል። በሁለት ዓመት ቆይታው የትምህርት ቤቱ የጋዜጣ ረዳት አዘጋጅ በመሆን አገልገሏል። ጥሩ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ችሎታ ያለው ፀሃፊ እንደነበረ ጹሁፎቹ ምስክር ናቸው። የአጻጻፉ ሥልት ከእነ ኃይሉ ገበረዮሐንስና ፀጋዬ ገብረ መድህን/ደብተራው/ ሰልፍ ላይ እንደ ነበር ጓደኞቹ ይናገራሉ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተቀላቀለ በኋላ፣ በ ሕዳር 18, 1961 ዓመተ ምሕረት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በተደረገው የሥነ ጽሁፍ ውድድር “የአዚናራው እሥረኛ” በሚል አርእስት ኢትዮጵያውያንን ከጣሊያን ወታደር ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ፣ መስዋዕትነት፣ ጀግንነት፣ ለአገር ታማኝነትና ፍቅርን የሚያሳይ ሰነ ጽሁፍ ጽፎ ከተወዳዳሪዎቹ ውስጥ የአንደኝነት ማዕረግ በመጐናጽፉ ሽልማት አግኝቷል። በየዓመቱ በሚከበረው የዩኒቨርሲቲው ቀን ላይ በመወዳደር ካሸነፉት ስመጥር ገጣሚዎችና ባለቅኔዎች አንዱ ዋለልኝ መኰንን ነበር። ዋለልኝ መኰንን ወደ ፖለቲካው ባያዘነብል ኖሮ ጥሩ ደራሲ ይሆን እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲነሳ የዋለልኝ መኰንን ሥም ሁሌ አብሮ ይነሳል። ዋለልኝ መኰንን ምኞቱ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምሕር እንደነበር ቢገለፅም፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ለአንድ ዓመት ከቆዬ በኋላ ከትምሕርት ፋካልቲው ወደ አርትስ ፋካልቲ በመለውጥ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ ሆነ። ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ሕይወቱ ወደ ፖለቲካው ዓለም አዘነበለ። በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚደረጉ ሕዝባዊ ትግሎች ውስጥ ግንባር ቀደም በመሆን ተሳትፏል። በዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ልሳን (ታገል ጋዜጣ) ላይ የተለያዩ ጽሁፎችን በማቅረብ አስነብቧል! አታግሏል! ስለ ብሔራዊ አገልግሎት፣ በትግሉ የሴቶች ድርሻ፣ ስለብሔር ጥያቄ፣ ቅኔዎችንና ሌሎችንም ጽሁፎች ለታገል ጋዜጣ በየጊዜው አቅርቧል። በተጭማሪም በ60ዎቹ ንጉሡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሬዲዮ ለሰጡት ማብራሪያ መልስ “ ለአዋጁ አዋጅ” የሚል ጽሁፍ አዘጋጅቶ ከታጋይ ጓዶቹ ጋር በሕዝቡ ውስጥ እንዲስራጭና እንዲነበብ አድርገዋል። በዚህ ጽሁፍ ምክንያት አገርና ሕዝብን ለመበጥበጥ በሚል ክስ ዋለልኝ መኰንን፣ ሄኖክ ክፍሌ፣ ታምራት ከበደ፣ ጌታቸው ሻረው፣ ፋንታሁን ጥሩነህ፣ አያሌው አክሎግና ገዘኸኝ መኰንን የተባሉት የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች አምስት ዓመት ተፈርዶባቸው አዲስ አበባ ከርቸሌ ከቆዩ በኋላ ተለቀዋል። ዋለልኝ መኰንን በዚሁ የኢትዮጵያን አርሶ አድሮችና ላበ አድሮች ነፃ ለማውጣት በ60ዎቹ ውስጥ በተደረገው የኢትዮጵያ ወጣቶች ትግል ውስጥ ዓብይ ሚና የተጫወተ ወጣት ነው። ጥላሁን ግዛው የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ፕሬዝዳንት ሆኖ ከተመረጠ በኋላ ባደረገው ከፍተኛ የትግል ተሳትፎ ከባድ ክትትል ይደረግበት ነበር። አፍንጮ በር አካባቢ ታህሳስ 19, 1961 ዓ.ም ጥላሁን ግዛው በጥይት ይመታል። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ሲፈጠር ዋለልኝ መኰንን አምስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ቤቱ ከጓደኞቹ ጋር ነበር። አንድ ወጣት ወደ ቤት ይመጣና ስለ ጥላሁን ግዛው በጥይት መመታት ይነግራቸዋል። እነሱም በድንጋጤ ተያይዘው ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ይሄዳሉ። ሐኪሞቹ ሕይወቱን ለማትረፍ ሞክረው እንዳልተሳካላቸው ይነግሯቸዋል።በዚህ ወቅት ዋለልኝና ጓደኞቹ የጥላሁንን አስከሬን ከሆስፒታሉ በመውሰድ ዩኒቨርስቲው ውስጥ ቅጥር ግቢ Morgue ውስጥ በስርዓት ያስቀምጡታል። ከዚህ በኋላ የተቃውሞ ትዕይንትና የቀብሩን ሥርዓት ዝግጅት ያደርጋሉ። ለኮሌጅና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ። የጥላሁን ሞት ትግላቸውን እንደማይገታው፣ ጥላሁን ቢሞት ሽህ ጥላሁኖች እንደሚፈጥሩ በመግለጽ ጽሁፎችን በሕዝብ መሃል ያሰራጫሉ። በዩኒቨርስቲው ውስጥ ያለውን የጥላሁንን አስከሬን ለመውሰድ ወታደሮች በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገባሉ። በዚህ አጋጣሚ ዋለልኝ ከፎቅ ላይ ሆኖ በድምፅ ማጉያ ጥላሁንን የሚቀብሩት የትግል ጓዶቹና ሕይዎቱን የከፈለለት ሕዝብ እንጂ ገዳዮቹ መቅበር እንደማይችሉ ይናገራል። የክብር ዘበኛ ወታደሮች በተማሪዎቹ ላይ ተኩስ ከፍተው አበበ በርሔ፣ ስብሃቱ ውብነህ፣ ጀማል ያሲን የተባሉ ተማሪዎችን ይገላሉ። በዚያን በሽብር ወቅት ዋለልኝ መኰንን ይተርፋል ያለ ሰው አልነበረም። ነገር ግን ዋለልኝና ጓደኞቹ ወደ ኮልፌ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ማሰልጠኛ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይታሰራሉ። ዋለልኝ ከአሁን በፊት በገደብ ስለተለቀቀ እንደገና ወደ ከርቸሌ እስር ቤት ይላካል። በአዲስ አበባ ዩኒበርስቲ ማህበርና(USUAA) በብሔራዊ የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማህበር(NUEUS) በከፍተኛ አመራር አባልነት ሚና ተጫውቷል። ከአንድ ጓድኛው ጋር በተደረግ ቃለ መጠይቅ ስለዋለልኝ ይህን ተናግረዋል። በጽሁፍ ችሎታ ይደነቅ የነበረው ዶክተር እሸቱ ጮሌ ነበር። ቀጥሎ በጸሃፊነቱ የማስታውሰው ዋለልኝ መኰንን ነበር ። የቃላት አጠቃቀሙና የሐሳብ ፍስቱ(Flow) ልዩ ነበር ብለዋል። ዋለልኝ መኰንን ከእስር ቤት ከተለቀቀ በኋላ የተማሪዎቹ ልሳን የነበረው ታገል መጽሄት ታገደ። ዋለልኝ መኰንንም እንደዚሁ!! ከትምህርት ቤቱ እገዳ በኋላ፤ በወቅቱ የመንገድ ማመላለሻ አስተዳደር ተብሎ ይጠራ የነበረው መንግሥታዊ ድርጅት ሥራአስኪያጅ አቶ ሽመልስ አዱኛ ሥራ እንዲጀምር ዕድል ይሰጡታል። በዚሁ ድርጅት ሥራ እየሰራ እያለ ብርሃነ መስቀል ረዳና ሌሎች የትግል ጓዶቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ድርጅት መሥራች ጉባዔ ስብስባ በርሊን ላይ በመጥራታችው፤ ዋለልኝም በዚህ ስብስባ ላይ ለመገኘት ወሰነ። ወደ ስብሰባው ለመቀላቀል አውሮፕላን ከመጥለፍ ሌላ አማራጭ አልነበረውም። ሕዳር 29, 1965 ዓመተ ምሕረት ከጥዋቱ አንድ ስዓት ተኩል ላይ ከአዲስ አበባ ተነስቶ (በአሥመራ በኩል ወደ አቴንስ ሮም ፓሪስ) ለመሄድ የተነሳውን የበረራ ቁጥር 708 ቦይንግ ጄት አውሮፕላን፣ ዋለልኝ መኰንን፣ ማርታ መብራቱ፣ታደለች ኪዳነ ማርያም ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ጌታቸው ሀብቴ፣ ዮሐንስ ፈቃዱና ተስፉ ቢረጋ ሊያስገድዱት ሞክረው ባለመሳካቱ ታደለች ኪዳነ ማርያም ስትተርፍ ዋለልኝ መኰንን እና ሌሎቹ በጸጥታ አስከባሪዎች በተተኮሰ ጥይት ሕይዎታቸው አልፏል። አባቱ አቶ መኰንን ካሣ ከአዲስ አበባ በልጅ ልጃቸው ስለአደጋው ሁኔታ ስለተገለጸላቸው ከደሴ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ከቀዳማዊ ምንሊክ ሆስፒታል አስከሬኑን ተረክበዋል። ከአዲስ አበባ እስከ ደሴ ባለው አውራጐዳና ላይ ችግር ቢፈጥር ሃላፊነቱን አቶ መኰንን ካሣ እንደሚወስዱ በጊዜው የፀጥታው ክፍል ሃላፊ የነበሩት ባለስልጣናት ግዴታ አስፈርመዋቸው ነው ጉዞ ወደ ደሴ የጀመሩት። በደሴ ከተማ የነበረው የፀጥታ አጠባበቅ የተጠናከር ቢሆንም የወይዘሮ ስሕን ትምህርት ቤት ተማሪዎች የትግል ጓዶቹ፣ ዘመድ አዝማድ በተገኘበት በመድሃኒ ዓለም ቤተክርስቲያን በክብር አርፏል።የሚገርመው ነገር በመንግሥት ላይ ያመፅ በመባል ፍትሃት አልተደረገለትም።http://walilegnfordemocracia.com/

No comments:

Post a Comment