Saturday, November 9, 2013

ከዕለቱ ቃለ ምልልሶች – የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ቀጣይ አንድነት በአብነት ትምህርት ቤት: የፕሮፌሰር ተከሥተ ነጋሽ አስተያየት

tegestemediaእ.አ.አ በ፲፱፻፵፯ ዓ.ም. በአሥመራ ከተማ ተወልደው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሥመራ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅማ ተከታትለዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአሥመራ ዩኒቨርሲቲ በሕግ አግኝተዋል፡፡ ከ፲፱፻፸፪ – ፲፱፻፸፬ ዓ.ም በአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩት ፕሮፌሰር ተከሥተ በሎንዶን ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹ስኩል ኦቭ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ›› ሁለተኛ ዲግሪ ያገኙ ሲኾን የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከስዊድን ኡፕሳላ ዩኒቨርስቲ በታሪክ ትምህርት ሠርተዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ዛሬ ታትሞ ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል÷ የኤርትራ ሕዝብ ዛሬ ያለበትን የነጻነት ኹኔታ ከቀድሞው ጋራ ማስተያየትንና “Ancient Eritreans” በሚል ርእስ የኤርትራ ቴሌቪዥን በቅርቡ ስላሳየው ዶኩመንታሪ የሚመለከት ነበር፡፡
የታሪክ ምሁሩ በተለይ ለሁለተኛው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፣ በኢትዮ – ኤርትራ መካከል ያለው ወቅታዊ ችግርና የሕዝቡ ቀጣይ አንድነት (በፕሮፌሰሩ አነጋገር÷ በኤርትራ በኩል እየተጠየቀ ያለውን ድንበር በማሥመር ሳይኾን ከደርግ ሽንፈት በኋላ የተሠመረውን ድንበር በማፍረስ ፍጽምና እንደሚያገኝ) አመልክተዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ በምላሻቸው ውስጥ፣ የሁለቱ መንግሥታት ግንኙነት በቆመበት ኹኔታ ውስጥ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኤርትራ) ወጣት ኦርቶዶክሳውያንን በድብቅ ወደ ጎንደር ለአብነት ትምህርት ይልኩ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ለምሳሌ ያህል÷ ጠብቃ ባቆየችው የአብነት ትምህርቷ እና ቤተ ጉባኤዋ በኩል በይበልጥም ለኦርቶዶክሳውያን ካህናትና ምእመናን ቀጣይ አንድነት ምክንያትና ለሁለቱ መንግሥታት ችግር የመፍትሔ አካል (cohesive institution) መኾን እንደምትችል አጠይቀዋል፡፡ ጥያቄውን በማስቀደምና ምላሹን በማስከተል በጡመራ መድረኩ አስተናግደነዋል፡፡
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ 18 ቁጥር 721 ቅዳሜ፣ ጥቅምት ፴ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
ኤልሳቤጥ ዕቊባይ
አዲስ አድማስ፡- የኤርትራ ሕዝብ አሁን ያለበትን የነጻነት ኹኔታ ከቀድሞው ጋራ ሲያስተያዩት ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?
ፕ/ር ተከሥተ ነጋሽ፡- እኔኮ በመጀመሪያም ኤርትራውያን ከማን ነው የሚገነጠሉት የሚል አቋም ነው ያለኝ? ማነው ከማን የሚገነጠለው? የደቡብ ወይም የኦሮሞ ሕዝቦች እንገነጠላለን ቢሉ ኖሮ ምክንያት ነበራቸው፡፡ የኤርትራ የነጻነት ጥያቄ በተነሣበት ወቅት ኤርትራውያኑና ከላይ የጠቀስኋቸው ሕዝቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ያገኙትን ዕድል (comparative advantage) ስናይ፣ ኤርትራውያኑ በጣም ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ በጣሊያን፣ በእንግሊዝ እና በፌዴሬሽኑ ዘመን፤ በ፲፱፻፷ዎቹ የዐዲስ አበባ ሀብታሞቹ እነርሱ ነበሩ፡፡ በትምህርት መስክ 25 በመቶ የዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ኤርትራውያን ነበሩ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችንም ካየሽ 25 በመቶ የሚኾኑት ኤርትራውያን ነበሩ፡፡ ይህን ዕድል ያገኙ ሰዎች ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን ሲሉ ምክንያቱን ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምንም ምክንያት አልነበራቸውም፡፡
ለናፅነት የተደረገው እንቅሰቃሴ ሠላሳ ዓመት ቢፈጅም ስድሳ ሺሕ ሕዝብ ቢሞትም በቂ ምክንያት አልነበረውም፡፡ የኔ ጥናት ‹‹የጣልያን ቅኝ አገዛዝ በኤርትራ›› የሚል ነው፡፡ እንዲገባኝ ሞክሬአለኹ፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል እንዳለባት የሚያሳይ ምንም ነጥብ አላገኙኹም፡፡ ነጻ ወጣን አሉ፡፡ ሁለት ዓመት ሳይቆዩ፣ ‹‹እኛ የታገልነው ለናፅነት ብቻ አይደለም፤ የኛ ዕድል ከኢትዮጵያ ጋራ ነው›› ማለት ጀመሩ፡፡ ይህን የሚሉት ተገደው ነው፤ ምክንያቱም የኤርትራ ኢኮኖሚ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ በራሱ ሊቆም የሚችል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ልዩ አገር ነች፤ ነጻነቷን ጠብቃ የቆየች አገር ነች፡፡
አዲስ አድማስ፡- የኤርትራ ቴሌቪዥን በቅርቡ “Ancient Eritreans” (የጥንት ኤርትራውያን) የሚል ዶክመንታሪ አቅርቦ ነበር፡፡ አይተውታል?
ፕ/ር ተከሥተ ነጋሽ፡- (ረጅም ሣቅ) አላየኹትም፡፡ ግን ምንም ዐዲስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ወጣቶቹ ኢትዮጵያን አያውቋትም፤ ነገር ግን መንግሥት የሚያደርገው አንድ ነገር ነው፤ ሕዝቡ የሚያስበው ሌላ ነገር ነው፡፡ መንግሥት በቴሌቪዥን የሚያሳየውና ሕዝቡ የሚያስበውና የሚመኘው ሌላ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ብትለያይም ወጣቶቻቸውን በድብቅ ለትምህርት ወደ ቤጌምድር(ጎንደር) ይልኩ ነበር፡፡
የ[ፕሬዝዳንት]ኢሳይያስን መረጃ በማየት ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ኤርትራዊውን ማን አገኘው? የተለየን ነን የሚል አቋም የት ነው ያለው? በኤርትራ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ምን ያህል አለ ለሚለው መልስ ለማግኘት ድንበሩ መፍረስ አለበት፡፡ ለሁለቱ ሕዝቦች መፍትሔ የሚኾነው በኤርትራ በኩል እየተጠየቀ ያለው ድንበር ሲሠመር ሳይኾን ከደርግ ሽንፈት በኋላ የተሠመረው መሥመር ሲፈርስ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment