Monday, November 4, 2013

“የኢህአዴግ የአፈና ገመድ ነትቧል፣ ድርጅቱ ተናግቷል”




በህወሃት ውስጥ የዕርቅ ሃሳብ መነሳቱ ተሰማ
tplf1
November 4, 2013 
ኢትዮጵያ ግራ በሚያጋባና ሊተነበይ በማይችል የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ መገኘቷን ያመኑ የህወሃት ሰዎች መካካል የእርቅ ሃሳብ ላይ ለማተኮር እቅድ እንዲያዝ ሃሳብ ማንሳታቸው ተሰማ። ኢህአዴግ የቀድሞው የአፈና ገመዱ መንተቡን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየታቸውና አለመተማመን መንገሱ ተጠቆመ።
ጎልጉል መረጃ በመስጠት የሚታወቁ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራርና ዲፕሎማት እንዳሉት ህወሃት ውስጥ “እርቅ አስፈላጊ ነው” በሚል እቅድ እንዲያዝና እንዲሰራበት ሃሳብ ቀርቧል። በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ አለመተማመን ሳቢያ ስጋት የገባቸው የህወሃት ሰዎች የእርቅ ሃሳብ እንዲሰራበት ያቀረቡት ሃሳብ ግን በመደበኛ ስብሰባ አይደለም።
በህወሃትና ህወሃት በሚያዛቸው አቻ ፓርቲዎች መካከል ያለው የመከባበርና የመገዛት ስሜት ከመለስ ሞት በኋላ መበላሸቱ፣ በኢህአዴግም ሆነ በህወሃት ደረጃ የተፈጠረው ልዩነትና በሙስና ስም የተጀመረውን ዘመቻ ተከትሎ የተነሳው አለመግባባት አደጋ እንዳያስከትል ተፈርቷል። የመረጃው ምንጭ እንደሚሉት በጣም ጥቂት ካልሆኑ በስተቀር ከሙስና የጸዱ አለመኖራቸው “ማን ንጹህ ሆኖ ማንን ይጠይቃል?” የሚል ቅሬታ አስነስቷል።
ህወሃት ባሰበው በሁሉም መንገድ የበላይ ሆኖ ሊቀጥል እንደማይችል ከየድርጅቶቹ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በስፋት እየተነገረ መሆኑንን ያነሱት እኚሁ ሰው፣ ይፋ ባልሆነ መንገድ የቀረበው እርቅን የመቀበል ጥያቄ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ የተነሱት አስደንጋጭ ችግሮች ተከትሎ መሆኑን አልሸሸጉም።
ሊታመን በማይችልና ባልተለመደ መልኩ የሃይማኖት አባቶች ኢህአዴግን አንደበታቸውን ከፍተው በግልጽ ማውገዛቸውን፣ “አገሪቷን ገደላችኋት” በማለት መኮነናቸውን ተከትሎ በኢህአዴግ ዘንድ መደናገጥ እንደተፈጠረ ለማወቅ ተችሏል። የእምነት ጉዳይ ጥንቃቄ የሚያሻው በመሆኑ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት የተቆጠቡት ዲፕሎማት “ኢህአዴግ በቀድሞው ፓትሪያርክ ፈቃድና ውዴታ ያደርግ እንደነበረው አሁንም በደኅንነት ሃይሎች ቤተክርስቲያኒቱን መቆጣጠርና አመራሮቹን አንደበታቸውን ማፈን የማይችልበት ደረጃ መድረሱን አምኖ ተቀብሏል። በዚህ ላይ ደግሞ እስካሁን ምላሽ ያላገኘ የድምጻችን ይሰማ ጉዳይ አለ” ኢህአዴግ እንደተምታታበት አመላክተዋል።
