Thursday, December 5, 2013

በኢትዮጵያ የሚታየው የግብር አሰባሰብና ሙስና ህዝቡን እያስመረረ ነው



ህዳር ፳፭(ሃያ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በደብረማርቆስ ከተማ ተደርጎ በነበረው የህዝብ ስብሰባ ላይ ነርካታ ነጋዴዎች በታክስ መማረራቸውን ገልጸዋል።
መቶ አለቃ ስመኝ መኩሪያው እንዳሉት መንግስትን አክብረን በቫት ብንገባም በአንድ አነስተኛ የንግድ ሱቅ በየወሩ እስከ 73 ሺ ብር ተጠይቀን ፤ መንቀሳቀስ አልቻልንም የምንነግደውን ሊወርሰን የሚሽከረከረው መንግስት ሚዛኑ የሚጥልብን ግብር አስመርሮናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “የምንሰራውን ስራ በማቋረጥ አሰረክበን እንድንቀመጥ አሰገድዶናል ፣ ሃገራችንን እንዳናለማ ፈጽሞ መንግስት አለመፈለጉን ነው የሚያሳየው ሲሉ በከተማዋ የመልካም አሰተዳደር ውይይት መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡ “አቤቱታ ብናቀርብም የሚቀበለን አጥተናል፡፡ምላሽ የሚሰጥ የለም” በማለት አማረዋል

ሞላ ቢሻው የተባሉ የከተማው ነጋዴ ፤ በመልካም አሰተዳድር ችግር ምክንያትና የተገናዘበ ግብር ባለመኖሩ በጨለማ ውስጥ ነን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “በአሁኑ ሰዓት መንግስት አንድ ሚልየን ብር ግብር ጥሎብኛል፡፡ ግብሩ ለከተማው በጀት ነውን?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “መንግስት ፍትሃዊ ግብር አይጥልም ፤አቅርቦ አያወያይም ፣ ከአራት አመታት ወዲህ ሁሉም ነገር የጨለማ ጉዞ ሁኖብናል ፣ ከዞን እስከ ክልል እና ፌዳራል ድረስ ለማስፈጸም ጨለማ ሆኖብናል ሲሉ ተናግረዋል።

የተለያዩ በግንባታ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችም በመስኩ ስላለው ከፍተኛ ሙስና ተናግረዋል።

የከተማዋ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው መንግስቱ በአስተዳድሩ ውስጥ የገንዘብ ጉዳለት መገኘቱን አምነዋል።

የከተማ አሰተዳደሩ ከንቲባ አቶ ደረጀ ደነቀው በበኩላቸው ለባለሃብቶች መሰደድ፤የአመራሩ ብቃት ድክመት ማነስ ፤ መንግስት በግምት ላይ የተመሰረተ መረጃ አልባ የግብር ግምት አወሳሰን መከተሉ፤ እና ባለሃብቶች ከመንግስት ጋር መተማመን ማጣት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ባለብቶች ገቢያቸውን ባይደብቁ ኖሮ ችግሩ አይፈተረም ነበር ብለዋል.

No comments:

Post a Comment