Thursday, December 5, 2013

ነግ በኔ


ዛሬ በኢትዮጵያ ውስት እየደረሰ ያለው መከራና ውርደት ወቅቱን ጠብቆ ነገ በሌላ ሕዝብና መንግሥት ላይ ይደርሳል – እንደእስካሁኑ ሁሉ፡፡ይህ አነጋገር የትንቢት ጉዳይ ሣይሆን ማንም አእምሮ አለኝ የሚል የዓለም ዜጋ ሁሉ ሊረዳው የሚችል ነባራዊ እውነታና የማይሸሹት ወረፋ ነው – 

ወረፋ እስኪደርስ ያለው የጊዜ እርዝማኔ እያነሆለላቸው ብዙዎች ይሞኛሉ፡፡ ያዋጣ የነበረው አካሄድ ግን በምንም ዓይነት የልዩነት አጥር ራስን ሳያካልሉ በሰው ልጅነት ብቻ አንዱ የአንዱን ችግር ለማስወገድ መጣር ነበር፡፡ በሆነ አጋጣሚ አንድኛችን ከሌላኛችን በተለዬ ሁኔታ ወደአውሬነት በምንለወጥበትና እንደሳዑዲዎች አንድ ምሥኪን ወገን ላይ ቀን የሰጠንን ኃይልና ጉልበት በምናሳይበት ጊዜ በዝምታና በአግራሞት ማለፍ ሣይሆን ሃይ ብንልና ብናስቆም ተጠቃሚዎቹ ሁላችንም የሰው ዘሮች በሆንን ነበር፡፡ ሰዎች ግን ለዚያ አልታደልንምና የዘራነውን እንዳጨድን ዝንታለማችንን በየተራ ስናለቅስ እንኖራለን፡፡

 ወደኋላው ላይና ቋቱ ሲሞላ ግን ሁላችንም በኅብረት የምናለቅስበት ዘመን መምጣቱ አይቀርም – ያኔ ታዲያ አልቃሽም አስለቃሽም፣ ፊሽካ ነፊም አስተኳሽም … ሁሉም ተያይዞ የደም ዕንባ እንደጎርፍ ያወርዳል፡፡ የምናስቀምጠው ነገር ሁሉ የኛው ነው – ማንም አይወስድብንም፡፡ 

በባንክ የምናኖረውን ገንዘብ ሲያስፈልገን አውጥተን እንደምንጠቀምበት ሁሉ በሰዎች ላይ የምንሠራውን የግፍ መዝገብም ሁሉ የምናወራርድበት ጊዜ ሲመጣ በእጃችን የገቡ ሌሎች ምሥኪኖችን ባስለቀስነው መጠንና ከዚያም በላይ እኛም እናለቅሳለን፡፡ አሁን ግን በብረት አጥር ውስጥ የምንኖርና መቼም ቢሆን ምንም ችግር እንደማይደርስብን የምንቆጥር ወገኖች አንዳችን በአንዳችን ችግር እየተዝናናን መኖርን መርጠናል፡፡ የምንመርጠው መንገድ ሁሉ ግን አዋጭ ሊሆን እንደማይችል ከታላቁ መምህር ከታሪክ መማር በተገባን ነበር፡፡ ያለቀሱ ይደሰታሉ፤ ያስለቀሱም ያለቅሳሉ፡፡

መታሰቢያ ታደሰ
እግዚአብሄር ኢትዮጲያን ይባርክ

No comments:

Post a Comment