Thursday, December 19, 2013

ህወሓት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ጥያቄ ላይ ሊታመን አይችልም!(ሸንጎ)


ህወሓት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ
ጥያቄ ላይ ሊታመን አይችልም!
ያለፉት አራት አሥርት ዓመታት የህወሓት/ኢህአዴግ ታሪክ ያስገነዘበን ነገር ቢኖር ገና ከጅምሩ
በጠባብ ብሔረተኝነት አጀንዳ የራሱን ጥቅምና ሥልጣን የማስከበርና የማቆየት ዓላማ እንዳለው
ብቻ ነው። ይህንንም ተልዕኮውን እውን ለማድረግ የተከተላቸው ፖሊሲዎችና አካሄዶች በተለያዩ
ጊዚያት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነትና ሉዓላዊነት የሚጻረሩ ሆነው እንደቆዩ እንረዳለን።
መለስ ዜናዊና የአገዛዙ አባላት ከግልብ የፖለቲካ አመለካከት፤እንዲሁም ከገደብ የለሽ የሥልጣንና
ራስ ወዳድነት የተነሳ፤ ዕኩይ ዓላማቸውን በሥራ ላይ ለማዋል ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ተቀናቃኞች
ጋር ባደረጉት ድርድሮች የራሳቸውን ማንነት ከመካድ እስከ አገር መሸጥ የሚደርስ ሸፍጥ
ማካሄዳችው የአደባባይ ምስጢር ነው።
በተለይም በዚህ ወቅት በዋንኛነት ሊጠቀስ የሚገባው ህወሓት/ኢህአዴግ ገና ቀደም ብሎ
ከትጥቅ ትግል አጋሩ ከሻዕቢያና፤ ከፍተኛ ድጋፍና አሰተዋፅዖ ሲያደርግለት ከነበረው ከሱዳን
መንግሥት ጋር በምስጢር ያደረጉት ስምምነት ነው።የመለስና የሕወሃት/ኢህአዴግ አመራር
አባላት በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት መጠበቅ ላይ ግድ ያለመኖርና በአገሪቱ ብሔራዊ ሉዓላዊነት
ላይም ባላቸው ሥር የሰደደ ጥላቻ የተነሳ፤ ገና ከጅምሩ ከማንም የበለጠ በዋነኛነት የኤርትራ
የቅኝ ግዛት ጥያቄ ተቆርቋሪና አራማጅ ብቻ ሳይሆን የሱዳን የድንበር መሬት ይገባኛል ጥያቄም
ደጋፊና አቀንቃኝ ሆነው መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
  1በዚህም ምክንያት ነው ገና ወደ ሥልጣን ሳይመጡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በስተጀርባ የአገሪቱን
ብሔራዊ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት አሳልፈው ለመስጠት ከእነዚሁ ኃይሎች ጋር በሚስጥር
ስምምነት ላይ የደረሱት።
ይህንንም በተግባር ለማስፈፀም መለስና ህወሓት/ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከወጡ በኋላ ብዙም
ጊዜ ሳያጠፉ ምናልባትም ከዚህ ቀደም የትም ቦታ ታየቶ በማይታወቅና ለማመን በሚያዳግት
መልኩ ነበር የኤርትራን “ቅኝ ተገዢነት” የፈጠራ ታሪክ በጭፍን በመቀበል እንድትገነጠል
የኢትዮጵያ ‘ርዕሰ ብሔር’ ተብዬው ዋና አስፈፃሚ ሆኖ የቀረበው።
ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ፀረ-ኢትዮጵያ ጥፋታቸውን በመቀጠል ከኢትዮጵያ ሕዝብ በስተጀርባ
በምስጢር ከሱዳን መንግሥት ጋር ውል በመፈራረም፤ ርዝመቱ 1,600 ኪ.ሜ ስፋቱ ከ30 እስከ
50 ኪ.ሜ የሚደርሰውን በምዕራብ ኢትዮጵያ ድንበር የሚገኝ ለም መሬት ሱዳን በትግል ወቅት
ለሰጣቸው ድጋፍ እንደ ገፀ-በረከት ለማቅረብ ተስማሙ።
እዚህ ላይ ይህንን ብሔራዊ ወንጀል ልዩ የሚያደርገው ይህ ምስጢራዊ ውል ከኢትዮጵያ ሕዝብ
ዕውቅና ውጪ መፈፀሙና፤ ለመጀመሪያ ጊዜም ኢትዮጵያውያን ስለ ስምምነቱ ያወቁት ከሱዳን
ጋዜጦችና ዜና ማሰራጫዎች መሆኑም ጭምር ነው። ምንም እንኳን ህወሓት/ኢህአዴግ ለብዙ ጊዜ
ይህንን ስምምነት ማድረጉን ሲያስተባብል ቢቆይም ስምምነቱን ተከትሎ የሱዳን ሠራዊት ይገባኛል
የሚለውን የተወሰኑ የኢትዮጵያን መንደሮች በመውረር፤ ቤቶችን በማቃጠል ኗሪዎችን በማጥቃትና
አንዳንዶቹንም አግቶ ወደ ሱዳን በመውሰድ ያደረገው ጥቃት ጉዳዩን የበለጠ ይፋ እንዲወጣ
አድርጎታል።
በዚያን ወቅት በፓርላማው ውስጥ በጉዳዩ ላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምንም እንኳን የውጭ ጉዳይ
ሚኒስትሩ ስዩም መስፍን ጉዳዩን ቢክድም በኋላ ግን መለስ ዜናዊ ራሱ ካንድ ሱዳን መሪ የተነገረ
በሚመስል መልኩ ኢትዮጵያኖችን በሚኮንንና ጥፋተኛ በሚያስመስል አነጋገር ሱዳኖች ትክክለኛና
“እንዲያውም እስካሁን ስለቻሉን ትዕግሥተኞች ናቸው” በሚል መልክ ለማመን የሚያስቸግር
አሳፋሪ ንግግር ማድረጉ በአርምሞ የሚታወስ ነው።
  2 መለስ ዜናዊ ስለድንበሩም ሲናገር ከዚህ በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ መንግሥታት ያልተቀበሉትን
ኢትዮጵያን የሚጎዳ፤ ሉዓላዊነቷን አሳልፎ የሚሰጥና ተቀባይነት የሌለውን የቅኝ ግዛት ስምምነትና
ካርታ እንደሚቀበል ግልፅ አድርጎ ነበር።
ምንም እንኳን ይህ ውል ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተደበቀ ቢሆንም አገዛዙ በድንበሩ አካባቢ
በሚኖረው ሕዝብ ላይ በተለያየ መልክ ጫና በማድረግ ስምምነቱን እንዲቀበሉና ለሱዳን ወደ
ተሰጠው ክልል በመሄድ ከብቶቻቸውን ውኃ እንዳያጠጡ እነሱም በእርሻ እንዳይሰማሩ ተፅዕኖ
ሊያደርግ ሲሞክር ባካባቢው ኗሪም ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥመው ቆይቷል። ሱዳኖችም ለ100
ዓመታት የሚያናግረን ሰሚ እንኳን አጥተን ያልቆየነውን ያህል አሁን ግን በዚህ “ቅን መንግሥት”
መሬታችንን አገኘን እያሉ እየፃፉና እየተናገሩ ድንበሩን ለማካለል በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ መቆሙን በምንም መልክ ያላሳየው ጠ/ሚኒስተር
ተብዬው ኃ/ማርያም ደሳለኝም ባለፈው ሳምንት ይህንኑ ሀገራችንን የሚጎዳ የድንበር ማካለል ሥራ
ለማስጀመር የሚያስችለውን ስምምነት ወደ ሱዳን በመሄድ ተፈራርሞ መመለሱን በዜና
ማሰራጫዎች ተዘግቧል። ከኢሳያስ አፈወርቂና ሻቢያም ጋር ቢሆን ተመሳሳይ ሴራ እያውጠነጠነ
እንደሆነ ተጋልጧል።
አንዳንዶች ከህወሓት/ኢህአዴግ ታሪካዊ አመጣጥ በመነሳት ይህን ያሁኑን ድርጊቱን የኢትዮጵያን
ሉዓላዊነት የማስደፈር አጀንዳው ቀጣይና አንዱ አካል አድርገው በመቁጠር ብዙም የሚያስገርም
ሆኖ ባያገኙትም፤ ይህንን የመሰለውን ይቅር ሊባል የማይችል አፄ ዮሐንስ ሕይወታቸውን
የሰዉበትና አፄ ቴዎድሮስ ደማቸውን ያፈሰሱለት የኢትዮጵያ አካል በፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች
እንደ ቀልድ አሳልፎ ሲሽጥ ትውልድ ይቅር ሊለው የማይገባ ብሔራዊ ወንጀልና ክህደት በመሆኑ
በጥብቅ ሊወገዝ ይገባዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ይህንን የአገርና የግዛት አንድነትን የሚያህል ትልቅ ጉዳይ
