Thursday, November 28, 2013

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 3ኛ ዓመት ተማሪዎች ሲጮኹ ዋሉ፤ ዲኑ ተማሪዎቹን “በዩኒቨርሲቲው በቀን ሦስቴ እየበላችሁ ጠገባችሁ” አሉ


የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 3ኛ ዓመት ተማሪዎች ሲጮኹ ዋሉ፤ ዲኑ ተማሪዎቹን “በዩኒቨርሲቲው በቀን ሦስቴ እየበላችሁ ጠገባችሁ” አሉ
NOV 27,2013
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 3ኛ ዓመት ተማሪ የሆኑ ተማሪዎች ከውጤት አሰጣጥ ጋር ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ሲጮኹ መዋላቸውን የዘ-ሐበሻ የባህርዳር ዘጋቢዎች ከስፍራው ዘግበዋል። እንደ ዘጋቢዎቻችን ገለጻ የ3ኛ ዓመት ተማሪዎቹ ጩኸታቸውን ሲያሰሙ ከዋሉ በኋላ የዩኒቨሲቲው ዲን ዶ/ር ባየልኝ ዳምጤ ሰብስበው ያነጋግሯቸው ቢሆንም፤ ዶ/ሩ ችግሩን ከማብረድ ይልቅ እሳት ለኩሰውበት ሄደዋል ሲሉ ተማሪዎቹ ለዘ-ሐበሻ ዘጋቢ ነግረውታል።
ዩኒቨርሲቲው አዲስ ባወጣው መመሪያ መሠረት በተማሪዎች ማርክ አሰጣጥ ላይ ከዚህ ቀደም 85 የነበረው ወደ 95 ያድጋል ባለው መሠረት ተማሪዎቹ ልክ እንደ 1ኛ እና 2ኛ ዓመት ተማሪዎች ማርክ ሊያዝልን ይገባል በሚል የዛሬው የባህርዳር ዩኒቨሲቱ ሁከት መፈጠሩን የገለጹት ዘጋቢዎቻችን፤ ይህን ተከትሎም በሃገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ፖለቲካ የሚመለከቱ መፈክሮችን ተማሪዎቹ ሲያሰሙና ሲጮኹ ከዋሉ በኋላ ዶ/ር ባየልኝ ዳምጠው ጠርተው አንጋግረዋቸዋል። ተማሪው ዶ/ር ባየልኝ ወደ ጠሩት ስብሰባ ሲገባ የተለያዩ መፈክሮችን እያሰማ ሲጮህ ነበር ያሉት ዘጋቢዎቻችን ዲኑ ስብሰባውን ሲመሩ የነበረው እንደተማረ ሰው አልነበረም የሚሉ አስተያየቶች ከ3ኛ ዓመት ተማሪዎቹ ተሰምቷል።
ዶ/ር ባየልኝ ተማሪውን ሰብስበው “በቤታችሁ በነበራችሁበት ጊዜ በቀን 2 ጊዜ የምትበሉ ተማሪዎች እዚህ ዩኒቨሲቲ ውስጥ በቀን 3 ጊዜ እየበላችሁ ጠገባችሁ፤ ይሄ ጥጋብ ነው ስለማርክ አሰጣጥ ጥያቄ ያስነሳችሁ” የሚል አንባገነናዊ ንግግር በመናገራቸው ተማሪው ቁጣውን እንዳሰማ የገለጹት የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች “እኛ በችግረኛ ሃገር ላይ ሆነንና የትምህርት ጥራት በሌለበት መልኩ ያደጉ ሃገራት የትምህርት ፖሊሲ መሞከሪያ አንሆንም” በሚል የ3ኛ ዓመት ተማሪዎቹ ቁጣቸውን ገልጸዋል ብለዋል። ይህን ተከትሎም ጉዳዩ እኛንም ይመለከተናል በሚል የባርዳር ዩኒቨርሲቲ 1ኛ እና 2ኛ ዓመት ተማሪዎች የ3ኛ ዓመት ተማሪዎቹን ጥያቄ መቀላቀላቸው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ዘ-ሐበሻ ወደ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ዲን ቢሮ ደውላ የነበረ ቢሆንም ዶ/ር ባየልኝ ዳምጤን ማግኘት አልቻለችም። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አሁንም ውጥረቱ እንዳለ የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment