Thursday, December 5, 2013

የበንቲ የዘመመች ህይወት በአሜሪካ (ከእየሩሳሌም አርአያ)

በንቲ ይባላል፤ ሻሸመኔ ተወልዶ ያደገው የ47 አመቱ ጎልማሳ በንቲ አሜሪካ ከመጣ 13 አመት ሆኖታል። የዲግሪ ምሩቅ ሲሆን በሻሸመኔ መምህር ሆኖ ይሰራ ነበር። ዲቪ ደርሶት ዲሲ መጣ። ምንም አይነት ሱስ የለበትም፤ ሌላው ቢቀር ቢራ እንኳ አይቀምስም። በመደብሮችና በጋዝ እስቴሽን ተቀጥሮ ይሰራ ነበር። ቤተሰብ ያልመሰረተው ይህ ወገን ከአራት አመት በፊት ህይወቱ ቀውስ ገጠማት። አእምሮው ተቃወሰ። ጓደኞቹ ብዙ ጥረት እንዳደረጉ የሚያውቁት ይናገራሉ። በተለይ ብሩህ አእምሮ እንዳለው የሚያውቁት ሲናገሩ በሃዘን ጭምር ነው። በየጎዳናው ለብቻው ሲለፈልፍ ውሎ በየጎዳናው የሚያድረው በንቲ በቅርቡ አገኘሁት። ሲናገር ፈጠን..ፈጠን ይላል። ሰላምታ ሰጥቼው በእርጋታ ተጠጋሁት። ለምጠይቀው ጥያቄ የጎሪጥ እያየኝ ነበር የሚመልሰው። ከየት አካባቢ እንደመጣና ስሙን ነገረኝ። « ምን ሆነህ ነው?» ስል ጠየኩት። እርሱም « አላኖር አሉኝ፤ ስራዬ ቦታ ያሉት ከሲ.አይ.ኤ ጋር ሆነው ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ። ..እ..እ…እ አሁንም ይከታተሉኛል፤..እ..እ..እ.. አውቄያቸዋለሁ። ቆይ ግን…ምን አድርጌያቸው ነው?…እ..እ..እ.. ቆይ አንተ ማነህ?…ሲ.አይ. ኤ …» ፈጠን ባለ ንግግሩ የሰጠኝ ምላሽ ነበር። ..እጅግ አዘንኩ። የበንቲ ብሩህ አዕምሮ እንዲህ መሆኑ የሚያውቁትን ብቻ ሳይሆን የማያውቁትን ወገኖች ጭምር የሚያስቆጭና የሚያሳዝን ነው። በየአገሩ በስደት እየተዋረደ፣ እየተገደለ፣ እየተሰቃየ፣ ውቂያኖስና በረሃ እየበላው፣ አገርና ወገን እንደሌለው በየጎዳናው እየተንከራተተ የሚገኘው ሃበሻ ወገኔ…ፈጣሪ ይድረስለት! ከማለት ውጭ ምን ይባላል!?..የበንቲ የዘመመች ህይወት ፈጣሪ ያቃናት!!
( በፎቶው በንቲ ጎዳና ላይ ሆኖ…)
source:freedom4ethiopian

No comments:

Post a Comment