Sunday, December 15, 2013

ለባለስልጣናት እንጸልያለን፤ ግፍን ግን አንታገስም ! ግርማ ካሳ


December 15/2013

በቅርቡ በአቶ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ላይ ጠንካራ ትችት ያዘለ ጽሁፍ ለአንባቢያን አቅርቤ ነበር። አዉራምባ ታይምስ ጽሁፌን «What’s the hell is wrong with Haile Mariam Desalegn”  በሚል ርዕስ  ነበር ለአንባቢያኑ ያቀረበዉ። ይህ  ርዕስ ፣  የአዉራምባ ታይምስ ኤዲተር ምርጫ እንጂ የኔ እንዳልሆነ በቅድሚያ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ።

አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ብዙዎች እንደ «እግዚአብሄር ሰው» ይቆጥሯቸዋል። በየቀኑ ጸሎት እንደሚያደርጉ፣ መጽሃፍ ቅዱስን እንደሚያነቡም ይናገራሉ። እርግጥ ነዉ፣ ሰዎች ጸሎት ሲያደርጉና መጽሃፍ ቅዱስ ሲያነቡ፣  መልካም ነዉ። ነገር ግን ጸሎት ማድረግና መጽሃፍ ቅዱስ ማንበብ፣ በራሱ የእግዚአብሄር ሰው ያሰኛል ብዬ አላስብም። ቄስ፣ ወንጌላዊ፣ ፓስታር፣ ጳጳስ ..መሆን የእግዚአብሄር ሰው አያሰኝም። መስቀል ይዞ መዞር፣ በያሬዳዊ ዜማ ቅኔ መዝረፍ፣ በልሳን መጸለይ ….የእግዚአብሄር ሰዉነት መመዘኛ አይደለም።
አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የተባረኩ ሴት ልጆች አሏቸው። ልጆቻቸው፣ የሚኒስቴር ልጆች ሆነዉ እያሉ፣ ሳይኮሩ፣ ከሌሎች በላይ ለመሆን ሳይሞክሩ፣  በሚሄዱበት ቤተ ክርስቲያን፣ እሁድ ከአምልኮ/ቅዳሴ  በኋላ፣  ሻሂ እያፈሉ ምእመናንን እንደሚያስተናግዱ አንብቢያለሁ። በአባታቸው ስልጣን፣ በሶሻል ስታተሳቸው ሳይመኩ፣ እራሳቸዉን አዋርደዉ፣  ሌላዉን ማገለገል መቻላቸዉ፣ በርግጥ የልጅ ትልቅ መሆናቸውን ያሳያል። የእግዚአብሄር ሰዉነት መመዘኛ እንግህ ይሄ አይነቱ ትህትና የተሞላበት ተግባር ነዉ። (የአቶ ኃይለማሪያም ባለቤት ወ/ሮ ሮማንም፣ ከአንድ አመት በፊት ቀዳማዊ እመቤት ከነበሩት የሰማይና ምድር ያህል የሚራራቁ፣   እንደ ቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ዉብአንቺ ቢሻዉ፣ ትሁትና ሰው አክባሪ እንደሆኑ ይነግራል )

አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ። አንድ ሰው ከኢያሪኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ ወንበዴዎች አገኙትና በሕይወትና  በሞት መሃከል እስኪሆን ድረስ ደብድበዉት ሄዱ። ሃዘኔታና ርህራሄ የሌላቸው፣ ሌሎች ሲሰቃዩና ሲጎዱ ምንም የማይመስላቸው፣ የሰው ልጅ ስብእናና ክብር እንደ መጫወጫ ካርታ የሆነባቸው፣ ሰዉን በዉሸት ክስ የሚያስሩ፣ እየተኮሱ የሚገድሉና የሚደበድቡ፣ በሰላማዉያን ላይ ሽብር በመንዛት፣ ሰዎች  በሰላም ወጥተዉ በሰላም እንዳይገቡ፣ የፈለጉትን እንዳይጽፉና እንዳይናገሩ፣ በአገራቸው እንደ ስደተኖች እንዲሆኑ የሚያደርጉ፣ እያስፈራሩ ሌላዉን የሚያሸማቅቁ፣ የዘመናችን «ወንበዴዎች» በአገራችን ኢትዮጵያ ብዙ አሉ። እንደዉም በስፋት በየሬዲዮና ቴሌቭዥኑ የምንሰማዉ እነርሱን ነዉ።
በመንገድ ዳር የወደቀውና የተደበደበው፣ የሚረዳው ፈልጎ እያቃሰተ ሳለ፣  ድንገት አንድ ቄስ/ፓስተር በመንገድ ዳር አለፉ። ካባ ለብሰዋል። በታላላቅ መንፈሳዊ ጉባኤዎች የእግዚአብሄርን ቃል የሚያስተምሩ፣ መጽሃፍ ቅዱስ የሚያነቡና ፣ የ«እግዚአብሄር ሰው» የሚባሉ ናቸው።  ነገር ግን የቆሰለዉን ሰው ባዩ ጊዜ እንዳላየ ሆኑ። መንገድ ቀይረው ፣ ለተገፋዉና ለተጎዳው እጃቸውን ሳይዘረጉ ጉዟቸውን ቀጠሉ። ትንሽ ቆይቶም አንድ ሌዋዊ (ዲያቆን)፣ ትንሹ የ«እግዚአብሄር ሰው»  መጣ። እርሱም እንደ ቄሱ እንዳላየ ሆነ አልፎ ሄደ።