ሲኖዶሱ በጉባኤው ያነሳቸው ነጥቦች ኢህአዴግ ነገሮች ቀስ በቀስ ከእጁ እንደወጡበት የሚያሳይ እንደሆነ ያመለከቱት የኢህአዴግ ሰው “ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የኢህአዴግ አባላት በልብ ከድርጅቱ ጋር እንደሌሉ ሪፖርት ቀርቧል። አብዛኛው አባልና ደጋፊ ባለሃብቶች የሚባሉትን ጨምሮ ሰላማዊ ለውጥ እንዲካሄድ ኢህአዴግ ወደ እርቅ መንገድ እንዲሄድ ይፋ (ኦፊሴላዊ) ባልሆነ መልኩ ያነሳሉ” በማለት ድርጅቱ የገባውን ስጋትና መሸርሸር ያስረዳሉ።
እርቅ ከተፈለገ ለምን በግልጽ አይቀርብም በሚል ለቀረበላቸው ሃሳብ ዲፕሎማቱ ምላሽ ለመስጠት አልፈለጉም። ይሁን እንጂ “ከማን ጋር ነው የምንታረቀው? እነማንን ነው ለእርቅ የምንጋብዘው? እርቅ ጠያቂ መሆን ያለበትስ ማን ነው?” የሚሉት በግልጽ ባይቀርቡም ተመሳሳይ የስጋት ጥያቄዎች እንዳሉ ሳይገልጹ አላለፉም።
በቅንጅት ጊዜም በተመሳሳይ የዕርቅ ፍላጎትና “ሥልጣን እናስረክብ” የሚል አቋም ተነስቶ እንደነበር ያስታወሱት ምንጫችን፤ በወቅቱ ሃሳቡ ተግባራዊ ያልሆነው “ወያኔዎችን ወደመጡበት ጠራርገን እንመልሳቸዋለን” በማለት አንድ የቅንጅት አመራር ለሕዝብ መፈክር ሲያወርዱ ከተሰማ በኋላ ነበር፡፡
በመከላከያ አዛዦችና በደህንነት የተለያዩ መምሪያዎች የሃላፊዎች ለውጥ እያካሄደ ያለው ኢህአዴግ ከአቻ ፓርቲዎች ጋር ውህደት በማድረግ ብሔራዊ ፓርቲ ለማቋቋም በሁለት ጉባኤዎች ሃሳብ ቢቀርብም ተግባራዊ አላደረገውም። ፓርቲው ህብረ ብሔር ከሆነ ህወሃት የገነባቸው የንግድ ድርጅቶችና በሞኖፖል የያዘውን ቁልፍ ስልጣን እንዲያጣ ስለሚያደርገው ጊዜ ሲያጓትት መቆየቱን ያመለከቱት የመረጃው አቀባይ “ይህ ፍርሃቻ አሁንም ሆነ ወደፊት ለሚፈለገው በሃሳብ ደረጃ ያለ እርቅ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል የውስጥ ለውስጥ ሃሜት አለ” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ሆኖም እጅግ የተወሳሰበ የፖለቲካ ትወና ውስጥ ያሉት ካልሆኑ በስተቀር በማናቸውም መልኩ እርቅን ለመቀበል የማያቅማሙ እንደሚበዙ ግን አልሸሸጉም፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ አለመተማመን መንገሱን የሚናገሩ ወገኖች “ለራሳቸው መተማመን ያቃታቸው ክፍሎች እንዴት ሌላውን አስማምተው ይመራሉ” በማለት መጠየቅ ከጀመሩ ቆይተዋል። በተለይም አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ወደ መንበሩ ከመጡ በኋላ አገሪቱ በደቦ መመራቷ የኢህአዴግን መሽመድመድ የሚያሳይ እንደሆነም እየተቹ ነው።
sebhat negaሁሉም ሰላም ነው፤ ልማት ነው፤ ዕድገት ነው፤ ህዳሴ ነው … በማለት አንድም ችግር የሌለበት ለመምሰል የሚሞክረው ህወሃት ደግሞ በውስጡ የመከፈል አደጋ አጋጥሞት እንደማያውቅ ምንነታቸውና የስራ ደርዛቸው በውል በማይታወቀው አቶ ስብሃት አማካይነት እያስታወቀ ነው። እሳቸው እንደሚሉት ችግር የህወሃት “ሰማያዊ ስጦታውና በረከቱ ነው” አቶ ሃይለማርያምም በበኩላቸው “ኢህአዴግ መካከል መከፋፈል አለ የሚሉ የዋሆች ናቸው” ሲሉ አንድነት የሰፈነበት አመራር እንዳለ ለማስተጋባት ሞክረዋል።
