Wednesday, February 12, 2014

የጋዜጠኛው ጥያቄ ጠ/ሚኒስትሩን አስቆጣ


የካቲት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጽ/ቤታቸው ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ታምራት ገብረጊዮርጊስ በቀረበላቸው ጥያቄ በመቆጣት ዘለፋ ሰነዘሩ፡፡

አቶ ታምራት ለጠ/ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥያቄ በአሁን ሰዓት አገሪትዋን የሚመራት ማንነው ነው የሚል ይዘት ያለው ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩም ብስጭታቸውን በምላሻቸው ወቅት አንጸባርቀዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጋዜጠኛውን ሂድና እዚያ ሐሜት የምትጽፍበት ገጽ ላይ ጻፈው በማለት መዝለፋቸው በርካታ ጋዜጠኞችን አስደንግጦአል፡፡

አንዳንድ ጋዜጠኞች ስለሁኔታው በሰጡት አስተያየት ጋዜጠኛ ታምራትን በማድነቅ አንድ ጋዜጠኛ በሕዝብ ውስጥ የሚነገርን ጥያቄ አውጥቶ መጠየቁ ተገቢና ሙያዊ ሃላፊነቱ መሆኑን በመጥቀስ ጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄው የቱንም ያህል ቢያበሳጫቸው በዚህ መልኩ ምላሽ መስጠታቸው ራሳቸውን ከማስገመት ያለፈ ትርፍ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ከአቶ መለስ ሞት በሃላ ወደስልጣን የመጡት አቶ ኃይለማርያም ቀደም ሲል በአቶ መለስ ብቻ ሲመራ የነበረውን የጠ/ሚኒስትር ስልጣን የጋራ አመራር በሚል ፈሊጥ ሶስት ቦታዎች በመክፈልና በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ ለኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ስልጣናቸው ማከፋፈላቸው በሕዝብ ዘንድ ያለስልጣን የተቀመጡ አሻንጉሊት መሪ እስከመባል አድርሶአቸዋል፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው ብዙ ሲባልበት የቆየውን ኢትዮ ሱዳን ድንበር ማካለል ጉዳይ ከውይይት ያለፈ ነገር እንደሌለ በመናገር የሚደርስባቸውን ትችቶች ያጣጣሉ ሲሆን አጀንዳውንም ከመጪው ምርጫ ጋር በማያያዝ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ሙከራ መሆኑን ለመናገር ሞክረዋል፡፡ በኢትዮ ሱዳን ድንበር ማካለል ጉዳይ በስፋት የዘገቡትና ሒደቱንም ያሳወቁት የሱዳን ጋዜጦች መሆናቸውን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡

ከኢህአዴግ ጋር በመደራደር አገር ውስጥ ገብተዋል ስለተባሉትም አቶ ሌንጮ ለታ ተጠይቀው ዋሽንግተን ለሚገኘው ኢትዮጽያ ኤምባሲ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ከመስማታቸው ውጪ ስለመግባታቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመናገር ጉዳዩን አስተባብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment