Saturday, February 22, 2014

የብአዴኑ አቶ አለምነው ህዝብን ይቅርታ ጠይቆ ለፍርድ መቅረብ አለበት


ብስራት ወልደሚካኤል
የብአዴን/ኢህአዴግ ዋና ፀሐፊ እና የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አለምነው መኮንን በግልፅ እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብ በመሳደቡ ያለምንም ማንገራገርና ማምታታት ይቅርታ ጠይቆ እራሱን ለፍርድ ማቅረብ አለበት፣ ማስተዋሉ ካለው፡፡ በርግጥ የኢህአዴግ መሪዎች የህዝብና የሀገር ክብር እንደሌላቸው ግልፅ ነው፡፡ ያው በትዕቢትና በጠመንጃ እንጂ አንዳቸውም ህዝባዊ ፈቃድና ይሁንታ አግኝተው እንደማይመሩ እራሳቸውም ያውቁታል፡፡
ነገር ግን እንደ አቶ አለምነው መኮንን በቆሸሸ አስተሳሰብ ህዝብን ያህል ነገር ባለጌ ስድብ የሚሳደብ አይደለም ህዝብን ቤተሰቡን የመምራት ብቃት አለው ብሎ ማመን ይቸግራል፤ ይበልጥ ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመዶቹ አዘንኩላቸው፡፡
ብአዴን/ኢህአዴግም ቢሆን ምንም እንኳ ለህዝብ ክብር ኖሮት ባያውቅም አቶ አለምነው መኮንንን በአደባባይ ፍርድ በማቅረብና ከስራ በማሰናበት ተገቢውን ፍርድ ሰጥቶ ተፈፃሚ ማድረግ አለበት እላለሁ፡፡ አለበለዚያ አቶ አለምነውን እከላከላለሁ ብሎ የሚል ከሆነ እራሱ ብአዴን ህዝብን የመምራት ሞራል እንደሌለው አምኖ ስልጣኑን ለህዝብ ማስረከብ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከዚህ በኋላ ህዝብን የመምራት፣ ከህዝብ ታክስ መሰብሰብ፣….የሞራል ብቃቱ የለውም፡፡ ሰውዬው የሰደበው የአማራውን ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላውን የሀገራችንን ህዝብ ነውና፡፡ ህዝብን የሚንቅና የሚሳደብ በህገመንግስቱም ቢሆን ቅጣቱ ከባድ ነው፣ ህግ የሚያከብርና የሚያስከብር ስርዓት ባይኖረንም፡፡
ስለዚህ የእሁዱ የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. አንድነትና መኢአድ የጠሩት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ከህግም ሆነ ከማህበራዊ እሴት አንፃር ተገቢም ትክክልም ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉ የአካባቢው ሰው በሰልፉ ላይ በመታደም እንዲህ ዓይነት ትዕቢተኛ መሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ የሞራል የበላይነት በመሆኑ አስተባባሪዎቹን ቀጥሉበት ቢባል የሚበዛ አይሆንም፡፡
ይህ የተቃውሞ ሰልፍ ግን በባህርዳር ከተማ ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ ምክንያቱም አቶ አለምነው መኮንን ላይ ገዥው ስርዓት እራሱ በግልፅ የእርምት እርምጃም ሆነ የይቅርታ ማስተባበያ ባለመስጠቱ ሁሉም ገዥውች ተመሳሳይ ንቀትና ትዕቢት እንዳላቸው የሚያመላክት ነውና፡፡ ህዝብን የናቀና የሚሳደብ ሰው ለሰከንድም ቢሆን ሊመራ አይገባም፣የሞራል ብቃቱም የለውም፡፡

No comments:

Post a Comment