የእርቅ ሃሳብ ተሰንዝሯል በማለት መረጃውን የሰጡን ዲፕሎማት ግን ይህንን አይቀበሉም። “በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚታይ ነው። አንዱ እኔ ነኝ። ሌሎችም አሉ። ብዙዎች ሰላማዊ ህይወት ናፍቆናል። የተወሳሰበውን አገራችንን ፖለቲካ አካሄድ ለመተንበይ ተቸግረናል። መፍትሔው የእርቅ ሃሳብ ብቻ ነው” በሚል ተከራክረዋል።
በድርጅታቸው ውስጥ የበላይና የበታች መጥፋቱን፣ የበታቹ የበላዩን እንደሚያዘው፣ አንዳንዴ የበላይ መስለው ምንም ዓይነት የውሳኔ ሰጪነት ሚና የሌላቸው ክፍሎች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር እንደሆነ የሚናገሩት እኚሁ ሰው፣ “እርቅና ዋስትና የሚሰጥ አግባብ ቢያገኝ የመጀመሪያው ስምምነት ፈራሚና ደጋፊ ስብሃት ነው። ቀሪውን የጡረታ ዘመኑንን በትዝታ ያለውን እየበላ መኖር ይፈልጋል። እሱ ብቻ ሳይሆን ብዙዎች ተመሳሳይ ፍላጎት አለን። አስከማውቀው ድረስ ችግሩ ከራስ ምግባርና ከድርጅት ተልዕኮ በመነጨ የተሰሩት ጥፋቶችና ሃጢያቶች መብዛታቸው ከለውጥ በኋላ የሚያመጣቸው የተጠያቂነት ጣጣዎች ናቸው” ብለዋል፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ ንጹህ ሰዎች አሉ ለማለት የማይቻልበት ደረጃ መደረሱን የሚያመለክቱት ዲፕሎማት፣ ህወሃትም ሆነ ኢህአዴግ አሁን የጋራ ነጠብ የሌላቸው፣ የርስ በርስ ትስስራቸው የላላና የተለያየ፣ አንዱ ሌላውን ለመንካትና ለመገምገም የሞራል ብቃት ያጣበት፣ እርስ በርሱ በወንጀል የሚጠቋቆምበት የውድቀት ጫፍ ላይ መድረሱን የውጪ አገር ወዳጆቹም ተረድተውለታል፤ አሁን ለእነርሱም ችግር የሆነባቸው ቁጭ ብለው ሥልጣን ላይ የሰቀሉትን ህወሃት አሁን ቆመው እንዴት ማውረድ እንደሚቻል መቸገራቸው ነው ብለዋል። የእርቅ ሃሳቡ ከውጪ አገር ወዳጆቻቸው ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ግን ፍንጭ አልሰጡም።
በህወሃትም ሆነ በኢህአዴግ ደረጃ የውስጥ ስጋት ቢኖርም “ሕዝብ እስኪ ዛሬን ልደር” በሚል የሞራል ውድቅት ውስጥ በከተተው ድህነት የተመታ በመሆኑ ለጊዜው ያምጻል የሚል ግምገማ አለመኖሩን ዲፕሎማቱ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ህዝብ በኢህአዴግ ደስተኛ አለመሆኑ፣ የጥበቃና የቁጥጥር መረቡ እንደወትሮው ትጋት ማጣቱ፣ የአካባቢ ስሜትና “ወገኔን ለምንና እስከመቼ አሳልፌ እሰጣለሁ?” የሚል አስተሳሰብ መበራከቱ፣ አጋጣሚ ተቃውሞ ቢነሳ መቋቋም እንደማይቻል፣ ረብሻ ከተነሳ የስርዓቱ ባለሟሎች ህልውና ጉዳይ አስጨናቂ እንደሚሆን ግንዛቤ ስለመኖሩ አላስተባበሉም። በማያያዝም እሳቸው በዚህ ደረጃ ስርዓቱን ከገመገሙና ችግሩን ከተረዱ በይፋ የማይከዱበትን ምክንያት ተጠይቀው “ለጊዜው በምስጢር ጠባቂነት የዝግጅት ክፍሉ ቃሉን ይጠብቅ። የቀረውን ወደፊት እናየዋለን” የሚል ድፍን መልስ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሰጥተዋል።

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡

No comments:

Post a Comment