ሳምራዊያን የሚባሉ ነበሩ። እግዚአብሄርን እንደማያውቁ ሐጢያተኞችና የረከሱ  ተደርገዉ የሚቆጠሩ።  ታዲያ አንድ ሳምራዊ፣  በወንበዴዎች ተደብድቦ የወደቀዉ ሰው ባለበት መንገድ አለፈ። ቁስለኛዉን ሲያይ ቆመ። ከበቅሎው ወረደ። ተጎነበሰ። ከአንገቱ ሰዉዬን ደግፎ፣ የያዘዉን ወይን ጠጭና ዘይት በሰዉዬዉ ቁስል ላይ አፈሰሰ። ሽሚዙን ቀደደና የሰዉዬዉን ቁስል አሸገ። ሰዉዬን ተሸክሞ በበቅሎው ላይ ጭኖ፣  እርሱ ግን በእግሩ፣  አብረው መንገድ ጀመሩ።  ቁስለኛዉን ወደ አንድ ሆቴል ቤት ገንዘብ ከፍሎ አሳረፈ። አስገራሚ ፍቅር ! አስገራሚ ሰብዓዊነት ! አስገራሚ ርህራሄ ! ይህ ታሪክ፣  ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣  የእግዚአብሄር ሰዉ፣  ምን ማለት እንደሆነ ለማስተማር የተናገረው ግሩም ታሪክ ነዉ። ቄሱ፣ ወይንም ዲያቆኑ ሳይሆኑ፣  «የእግዚአብሄር ሰዉ አይደለም» ተብሎ ይቆጠር የነበረው ሳምራዊዉ ነበር፣  በአምላክ ሚዛን የእግዚአብሄር ሰው የተባለው።

በመጽሃፍ ቅዱስ ፣ ኢሳያስ 1፡ 16 እንደተጻፈው፣ እግዚአብሄር ምን ያህል የፍትህ አምላክ እንደሆነ፣ ሲናገር «መባዎቻችሁንና ሰንበታችሁን፣ በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወደዉም። በደልንም የተቀደሰዉንም ጉባኤ አልታገስም። መባዎቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች። ሸክም ሆነዉብኛል። ልታገሳችሁ ደክሜያለሁ።  እጆቻችሁን ወደ እኔ ብትዘረጉ፣ አይኔን ከእናንተ እሰዉራለሁ። ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም …. ፍርድን ፈልጉ። የተገፋዉን አድኑ። ለድሃ አደጉ ፍረዱለት፤  ስለመበለቲቱም ተሟገቱ። » ነበር ያለው። ከሚደረጉ ዉጫዊና ሃይማኖታዊ ስርአቶች በላይ፣ እግዚአብሄርን የሚያስደስተው፣  የሰዉ ልጆች ደህንነትና ስብእና ነዉ።   አስር ሺህ ቅዳሴዎችና መንፈሳዊ ጉባኤዎች ይልቅ ፣ አንድን ሰው ከወደቀበት ማንሳት፣ አንድን በግፍና በዉሸት የታሰረን ሰው ማስፈታት፣ አንድ የተገፋና የተጮቆነን ሰው ቀንበር መስበር፣ አንድን ሰዉ ማዳን፣  በጌታ ፊት የበለጠ ክብር አለው። የእግዚአብሄር ሰው መሆን ማለት፣  ለፍትህ መቆም ማለት ነዉ። የእግዚአብሄር ሰው መሆን ማለት  ሙግት መፍጠር (መታገል) ማለት ነዉ። ምን አይነት ሙግት ?  የተቀደሰ ፣ ስድብና ጥላቻ የሌለበት፣  ሰላማዊ የሆነ፣  ለፍትህ የሚደረግ ሙግት!
በአገራችን ኢትዮጵያ ያሉ፣ ልንታገልላቸው ወይንም ልንሟገትላቸው የሚገባ  «መበለቶች» ብዙ ናቸው። ገዢዎች ከሚፈልጉት ዉጭ በመናገራቸው፣ እዉነትንና እኩልነትን በመስበካቸው ፣ በዉሸት ክስ፣  «ሽብርተኞች» ተብለው በወህኒ የተወረወሩ፣ ፍርድና ፍትህ የተነፈጉ ሁሉ «መበለቶች» ናቸው።  ሙስሊም ሊሆኑ ይችላሉ፣  ከርስቲያኖች ሊሆኑ ይችላሉ! ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወላይታ ሊሆኑ ይችላሉ! ጉዳዩ የሰብአዊነት እንጂ የሃይማኖት ወይንም የዘር አይደለም።

