Sunday, December 15, 2013

የአኝዋክ ጎሳን እልቂት ችግር ጉዳይ ከባዕዳን እጅ እንዲወጣ የኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል፣ የአቶ ኦባንግ ሜቶ ክቡር ተግባርም ሊደገፍ ይገባል።ማስታወሻው የአቶ ኦባንግ ሜቶን ቪድዮ ቃለመጠይቅ ይዟል።

አቶ ኦባንግ ሜቶ በጋምቤላ አኝዋክ ጎሳ ላይ በጅምላ እልቂት የተፈፀመበት እና ከ 400 በላይ አኝዋኮች የተገደሉበት( ታህሳስ 13/2003 ዓም እ ኤ አቆጣጠር) አስረኛ ዓመቱን ደፍኗል።በተለያዩ ወገኖች ስለ እልቂቱ የሚዘገቡት ዘገባዎች የድርጊቱ እጅግ ዘግናኝነት ያወሳሉ።ጉዳዩን ነፃ የዲሞክራሲ ስርዓት በሀገራችን ቢኖር ኖሮ በግልፅ ውይይት ከእየጎሳው የተውጣጡ ሽማግሌዎችን በማደራጀት በካሳ እና በይቅርታ በጉዳዩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ወንጀለኛ ባለስልጣትና (በየትኛውም የስልጣን እርከን ላይ ቢሆኑ) ለፍርድ እንዲቀርቡ በማድረግ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በደሉን ለመዝጋት መሞከር ከአስተዋይ መንግስት የሚጠበቅ ተግባር ነበር።ይህ ግን አልሆነም።ይልቁን በመንግስት በኩል ችግሩን የባሰ ማድበስበስ እንደአማራጭ ተወስዷል። ይህ እልቂት ከኢትዮጵያውያን ይልቅ በባዕዳን ብዙ ሲባልለት ይሰማል።ሆኖም ግን የእራሳችንን ችግር እና የሰብአዊ መብት ጉዳይ በተገቢው መንገድ ማሰብ መዘከር የሚገባን እኛው ነን።ባዕዳን ጉዳዮችን የሚያነሱበት መንገድ እራሱን የቻለ ችግር ይዞ ይመጣል። ምክንያቱም ችግሮቻችንን፣ህመማችንን እና ቁስላችንን የሚነግሩን ከእራሳቸው ስልታዊ ጥቅም አንፃር ነው።በመሆኑም በተለይ በባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአኝዋክን እልቂት ሻማ በማብራት ከተጎዱት ጎን በመሆን ማፅናናት እና በመሳሰሉት መርሃግብሮች ማሰብ የወቅቱ አንገብጋቢ ተግባራቸው መሆን ይገባዋል። አቶ ኦባንግ ሜቶ በጋምቤላ አኝዋኮች ላይ የተፈፀመውን ግፍ ለዓለም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከሚያሰሙት መካከል ናቸው።አቶ ኦባንግ ጉዳዩን የሚያነሱበት ጥግ እራሱ ከጎሳ ጉዳይ አውጥተው ”ችግሩ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ችግር ሲፈታ የጋምቤላውም፣ የአፋሩም ወዘተ ችግር ይፈታል” ብለው የሚያምኑ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው።አቶ ኦባንግ ሜቶ ይህንን ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር ”የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ” የተሰኘ ብሔራዊ አላማ ያለው ድርጅት መስርተው ይንቀሳቀሳሉ። የአኝዋክ ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው።ከዋሽግተን እስከ አውስትራልያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቢያንስ ይህንን እልቂት ሻማ በማብራት መዘከር ይገባቸዋል።በሀገርቤትም ያሉ ችግሩ መነሻው ከጎሳ ግጭት ተነስቶ መንግስት ወገን የያዘበት ጉዳይ መሆኑ ከትውልድ ወደትውልድ ሲቆይ ይዞ የሚመጣው የእራሱ የሆነ ቅርፅ በተለይ ባዕዳን በአካባቢው ካላቸው የሀብት ፍላጎት አንፃር ለማወሳሰብ መጣራቸው ስለማይቀር የሲቪል ማህበራት እና የሃይማኖት ተቅዋማት ችግሩን በሽምግልና ለመፍታት ቢያንስ ሂደቱን ዛሬ መጀመር ይገባቸዋል። ከእዚህ በታች ባለ ቪድዮ ላይ የተከበሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ ስለ ኢትዮጵያ ይናገራሉ።ቃለ መጠይቁ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት) ”ምን አለሽ መቲ” ከተሰኘ መርሃ ግብር የተወሰደ ነው።

No comments:

Post a Comment