Sunday, December 8, 2013

ኔልሰን ማንዴላ በሕይወት ቢለዩንም በመንፈስ አብረውን ይቆያሉ ( የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ህዝብ ግንኙነት )


በአፓርታይድ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በዩ. ኤስ. አሜሪካ ጭምር ሽብርተኛ ተብለው ሲሳደዱ፣ ሲታሰሩና ሲሰቃዩ የሕይወታቸውን አጋማሽ የጨረሱ፤ በመሣሪያ የታገዘ አመጽንና ሕዝባዊ እምቢተኝነትን አጣምሮ የያዘ ሁለ-ገብ ትግል በመምራት ለአፓርታይድ አገዛዝ ማብቃት ከፍተኛ ድርሻ ያለው የትግል አስተዋጽዖ ያደረጉ፤ ለመላው ዓለም የነፃነት ታጋዮች አርአያ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ አረፉ።
ኔልሰን ማንዴላ የነፃነት ትግልን በግንባር በመሰለፍ መርተዋል። ኢትዮጵያ ድረስ በመምጣት ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው ዘረኛዉን የፕሪቶሪያ አገዛዝ በመሣሪያ ታግለዋል። የእሳቸው ጠመንጃ ማንሳት ለበርካታ ወጣት ታጋዮች አርዓያ ሆኗል። እስር ቤት በቆዩባቸው 27 ዓመታት ደግሞ የድርጅታቸውንና የትግሉን አመራሩ ለጓዶቻቸው በመተው እርሳቸው ለነፃነትና ለእኩልነት በመታሰርና ስቃይን በመቀበል ትግሉን መርተዋል። በዚህም ምክንያት በትግል ሜዳም በእስር ቤትም መሪ እንደሆኑ የዘለቁ ታላቅ አፍሪቃዊ ናቸው።
ከነፃነት በኋላ ደግሞ ኔልሰን ማንዴላ በሕዝብ ነፃ ፈቃድ የተመረጡ የአዲሲቷ ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንትነት ሆነዋል። በየምርጫው ተወዳድሬ አሸንፌ በፕሬዚዳንትነት ልቀጥል ሳይሉ በአፍሪቃ ባልተለመደ ሁኔታም አንድ ዙር ብቻ አገልግለው ደግመው ላለመወዳደር ወስነው በጊዜ ሥልጣናቸውን በመልቀቅ መርተዋል። በመሆኑም ኔልሰን ማንዴላ ሥልጣን ላይ ሆነውም ሥልጣን ለቅቀውም መሪ መሆን የቻሉ ድንቅ አፍሪቃዊ ናቸው።
ኔልሰን ማንዴላ ታላቅ የነፃነት አርበኛ፣ ታላቅ የለውጥ አራማጅ፣ ታላቅ መምህር እና ታላቅ የእርቅ ሰው ነበሩ። ዛሬ ዓለም እኚህን ታላቅ አፍሪቃዊ አጣች።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በኔልሰን ማንዴላ ሕልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልፃል። ከእንግዲህ ማንዴላን የምናስባቸው ከእሳቸው ተሞክሮ የምንማረው ሲኖር ነው። በዘረኝነት እየተጠቃን ላለነው ኢትዮጵያዊያን የማንዴላ ትምህርት ሕያው ሊሆን ይገባል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ዘረኝነትን በጽናት የመታገል ሆኖም ግን ይቅር ባይ የመሆንን እሴቶች ተግባራዊ በማድረግ ማንዴላ በሕይወት ቢለዩንም በመንፈስ ሁሌም አብረውን እንዲኖሩ እናድርግ ይላል።

No comments:

Post a Comment