Monday, November 11, 2013

የኢሕአዴግ መንግሥት አሳምሮ ይፈራል! በኃይሉ አርአያ (ዶ/ር)


by Aseged Tamene

 የኢሕአዴግ መንግሥት አሳምሮ ይፈራል! በኃይሉ አርአያ (ዶ/ር) ሰሞኑን የኢሕአዴግ መንግሥት ይፈራል አይፈራም የሚል ጉዳይ ከፓርላማ ተነስቶ ወደ መገናኛ ብዙኃንም ደርሷል። ጉዳዩ የተነሳው የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ አዲሱ ፕሬዚዳንታችን በፓርላማ ያደረጉትን ንግግር አስመልክቶ ባቀረቧቸው የማማሻሻያ ሐሳቦችና ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሰጡት ምላሽ ዙሪያ ነው። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዝ ሪፖርተር ጋዜጣ ጥቅምት 13 ቀን 2006 ዓም በአወጣው ዕትሙ ‹‹’ፈሪ’ መንግሥት?›› በሚል ርዕስ ጋዜጠኛ የማነ ናግሽ ጥሩ ትንተና አቅርቧል። የፍርኃት ነገር ከተነሳ ጋዜጠኛው ያነሳውን ለማዳበር በእኔም በኩል የምለው አለኝ። የኢሕአዴግ መንግሥት አሳምሮ ይፈራል። የኢሕአዴግ መንግሥት አሳምሮ ይፈራል ስል ግን በደፈናው አይደለም። በርካታ የማይፈራቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ጦርነትን አይፈራም። በተለይ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ጥርሱን ነቅሎ ያደገበት ጉዳይ ነው። ሕግ መጣስን አይፈራም። ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን መጣስን አይፈራም። መዋሸትን አይፈራም። የኢሕአዴግ መንግሥት ይፈራል ስል በተለይ የማተኩረው በአንድ ጉዳይ ላይ ነው። እውነት ላይ። የኢሕአዴግ መንግሥት እውነትን ይፈራል። እውነትን ስለሚፈራ እሱ ራሱ በሚፈልገው መንገድ እንዲታወቅ ከሚፈልገው ውጪ ሕዝቡ እውነቱን እንዲያውቅ አይፈልግም። ይህ ደግሞ የአምባገነን አውራ ፓርቲዎች መንግሥታት አንዱና ዋናው የደባቂነትና የሸማቂነት መገለጫ ባህሪ ነው። የኢሕአዴግ መንግሥት እውነትን ለመፍራቱ በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለጊዜው ግን አራቱን ብቻ በምሳሌነት እንደሚከተለው ልጥቀስ። 1. ከቅርቡ የሶማሊያ ጦርነት ጋር በተያያዘ የእውነት መረጃን ከሕዝብ መደበቁ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎረቤት ሶማሊያ ውስጥ ገብቶ ከአክራሪና ከሽብር ኃይሎች ጋር ተዋግቷል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አሁንም እየተዋጋ ነው። ከማን ጋር ነው የተዋጋውም ሆነ የሚዋጋው? ለምንድን ነው የተዋጋው/የሚዋጋው? ጣልቃ ገብነቱ ሕጋዊ ነው አይደለም? ወደሚሉት ውስብስብ ጥያቄዎች አልገባም። እኔ የምገባው ወደ እውነት መረጃ አስፈላጊነት ነው። ጦርነት ነውና ወታደሮች ሞተዋል፣ ቆስለዋል። ገንዘብ ወጪ ሆኗል። የሞቱት የሕዝብ ልጆች ናቸው። ወጪ የሆነው የሕዝብ ገንዘብ ነው። ጦርነቱ የተካሄደው በውጭ ዕርዳታ ገንዘብ ነው እንዳልል፣ ነፍሳቸውን ይማርና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን አቶ መለስ ዜናዊ ጦርነቱን በተመለከተ ፓርላማ ፊት በመቅረብ የአውራ ጣታቸውንና የሌባ ጣታቸውን ጫፎች አነካክተው ዜሮን በማሳየት ‹‹ሳንቲም ዕርዳታ አላገኘንም›› ማለታቸውን አስታውሳለሁ። የሞቱት የሕዝብ ልጆች ናቸውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንት ልጆቹ እንደሞቱ እውነቱን ለማወቅ ይፈልጋል። እውነቱን የማወቅ መብትም አለው። የወጣው የሕዝብ ገንዘብ ነውና ሕዝቡ ያወጣውን ለማወቅ ይፈልጋል። እውነቱን የማወቅ መብትም አለው። እኔ እስከማውቀው ድረስ በተለይ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ የኢሕአዴግ መንግሥት የጉዳዩ ባለቤት ለሆነው ሕዝብ በይፋ የሰጠው መረጃ የለም። ምናልባት ለአሜሪካ፣ ለአፍሪካ ኅብረትና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ‹‹እኔ እንደ መንግሥት እየከፈልኩ ያለሁትን መስዋዕትነት ዕወቁልኝ›› በሚልና የባለውለተኛ ወሮታ ለማግኘት በሚስጥር አሳውቆ ሊሆን ይችላል። ይህ መደረጉ አይከፋም። መጀመሪያ መስማት ያለበት ግን ባለጉዳዩ ሕዝብ ነው። ለምንድን ነው ባለፈው እውነታውን ለሕዝብ ያላሳወቀውና አሁንም ቢሆን የማያሳውቀው? እውነትን ስለሚፈራ ነው። መደበቅና መሸመቅ ዓይነተኛ ባህሪው ስለሆነ ነው። ለሕዝብ የማወቅ መብት አክብሮት ስለሌለው ነው። ጦርነቱን በበጎ ጎኑ አይተነው፣ ሠራዊታችን ሶማሊያ የገባው ሉዓላዊነታችንን ላለማስደፈር፣ ድንበራችንን ለማስከበር፣ የአገራችንንና የአካባቢያችንን ሰላም ለመጠበቅና ከዚያም ባለፈ የዓለማችንን ሰላም ለማስከበር ለሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው እንበል። ታዲያ እንደዚህ ላለ ‹‹የተቀደሰ›› ዓላማ የተከፈለን መስዋዕትነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቶ ዓለም እንዲያውቀው ይደረጋል እንጂ ይደበቃል? ይህን አጭር ጽሑፍ ለማዘጋጀት ሳስብ እስቲ አሜሪካ በቪየትናም ጦርነት የሞቱባትን ወታደሮች ለሕዝብ በይፋ አሳውቃ እንደሆነ ልይ ብዬ ኢንተርኔት ውስጥ ገባሁ። “Us Soldiers Killed in Vietnam” በሚል ‹‹ጉግል›› ሳደርግ ያገኘሁት መረጃ ብዛትና ዝርዝር የሚገርም ነው። በአጭሩ ግን 58,220 ወታደሮች እንደሞቱ፣ የሟቾቹ ቁጥርም በዘር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በመጡበት ‹‹ስቴት››፣ በሠራዊት ምድባቸው (አየር ኃይል፣ ምድር ጦር፣ መርከበኛ፣ ወዘተ.)፣ በአሟሟታቸው ሁኔታ (በውጊያ፣ በድንገተኛ አደጋ፣ በሕመም፣ እርስ በርስ መገዳደል፣ ወዘተ.)፣ በጦርነቱ መጀመሪያ የሞተ ወታደር ስም፣ ጦርነቱ ሊፈጸም ሲል በመጨረሻ የሞተ ወታደር ስም፣ ወዘተ፣ ተዘርዝሮ ተቀምጧል። በተመሳሳይ ሁኔታ የኢራቅንና የአፍጋኒስታንንም አየሁ። መረጃው ከሞላ ጎደል በታመሳሳይ ሁኔታ ተቀምጧል። ወጪ የሆነው የገንዘብ መጠን ሁሉ ተቀምጧል። ከዚያ በኋላ እስቲ መንግሥታችንም ምናልባት ሳናውቀው መረጃ አስቀምጦ እንደሆን ብዬ ለማየት ሞከርኩ። የውጭ ጋዜጦችና ሌሎች የዜና ምንጮች በዜና መልክ ካስቀመጧቸው ጥቂት ተባራሪ መረጃዎች በስተቀር ምንም ነገር የለም። ለምንድን ነው የአሜሪካ መንግሥት ከላይ የተጠቀሱትን ጦርነቶች በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለሕዝቡና ለተቀረው ዓለም ሲሰጥ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊያ ያካሄደውን ጦርነት በተመለከተ መረጃ ትንፍሽ ያላለው? ይህን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ብዙ ማለት ይቻላል። በአጭሩ ግን የአሜሪካ መንግሥት መረጃ የሰጠው እውነትን ስለማይፈራ ነው። በራሱ ስለሚተማመንና ሕዝቡንም ስለሚያምን ነው። የሕዝቡን መረጃ የማግኘት መብት ስለሚያከብር ነው። የኢሕአዴግ መንግሥት መረጃ ያልሰጠው በእኔ እምነት እውነትን ስለሚፈራ፣ በራሱ ስለማይተማመንና ሕዝቡንም ስለማያምንና መረጃ የማግኘት መብቱንም ስለማያከብር ነው። በዲሞክራሲ የዳበሩ መንግሥታት ምንጊዜም እውነትን አይፈሩም፣ አይደብቁም፣ አይሸምቁም ማለቴ አይደለም። አልፎ አልፎ እውነትን ይፈራሉ፣ ይደብቃሉ፣ ይሸምቃሉ። ሆኖም እውነትን መፍራት፣ መደበቅና መሸመቅ እንደ አምባገነን መንግሥታት ዓይነተኛና መገለጫ ባህሪያቸው አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ነፃና ጠንካራ ፕሬስ፣ ነፃና ጠንካራ ሲቪክ ማኅበራትና ንቃተ ህሊናው የዳበረና ለመብቱ ቀናዒ የሆነ ሕዝብ ስላሉ እውነትን የሚፈራ፣ የሚደብቅና የሚሸምቅ መንግሥት ይዋል ይደር እንጂ ይጋለጣል። የአሜሪካው የዋተርጌትና የቢል ክሊንተን-ሞኒካ ለዊንስኪ ቅሌት እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጁሊያን አሳንጅና በኤድዋርድ ስኖውደን እንዲሁም በሌሎች ንቁና ተቆርቋሪ ዜጎች አማካይነት እየጎላ የመጣው የመረጃ ፍልፈላና ፍትለካ የዚህ አንድ ማስረጃ ነው። በዚህም ምክንያት ዲሞክራሲያዊ መንግሥታት እውነትን ከመፍራት፣ ከመሸመቅና ከመደበቅ ድርጊት በተቻላቸው መጠን ይቆጠባሉ። በአምባገነን ሥርዓት ግን የመንግሥት ፕሬስ አድር ባይ በመሆኑ፣ ነፃው ፕሬስ፣ ተቃዋሚዎችና ሲቪክ ማኅበራት ደካሞች በመሆናቸው፣ ሕዝቡም የታፈነና በፍርኃት ድባብ ውስጥ የሚኖር በመሆኑ መረጃ የመፈልፈልና እንዲያፈተልክ የማድረግ አቅም ያንሳቸዋል። ስለዚህ መንግሥት በእነዚህ ኃይሎች ድክመት ምክንያት በማናለብኝነት እንደፈለገው ይሆናል፣ እንደፈለገው ያደርጋል። 2. የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን በሞኖፖል መያዙ የኢሕአዴግ መንግሥት እውነትን የሚፈራ ለመሆኑ ሌላው ዋና ማስረጃ በሕዝብ ገንዘብ የሚሠሩ መገናኛ ብዙኃንን (ጋዜጣ፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን) በሞኖፖል መያዙ ነው። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ‹‹ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፤›› ይላል። በተጨማሪ በዚሁ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ 5 ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ በሚያስችል ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፤›› ይላል። የኢሕአዴግ መንግሥት እውነትን ከመፍራቱ የተነሳ በእነዚህ ንዑሳን አንቀጾች ውስጥ የተካተቱ መሠረታዊ መብቶች ፍርክስክሳቸውን አውጥቶታል። ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ይፈራል። እውነትን ይፈራል። ለዲሞክራሲ ሥርዓት መልካም አሠራር ሲባል የተለያዩና ጥርስ ያላቸው አስተያተቶች ማስተናገድን ይፈራል። ከመፍራቱ የተነሳ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ዘግቶ ይዟል። አልፎ አልፎ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ያቀረበ ለማስመሰል በቤት ልጆች እዚያው ተፈጭተው፣ እዚያው ተቦክተው፣ እዚያው ተጋግግረው የሚቀርቡ ፕሮግራሞችን ያይራል (Air) ያደርጋል። በምርጫ ሰሞንም ነፃነት ያለ ለማስመሰል የሚዲያ በሩን ለስሙ ገርበብ አድርጎ በመክፈት የተለያዩ ሐሳቦች ይቀርባሉ ለማስባል ይሞክራል። በዚህም ቢሆን የቀረቡ ሐሳቦችን በቅድሚያ ቀርፆ የሚፈራቸውን ሐሳቦች ቆርጦ (ሳንሱር አድርጎ) ነው የሚያቀርበው። በጋዜጣና በሬዲዮ የሚቀርቡ ሐሳቦችን ደግሞ ‹‹ይህን ካላስወጣችሁ››፣ ‹‹ይህን ካላስተካከላችሁ›› እያለ በቅድሚያ ሳንሱር የማያላውስ እንቅፋት ይፈጥራል። እንደ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አካሄድ ከሆነ፣ እንዲሁም በጎረቤትና በሩቅ አገሮችም እንደሚታየው ከሆነ ብዙ የግልና ነፃ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲሁም ጋዜጦች መኖር ነበረባቸው። የመንግሥት የሚባል ቴሌቪዥንም ሆነ ሬዲዮ መኖር አልነበረበትም። ትላልቅ የሚባሉ፣ በዲሞክራሲ የዳበሩና በራሳቸው የሚተማመኑ አገሮች የቴሌቪዥንም ሆነ የሬዲዮ ጣቢያዎች የሏቸውም። (ያሏቸው የሉም ማለት ግን አይደለም)። የእኛ መንግሥት ግን ሲጀመርም እውነተኛ ዲሞክራሲ የሚባል ነገር ስላልተዋሀደው፣ እንዲሁም በግል ቴሌቪዥና በግል ሬዲዮ ጣቢያዎች ሊንሸራሸሩ የሚችሉ እውነታዎችን ስለሚፈራና እውነትን በእውነት ለመጋጠም ችሎታውም፣ ድፍረቱም ስለሌው እነዚህ ተቋማት እንዳይኖሩ ከልክሏል። ተረጋግተው፣ በነፃነታቸው ተማምነው የሚሠሩ ነፃ ጋዜጦችም የሉም ማለት ይቻላል። ስለዚህ ሥራዬ ብሎ የመረጠው መንገድ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን የሕዝብን የተለያየ መረጃ የማግኘት መብትን በሚፃረር ሁኔታ በሞኖፖል በመያዝ እሱ የመረጠውን እውነታ ብቻ፣ እሱ በመረጠው ጊዜና መንገድ ለሕዝብ ማንቆርቆር ነው። የዚህ ዓይነት መንገድ የፍርኃት አካሄድ ነው። ጽጌረዳና ዲሞክራሲ አንድ ናቸው። ጽጌረዳ አበባዋ ውብ ነው። ከውብ አበባዋ ጋር ግን እሾህ አላት። እሾሁ የተፈጠረው ለክፉ ነገር አይደለም። የአበባዋን ውበት ከጉዳት የሚጠብቅ የተፈጥሮ መከላከያ ነው። እሾሁም የውበቷ አካል ነው። ስለዚህ ጽጌረዳን ስንወድ የተፈጥሮዋ አካል ከሆነው ከእሾህዋ ጋር ነው። ዲሞክራሲም ‹‹እሾህ›› አለው። የዲሞክራሲ ‹‹እሾህ›› ነፃነቱ፣ ሙያዊ ብቃቱና ትጋቱ ካለው ፕሬስ፣ ብቃቱና ቁርጠኝነቱ ካላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ነፃነቱና ጥንካሬው ካላቸው ሲቪክ ማኅበራት፣ ንቃቱ ካላቸው ዜጎች የሚሰነዘሩ ገንቢና ሂሳዊ እውነታዎች ናቸው። የኢሕአዴግ መንግሥት ከእነዚህ አቅጣጫዎች የሚመጣውን እሾህ ስለሚፈራ እውነተኛ ዲሞክራሲን በሩቁ ብሏል። 3. ኢትዮ ተሌኮምን በሞኖፖል መያዝ ቴሌኮሙዩኒኬሽን በዘመናዊ መልኩ ቴክኖሎጂ የወለደው የእውነት መረጃ መንሸራሸሪያ ጎዳና ነው። በሌላው ዓለም እንደ ፀጋና እንደ ልማት መሣሪያ ሲወሰድ በአምባገነን ሥርዓቶች ግን እንደ አደገኛ መሣሪያ ይወሰዳል። በዚህ ምክንያትም በአገራችንም ይህን ‹‹አደገኛ›› መሣሪያ ለመቆጣጠር ሲባል መንግሥት በሞኖፖል ይዞታል። መንግሥት እንደሚለው ኢትዮ ቴሌኮምን በሞኖፖል የያዘው ለልማት የሚውል ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ (‹‹የምትታለብ ላም››) ስለሆነ ብቻ አይደለም። የመረጃ መንሸራሸሪያ ጎዳናና የእውነት ምንጭ ስለሆነ ነው። እንዲያውም የኢሕአዴግ መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምን በሞኖፖል ለመያዙ ዋናው ምክንያት የከፍተኛ ገንዘብ ምንጭ ከመሆኑ ይልቅ የመረጃ መንሸራሸሪያ፣ የሕዝብ መገናኛና የእውነት ምንጭ የመሆኑ ፍራቻ ነው ብዬ አምናለሁ። የኢሕአዴግ ምንግሥት መረጃ ኃይል የመሆኑን እውነታ ጠንቅቆ ያውቃል። ይህንን እውነታ ይፈራል። 4. በአሳሪና አስፈሪ ሕጎች ራሱን ማጠሩ የኢሕአዴግ መንግሥት ዙሪያውን በአስፈሪና አሳሪ ሕጎች በማጠር የእውነት ፍርኃቱን ለመቀነስ ይሞክራል። የእውነት መምጫ መንገዱ ብዙ ነው። ለምሳሌ በነፃ ፕሬስ አማካይነት ይመጣል። በጠንካራ ሲቪክ ማኅበራት አማካይነት ይመጣል። የጠያቂነትና የለምን ባይነት መንፈስ ባላቸው ዜጎች አማካይነት ይመጣል። እውነትን የሚፈራው የኢሕአዴግ መንግሥት አንዱ ዋነኛ ሥራው ሆኖ የተገኘው የእውነት መንገዶችን የሚዘጉ አስፈሪና አሳሪ አዋጆችን ማውጣት ነው። ነፃው ፕሬስ የእውነት መምጫ መንገድ እንዳይሆን በአሳሪና አስፈሪ የፕሬስ አዋጅ ታጥሯል። ሲቪክ ማኅበራት የእውነት መምጫ መንገዶች እንዳይሆኑ በሲቪክ ማኅበራት አዋጅ ታስረው እንዲሽመደመዱ ተደርገዋል። የጠያቂነትና የለምን ባይነት መንፈስ ያላቸው ዜጎች የእውነት መንገድን እንዳያሳዩ በሽብር ሽፋን በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ እንዲሸማቀቁ ተደርገዋል። ከዚያም ባለፈ ወደ ወህኒ እንዲወርዱ የተደረጉም አሉ። ኢትዮጵያ የሽብርተኝነት ሥጋት የለባትም ማለት አይደለም። የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ስታወጣም የመጀመሪያ አገር አይደለችም። ሌሎች አገሮችም አውጥተዋል፣ በተለይ በዲሞክራሲ የዳበሩ አገሮች። ትልቁ ጥያቄ ‹‹የወጣው ፀረ ሽብር አዋጅ በማን እጅ ነው? በምን ዓይነት መንግሥት እጅ ነው?›› የሚለው ነው። በዲሞክራሲ በዳበሩ አገሮችና በእኛ አገር ያለው ሁኔታ የሰማይና የምድር ያህል ይራራቃል። በዲሞክራሲ የዳበሩ መንግሥታት ራሳቸው የዜጎቻቸው መብቶች እንዳይነኩ በከፍተኛ ደረጃ የሚጨነቁ፣ የሚጠበቡና የሚጠነቀቁ ናቸው። አርባ ዓመት ለመግዛት ዕቅድ በማውጣት ቸክለው የተቀመጡና ሥልጣናቸውን ለመከላከል ከፀሐይ በታች ባለ በማንኛውም ዓይነት ስልት ከመጠቀም ወደ ኋላ የማይሉ አይደሉም። የፍትሕ ተቋሞቻቸው ነፃ ናቸው፣ የአስፈጻሚ አካላት ትእዛዝ ፈጻሚዎች አይደሉም። ፖሊሶቻቸውና የደኅንነት ሰዎቻቸው በከፍተኛ ደረጃ የሠለጠኑ፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች የሚያከብሩ፣ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግን በሚገባ የሚያውቁና የሚያከብሩ ናቸው። ስንዝር ሥልጣን ሲሰጣቸው ክንድ የሚወስዱ አይደሉም። ፀረ ሽብር አዋጆቻቸውም በአመዛኙ የሚያተኩሩት ከውጭ በሚመጡ አደጋዎች ላይ ነው። በእኛ አገር በአሁኑ ጊዜ የአዋጁ ዋና ሰለባ የሆኑት በአመዛኙ የአገሪቱ ዜጎች ናቸው። ስለዚህ የኢሕአዴግ መንግሥት በፀረ ሸብር ሽፋን አዋጁን ተቃዋሚዎችንና የጠያቂነትና የለምን ባይነት መንፈስ ያላቸውን ዜጎች ለማጥቃትና በአጠቃላይ ሕዝቡን ለማሸማቀቅና ለማሸበር በመሣሪያነት ይጠቀምበታል የሚል ከፍተኛ ሥጋት አለ። የኢሕአዴግ መንግሥት አፈ ቀላጤዎች ‹‹የፀረ ሸብር ሕጉን የሚፈሩት ሕገወጦች ብቻ ናቸው›› ይሉናል። አዎ፣ እውነት ነፃ በምታወጣበት አገር አባባሉ ያስኬዳል። በእኛ አገር ግን እውነት ነፃ ታወጣለች ብሎ መተማመን አይቻልም። በዚህ ምክንያት ንፁኃን ዜጎችም ፀረ ሽብር ሕጉን ይፈራሉ፣ ሽብርተኞች ሆነው ግን አይደለም። ዜጎች ሽብርተኝነትን ያወግዛሉ። የሚፈሩት የኢሕአዴግ መንግሥት አዋጁን እንደሚፈልገውና እንደሚያመቸው በመለጠጥ ያለ ኃጥያታችን ሊወነጅለንና ሊጎዳን ይችላል ከሚል ሥጋት በመነሳት ነው። ሥጋታቸው ደግሞ ያለመሠረት አይደለም። እንግዲህ የኢሕአዴግ መንግሥት ከነፃው ፕሬስ፣ ከነፃና ጠንካራ ሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም የጠያቂነትና የለምን ባይነት ባህሪ ካላቸው ዜጎች የሚመጣ እውነትን ለመከላከል በተደራራቢ አዋጆች ዙሪያውን አጥሯል። ይህ ደግሞ እውነትን ለመፍራቱ ግልጽ ማሳያ ነው። ለመሆኑ የኢሕአዴግ መንግሥት እውነትን መፍራትና መበርገግ የጀመረው ከመቼ ጀምሮ ነው? መፍራት የጀመረው እውነትን ፊት ለፊት ያየ ዕለት ነው። ያ ዕለት ደግሞ ሚያዝያ 30 ቀን 1997 ዓ.ም. ነበር። በዚያን ዕለት ያየውን እውነት በሳምንቱ ግንቦት 7 ቀን 1997 ደግሞ አየው። ይህ ዕለት ደግሞ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሳይሆን በሕዝብ ድምፅ መሸነፉን የተረዳበትና ይበልጥ የበረገገበት ዕለት ነበር። የአቶ መለስ ዜናዊ የግንቦት 7 ምሽት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም የዚህ መበርገግ ዓይነተኛ ምልክት ነበር። ከእነዚህ የእውነት ቀናት ጀምሮ እስካሁን ድረስ የኢሕአዴግ መንግሥት እንደበረገገ አለ። የእነዚያን ቀናት የሽንፈት እውነታ ዳግም ላለማየት የማይፈነቅለው ድንጋይ፣ የማይወስደው ዕርምጃ፣ የማያወጣው ግልጽም ሆነ ስውር መመርያ፣ የማይቀይሰው ስትራቴጂ፣ የማይደነቅረው መሰናክል፣ የማያወጣው ወጪ፣ የማይጥሰው እሴት የለም። በምርጫ የመሸነፍ እውነታን ሲያስበው ስለሚያስበረግገው፣ ለ2007 ምርጫ ዝግጅት የጀመረው በ2002 ምርጫ ማግሥት ነው። የ2002 ምርጫ ዝግጅት የጀመረው በ1997 ምርጫ ማግሥት ነው። (ይህ አካሄድ በእንድ ጎኑ ሲታይ የሚደነቅ ነው። ምርጫ ወራት ብቻ ሲቀረው የሚንደፋደፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ ብዙ ትምህርት ሊቀስሙ ይችላሉ፣ እስካሁን አላደረጉትም እንጂ)። ለማጠቃለል የኢሕአዴግ መንግሥት አሳምሮ ይፈራል። አልፈራም ካለ አለመፍራቱን በድርጊቶቹ ያሳይ። በሶማሊያ ጦርነት የኢትዮጵያ ሕዝብ የከፈለውን መስዋዕትነት በተመለከተ ትክክለኛና ይፋዊ መረጃ በመስጠት የሕዝብ መረጃ የማግኘት መብቱን ያክብር። የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች (እውነተኛ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ) ለሚመጡ ሐሳቦች መንሸራሸር በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ ሳይሆን ዓመቱን በሙሉ ክፍት ያድርግ። በተጨማሪ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፉንና ኢትዮ ቴሌኮምንም ለግሉ የንግድ ዘርፍ ክፍት ያድርግ። አሳሪና አስፈሪ ሕጎችን በመሰረዝ ወይም በማሻሻል እንደ ምሽግና እንደ ማጥቂያ መሣሪያ መጠቀምን ያቁም። የኢሕአዴግ መንግሥት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ካላመጣ አሥር ጊዜ በቃል ‹‹አልፈራም!›› ቢልም እውነትን ለመፍራቱ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ተጽፈው የሚታዩ ጉልህና ተጨባጭ ማስረጃዎች ሆነው ይቀጥላሉ። ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ቀደም ሲል የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ አመራር የነበሩ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው hawsba3@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
SOURCE: REPORTER

No comments:

Post a Comment