Monday, November 4, 2013

ጤፋችንን ማን ሰረቀው?
“ኢትዮጵያ የጤፍ ውጤቶችን ወደአውሮፓ መላክ አትችልም” 
 
by Addis Guday
መላው ዓለም የጤፍ መገኛ ሃገር ኢትዮጵያ መሆኗን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በተለይ በሐገሪቱ ጥቂት ቀናት ለማሳለፍ የቻሉ ወይም የስነ ምግብ ተመራማሪዎች እኛ በተለምዶ “የማይረባ” የምንለውን ነገር ግን እነርሱ ታዕምራዊ ወይም (super grain) እያሉ የሚጠሩትን ጤፍን ብቻ ሳይሆን እንጀራችንን ጭምር ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በዚህ የራሷ የሆነውንና የምትታወቅበትን ጤፍ ወደ አውሮፓ ሐገራት ሆነ ወደ ሰሜን አሜሪካ ሌላው ቀርቶ ወደ ሩቅ ምስራቋ ጃፓን በመውሰድ ተጠቃሚ ለመሆን አትችልም፡፡ ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ኢትዮጵያ በገዛ ጤፏ በማንኛውም መልኩ ወደውጭ በሚካሀ ንግድ ላይ በመሳተፍ ለመጠቀም ብትሞክር የከፋ ቅጣት የሚያስከትልባት መሆኑ ነው።ለዚህ ዋንኛው ምክንያት ደግሞ አንድ የሆላንድ ካምፓኒ የኢትዮጵያን ተፈጥሮአዊ ስጦታ ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ደባ ሊዘርፍ በመቻሉ ነው፡፡
ጉዳዩ እጅግ በጣም አሳሳቢ እና ፈጣን የሆነ ብሔራዊ ንቅናቄን በመፍጠር ጠንከር ያለን መፍትሄ የሚሻ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ሰፊ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ለመካሄዱ ምንም ይፋዊ የሆነ መግለጫ አልተሰማም፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያልተወለዱትም ያላደጉት የኖርዌይ ተመራማሪዎች ለኢትዮጵያ በመቆርቆር በጉዳዩ ላይ ሰፊ ምርመራን በማድረግ በዚህ አሳፋሪ ሊባል በሚችል ውንብድና ዙሪያ አይንገላጭ የሆነ ጥልቅ ጥናታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶም ጉዳዩ ሰፊ የሆነ ትኩረት አግኝቷል፡፡ በተለይ በመስኩ እየተደረጉ ያሉ ጥናቶች በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው በጥንቃቄ የተከናወነው ወንጀል በጣም ድርብርብ የሆነ ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱን ዘላቂ ጥቅም በመጉዳት እንደ ሃገር የሆነውን ለመቀበል በጣም የሚያሳፍር መሆኑን የተለያዩ ታዛቢዎች በምሬት ጭምር እያወሱ ነው፡፡ ምንም እንኳን ነገሩ አሁን ላይ በጣም የተወሳሰበ ሁኔታ ቢፈጠርም ከዚህ የበለጠ የከፋ ጉዳት በሃገሪቱ ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ ጠንከራ ምላሽ እና በጠራራ ፀሀይ የመዘረፉን ትልቅ የተቀነባበረ ውንብድና በማጋለጥ ሐገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት አፋጣኝ የሆነ እርምጃ መውሰድ ያለበት መሆኑን የሃገር ውስጥ እና የውጭ ምሁራን እያሳሰቡ ይገኛሉ፡፡ ይሄንኑ አንገብጋቢ ጉዳይ መነሻ በማድረግ የጤፋችንን በጠራራ ፀሐይ የመዘረፋችንን አሳዛኝ እውነታ በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡
በእርግጥ ጤፍ የኢትዮጵያ ብቻ ነው? 
አንድን የብዝሃ አካል “ሃገር በቀል” ለመሰኘት በሌሎች ሐገራት ያለመብቀሉ በጥንቃቄ መረጋገጥ አለበት፡፡ የጤፍን ምንጭ በተመለከተ ለማወቅ በተደረገው ከ85 ዓመታት በላይ የፈጀ ሰፊ ጥናትና ምርምር ኢትዮጵያ የጤፍ መገኛ ምንጭ መሆኗ ተረጋግጧል፡፡ ታዋቂው ሩሲያዊው ቦታኒስት አግሮኖሚስት፣ የዘር አጥኚው ሁለገቡ ተመራማሪ ኒኮላይ ኢቫኖሺችን ጨምሮ የአሜሪካው ዕውቁ የዘረ መል አጥኚው ጃክ ሐርላንን የመሳሰሉ የዘርፍ ምሁራን ጤፍ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከኢትዮጵያ ወጥቶ በግብፅ እና ህንድ የበቀለበት ሁኔታ ቢኖርም በዋንኛነት ግን መነሻው ኢትዮጵያ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡ በተለይ አሜሪካዊው የብዝሃ ህይወት ተመራማሪው ጃክ ሐርላ ጤፍን “the nobel cereal of Ethiopia” በማለት ከኢትዮጵያ ከሚገኙ እህሎች በእጅጉ ልዩ መሆኑን መስክሮለታል፡፡
በሐገሩ የተናቀው ጤፍ አስደናቂ ጥቅሞች
በተለምዶ በሐገራችን ጤፍ ያለው ንጥረ ነገር ብረት እንጂ ከዛ ውጪ ግን ሆድን ከመንፋቱ ባለፈ አንዳችም ፋይዳ የሌለው ስለመሆኑ በስፋት ይወሳል፡፡ ነገር ግን የጤፍን ዘር በጥንቃቄ የመረመሩ የመስኩ ሙያተኞች ግን በገዛ ሐገሩ የተናቀው ጤፍ የበርካታ ዘርፍ ብዙ ጥቅሞች መነሻ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በመጠናቸው በጣም ደቃቃ ከሆኑ ጥራጥሬዎች መካከል በቀዳሚነት የሚወሳው ጤፍ በተለይ በመስኩ ምሁራን ዘንድ “super-grain” (ልዕለ ጥራጥሬ) በመሰኘት ይሞካሻል፡፡ ጤፍን ከሌሎች ጥራጥሬዎች በእጅጉ የተለየ እንዲሆን ያስቻላቸው ደግሞ በውስጡ የያዛቸው በርካታ የንጥረ ነገር ይዘቶች እና በተለይ በጣም አስቸጋሪ በሆነ የአየር ፀባይ ውስጥ ጭምር ለመብቀል በመቻሉ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ጤፍ 2.6 በመቶ ፋት በመያዝ ከፍተኛ የሀይል ምንጭ፣ በአማካይ የ11 በመቶ የፕሮቲንን ይዘትን በማቀፍ የጥንካሬ ምንጭ እንዲሁም የብረትና ካልሲየም በመሳሰሉ ይዘቱም በንጥረ ነገሮች የዳበረ ነው፡፡ ከዚህ በላይም ቀላል የማይባል የቫይታሚን ይዘትን በውስጡ አቅፎ በመያዝ በተለይ አኒሚያ (ደም ማነስ) በብዛት በሚኖርበት የሃገሪቱ አካባቢ በውስጡ በያዘው ሚኒራል አማካኝነት ሰዎችን በመፈወሱ ረገድ የላቀ ጠቀሜታ አለው፡፡ 
ጤፍን በተለይ በአውሮፓ በእጅጉ ተወዳጅ ካሰኙት ነገሮች መካከል አንዱ `ግሉቲን` (gluten) የተሰኘው ንጥረ ነገር በውስጡ የሌለ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም በተለይ ለስንዴ ምርቶች አለርጂ የሆኑ ሰዎች ዕድሜ ልካቸውን ከዳቦ እና መሰል እንደ ኩኪስ ካሉ የስንዴ ውጤቶች እንዳይርቁ ልዩ መፍትሔን ለመያዝ በቅቷል፡፡
ጤፋችን እንዴት ተሰረቀ?
