Sunday, February 16, 2014

ቤተመንግሥቱን የከበበው መስቀል የሃይማኖት መሪዎቹን አነጋገረ


.“በአክሱም አንዲት ጎጆ መስጊድ እንኳ ለመገንባት እንዴት አልቻልንም?”
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮና መኖርያ ቤት በሚገኝበት ታላቁ ቤተ መንግሥት አጥር ዙሪያ ገባው ላይ የሚገኘው የመስቀል ቅርጽ፣ የእስልምናና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ሃይማኖቶች መሪዎችን አነጋገረ፡፡
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ በሐዋሳ ባካሔደው የምክክር መድረክ ላይ ‹‹አገሪቱና መንግሥቱ የእኩልነትና የዜጎች መንግሥት ነው፤›› ያሉት የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ኪያር ሙሐመድ አማን÷ ከቀድሞው ሥርዐት አንጻር አሁን የሚያበረታቱ ነገሮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
ይኹንና በሴኩላሪዝምም ቢኾን ፍጹምነት ባለመኖሩ ‹‹አገር የጋራ ነው ከተባለ በኋላ የጎደለ ነገር አለ፤›› በሚል አዘውትረው ጥያቄ የሚያቀርቡላቸው ሰዎች መኖራቸውን ሸኽ ኪያር ጠቅሰዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ይቀርቡልኛል ካሏቸው ጥያቄዎች መካከል ‹‹ለምሳሌ፡- ታላቁ ቤተ መንግሥት በመስቀል ነው የተከበበው፤ ይህ መጥፎ ነገር ሊያመለክት ይችላል›› የሚሏቸው እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
ታላቁን ቤተ መንግሥት የከበበውን መስቀል፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ፊት ለፊት እንደቆመው የደርግ ሐውልት ያህል እንዲታይ በሚል ለጥያቄው መልስ እንደሚሰጡ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፣ “በአክሱም አንዲት ጎጆ መስጊድ እንኳ ለመገንባት እንዴት አልቻልንም?” ተብለው ሲጠየቁ የዚህን ያህል ‹‹የቀልድ መልስ እንኳ ለመስጠት አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገሮችን ለማከም መቅደድ አለብን›› የሚል የዐረብኛ ብሂል እንዳለ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ሁልጊዜ ጥላሸት መስለው ይታያሉ ያሏቸውን ችግሮች ለመፍታትና መልስ ለመስጠት ይቻላል ወይስ አይቻልም ሲሉ በፈገግታ የታጀበ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
በጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸኽ ኪያር ጥያቄ ላይ ፈጥነው አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ሸኽ ኤልያስ ያቀረቧቸው ነገሮች ሌሎች ስለጠየቋቸው እንጂ ራሳቸው ፕሬዝዳንቱ አምነውበት እንዳልሆነ ከአነጋገራቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጥያቄው ስለ መስቀልም ስለ አክሱምም መነሣቱን ያስታወሱት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ሁለቱም የቆዩ ናቸው እንጂ አሁን የተፈጠሩ አይደሉም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፤ ‹‹በዚህ ግቢ (ስብሰባው በተካሔደበት ሌዊ ሪዞርት ማለታቸው ነው) ያየናቸው ዋርካዎች ድሮ የነበሩ ናቸው፤ አሁንም ይጠቅማሉ፤ ከቆረጥናቸው ጉዳት ነው፤ ከኖሩ ይጠቅሙናል፤›› በማለት የቆየው ታሪክ መጠበቅ እንዳለበት በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የመስቀሉ ቅርጽ የቆየ ታሪክ ነው፤ በታሪካዊነቱ ተከብሮ ተጠብቆ መኖር አለበት፤ በአክሱም ስላለው ነገር ከተነሣም የእኛም ጥያቄ ወደ ረጅምና ዝርዝር ነገር ይሔዳል፤›› በማለት የሁሉም ታሪክ በየራሱ መታወቅና መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
መከባበርም መቻቻልም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት ፓትርያርኩ፣ “አገሩ የኹላችንም ነው፤ የነበረው ታሪክ ደግሞ በታሪካዊነቱ ተከብሮ መኖር አለበት” በሚል ለሸኸ ኪያር ጠያቂዎቹ ምላሽ መስጠት እንደሚቻል በፈገግታ የታጀበ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የውይይቱ ተሳታፊ ከኾኑ ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችም ሆነ የምክክር መድረኩን ከመሩት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች የተሰጠ ምላሽና አስተያየት አልነበረም፡፡
የመስቀልና ዘውድ አምሳል በተቀረጹባቸው አጥሮች የተከበበው ታላቁ ቤተ መንግሥት፣ የምኒልክ ቤተ መንግሥት በመባል የሚታወቅ ሲሆን ንጉሡ በ1878 ዓ.ም ያሠሩት መንበረ መንግሥታቸው ነበር፡፡ የተለያዩ መኖርያ ቤቶችን፣ እልፍኞችንና አዳራሾችን እንዲሁም ቤተ ጸሎቶችን ያካተተው ቤተ መንግሥቱ÷ የታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም፣ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እና የሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ይዋሰኑታል፡፡
በተለይ የዘውድ አምሳል በጉልላቱ ላይ የሚታይባት የበኣታ ለማርያም ገዳም የንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፣ የንግሥታቱ እቴጌ ጣዪቱና ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንዲሁም የልዕልት ፀሐይ ኃይለ ሥላሴ ዐፅሞች ያረፉበት ሲኾን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮና መኖርያ የኾነው ከደርግ መንግሥት ጀምሮ ነው፡፡
ለሁለቱ የሃይማኖት መሪዎች መነጋገርያ የኾነው ጉዳይ መነሻ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ የግጭትና ሰላም ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር በኾኑት ዶክተር ታረቀኝ አዴቦ የቀረበው ‹‹በአገራችን የሃይማኖት ተቋማትና ተከታዮች በሰላም አብሮ የመኖር ወርቃማ ተሞክሮና የማስቀጠል ፋይዳው›› የተሰኘ ፅሁፍ ነው፡፡
የአገራችን ሕዝቦች ‹‹እንኳን በብርሃን ዘመን በጨለማው ዘመንም ጭምር›› የሃይማኖት ብዝሐነትን በመሠረቱ ያለመግባባትና የግጭት መነሻ ሳያደርጉ በሰላም አብረው እንደኖሩ የሚያትተው የጥናት ጽሑፉ፣ በሰላም አብሮ መኖር÷ ብዝሐነትን እንደ ነባራዊ ኹኔታ የመቀበል፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል ስልት የመከተል፣ የብዝሐነቶች ነጻነትና እኩልነት መረጋገጥ አስተሳሰቦች ጥምረት መኾኑን ይገልጻል፡፡
የሃይማኖት መሪዎች በሰላም አብሮ የመኖር አርኣያ በመኾን ከቅድመ አያቶቻችን ጀምሮ ለዘመናት የቆየውን በሰላም አብሮ የመኖር ዕሴት በውስጣቸውም ይኹን በመካከላቸው፣ አስተሳሰቡንና ተግባሩን በማስፈን ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ ታሪካዊ አደራና የዜግነት ግዴታ እንዳለባቸው ያስገነዝባል- ጥናታዊ ፅሁፉ፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት፣ ያለፈውን ታሪካዊ እውነታ ተቀብሎና ዕውቅና ሰጥቶ፣ የወቅቱን ነባራዊ ኹኔታ መሠረት አድርጎ ወደፊት በመቃኘት፣ በአገራችን ብዝሐነትን ተቀብሎ በተገቢው ኹኔታ ለማስተናገድ አቅጣጫ ያስቀመጠ ብቸኛው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ነው የሚሉት ሌሎች የጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎች÷ መንግሥታዊ ሃይማኖትን ከሠየመው የንጉሣዊው ሥርዐት ሕገ መንግሥትና ፀረ - ኹሉ ከነበረው የወታደራዊ ሥርዐት ሕገ መንግሥት፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት የሚለይባቸውን መርሖዎችና ድንጋጌዎች ዘርዝረዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ለተከታዮቻቸው የማስተማር ሓላፊነታቸውን በተጠናከረ መልኩ መወጣት ይኖርባቸዋል ያሉት ጽሑፍ አቅራቢዎቹ፣ የመንግሥትና የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትና ሠራተኞችም ሴኩላሪዝምንና ሃይማኖት ነክ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በጥብቅ በመተግበር፣መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን ያረጋገጠውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ማስከበር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ Addisadmas news paper// golgul

No comments:

Post a Comment