የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ጽ/ቤት (UNHCR) በኢትዮጵያ የሚገኙ 3 800 ስደተኞችን ወደ ሶስተኛ ሀገር ሊያዛውር ነው፡፡
ወደ አሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የሚዛወሩት ስደተኞች ከዚህ በፊት ይህን መሰል ማዛወር ባልተካሄደባቸው የቶንጎ፣ በረኸሌና ቦኮልማንዬ የስደተኛ ጣቢያዎች የሚገኙ ስደተኞች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ስደተኞችን ወደ ሶስተኛ ሀገር የማዛወር ዘመቻ በኢትዮጵያ መንግስት፣ በዓለማቀፉ የስደተኞች ተቋም (IOM) እና UNHCR ትብብር እ.አ.አ በ2006 በተለይ ለኤርትራውያን ስደተኞች የተጀመረ ሲሆን የአሁኑ የሚያተኩረው ግን ለሴቶች፣ ህጻናት፣ እናቶችና የድብደባ ሰለባ ለሆኑ ስደተኞች ይሆናል ተብሏል፡፡
በሳዑዲ ተከስቶ የነበረውን ቀውስ ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን…ለመሆኑ በየሀገሩ ያሉ ዜጎቻችን ብዛት ምን ያህል ነው ብለው ሲጠይቁ ከርመዋል፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በውል አይታወቅም፡፡
…የተጠናከረ የምዝገባ ስርዐት ያለመኖር፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ፣ እንዲሁም ለተለያየ ምክንያት ውጭ ሀገር ሄዶ የሚቀረውና በህገወጥ መንገድ የሚጓዘው ቁጥሩ ስለማይታወቅና፣ ለበርካታ አስርት አመታት በቆዩበት የውጭ ሀገራት የሚሞተውና የሚወለደውን ቁጥር በትክክል ማወቅ ስለማይቻል፣ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በየሀገሩ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር በተመለከተ ከግምት የዘለለ የተጨበጠ አሀዝ ይኖረናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ለመሆኑ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ የሌሎች ሀገራት ስደተኞች ምን ያህል እናውቅ ይሆን…ምን ያህል የጎረቤት ሀገር ስደተኞች ናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ያሉት…? አርብ ዕለት የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚጠቁመው ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ5 000 በላይ የሚሆኑ ስደተኞችን ከተጎራባች ሀገራት ተቀብላለች፡፡ ይህም በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያሉትን የጎረቤት ሀገር ስደተኞች ቁጥር 427 000 ያደርሰዋል፡፡
በቅርብ ጊዜ ወደ ሀገራችን የገቡት ስደተኞች በአብዛኛው ከኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የመጡ ሲሆን…በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ 240 000 ሶማሊያውያን፣ 81 000 ኤርትራውያንና 70 000 የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ይገኛሉ፡፡ የተቀሩት 36 000 ደግሞ ከኬንያ፣ ሱዳንና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የመጡ መሆናቸውን የUNHCR ሪፖርት ያስረዳል፡፡