ከሕዝብ ዕውቅና ውጪ አሳልፎ ለመስጠት የሚደረገውን የመጨረሻ ሰዓት መሯሯጥ በጥብቅ
ያወግዛል።
  3 ከዚህ በፊት በነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥታት ተቀባይነት ባላገኘ ውል የኢትዮጵያን ብሔራዊ
ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ የድንበር ማካለል ስምምነት በምንም መልኩ በሕዝባችንም ሆነ በቀጣይ
መንግሥታት ተቀባይነት እንደማይኖረው ሸንጎው በጥብቅ ለማስገንዘብ ይወዳል።
በተጨማሪም ህወሓት/ኢህአዴግ ከሕዝብ ጀርባ የሚያደርገው ሽፍጥና ደባ የተመላበት ስምምነት
የህዝብ አወንታን ያላገኘ የአገሪቷን ሉዓላዊነት የሚያስደፍር ወንጀልና ክህደት በመሆኑ ሸንጎው
እያወገዘ፤ በድብቅ የሚደረገው ስምምነትና የድንበር ማካለል ስራ ላካባቢው ችግር ዘላቂ መፍትሄ
የሚሰጥ ሳይሆን ማለቂያ የሌለው ውጥረትና ግጭት እንዲቀጥል አስተዋፅዖ የሚያደርግ አርቆ
ማስተዋል የጎደለው ተግባር እንደሆነ ሁሉም እንዲገነዘበው ያሳስባል።
የድንበር ጉዳይ መፈታት ያለበት ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና በተለይም
በጉዳዩ ከዚህ በፊት ጥናት ያካሄዱ ምሁራን ሙሉ ተሳትፎ ባለበትና፣ የኢትዮጵያን ህጋዊ
ታሪካዊና ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅና አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን በሚያስከብር መልክ መሆን
እንዳለበት ሽንጎው በጥብቅ ያምናል።
በዚህም ምክንያት ለአገሩ ቀናዒ የሆነ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ተደራጅቶ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ
ይሄንን ቀጣይ የሕወኃት/ኢህአዴግ ፀረ-ኢትዮጵያ ክሀደት በፅኑ እንዲያወግዝ፤ አጥብቆም
እንዲቃወምና እንዲታገል ሸንጎው በጥሞና ያሳስባል።
በተጨማሪም ባሁኑ ሰአት በሀገራችን የምእራብ ድንበር ብቻ ሳይሆን በሰሜኑና በሰሜን ምስራቁም
በኩል ከኢሳያስ አፈወርቂና ሻዕቢያ ጋር ቀደም ሲል የተጀመረውን ጸረ-ኢትዮጵያ ሴራ በሻዕቢያ
አሸናፊነት ለማጠናቀቅ የሚደረገውንም ሩጫ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲያውቀውና አምርሮ
እንዲታገለው ጥሪያችንን ደግመን እናቀርባለን።
የኢትዮጵያን ህጋዊ ታሪካዊና ብሄራዊ አንድነት እንዲሁም ጥቅም ማስጠባቅ የሁሉም ዜጋ ታሪካዊ
ግዴታ ስለሆነ አባቶቻችንና እናቶቻችን እንዳደረጉት ዛሬም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻችንን
  4ወደ ጎን ትተን ይህ ታላቅ ሴራ እንዲከሽፍ በነጠላም ይሁን በቡድን በሚቻለው መንገድ ሁሉ
የተጠናከረ ትግል እንድናደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን ።
የህወሓት/ኢህአዴግን ሌላ ዙር የብሔራዊ ሉዓላዊነት ክህደት እናወግዛለን! እንታገለውማለን!
የአምባገነኖችና የፀረ-ኢትዮጵያ ሀይሎች ዕድሜ ዘላቂነት የለውም!
የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት በቋራጥ ልጆቿ ትግል ይከበራል!
Source-http://www.abugidainfo.com/

No comments:

Post a Comment