Wednesday, December 4, 2013

ሳውድ አረቢያ የውጭ ዜጎችን ማስወጣቱዋን እንደምትቀጥል አስታወቀች


1460039_234136773416524_1739055042_nDec 4,2013
ህዳር ፳፭(ሃያ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካለፈው ወር ጀምሮ ህጋዊ ወረቀት የላቸውም በሚል የውጭ ዜጎችን ማባረር የቀጠለችው ሳውድ አረቢያ፣ ከአለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ትችት ቢደርስባትም፣ ዜጎችን ማስወጣት እንደምትቀጥል አስታውቃለች። አረብ ኒውስ እስካሁን በተወሰደው እርምጃ 126 ሺ ሰዎች ከአገሪቱ መውጣታቸውን ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ 90 ሺ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መግባታቸውን ገልጸዋል።
አረብ ኒውስ አንድ ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ውጭ ዜጎችን የማስወጣት እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል። ኢትዮጵያውያን በአለማቀፍ መድረኮች ያሰሙትን ተቃውሞ ተከትሎ የሳውዲ የጸጥታ ሀይሎች በኢትዮጵያውያን ላይ የሚወስዱትን እርምጃ ቢቀንሱም፣ አሁንም ግን ከ40 ሺ ያላነሱ እስረኞች በእየሰር ቤቶች ወንጀለኞች ተብለው ታስረው እንደሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን በአረብኛ የሚታተሙ ጋዜጦችን በመጥቀስ ተናግረዋል።
 አረብ ኒውስ ዛሬ ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ ከወጡ በሁዋላ ወንጅል በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል ብሎአል።
ሂማውን ራይትስ ወች ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያውያንን ለማስወጣት ያቀደው የሳውዲ መንግስት፣ እርምጃ ከመውሰዱ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ ” ኢትዮጵያውያንን የሚያጥላላ ዘገባዎችን ያሰራጭ እንደነበር መጥቀሱ ይታወቃል። የሳውዲ ጋዜጦች ኢትዮጵያውያንን ማጥላላት መቀጠላቸው የሳውዲ መንግስት በሂደት ለሚወስደው እርምጃ ጋዜጦቹ ከአሁኑ መከላከያ እያዘጋጁለት ነው በማለት በሳውዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።
አሁንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወረቀት የላቸውም በሚል እንደሚባረሩ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የሳውዲ መንግስት የምህረት አዋጁን ሊያራዝም ይችላል በሚል ወደ አገር ለመመለስ እአመነቱ እንደሆን ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ በተለይም በጅዳ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ተመሳሳይ ከአገር የማስወጣት ዘመቻ ሊካሄድ እንደሚችል የደረሰን መረጃ አመልክቷል። በጂዳ ሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሳይዘናጉ አጋጣሚውን በመጠቀም ቶሎ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያነጋገርናቸው ሰዎች መክረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውንም የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። መንግስት ይህን ያክል ህዝብ በአንድ ጊዜ ለመቀበል አቅም እንደሌላው እየገለጠ ይገኛል።

No comments:

Post a Comment