ለምሳሌ እነ እስክንደርን እንዉሰድ። በግለሰብ ደረጃ እስክንድር ነጋን እና አንዱዋለም አራጌን አውቃቸዋለሁ። ብዙ ጊዜ በአገራችን ዙሪያ የተለያዩ ሃሳቦችን በግል ተለዋውጠናል። ስለ ትጥቅ ትግል፣ ስለ ግንቦት ሰባት ወዘተረፈ ያላቸውን አመለካከት በሚገባ አውቃለሁ። የጻፉትን እና በአደባባይ የተናገሩትን ተከታትያለሁ። የነርሱን አገር ወዳድነትና ሰላማዊነት፣ በየትኛዉም ፍርድ ቤት ሆነ አደባባይ፣  እጆቼን መጽህፍ ቅዱስ ላይ ጭኔ የምመሰክረው ነዉ።  እግዚአብሄርን  የሚወዱ፣ ቤተሰባቸዉን የሚወዱ፣ በአገራችን እርቅና ሰላም እንዲመጣ የሚናፍቁ፣ ማንም የማያነቃንቃቸው የሰላም አርበኞች ናቸው።  እስክንድርና አንድዋለም እንዲሁም ሌሎች የሕሊና እሥረኞች የአገራችን «መበለቶች» ናቸው። እስክንደርና አንዱዋለም እንዲሁም ሌሎች፣ በመንገድ ዳር ወንበዴዎች እንደደበደቡት ሰዉዬ ናቸው።

እንግዲህ «መጽሃፍ ቅዱስን እናነባለን፤ እግዚአብሄርን እናምናለን. ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንከተላለን» ካልን፣   እየመረጥን አይደለም እግዚአብሄርን የምንታዘዘው። ለተገፉ፣ ለወደቁ፣ በዉሸት ለታሰሩ፣ ፍትህ ለተነፈጉ፣  ወገኖቻችን መቆም መጀመር አለብን።  በጣም አሰምርበታለሁ። ለታሰሩ እስረኞች መቆም ክርስትና ነዉ !  ለፍትህ ለዜጎችን ነጻነት መቆም፣  መጽሃፍ ቅዱሳዊ ነዉ። የእግዚአብሄርን ቃል መታዘዝ ነዉ።

በአንጻሩ፣ ግፍ፣ ቀንበር፣ ጭቆና እያየን፣  ዝምታን ከመረጥን፣ የእግዚአብሄር ቃል እንደሚለዉ  መባዎቻችንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችንን እግዚአብሄር አይወደዉም። እጆቻችንን ወደ እርሱ ብንዘረጋ፣ አይኖቹን  ከእኛ ይሰዉራል።  ልመናንም ብናበዛ አይሰማንም።  ሌላዉ በግፍ ሲታሰር ዝም ማለት፣ ከራሳችን ጥቅምና ምቾት አልፈን አለመሄድ፣ የዘመኑ ጡንቸኞችን ቢያስደስትም፣ ጥቂት ፍርፋሬዎች ቢወረወርልንም፣  የዘላለም አምላክ እግዚአብሄርን  የማያስደስት  እርግማን ነዉ። ነዉር ነው።

አንዳንዶች የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ተቃዉሞ ማንሳታችንን ተገቢ እንዳልሆነ ለማሳየት፣ ከመጽሃፍ ቅዱስ አንድ ጥቅስ ነጥለው በማውጣት ለማስተማር የሚሞክሩ፣ ቄስ/ፓስተር ተብዬ የአገዛዙ ካድሬዎች አሉ።  «ለባለስልጣን ጸልዩ፣ ታዘዙ» ተብሎ ስለተጻፈ «ፖለቲካ ዉስጥ ሳንገባ ፣ ታዘን መኖር ነው ያለብን» ይሉናል። አዎ ፣ በዚህ ምክንያት የአገሪቷን ሕግ እናከብራለን። ግብር በጊዜው እንከፍላለን። በትክክል የአገሪቷን ሕግ ከጣስን መቀጣታችን ተገቢ ነዉ እንላለን። ለአቶ ኃይለማሪያም ፣ ልቦና እንዲሰጣቸው፣ በልጆቻቸው ያለው የርህራሄና የፍቅር መንፈስ በርሳቸውም እንዲሰርጽ ፣ አብረዋቸው ያሉ የሰይጣን መልእክተኖችን ሳይሆን የእግዚአብሄርን መንፈስ ማዳመጥ እንዲጀምሩ፣ ሕዝብን ማስተዳደር የሚችሉበት ጥበብ  ጌታ እንዲሰጣቸው ሊጸለይላቸው ይገባል። እኛም እንጸልያለን።

ነገር ግን ባለስልጣናት ግፍ ሲፈጽሙ፣ ለነርሱ እንደምንጸልየዉ ሁሉ ፣ እነርሱን መሟገትንና መታገል  የግድ ነዉ። ነብዬ ናታን ንጉስ ዳዊት ስልጣኑን ተጠቅሞ የሰው ሚስት ደፍሮ፣ የደፈራትም ሴት ነፍሰ ጡር ስትሆን፣  ሐጢያቱን ለመደበቅ ባሏን ባስገደለ ጊዜ፣  ንጉሱን  ፊት ለፊት አወገዘ፣ ተቃወመ። «ለባለስልጣን ታዘዝ» ተብያለሁ ብሎ ዝም አላለም። ንጉስ ሄሮድስ አንቲጳስ፣ የወንድሙን ፊሊጵስ ሚስት ሄሮድያዳን ነጥቆ የራሱ በማድረግ ጸያፍ ተግባር በፈጸመ ጊዜ፣ መጥምቁ ዮሐንስ፣ በአደባባይ ነዉ «ንስሐ ግባ»  ብሎ ያወገዘዉ።  በዚህም ምክንያት ሄሮድስ የመጥምቁን አንገት ሁሉ አስቆርጧል።

የእምነት ሰው መሆን ማለት፣  ባርነትን መቀበል ማለት አይደለም። የእምነት ሰው መሆን ማለት አደርባይ መሆን አይደለም። የእምነት ሰው መሆን ማለት የፍትህ፣ የሰላምና  የነጻነት አርበኛ መሆን ማለት ነዉ። የእምነት ሰው መሆን ማለት እንደነ ነብዩ ናታን፣  ባለስልጣናት ስልጣናቸውን ተጠቅመዉ የሚፈጽሙትን ግፍ ማውገዝና መቃወም ማለት ነዉ። እነ ነብዩ ናታን እንዳደረጉት እኛም፣ ግፍን በምናወግዝበት ጊዜ፣ «እግዚአብሄርን እናምናለን»  የሚሉ ሊቀላቀሉን ይገባል እንጂ ዝም እንድንል ሊነግሩን አይገባም።

አቶ ኃይለማሪያምን  እንወዳቸዋለን፤ መልካም ሲሰሩ ፣ ደግፈናቸዋል፤ ወደፊትም እንደግፋቸዋለን። ነገር ግን ክፋታቸውን፣   አይተን ዝም አንልም። በሽብርተኝነት ስም ፍርድ ሲያዛቡ፣  በዜጎች ላይ ሲዝትኑ ዜጎችን ሲያስፈራሩ ዝም አንላቸዉም። «ባርነት ፣ ጭቆና፣ ግፍ፣ ዘረኝነት፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ .. በቃ ! »  ብለናል።  ግፍን አንታገስም። ጥቂቶች የሕዝቡን መብት ረግጠው እንዲቀጥሉ አንፈቅድላቸዉም። ይሄን እንሟገታለን፤ ይሄን እንታገላለን። ጆሮ ያለው ይስማ። ልብ ያለው ያስተውል። እግዚአብሄር ልቦናችንን በፍቅሩ፣ አይምሯችንን በጥበቡ ይሙላልን ! አገራችን ኢትዮጵያ እንዲሁም ኤርትራን ይባርከልን !

No comments:

Post a Comment