Tuesday, February 11, 2014

አሥራ አንድ ሰዓታት የፈጀው ክርክር – ሃብታሙ አያሌው (የአንድነት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ)

ክፍል አንድ

በቀናት አቆጣጠር ሰባተኛው እረድፍ በምትይዘው በዕለተ ቅዳሜ ከዚህ ቀደም በጸረ ሽብር አዋጁ ዙሪያ ካደረግነው የተሟሟቀ ክርክር በኋላ ከገዥ ፓርቲ ጋር በሃሳብ ክርክር ለ11 ሰዓታት የተሟገትነው ቅዳሜ ጥር 17 ቀን 2006 ዓ.ም ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ ይህ መድረክ የተዘጋጀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን የድህረ ምረቃ ተመራቂ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ጋር በመተባበር እንደነበረ ከደረሰን የመጥሪያ ደብዳቤ ለመገንዘብ ችለናል፡፡
በዚህ ወቅት በዚህ ጉዳይ ሲምፖዚየም ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያት ምንድነው ? ለሚለው ጥያቄያችን የሲምፖዚየሙ ርዕስ ግልፅ ምላሽ ነበረው፡፡ ‹‹ የዴሚክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት እና የመገናኛ ብዙኃን ግንኙነት›› (Nexus) ማጠንጠኛው ነበር፡፡
የኢህአዴግ መንግስት ‹‹በአቢዮታዊ ዴሞክራሲ ›› ፍልስፍና (ፍልስፍና ሊባል ከቻለ) እስከ 1991 ዓ.ም ከተንገዛገዘ በኋላ የባድሜውን ጦርነት እና የህወኃትን መሰንጠቅ ተከትሎ የፓርቲው የኃይል አሰላለፍ ሲቀየር ተቀጥላ ልማታዊ የሚለው ሥያሜ ጎላ ያለ ስፍራ እንዲያዝ መድጉ አይዘነጋም፡፡
ልማታዊ መንግስት ሲሉ አቢዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለውን ስያሜ ለአንጃው ለመተው የፈለጉት አቶ መለስ ይህንን መጠሪያ የገነገነ ጥላታቸውን በመበታተን ተሸንፈው ከቆሙበት ጥግ ወደ መሃል ለመግባት ወሳኝ ብልሃት አድርገውት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አቶ መለስ ለኤርትራ መንግስት ያሰዳዩ የነበረው ከፍተኛ ወገንተኝነት ኢትዮጵያን ያለወደብ ከማስቀረት ተሸግሮ በኢትዮጵያ ምርቶች ኤርትራ በአለም የንግድ ገበያ ስሟ መጠራት መጀመሩ፤ በኢትዮጵያ ብር እየተገበያየች የዶላር ክምችቷን ከፍ ማድረጓ እና በወጪ እና ገቢ ሸቀጦች እረገድም በምንም ዓይነት የታክስ ሥርዓት አለማለፏ እና የመሳሰሉት አንደኛው የኩርፊያ መሰረት እንደነበረ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ የአንደኛው የሃሳብ የበላይነት ብዙ እርቀት ሳይሔድ በቀጭን ትዕዛዝ ጦርነቱን ያስቆሙት አቶ መለስ መንግስታቸው ልማታዊ መሆን ሲገባው ጦረኝነትን እንደመረጠ እና እንደበሰበሰ በመግለፅ የታይላንድ፤ ታይዋን እና ደቡብ ኮርያን መንግስታት ሥርእት በመተንተን ከአንጃው ካምፕ ብዙዎችን ማረኩ፡፡ ከዚያም ያልተደራጁ እና ስልት አልባ የነበሩ ተቃዋሚዎቻቸውን በታትነው ጥቂቶችን ዘብጥያ በመጣል አሸናፊ ሆነው ብቅ ያሉበት ነበር፡፡
‹ልማታዊ መንግስት›
አቶ መለስ ልማታዊ መንግስት ሲሉ መከራከሪያቸው ‹‹በውቅቱ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ድፍረው በገዛ ምድራችን ምሽግ ቆፍረው ሊወጉን እየተዘጋጁ እንደነበረ ብናውቀውም ወደ ጦርነት ያልሄድነው ልማት ይቀድማል ከሚል ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው፡፡›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ግን ጥሩ የማደናገሪያ ስልት እንኳ መምረጥ እንዳልቻሉ የሚያሳይ እንጂ የሃሳብ የበላይነት እንደነበራቸው የሚያመላክት አልነበረም፡፡ አንደኛ በወቅቱ ምንም አይነት የልማት አጀንዳ ያልነበራቸው መሆኑ፤ በሌላ በኩል የሀገር ሉዓላዊ ድንበር ተደፍሮ፤ የሌላበ ሀገር ሰራዊት ምሽግ እየቆፈረበት ልማት ስላሳሰበኝ ሀገር አልጠብቅም ማለት ጀነራል ሳሞራን እና እነአባዱላ ገመዳን ካልሆነ በቀር የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያሳምን ሃሳብ አይደለም፡፡
የምንረዳው ቁምነገር ቢኖር እንደ ሀገር ለኢትዮጵያ ከነበራቸው የተንሸዋረረ አመለካከት እና ከያዙት የተሳሳተ አቋም በመነሳት በጫካ ውላቸው መሰረት ኤርትራ ራሷን የቻለች እና የበለጸገች ሀገር እንድትሆን እንደ አቶ ኢሳይያስ ምኞት ‹‹በ10 ዓመታት ውስጥ ኤርትራ አፍሪካዊዋ ሲንጋፖር ትሆናለች፡፡›› ከሚለው ቅዠት ጋር እየቃዡ የነበረ መሆኑን ነው፡፡
ለኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት፤ ለታሪክ እና ለብሔራዊ አንድነት ግድ የማይሰጣቸው አቶ መለስ ጦርነቱ ተጀምሮ በኤርትራ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የተከላከሉበት ‹‹የልማታዊ መንግስት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዳይ›› የሙት መንፈሳቸው እንደገና በያዝነው የ2006 ዓም የመጀመሪያ መንፈቅ አጀንዳ አድርጎታል፡፡ ይህ ወቅት በሙት መንፈሳቸው የሚመራው የኃይለማርያም መንግስት ታሪካዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ግዛቶችን ሰቲት ሑመራን፤ ምዕራብ አርማጭሆን እና ቋራን ለሱዳን አሳልፈው በመስጠት ድነበር ለማካለል እያሴሩ ያሉበት ወቅት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የልማታዊ መንግስት አጀንዳ የባድሜን መሬት ለመስጠት በተሰላ ጊዜ ከገነነ በኋላ የፊት ሌቱን ገፅ ለቆ ቢቆይም የጎንደርን መሬት ለመስጠት ሲታሰብ እንደገና አብይ አጀንዳ ሆኖ ብቅ በሏል፡፡ ጥር 17 ቀን በኢንተር ኮንትኔንታል የተካሄደው ሲምፖዚየምም፤ የዚሁ የልማታዊ መንግስት አጀንዳ ማደናገርያ ክፍል አንድ ሊባል ይችላል፡፡
አሥራ አንድ ሰዓት የፈጀው ውይይት
ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ገደማ የጀመረው ውይይት የተጠናቀቅ ከምስቱ 1፡35 ደቂቃ ነበር፡፡ ከፍተኛ ምስጋን የሚገባቸው የድረህረ ምረቃ ተመራቂ ተማሪዎች ካዘጋጁት መድረክ በስተጀርባ የተደገሰውን የፖለቲካ ዓላም ግን በግልፅ የተገነዘቡት አይመስልም፡፡ በፍጸም ገለልተኝነት የሃሳብ ክርክር እንዲደረግ የተቻላቸው ሁሉ ሲያደርጉ ተገንዝቤያለሁ፡፡
በውይይቱ ማጠናቀቂያም የጋበዟቸው የገዥው ፓርቲ ሰዎች አጀንዳውን ወደ ፖለቲካ ጎትተው ለፖሊሲ ስርጸት ለመጠቀም መሞከራቸው ተገቢ እንዳልነበረ በድፍረት አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡ ከገዥው ፓርቲ፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ከዩኒቨርስቲ መምህራን ከመገናኛ ብዜሃን አካላት እና ሌሎች ምሁራን መካከል ጥሪ ተደርጎላቸው እንደተገኙ በተገለጸው በዚህ መድረክ ከገዥው ፓርቲ አቶ ሽመልስ ከማል፤ አቶ ዛድቅ አብርሃ፤ አቦይ ስብሃትን እና በስም የማላውቃቸውን አስተውያለሁ፡፡ ከምሁራን መካከል ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፤ ዶክተር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ፤ ዶክትር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ሲሆኑ በስም የማላውቃቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታሉ፡፡
በእኔ ግምት በጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ድህረ ምረቃ ተማሪዎች ሲምፖዚየሙን አዘጋጀን ካሉበት አላማ አንጻር በዶክተር አብዲሳ ዘርዓይ {Media in Democratic Developmental State the Ethiopian Quandary } በአቶ ታምራት ኃ/ጊዮርጊስ The concept of democratic developmental state vis-a- vis The Ethiopian constitution እና በአቶ ሙሼ ሰሙ freedom of the press in the environment of a democratic developmental state የሚሉት ሞያዊ ዝንባሌ የታየባቸው academic discourse ከሚባሉት የሚመደቡ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡
በአንጻሩ በአቶ ወልዱ ይምሰል እና በአቶ ዛድቅ አብርሃ የቀረቡት ደግሞ ከተማሪዎቹ ሃሳብ በስተጀርባ የሙት መንፈስን ሃሳብ ለመጫን ያለሙ political discourse ነበሩ፡፡ በዚህ ሲምፖዚየም በልማታዊ መንግስት ፅንሰ ሃሳብ እና በሚድያ ነጻነት ዙሪያ ሰፊ ክርክ ተደርጓል፡፡ በአቶ ታምራት ኃይለጊዮርጊስ የቀረበው ጥናት በኢትዮጵያ የሚዲያ ነጻነት አለመኖሩ እና ይልቁንም በህገ መንግስት የተሰጡ የሚዲያ ነጻነቶችን ገዥው መንግስት በሌሎች ህጎች እንዳፈናቸው ዝርዝር ማብራሪያ ቀርቦበታል፡፡ እንደ አቶ ታምራት ገለጻ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት የቡድን መብት ሲል ካስቀመጣቸው ጥቂት ተቀባይነት የሌላቸው አንቀጾች በቀር ጥሩ እና ሊበራል አስተሳሰብን ከፍ የሚያደርግ ነው ሲል መከራከሪያ አቅርበውታል፡፡ ይህ ሃሳብ ከገዥው ፓርቲ ተወካይ ከአቶ ዛድቅ ቁጣ የተቀላቀለበት ምላሽ የተሰጠበት ሲሆን አቶ ዛድቅ ሊበራል ሳይሆን ህገ መንግስታችን ካፒታሊስት ሥርዓት የሚገነባ ነው በማለት ካፒታሊዝም ለሊበራሊዝም ተቃርና እንደ ሆነ አድርገው ሲከራከሩ ተገርመን አስተውለናል፡፡ (እንደ አቶ ዛድቅ ገለጻ ከሆነ አዲሱን ልማታዊ መንግስት ለማነበር ካፒታሊስቱን ህገ መንግስት መሻር ግድ ሊለን ነው፡፡)
በዶክተር አብዲሳ ዘርዓይ ከተሰነዘሩ ሃሳቦች መካከል በ1980ዎቹ አካባቢ የታየው የሚድያ ነጻነት ክፉኛ እንደተመታ እና በአሁኑ ወቅት ያለው የሚድያ ነጻነት ደረጃ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ በጥናታቸው አስምረዋል፡፡ በዶክተሩ ጥናት ላይ መከራከሪያ የሚመስል ሃሳብ በማቅረብ አጸፋ ያሉትን ያቀረቡት የፋነው ስራስኪያጅ አቶ ወልዱ በበኩላቸው በ1980ዎቹ የነበረው የሚድያ ነጻነት መረን የለቀቀ እና በጦርነት የተሸነፈው የደርግ ኃይል በሚድያ ጦርነት የጀመረበት ወቅት ነበር ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
በዚህ ወቅት ከፍተኛ ክርክር የተጀመረው በዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ እና በኢህአዴግ ተወካዮች መካከል ነበር፡፡ የተበተነው የደርግ ሰራዊት በእጁላይ በነበረው መሳሪያ በሀገር እና በህዝብ ላይ ጉዳት ሳያደርስ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሰራዊት ጨዋነት ማስመስከሩ ሊያስመሰግነው እንደሚገባ፤ እዚህ ኢህአዴግ እንደሚከሰው ወደ ሚዲያ ጦርነት ሂደው ከነበረም መሳሪያ ጥለው በብዕር ክርክር ፍልሚያ መካፈላቸው ጠላት ሊያሰኛቸው አይገባም ነበር፡፡ ነገሩ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ‹‹ኢህአዴግ አንድን ጋዜጠኛ ከአንድ ባታሊዎን ጦር በላይ የፈራል›› እንዳለው ሆነ እንጂ ፡፡ በአንጻሩ የተበተነው ሰራዊት ወይም የኢሰፓ አመራሮች ሳይሆኑ በሚድያ ሃሳብ ይሰነዝሩ የነበሩት ምሁራን እና የ1960ዎቹ የሃሳብ እኩዮቻቸው እንደነበሩ መከራከሪያ ቀርቧል፡፡
