Sunday, December 15, 2013

ሁለገብ ትግል – ከኔልሰን ማንዴላ ጋር የምንጋራው የትግል ስትራቴጂ ግንቦት 7 ለፍትህና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ


ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄም በኔልሰን ማንዴላ ዜና እረፍት የተሰማውን ሐዘን በመግለጽ መግለጫ ያወጣ ቢሆንም የትግል ተሞክሯቸው ለአገራችን ስላለው ጠቀሜታ ተጨማሪ ቁም ነገሮችን ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል። ኔልሰን ማንዴላንና የትግል ጓዶቻቸው መሣሪያ እስከማንሳት ያደረሳቸው የደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ አገዛዝ ዋነኛው መገለጫው የባንቱስታን ሕግ ነበር። በዚህ ህግ መሠረት ደቡብ አፍሪቃ ዘርን መሠረት ያደረጉ አስር “ባንቱስታ” የተሰኙ “ራስ ገዝ” ግዛቶች ተቋቁመው ነበር። ያኔ በደቡብ አፍሪቃ አገዛዝ ሥር በነበሩ የደቡብ ምዕራብ ግዛቶች ደግሞ ሌላ አስር ባንቱስታዎች ነበሯቸው።
በእያንዳንዱ ደቡብ አፍሪቃዊ መታወቂያ ባንቱስታው እንዲገልጽ ህጉ ያስገድዳል። የአንዱ ባንቱስታ ነዋሪ ያለልዩ ፈቃድ ወደሌላው ባንቱስታ መሄድ አይችልም። ከዚህም ሌላ ለነጮች ብቻ በተከለሉ ቦታዎች ጥቁሮች ለሥራ ካልሆነ በስተቀር ለሌላ ማናቸው ተግባር እንዳይገኙ ህጉ ያዛል። አፓርታይድ የደቡብ አፍሪቃ ዜጎችን በየዘር ክልሎቻው ውስጥ አጉሮ አገራቸውን እስር ቤታቸው እንዲሆን አደረገው። ይህንን ለመቃወም ኔልሰን ማንዴላ እና የወቅቱ ታጋዮች በመጀመሪያ ሰላማዊ ትግልን ሞከሩ፤ ያ አላዋጣ ሲል መሣሪያ አነሱ። በአሁኑ ሰዓት ባንቱስታን መሰል የክልል አስተዳደር ያለው በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። ልክ በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪቃ እንደነበረው ሁሉ የኛም መታወቂያዎች ዘራችንና ክልላችንን ይገልፃል። በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪቃ እንደነበረው ሁሉ እኛም ከክልላችን ውጭ ተንቀሳቅሰን መሥራትና መኖር አንችልም።
ከቤንሻንጉል-ጉሙዝ እና ከደቡብ ክልሎች ተፈናቅለው ለጎዳና ኑሮ የተዳረጉት የአማራ አርሶ አደሮች የዚህ ፓሊሲ ሰለባዎች ናቸው። ኔልሰን ማንዴላ እና ድርጅቱ ኤ. ኤን. ሲ. በሰላማዊ ትግል ብቻ አፓርታይድን ማስወገድ እንደማይቻል የተገነዘቡት ከስዊቶ እልቂት ነው። በስዊቶ እልቂት 176 ዜጎች እንደተገደሉ ይነገራል። እኛ አገር ብዙ ስዌቶዎች አሉ። በበደኖ፣ በአዋሳ፣ በሀረር፣ በጋምቤላ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በአዲስ አበባ እና በሶማሊያ የደረሱት እልቂቶች እያንዳንዳቸው የስዌቶን እልቂት ያክላሉ። በዚህም ላይ በሰቲትና በሁመራ የተደረገው ስልታዊ የዘር ማጥራት፤ የወጣቶች ያላባራ ስደት የዚሁ ፓሊሲ አስከፊ ውጤቶች ናቸው። ሰላማዊ ትግል ብቻውን የደቡብ አፍሪቃ ዘረኛ አገዛዝን ማስወገድ አልቻለም። ሰላማዊ ትግል ብቻውን ወያኔ በአገራችን ላይ የጫነብን ዘረኛ አገዛዝ እንዲያበቃ ማድረግ ይችላል ብሎ ማመን አዳጋች ነው። ስለዚህም ነው ማንዴላ እንዳደረገው ሁሉ ግንቦት 7ም ሁለገብ ትግልን እንደ ትግል ስትራቴጄ ለመያዝ የተገደደው። ሁለገብ ትግል ሕዝባዊ አመጽ እና ሕዝባዊ እምቢተኝነትን አጣምሮ መያዝ ይጠይቃል። ሁለገብ ትግል መጨከንን ያም ሆኖ ለእርቅ አንድነት ለሀገር እና ለወገን የጋራ ጥቅም መሥራትን ይጠይቃል። ሁለገብ ትግል ዘረኝነትን በጽናት የመታገል ሆኖም ግን ይቅር ባይ መሆንን ይጠይቃል።
ግንቦት7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሁለገብ የትግል ስትራቴጂን በአማራጭነት ሲወስድ ከወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ጋር ተመሳሳይ የሆነውን የደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ ሥርዓትን ለመለወጥ የነበረውን ፍቱንነት በጥልቀት በማጤን ነው።
ዘላለማዊ እረፍት ለኔልሰን ማንዴላ
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment