Wednesday, November 13, 2013

በአዲስ አበባ ፍተሻው በአዲስ መልክ ተጀመረህዳር (ሦስት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-አልሸባብ የተባለው አሸባሪ ቡድን እና በኤርትራ መንግስት እገዛ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች በኢትዮጽያ ውስጥ የተለያዩ ስፍራዎች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም እየተዘጋጁ መሆናቸውን የሚያሳይ አስተማማኝ መረጃ ያለው መሆኑን የብሄራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ የፀረ ሽብር ግብረ ሃይል ጥቅምት 27 ቀን 2006 ዓ.ም ካስታወቁ በኃላ በአዲስአበባ በመንግስት በግል ተቋማት ከወትሮው የተለየ ፍተሻ በአዲስ መልክ ተጀምሯል፡፡
ግብረኃይሉ በዚሁ መግለጫው በየአካባቢው ሆቴሎች፣ ሕዝባዊ ተቋማት፣ የፍተሻ ኬላዎች ላይ የሚሰሩ የፍተሻ ስራተኞች ተግባራቸውን ከወትሮ በተለየ ጥንቃቄ እና አትኩሮት ማከናወን እንዳለባቸውም መግለጹን ተከትሎ በተለይ በሆቴሎችና በሕዝባዊ መዝናኛዎች ለየት ያሉ ፍተሻዎች እየተካሄዱ ነው፡፡
በካዛንቺስ አካባቢ የሚገኙ ራዲሰን ብሉ እና ጁፒተር ኢንተርናሸናል ሆቴሎች የመፈተሻ ዘመናዊ ማሽኖች ጭምር ገዝተው ለመግጠም የተገደዱ ሲሆን አነስተኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሰዎች መፈተሸ ኤሌክትሮኒክስ የደህንነት መፈተሻ መሳሪያዎችን በብዛት በመሸመት በስራ ላይ እያዋሉ ነው፡፡
ይህንን ተከትሎ ፖሊስ ጠርጥሬአቸዋለሁ ባላቸው እንደሳሪስ ባሉ አካባቢዎች ድንገተኛ የቤት ለቤት ፍተሻ ሰሞኑን ያካሄደ ሲሆን በአዲስአበባ ዋና ዋና መንገዶች ላይም ተሸከርካሪዎችን በማቆም ረጅምና አሰልቺ ፍተሻዎችን ሲያካሂድ ታይቶአል፡፡
የጋራ የፀረ ሽብር ግብረ ሃይሉ የተላለፈው ይኸው መግለጫ ባለፈው ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አካባቢ ለሽብር ተግባር ሲሰናዱ በራሳቸው ላይ ባደረሱት አደጋ ህይወታቸው ጠፋ በተባሉ ሁለት ሶማሊያዊያን አሸባሪዎች ጉዳይ ላይ ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱን ያስታውሳል፡፡
እነዚህ ሁለት ግለሰቦች በወቅቱ የኢትዮጵያና የናይጀሪያ ብሄራዊ ቡድኖች የሚያደርጉትን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር በሚከታተሉ የስፖርት አፍቃሪዎች ላይ አደጋ ለማድረስ ዓላማ እንደነበራቸው የሚያሳዩ መረጃዎች መገኘታቸውን መግለጫው በተጨማሪ ያስታውቅ እንጂ ፍንዳታው በእርግጥም በአሸባሪ ቡድኖች ስለመፈጸሙ ለሕዝብ እስካሁን በተጨባጭ የገለጸው ነገር የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ወገኖች በ1997 ዓ.ም  ገዥው ፓርቲ ራሱ ፈንጂ ቀባሪ፣ ራሱ አምካኝ የሆነበትንና የተጋለጠበትን ክስተት በማስታወስ ነገሩን በጥርጣሬ እየተመለከቱት ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም ሆቴሎቻቸውንና መኖሪያ ቤታቸውን የሚያከራዩ ባለንብረቶችና ባለ ይዞታዎች በተለይ የውጭ ሀገር ዜጎችንና የማያውቋቸውን ኢትዮጵውያንን አድራሻ በአግባቡ መዝግበው በመያዝ መረጃን ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ የህግ ግዴታ እንዳለባቸው መግለጫው በጥብቅ አስጠንቅቋል፡፡
በተመሳሳይ መኪናዎቻቸውን የሚያከራዩ ግለሰቦች፣ድርጅቶችና የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለታክሲዎች የደበኞቻቸውን ማንነት የሚገልጽ ሙሉ መረጃ የመያዝና የማሳወቅ እንዲሁም የሚጭኗቸውን ማናቸውንም ዕቃዎች የማወቅ ግዴታም ያለባቸው መሆኑን የፀረ ሽብር ግብረ ሀይሉ አስታውቋል፡፡ ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥመው ሁኔታውን በአቅራቢያው ላሉ የፖሊስና የፀጥታ ሀይሎች እንዲያሳውቅም አሳስቧል፡፡

No comments:

Post a Comment