Monday, December 9, 2013

አገር ማለት ሰው ነው ካላችሁ!

ህዳር 29 በደረሰ ቁጥር ኢህአዴግ ሳያውቀው የሚዘምረው አንድ መዝሙር አለው፡፡ ‹‹አገር ማለት ሰው ነው….ሰው ነው ሰው ነው አገር…››፡፡ በእርግጥ እንዲሁ ላዳመጠው መዝሙሩ ይስባል፡፡ ይህ መዝሙር ኢህአዴግ ለአገሪቱ ዳር ድንበር እንደማይጨነቅ ለሚነሳበት ትችት መልስ ለመስጠት ታስቦ የተሰራ ነው፡፡ ለዳር ድንበር የሚጨነቁትን ደግሞ ‹‹ወራሪዎች›› ብሎ ለመውቀስ፡፡ በነገራችን ላይ የሞሶሎኒ ፋሽስትና የሂትለር ናዚስት ፓርቲዎች በተመሳሳይ ዜማዎች ህዝብን አወናብደዋል፡፡ስለ እውነት ባዶ መሬት የአገር ክፍል እንጅ ብቻውን አገር ሊሆን አይችልም፡፡ ሰውም ብቻውን አገር ሊሆን አይችልም፡፡ አገር አገር ለመሆን ሰው(ህዝብ)፣ መሬት፣ ዓለም አቀፍ እውቅና መንግስት ያስፈልገዋል፡፡   እናም እጠይቃለሁ!!!!!!!!

አገር ማለት ሰው ብቻ መሆን ከቻለ፣ መሬት ለአገር ምንም ካልሆነ ስለምን ለምድረ በዳው ባድመ 70 ሺህ ህዝብ (አገር) አስጨራሳችሁ?
አገርን ዓለም አቀፍ እውቅና ፖለቲካ ሳይሆን ሰው ብቻ የሚወስነው ከሆነ ለምን ኮሶቮ፣ ሶማሊ ላንድ፣ ኩቤክ፣ አብካዚያ፣ ታይዋን…..አገር ይሆኑ ዘንድ እውቅና አትሰጡም?
መሬት ሳይሆን ሰው ከሆነ አገር ስለምን ዜጎቻችን ከቤንሻንጉልና ከደቡብ ‹‹መሬታችሁ አይደለም!›› ተብለው ይባረራሉ? መሬት አገር ካልሆነ፣ ከሰው በላይ አድርጋችሁ ካላያችሁት በብሄር ስም በየጊዜው በፈለጋችሁት መልክ እየከለላችሁ አገር ያላችሁትን ሰው (ህዝብን) ማቆራረጡ ለምን አስፈለጋችሁ?
ህዝብን እያፈናቀላችሁ መሬቱን አገር ለመሰረቱት ህንዶች፣ ቻይናዎች፣ ሳውዲዎች በሲጋራ ዋጋ ስትቸበችቡ አገር ማለት ሰው መሆኑን እንዴት አላስታወሳችሁም? ህዝብ እንዲያውም መነኩሳትንና አጽማቸውን የትም ጥላችሁ መሬቱን በሀይል ስትነጥቁስ? ህዝበ ሙስሊሙ፣ ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ዲያስፖራው የሚታሰረው፣ የሚሰቃየው፣ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የሚከለከለው ሰው (አገር) ስላልሆነ ነው?
በዘቀጣችሁበት ሙስና፣ በጫናችሁት ጭቆና፣ ባሰፈናችሁት ኢፍትሃዊነት፣ ህዝብ (አገር) በኮንቴይነር፣ በባህርና ውቅያኖስ እግሬን አውጭኝ ሲል የት ነበራችሁ?
እኔ፣ እሱና እሷ እንደ ሰው (ግለሰብ) አገር መሆን ከቻልን ኢትዮጵያን ስለምን ምንነታቸው፣ ማንነታቸው በግልጽ ለማይታወቅ ‹‹ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች›› አሳልፋችሁ እንደሰጣችሁ ትፎክራላችሁ?
ለምን? ለምን? ለምን? አገርን ሳታውቁ ስለ አገር፣ ሰውን ሳታውቁ ስለ ሰው፣ ኢትዮጵያን ሳታውቁ ስለ አገራችን ታደነቁሩናላችሁ? ለምን? ለምን? ለምን?
source: freedom4ethiopian
Getachew Shiferaw

No comments:

Post a Comment