በተለይም ከዚህ ክርክር የተረዳነው ቢኖር ገና በጠዋቱ ኢህአዴግ በሚዲያ ላይ የያዘው የተዛባ አመለካከት ከፍተኛ መሆኑን እና የተለየ አስተሳሰብን በሚድያ ማንጸባረቅ እንደ ወንጀል የሚቆጠጥር ነው፡፡ (በተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እንደተከሰሰ ልብ ይሏል፡፡) በሲምፖዚየሙ ከፕሬስ ነጻነት አንጻር ክፉኛ የተተቸው የፕሬስ አዋጅ፤ የጸረሽብር አዋጅ፤ እንደተጠበቀ ሆኖ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ሲሻሻል የፕሬስን ጉዳይ በሚመለከት የተካተተው ህግ በሲምፖዚየሙ ትኩረት የሳበ ሆኖ ውሏል፡፡
በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ላይ የሰፈረው ፕሬስን የሚመለከት አንቀጽ ሆን ተብሎ ሚድያውን ለማፈን እና ጋዜጠኞችን ለማሳደድ የተካተተ በግልጽ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን የሚድያ ነጻነት የሚጥስ እና የሚደፈጥጥ ነው፡፡ በሚል መከራከሪያ ቀረበ፡፡ በዚህ ጊዜ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአይኔ ላይ ውል አለ፡፡ በዚህ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ተወንጅሎ ፍርድ ቤት እየተመላለሰ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ጥያቄና አስተያየቱም ቁጡነት እና እልህኝነት ይታየበት የነበረውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
ይህንን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አስመልክቶ የፎርችኑ አቶ ታምራት ህጉ በግልፅ ህገ መንግስቱን የጣሰ እና ተገቢ ያልሆነ ህግ እንደሆነ አስረግጦ ተከራክሯል፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ግን ለዚህ ምላሽ የሰጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር ድኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ‹‹በእርግጥም የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ላይ ፕሬስን በተመለከተ የተቀመጠው አንቀጽ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን እና ተገቢ ያልሆነ መሆኑን እንደ መንግስትም ተገንዝበናል፡፡ እንደ እኔ ግምት ይህንን ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ያሻሻሉ ሰዎች በጭንቅላታቸው ቆመው የሰሩት ይመስለኛል፡፡›› ሲሉ በግርምት አድምጠናል፡፡
በዚህ ጊዜ አቶ ታምራት ኃ/ጊዮርጊስ እንዲህ በማለት ሃሳባቸውን አቅርበው ነበር፡፡ ‹‹ ክቡር ሚነንስትር ድኤታ በእርግጥ ስህተት ነው ባለው በግልዎም እንደ መንግስትም ማመንዎን አደንቃለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ ስህተት በህግ አሻሻዮቹ አለማስተዋል እንደተሰራ ማስመሰል ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ አንቀጽ ሆን ተብሎ ሚድያውን ለማፈን ዜጎች በህገ መንግስት ያገኙትን መብት ለመንፈግ የወጣ ነው፡፡ በእኔ ግምት ያሻሻሉት በጭንቅላታቸው ስለቆሙ አይመስለኝም፡፡ ዳኞች ይህንን አንቀጽ እየጠቀሱ ዜጎች ታስረዋል፤ ብዙዎች እንዲሰደዱ እንዲንገላቱ ምክንያት ሆኗል……››
በእርግጥ ወንጀለኛ መቅጫ ህጉን ያሻሻሉት በጭንቅላታቸው ስለቆሙ ነው ወይስ የፕሬስ ህግ፤ የጸረሽብር ህግ፤ የሲቪል ማህበራት ህግ ወዘተ…ጭምር ሲረቀቁ አቶ መለስ በአርቃቂዎች ጭንቅላት ላይ ስለቆሙ ? በቀሪዎቹ እና በአወንታዊ ነጥቦች ላይ እመለስበታለሁ፡፡
Source/www.ethiomidia.com

No comments:

Post a Comment