ጉዳዩ ከተፈፀመ ስምንት ዓመታት አልፎታል፡፡ የኢትዮጵያ የብዝህ ህይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩትና ከኢትዮጵያው የእርሻ ጥናት ድርጅት ጋ በተመባበር የሆላንዱ የሄልዝ ፐሮፎርማንስ ፍድ ኢንተርናሽናል በስፋት በሚታወቅበት የእንግሊዘኛ ምህፃረ ቃል (HPFI) ካምፓኒ ጋ በጤፍ ዘር አጠቃቀም ዙሪያ የጋራ ስምምነትን ያደረጋሉ፡፡ በዚህ ሰፊ ዝርዝርን ባካተተው ስምምነት መሰረት የሆላንዱ ካምፓኒ የተፈቀደለትን የጤፍ ዘር ከኢትዮጵያ ወስዶ በስፋት ጤፍን በማምረት በኢትዮጵያ በባህላዊ መንገድ በጥቅም እየዋለበት ከሚገኘው እንጀራ አድርጎ ከመሸጥ ባለፈ በፈለገው አዲስ መንገድ የጤፍ ግብዓትን ተጠቅሞ አዲስ የሆነ የምርት አቅርቦትን የማቅረብ ልዩ መብት ተሰጥቶታል፡፡ ይሁን እንጂ HPFI የተሰኘው ካምፓኒ ከሚያገኘው ትርፍ የጤፍ መገኛ ለሆነችው ኢትዮጵያ ተገቢውን የትርፍ ማጋራት የመፈፀም፣ ከጤፍ አመራረት ጋ በተያያዘ የደረሰበትን ግኝት የማካፈል፣ ከኢትዮጵያ ላገኘው ፈቃድ መደበኛ ክፍያ መፈፀም በተለይም የሆላንዱ ካምፓኒ በማንኛውም መልኩ የጤፍ ምርትን በሚያቅርበበት ወቅት የጤፍ መገኛ ኢትዮጵያ መሆኗን የማሳወቅ ግዴታ ተጥሎበት ነበር፡፡ የሆላንዱ ካምፓኒ ግን ለዚህ ግዴታ ለመገዛት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ከዚህም አልፎ አሳዛኝ የሆነን ውንብድና በሀገሪቱ ላይ ፈፅሟል፡፡
ጤፍ በጁስ መልክ እና በኩኪስ መሰል ምርቶች ቢቀርብ በመላ አሜሪካ እና አውሮፓ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ እንደሚያስገኝ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዋንኛው መንስኤ ደግሞ ጤፍ በውስጡ ግሉቴን የተሰኘ ንጥረ ነገር የማይገኝበት ስለሆነ እና የንጥረ ነገር ይዘቱ እጅግ በጣም የላቀ በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ለጤፍ ግንዛቤ ያላቸው በሙሉ ከጤፍ የተገኙትን ማናቸውም ውጤቶች ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ሁሉ ተፈላጊነቱ ጤፍን በቀላሉ አትራፊ ቢያሰኝም የሆላንዱ ካምፓኒ ግን ሆን ብሎ ከስሬያለሁ በሚል ከኢትዮጵያ ጋ ያለውን ግንኙነት በይፋ አቋረጠ፡፡
የሆላንዱ ካምፓኒ ከስሬያለሁ ብሎ ይዘጋ እንጂ በመላ አውሮፓ በአሜሪካ ብሎም በጃፓን ጭምር ከጤፍ ምርት ጋ በተያያዘ የባለቤትን መብት (ፓተንት) ተቀብሏል፡፡ በዚሁ መሰረት ካምፓኒው ከስሬያለሁ ቢልም ውስጥ ለውስጥ ግን ይህን የባለቤትን መብቱን ለሌላ ሶስተኛ ወገን ሽጦታል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ልታገኘው የሚገባት እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም በአደባባይ ልታጣ ትችላለች፡፡ ይሄ ደግሞ የዓለም አቀፍን የብዙሃ ሕይወት ስምምነት ሆነ ሌሎችንም የባለቤትነት መብቶች የጣሰ ነው፡፡ ከዚህ የሚከፋው ግን ከስሬያለሁ ያለው የሆላንዱ ካምፓኒ ዋና ዳይሬክተሩን ጨምሮ ሌሎችንም ሠራተኞቹ ወደ አዲስ ካምፓኒ በማዘዋወር የጤፍ ዱቄት እና ሌሎችንም በዘመናዊ መልኩ በጤፍ ግብዓት የተመረቱ ውጤቶችን በሆላንድ እና በሌሎችም ሐገራት በስፋት በማዘዋወር ከፍተኛ ትርፍን እያጋበሰ መሆኑ ነው፡፡ 
ኢትዮጵያ ግን ከባለቤትነት መብቷ የትርፍ ድርሻ ተጋሪነቱ ሆነ ሌሎች መሰል ጥቅሞችን ልታገኝ ቀርቶ ካምፓኒው አስቀድሞ የጤፋ እና ተያያዥ ምርቶች ባለቤትነቱን በአውሮፓ በማስመዝገቡ በገዛ የተፈጥሮ ስጦታዎ መጠቀሟ እንኳን ሊያሰቀጣት የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩ በርካቶችን አሳዝኗል፡፡ በተለይ አስቀድሞ በሆላንድ የነበረው የጤፍ ባለቤትነት መብት በአውሮፓ ባለቤትነት መብት ጽ/ቤት በኩል እንዲዘገብ በመደረጉ በመላ አውሮፓ ካምፓኒው የጤፍ ምርቶች ብቸኛ ባለቤት እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በዛ ላይ የባለቤትነት መብቱ “ጤፍን አቡክቶ ለተለያዩ ጥቅምች ማዋል፣ ለዳቦ፣ ለፓን ኬክ፣ ለኩኪስ፣ ለጣፋጭ መጠጦች ሆነ ለሌሎችም በርካታ አይነት ምርቶች ከድርጅቱ በቀር በአውሮፓ ምድር ማንም መጠቀም አይችልም፡”፡ የሚልን ሐሳብ ያዘለ ነው፡፡ የሚገርምው ይሄን የባለቤትነት መብትን ሲጠይቅ የሆላንዱ ካምፓኒ ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት ያቀረበው ምክንያት ሃገሪቷ በከፍተኛ ደረጃ ከጤፍ ውጤቷ ትጠቀም ዘንድ በማሰብ ነው፡፡ ቢልም በስተመጨረሻ ግን በተሰራው ሸፍጥ ሃገሪቱ ከባለቤትነት መብቱ ውጪ እንድትሆን ተደርጋለች፡፡ 
በዚህ ብቻ ሳያበቃም ካምፓኒው በባለቤትነት መብቱ ውስጥ በፍጹም ያለ ኢትዮጵያ ፍቃድ በቀር እንኳን ባለቤት ሊሆን ቀርቶ ገንዘብ ለማግኘት የማይችልበትን የሃገራችንን ሐገር በቀል እውቀት ጨምሮ የባለቤትነት መብት በመጠየቁ በግልፅ የሕግ ጥሰት በመፈፀሙ እንደ ኖርዌዩ ተመራማሪ ጋን አንደርሰን እና የብዙሃ ሕይወት ተመራማረው ቶን ዊንግዝ ከሆነ “ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን የባለቤትነት መብቷን ለማስጠበቅ ዕድል አላት፡፡” ይሁን እንጂ በህግ ዕውቀት ማነስ እና ለክርክሩ የሚውል በጀትን ባለማግኘት ሐገሪቱ ማግኘት ያለባትን ድርብርብ ጥቅሞችን አጥታለች፡፡ ጉዳዩን ዝም ብሎ ለማየት ግን መንግስት ባለበት ሐገር የሚበጅ መፍትሄ አይደለም

No comments:

Post a Comment