Sunday, December 8, 2013

ዴሞክራሲ ምን ይፈልጋል?




ዴሞክራሲ ሂደት እንጅ ግብ አይደለም ብለን ብንነሳም፤ የዴሞክራሲ የመጨረሻ ግቡ ግን የጋራ ሰላም (Mutual security) እና መልካም ሕይወት (Good life) እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ስለዚህም እነዚህን ዋነኛ ዓላማዎች ለማሳካት ዴሞክራሲ በዋናነት ከዜጎች እና ከፖለቲካው ተዋናዮች የሚፈልጋቸው ዋነኛ ግብአቶች አሉት፡፡

የመጀመሪያው እና ዋነኛው የዴሞክራሲ ምሰሶ፤ ሰላማዊ እና ሕግን መሰረት ያደረገ ውድድር ነው፡፡ ይህም ማለት ዴሞክራሲ ዜጎች የሚሻላቸውን አካል የሚመርጡበት ስርዓት ነውና ተወዳዳሪዎች ሰላማዊ ይሆኑ ዘንድ ዴሞክራሲ ትፈልጋለች፤ ነውጠኛ አማራጭን ዜጎች የጋራ ሰላምን በዴሞክራሲ አማካኝነት ለመቀዳጀት የሚያደርጉትን ትግል እጅግ ይጎዳዋልና፡፡ ሌላው ከፖለቲካ ተዋናዮች የሚጠበቀው ቅድም ሁኔታ ደግሞ ሕግ አክባሪነት ነው፡፡ ምንም እንኳን የፖለቲካ ተዋንያን የተሻለ ሕግ እና ስርዓት ለዜጎች ለመስጠት ቢነሱም፤ የተሻለ ሕግ እና ስርዓት ለማምጣት ያለውን ሕጋዊ ስርዓት አክብረው ቢጀምሩ ለዴሞክራሲ መጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ አዲስ ስርዓትንም ‹ሀ› ብሎ ከመጀመር ይታደጋል፡፡

እንግዲህ ሰላማዊነት እና ሕጋዊነት ከፖለቲካ ተዋንያን የሚጠበቁ ዴሞክራሲ ቅድመ ሁኔታዎች ከሆኑ፤ ከህዝቡስ ምን ይጠበቃል? የሚለው ጥያቄ ወሳኝነት ይከተላል፡፡ በህዝቡ ዘንድ በዋናነት እንዲዘጋጅ የሚጠበቀው የዴሞክራሲ ስንቅ ሰጥቶ መቀበል እና የጋራ ጥቅምን ማሰስ (Cross cutting cleavage) ነው፡፡ ይሄም ማለት በሕዝቡ ዘንድ የዴሞክራሲ መዘርጋት ለሁላችንም የጋራ ሰላም ይሰጠናል፤ ስለዚህም ከራሴ/ከቡድኔ ጥቅም ይልቅ ይሄን ለሁላችንም ጥቅም ሊሰጠን የሚችልን አካሄድ መምረጥ አለብኝ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ የጋራ ጥቅምን ከማስፋት ይልቅ መግፋትን በሚመርጥ ሕብረተሰብ ውስጥ ዴሞክራሲን መመስረት የማይቻል እንደሆነ ዘርፍ አጥኝዎች የብዙ ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ የሚያሳዩት ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም የዴሞክራሲ ዋነኛ ግብ የጋራ ሰላም (Mutual security) እና መልካም ሕይወት ነውና፡፡

No comments:

Post a Comment