Sunday, February 9, 2014

ለግንቦት 7ም ሆነ ለሌሎች ተቃዋሚዎች ያለመተቸትን ከለላ ማን ሰጠ? የእነ “… ወይም ሞት” ፖለቲካ

Posted: February 8, 2014 in Articles by Admin
0
ከያሬድ ኃይለማሪያም
ከብራስልስ፣ የካቲት 1፣ 2006
ከ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ የአገራችንን ፖለቲካ የተጠናወተው የ“…. ወይም ሞት” አስተሳሰብ ከአስርት አመታት በኋላም አለቅ ብሎን ዛሬም እኔ ከምደግፈው ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ቡድን ወይም አስተሳሰብ ውጭ ያለው መንገድ ወይም አማራጭ ሁሉ ገደልና ሞት ነው ብለው የሚያስቡ ፖለቲከኞችና ዓጃቢዎችን ቁጥር በብዙ እጥፍ አባዝቶ ቀጥሏል። በ‘ደርግ ወይም ሞት’ የጀመረው የኼው የተወላገደ እና ጸረ-ዲሞክራቲክ የሆነው አስተሳሰብ ሳንወጣ ዛሬም ‘ወያኔ ወይም ሞት’፣ ‘ግንቦት 7 ወይም ሞት’፣ ‘ኦነግ ወይም ሞት’፣ ‘… ወይም ሞት’ በሚሉ ካድሬዎችና ስሜታዊ የድርጅት አምላኪዎች ተተክቶ እያደናበረን ይገኛል። ለአንድ የፖለቲካ ማኀበረሰብ በዲሞክራሲያዊ ጎዳና ለማቅናትም ሆነ እራሱን ከፍ ወዳለ የሥልጣኔ ባህል ለማደግ ትልቁ መሣሪያ ነጻ አስተሳሰብ እና ግልጽ ውይይት ነው። ባጭሩ በነጻነት የማሰብ (freedom of thought)እና ያሰቡትን በነጻነት የመግለጽ (freedom of expression) በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ በአግባቡ ሲተረጎሙ ነው ያ ማኅበረሰብ ወደ ጤናማ የፖለቲካ ባህል የሚሸጋገረው። ይህ ማለት ግን አንድ ሰው ያሻውን የማሰብ ነጻነት ቢኖረውም ሃሳቡን በተለይም አገራዊና ሕዝባዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ አውጥቶ ከሌሎች ጋር ሲወያይ ሊያከብራቸው የሚገቡ የሥነ-ምግባር እና የሕግ ገደቦች አይኖሩም ማለት አይደለም። ለጋራ ጥቅም ተብለው ከተቀመጡት የሕግና የሞራል ወሰኖች መለስ ግን ፍጹም ስልጡን በሆነ መልኩ ሃሳብን ማፍለቅ እና መወያየት የጭዋነት መለኪያ ብቻ ሳይሆን ሊሚናገሩትም ነገር ኃላፊነት የመውሰድን ግዴታንም አብሮ የያዘ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ስለሆነ ሰዎች ባደባባይ ወጥተው ያሰቡትን ከመናገራቸው በፊት በቅጡ እንዲያስቡ ያደርጋል። ያለመታደል ሆኖ ከሃገር መሪዎች አንስቶ የፖለቲካ ተሿሚዎች፣ ካድሬዎችና ደጋፊዎች ለዚህ አይነቱ ኃላፊተት ብዙም ሳይጨነቁ ባደባባይ ያሻቸውን ይናገራሉ፣ የዘላብዳሉ፣ ይሳደባሉ፤ የሚጠይቃቸውም የለም።
ብዙ ጊዜ በእንዲህ ያለው ማኅበረስብ ውስጥ ኅብረተሰቡን በማንቃት፤ እንዲሁም ፖለቲከኞችን በማረቅና ለሚናገሩትም ሆነ ለሚሰሩት ነገር ተጠያቂ በማድረግ የፖለቲካው ባቡር ሃዲዱን ስቶ ሕዝቡንም ይዞ ቁልቁል መቀመቅ እንዳይወርድ ትልቁን ድርሻ የሚጫወቱት ነጻ የመገናኛ ብዙሃን እና ገለልተኛና ደፋር የአደባባይ ምሁራን ናቸው። ነጻ ሚዲያ በሌለበት ወይም በተዳከመበት እና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን ነጻ ባልሆኑበትና በማይከበሩበት አገር ሁሉ ጨለምተኝነት፣ አክራሪነት፣ ጽንፈኝነት፣ ጎጠኝነት እና አንባገነናዊነት ይነግሳሉ። በእንዲህ አይነቱ ማኅበረሰብ ውስጥ በጠመኝጃ አፈሙዝ ሥልጣን የተቆናጠጠ የወያኔ አይነት አምባገን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ትናንሽ አምባገነን ድርጅቶችና ግለሰቦችም እንደ አሸን ይፈላሉ። ምክንያቱም የሚፈሩት ሕዝብ የለማ። ትንሹ አምባገነን ትልቁን፤ ትልቁም ትንሹን ይፈራል እንጂ ሕዝብን አይፈሩም። የሰሉና የተደራጁ ነጻ የመገናኛ መድረኮችና ብቃት ያላቸውና ለሕሊናቸው ያደሩ ጋዜጠኞች ባሉበት አገር አንድ ግለሰብ በሕዝብና በአገር አናት ላይ ቆሞ ያሻውን መናገርና መዘባረቅ ይቅርና ገና የፖለቲካ ጎራውን ሲቀላቀል ከልጅነት እስከ አዋቂነት የሄደበትን ጉዞና የሕይወት ታሪኩን በማጥናት ያ ሰው በሕዝብና በአገር ጉዳይ እጁን የማስገባት ሞራላዊም ሆነ ፖለቲካዊ ብቃት ያለው መሆኑን ሕዝቡ እንዲመዝን ያደርጋሉ። ይህ የፖለቲከኞቻችንን ሥነ-ልቦናዊም መሰረትም ሆነ ምሁራዊ ብቃት እንድናውቅ ከማገዙም ባሻገር የተጠያቂነትንም ባህል ያጎለብታል። በአንድ ወቅት በሕዝብና በአገር ጥቅም ላይ ጉዳት ያደረሰ፣ ወይም በመጥፎ ሥነ-ምግባር ውስጥ ያለፈ፣ ወይም ከቤተሰቡ አንስቶ በሚኖርበት አካባቢ በመልካም ተግባሩ የማይታወቅ ሰው በምንም መንገድ አገራዊ ኃላፊነት እንዳይጣልበት ያደርገዋል። እስኪ ዛሬ አገሪቷን ተቆጣጥረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ደም እንባ እያስለቀሱ ካሉት የወያኔ ባለሥልጣናት እና በተቃዋሚ ጎራ ተሰልፈው ካሉት የፖለቲካ ተዋናዮች መካከል ስንቶችን በቅጡ እናውቃቸዋለን? በሁሉም ጎራ ስለተሰለፉት ፖለቲከኞቻችን ያለን መረጃ ምን ያህል ነው? እንዴነ እጅግ ውሱን ነው፤ ስም፣ የትምህርት ድረጃ፣ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የአንዳንዱን እድሜና ጥቂት ነገሮች። የእያንዳንዳቸውን ጀርባ እናጥና ከተባለ ጉዱ ብዙ ነው። በቅርቡ እንኳን ከሟቹ መለስ ዜናዊ እኩል ወይም በተወሰነ ደረጃ ባላፉት ሃያ መታት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የወያኔ አገዛዝ ሥርዓት ለፈጸማቸው አስከፊ የሰብአዊ መብቶች እረገጣዎች በሕግ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው እንደ እነ አቶ ስዮ አብረሃ (የጦር ሚኒስትር እና የሥርዓቱ ቁልፍ ሰው የነበሩ) አይነት ሰዎች ከወያኔ ጋር ስለጠጣሉ ብቻ በሕግ ይቅርና በፖለቲካ መድረክ እንኳን ያለመጠየቅ ከለላ ተሰጥቷቸውና ወቃሽ ሳያገኙ የዲሞክራሲ ኃይሉ አካል ተደርገው ትግሉን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።
ባጭሩ ያጎለበትነው የፖለቲካ ባህል ቁጥራቸው ቀላል ለማይባሉ እጃቸው በንጹሃን ደም ለጨቀየ፣ በርሃብና በድህነት በሚሰቃየው ሕዝባችን ውድቀት ሞስነው ለጠበደሉ፣ በግል ህይወታቸውም ሆነ በሙያቸው ላልተሳካላቸው አዳዲስ እና ነባር ፖለቲከኞች መደበቂያ ጫካ ሆኗል። በቅርቡ “የፍርሃት ባህልን እያነገሰ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ” (http://humanrightsinethiopia.wordpress.com/) በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሑፍ ላይ እንደገለጽኩትም የገዢዎቹንም ሆነ የነጻ አውጪዎቹን፤ በጥቅሉ የፖለቲካ መዘውሩ ዙሪያ ያሉ ግለሰቦችን ማንነትና ጀርባ በቅጥ ማወቅ አለመቻል አንዱ ኅብረተሰብን ለፍርሃትና ከፖለቲካ ተሳትፎ እንዲቆጠቡ የሚዳርግ ምክንያት ነው። እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ከግምት በማስገባት ከዋናው ርዕስ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ።
በዚህ ርዕስ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፤ የወያኔ ሳያንስ የነፃ አውጪዎቻችን (የግንቦት 7) የግፍ ተግባር እና የመገናኛ ብዙሃን ዝምታ” በሚል ርዕስ ከአንባቢዎች የተሰነዘሩ አስተያየቶች ናቸው። ሦስት አይነት ነቀፌታ አዘል አስተያየቶች ጽሑፌን አትመው ባወጡ ድኅረ-ገጾችና በማኅበረሰብ የመወያያ መድረኮች ላይ ተነበዋል። ለእያንዳንዱ አስተያየት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ለኔም አመቺ ሆኖ ስላገኘሁት በሦስቱ ጎራ ላሉት አስተያየቶች ምላሽ ልስጥ። የመጀመሪያው አስተያየት ባነሳሁት ፍሬ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሳይሆን ብስጭትና ንዴት በተቀላቀለበት ስሜት ዝልፊያና ‘ዋናው የአገር ጠላት ወያኔ እያለ እንዴት ግንቦት 7ን ትተቻለ’፣ ግንቦት 7ን የነቀፈ ሁሉ ‘ወያኔ’ ነው፣ ተቃዋሚዎችን መተቸት ‘ትግሉን’ ያዳክማል፣ ተቃዋሚዎች ከነሃጢያታቸው መደገፍ ብቻ ነው ያለባቸው፣ ገፋ ብሎም ወንጀልም ቢሰሩ እንኳን ሊጠየቁ አይገባም ወያኔን እስከታገሉልን ድረስ የሚሉ ሃሳቦች የታጨቁበት ነው። እውነት ለመናገር ከእንደነዚህ አይነት ግራ ከተጋቡ ሰዎች ጋር ለመወያየት ያስቸግራል። ስለፖለቲካም ያላቸው ግንዛቤ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ከዚህ በፊት በሌሎች ጽሑፎቼም እንዳልኩት እነኚህ ሰዎች ገሚሱ በቅን ልቦና ለውጥን ብቻ ከመናፈቅ፣ ገሚሱም አዕምሯቸው በቂምና በበቀል ስሜት ተወጥሮ ፖለቲካውን መሳሪያ ያደረጉ፣ ገሚሶቹም ስለ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል ያላቸው ግንዛቤ ውሱን ወይም የተዛባ በመሆኑ መፈክራቸው ሁሉ ‘ግንቦት 7 ወይም ሞት’፣ ‘ኢሳት ወይም ሞት’፣ ወዘተ የሚል ነው። እነዚህ ሰዎች አዕምሮዋቸውን ከፈት አድርገው በፃነት እንዲያስቡ እና ከካድሬነትና ጭፍን ድጋፍ ወደ ሰላና በእውቀት ላይ ወደተመሰረተ የፖለቲካ ደጋፊነት እራሳቸውን እንዲያሳድጉ እመክራለሁ።
ሁለተኛው አስተያየት ሰጪዎች “ከግንቦት 7 ወይም ሞት’ የወጡ ቢሆንም አሁንም በተነሳው ፍሬ ነገር ላይ ያተኮሩ ሳይሆኑ በጸሃፊው (በእኔ) ማንነትና በአስረጂነት በጽሁፌ ላይ ባጣቀስኩት ድኅረ-ገጽ ባለቤቶች ማንነት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ይህም አስተያየት ቢሆን ያው ‘ፍሬውን ትቶ ገለባውን’ የመውቀጥና ከአስተሳሰብ መዛነፍ የመነጨ ነው። ገሚሶቹ ድብቅ ተልዕኮ ከሌለህ ግንቦት 7ን በአደባባይ መተቸት አልነበረብህም፣ ችግሩ ተከስቶም ቢሆን ባደባባይ ሳይሆን ውስጥ ለውስጥ ነው ጉዳዩን መግለጽ ያለብህ የሚል ነው (ወያኔ እንዳይሰማ መሆኑ ነው)። ሌሎቹ ደግሞ ‘የወያኔ’ መልዕክተኛ ነህ በሚል ፈርጀውኛል። እኔን ብቻ ሳይሆን የመረጃው ምንጭ ተደርገው የተጠቀሱትንም አካላት ወያኔዎች ናቸው ብለው ደምድመዋል። ለነገሩ እንዲህ ያለው ፍረጃ በተሰነካከለው የፖለቲካ ባህላችን ውስጥ ትችቶችን ለማፈን፤ ለማስቆምና የሰላ ትችት የሚሰነዝሩ ሰዎችን ዝም ለማስባል እንደ ስልት ገዢው ወያኔም ሆነ አንዳንድ ተቃዋሚዎች የሚጠቀሙበት ስልት ስለሆነ አያስገርምም። በፖለቲካችንም ውስጥ ይህ አካሄድ የቆየ እድሜ አለው። ይሁንና እኔንም ዝም አያሰኘኝም፤ እውነታውንም የመሸፈንም ሆን የመቀየር አቅም የለውም። እውነት ደግሞ ጊዜን እየጠበቀች የምትፈካና ከተገለጠችበት የምትወጣበት አንዳች ተፈጥሯዊ ኃይል ያላት ስለሆነች እንዲህ ያሉ ፍረጃም ሆነ ማደናገሪያ ጭርሱኑ አያጠፏትም። ይልቅ እንደ ሰለጠነ ማኅበረሰብ ችግሩን መመርመረሃ ምፍትሄ መሻት ይበጃል፤ ለአገርም ለድርጅቶቹም ቢሆን።
ሦስተኛው አስተያየት ኃላፊነት ከሚሰማቸውና የጉዳዩን ክብደት በቅጡ ከተረዱ ወገኖች የተሰነዘረ ነው። ይህውም ጉዳዩ የሰብአዊ መብትን የሚለለከት ስለሆነ በተበዳዮቹ ላይ ደረሱ ለተባሉት ጥቃቶች በቂ ማስረጃ አለህ ወይ? የሚል ነው። በመጀመሪያ እንኳን ለፍትሕ፣ ለዲሞክራሲና ለነጻነት እንታገላለን ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎች ይቅርና አለም በሰብአዊ መብቶች እረጋጭነት ያወቀወን አንባገነናዊ የወያኔ ሥርዓት ለመተቸትም ሆነ ለመንቀፍ የሁል ጊዜ መነሻዬ ማስረጃዎች ናቸው። እንደ አንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች መረጃና ማስረጃዎች ያላቸውን ልዩነትም ሆነ ጠቀሜታ ጠንቅቄ ስለማውቅ ያለመረጃም ሆን ያለ ማስረጃ ማንንም ባደባባይ ለመውቀስም ሆነ ለመተቸት አልደፍርም። በተነሳው ጉዳይ ላይም በቂ ብቻ ሳይሆን ከበቂ በላይም ማስረጃዎችን መዘርዘር ይቻላል።
ጽሑፌን ለመደምደም በመጀመሪያ ወደ እዚህ ውይይት ያመራንን ጽሑፍ በማተም የጋዜጠኝነትና የመረጃ መድረክነታችውን ባግባቡ ለተወጣችሁ ድኅረ-ገጾችና የመወያያ መድረኮች ምስጋናዬ የላቀ ነው። የኔን ጽሑፍ በማስተናገዳችሁ የተነሳ ‘ወያኔ’ ተብላቸሁ የተሰደባችሁም ለእውነት መቆም የሚያስከፍለውን ዋጋ ነው እና እየከፈላችው ያላችሁት ግፉበት። ጽሑፌን አሉ ለተባሉት ድኅረ-ገጾች ሁሉ ነው የላኩት፤ መልእክቱም የደረሳቸው መሆኑን ከራሳቸው በተላከ ኢሜል አረጋግጫለሁ ይሁንና በሥራ ብዛት ይሁን በሌላ ያላስተናገዳችሁንት ወደፊት እንደምታትሙት እየጠበኩኝ የፍረጃ ፖለቲካውን ፈርታችሁ ወይም እናንተም የ’… ወይም ሞት’ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ገብታችሁ አቋም ለያዛችሁትም ሁሉ እግዚያብሄር ለእውነት የምትቆሙበትን ልቦና እና መንፈሳዊ ወኔ ይስጣቸሁ በሚል ልሰናበት።
እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል።
በቸር እንሰንብት።

No comments:

Post a Comment