Friday, December 20, 2013

በአዲስ አበባ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ለመንግስት ከሚሠራ ሰው፤ የቀን ሠራተኛ ደመወዝ ይበልጣል

December 19/2013


ቱሉ ከአዲስ አበባ

አምና ከዩኒቨርስቲ ‹‹ከነሙሉ ክብሩና ጥቅሙ›› ‹በተሰጠው› የመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ ዘንድሮ በ2006 የመንግስት ስራ የያዘ ጀማሪ ሰራተኛ ጠቅላላ ደሞዙ 1600 ብር ነው፡፡ የጡረታ መዋጮና ሌሎች ተቆራጮች ሳይታሰቡ የመንግስት የስራ ግብር ሲቀነስ ተከፋይ ደሞዙ ከ1300 ብር ያንሳል፡፡ ይህ ለ30 ቀናት ሲካፈል የቀን ገቢው ብር 45 ያህል ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ በወቅቱ ያዲሳባ የጉልበት ስራ ገበያ ከቀን ሰራተኛ ደሞዝ (ብር 60) ያንሳል፡፡ የቀን
ሰራተኛ ማለት ምንም የሙያ ስልጠናና ትምህርት የሌለውና ተፈጥሯዊ ጉልበቱን ብቻ የሚሸጥ ሰራተኛ ማለት ነው፡፡ ይህም በዛሬ ሁኔታ መማር ምንም ክብርና ጥቅም እንደማያስገኝ ከማሳየቱም በላይ ኪሳራ መሆኑንም ይጠቁማል፡፡

ይህ አስከፊ ሁኔታ በዚህ የሚቆም አይመስልም፡፡ የቀን ሰራተኛ ደሞዝ ካሁኑ ደረጃ የደረሰው የየጊዜውን የኑሮ ውድነት መነሻ በማድረግ ባሳየው ለውጥ እንጂ ከአምስት ዓመት በፊት 20 ብር እና ከዚያም በታች ነበር፡፡ ዛሬ በሦስት እጥፍ አድጓል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ከሁለት እስከ አምስት እጥፍና ከዚያ በላይ ጭማሪ ያሳዩ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ምግብ፣ የሚከራይ ቤትና ትራንስፖርትን ብቻ ማንሳት ይበቃል፡፡ 800 ብር የነበረው ባለ አንድ ክፍል የኮንዶሚንየም ቤት ከ1600 ብር በላይ ሆኗል፡፡ ባዲሳባ ስርቻዎች ውስጥ ከሚገኙ ቤቶች አንድ ዝቅተኛ መጠለያ ለመከራየትም ከ800 ብር በላይ ይጠይቃል፡፡ የወር ገቢው 1300 ብር የሆነ አንድ የመንግስት ሰራተኛ የደሞዙን ሁለት ሦስተኛ (ብር 800) ለቤት ኪራይ ከፍሎ በሚቀረው በቀን ከ16 ብር በታች በሆነ ገንዘብ ጎስቋላ ኑሮ ለመኖር ይገደዳል፡፡

የመንግስት ደሞዝ የገበያውን ለውጥ ተከትሎ ስለማይለወጥ የመንግስት ሰራተኛው መሽቶ በነጋ ቁጥር የሚቆለለውን የኑሮ ሸክም ለመቋቋም እየተንገዳገደ ፍዳውን ያያል፡፡ በዝቅተኛ የመንደር ምግብ ቤቶች አንድ የሽሮ ምግብ 17 ብር በሚያወጣበት በዚህ የኑሮ ውድነት አንድ ሰው ከ16 ብር ባነሰ ገንዘብ እንዴት መኖር እንደሚችል ለመግለጽ ኢኮኖሚክስ ብቁ ዘዴ አይደለም፡፡ ከሱ ይልቅ ሰው ረሀብን፣ ጉስቁልናንና አዋራጅ ኑሮን ለመቋቋም ያለውን አቅም የሚያጠና ሌላ ሳይንስ ያስፈልጋል፡፡

ይህን አዋራጅ ሁኔታ ከሚገልጹት ነገሮች መካከል ዋነኛው የመንግስት ሰራተኛው ለአገልግሎቱ የሚገባውን ዋጋ የመወሰን ነጻነት የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ገበያው ለጫማ ጠራጊው ያገልግሎት ዋጋን የመወሰን አንጻራዊ ነጻነት ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ ጫማ ጠራጊው ባለፉት አምስት ዓመታት አንድ ጫማ ለመጥረግ የሚጠይቀውን ዋጋ ከ1ብር ወደ 2ብር፣ ከ2ብር ወደ 3ብርና ከዚያም በላይ ከፍ በማድረግ የቀን ገቢውን ከ60 ብር በላይ አሳድጓል፡፡ የየወቅቱ ገበያ የሚወሰነውም የአገልግሎታቸውንና የምርታቸውን ዋጋ ገበያ በሚሰጣቸው አንጻራዊ ነጻነት እየተጠቀሙ ከፍ በሚያደርጉ አምራቾች፣ አገልግሎት ሰጪዎችና ነጋዴዎች ነው፡፡ የመንግስት ሰራተኛው ሁሉም የገበያ ሸክማቸውን ለማቅለል በምርታቸውና አገልግሎታቸው ላይ በየጊዜው የሚጨምሩትን ጭማሪ በራሱ የአገልግሎት ዋጋ ላይ አምስት ሳንቲም ሳይጨምር መሸከም ግዴታው ነው፡፡ ያለው ነጻነት የተሰጠውን ክፍያ ተቀብሎና ሌሎች የገበያ ኃይሎችና ግብር ጣዩ መንግስት በየጊዜው የሚቆልሉበትን የኑሮ አሳር ተሸክሞ ማገልገል ወይም ስራውን መተው ብቻ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ የተማረው የመንግስት አገልጋይ ክብርና ጥቅም ከቀን ሰራተኛውና ከጫማ ጠራጊው ክብርና ጥቅም ማነሱን ከማመልከቱም በላይ የመንግስት ስራ ክብር ማጣቱንና ውስጣዊ ጤናማነቱም ፈተና ላይ መውደቁን ያሳያል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው አገልጋይነት ወደ ባርነት በመቀየር ላይ መሆኑ የችግሩ መነሻ ነው፡፡ ባርያ ማህበራዊ ፍትህን ሊያገለግል የሚችለው እንዴት ነው? ይህ ነው ፈተናው፡፡ መንግስት የሚባለው ተቋም ፍትሀዊ ህሊና እንዳለው ይታመናል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው ገበያ የሚነፍገውን ነጻነት የሚያካካስለትም ለገዛ ተቀጣሪው ማህበራዊ ደህንነት የሚቆረቀረው ይኸው ፍትሀዊ ህሊና ነው፡፡ ይህ ህሊና ግን አሁን እየሰራ አይመስልም፡፡ ሰራተኛው እያደር በሚያሸቅበው የገበያ ሁኔታ በአስከፊ የኑሮ አረንቋ እየተዋጠ፣ ወደ አዘቅት እየወረደ ነው፡፡ የተማረው የመንግስት አገልጋይ ‹‹ሙሉ ክብርና ጥቅም›› ገደል ገብቷል፡፡

No comments:

Post a Comment