Saturday, February 8, 2014

እውን ሻዐቢያ እና ህወሀት ተጣልተዋልን?

እውን ሻዐቢያ እና ህወሀት ተጣልተዋልን?

(ሁኔ አቢሲኒያዊ)
Zehabesha  ማማ እና የሾላ ወተት ሁለቱም ወተት ናቸው የሚለያቸው ነገር ቢኖር ማማ ማማ መባሉ ሲሆን ሾላ ደግሞ ሾላ መባሉ ነው እንደዚሁ ህወሀት እና ሻዐቢያም የስም እንጂ የይዘትም ሆነ የአላማ ልዩነት የሌላቸው ጸረ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ፀረ ኢትዮጵዊ መሆናቸው ሀቅ እና ምስጢር ያልሆነ ነው ይልቁንስ በዚህች አነስተኛ ጦማር ማሳየት የፈለኩት ሻዐቢያን አምነው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመቀየር ከኢሳያስ ጋር ስለተወዳጁ ወገኖቻችን ጉዳይ ነው።
isayas afewerki
ምርጫ 2002 በተቃረበበት ወቅት በኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀረበ የተባለው እና በፊታውራሪ ህወሀቶች ጭምር ድጋፍ ተሰጥቶት ነበረ የተባለው የስልጣን እንልቀቅ ጥያቄ ውድቅ የተደረገው እኛ ስልጣን ከለቀቅን ሻዐቢያ በእጅ አዙር ሀገሪቷን ሊመራት ስለሚችል ስልጣን መልቀቃችን ሊታሰብ የማይችል ነው ሲሉ በተላላኪ ጋዜጠኞቻቸው በኩል አስነገሩ ብዙሀኑ ምስኪን የግል ጋዜጦችም ይህንን ጉዳይ አንስተው ከሁሉም ጆሮ እንዲዳረስ አደረጉ፡፡ ይህ ሁኔታ ወያኔ ኢህአዴግን በሁለት መንገድ ተጠቃሚ አደረገው እነርሱም፡-
1. ሻዐቢያ እውነትም ፀረ ኢትዮጵያዊ ነው ኢህአዴግ ከወደቀ ደግሞ ሻዐቢያ ኢትዮጵያን ይቆጣጠራል የሚለው አስተሳሰብ ውስጥ ብዙሀኑ ኢትዮጵያዊ ጥልቅ ብሎ እንዲገባ ያስቻለ ሲሆን
2. በሌላ በኩል ዲያስፖራ ላይ የመሸጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እነ ኦነግ ከኢሳያስ ጋር ተለጥፈው ለምን ውጤታማ ሳይሆኑ ቀሩ እንኳን ብለው ሳያጤኑ ሻዐቢያ የወያነ ጠላት ስለሆነ ለእኛ እና ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ብቸኛው ኢትዮጵያን ነጻ የማውጫ መንገድ አስመራ ላይ መክተም ነው ብለው አውጀው የማይታመነውን ኢሳያስን አምነው አስመራ ከተሙ፡፡
እነዚህ ሁለት ከላይ የጠከስኳቸው ሁለት አብይት ጉዳዮች ወያኔን ተጠቃሚ ያደረጉ እንዲሁም የኢትዮጵያን ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲዳከሙ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ነበሩ፡፡
– እውን ህወሀት እና ሻዐቢያ ተጣልተዋል ወይስ ጥላቸው ለሚዲያ እና ለህዝቡ ጆሮ ብቻ ነው?
- ኤርትራ የከተሙ ፓርቲዎችስ ስለምን ውጤታማ አልሆኑም?
- እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ እስኪ በቅድሚያ ይህንን ሀሳብ በአዕምሯችን እናሰላስለው
- ሻዐቢያ አሰብ የራሱ እንዲሁም የኤርትራ ንብረት እንደሆነ ያምናል
- ህወሀትም አሰብ የኤርትራዊያን ንብረት እና ሀብት ነው ብሎ ያምናል
በተቃራኒው ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሰብ የኢትዮጵያ ነው አልፎም ተርፎ የኤርትራን መገንጠል የማይደግፉ ናቸው ታድያ የኛ ፓርቲዎች እንደምን ብለው ነው ኢሳያስን አምነው አስመራ ላይ የከተሙት እውን ኢሳያስስ አሰብ የኢትዮጵያ ናት ብለው የሚሰብኩት ተቃዋሚዎች ይሻሉታል ወይስ ኤርትራ ነጻ ሀገር ነች አሰብም የኤርትራ ነች የሚለው ወያኔ?
ህወሀት እና ሻዐቢያ በስልጣን ላይ ለመቆየት የማይገድሉት ሰው የማይቆፍሩት መሬት የለም በኤርትራ ሪፈረንደም ወቅት እስካሁን ትርጉሙ ሊገባኝ ባልቻለ መልኩ የመለስ ዜናዊ እናት ኢትዮጵያ ሬድዮ ላይ ቀርባ ኤርትራዊያን ነጻ ሀገር ስለሆኑ እንኳን ደስ ያላቹህ ያሉ ሲሆን ነጻነቱም እንደሚገባቸው ተናግረዋል ነገር ግን ከአመታት በኋላ እነዚሁ የህወሀት ባለስልጣናት እናቶቻቸውን ሁሉ ያስደሰተውን መልካ ግኑኝነት ወደኋላ ብለው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ተፈጠረ ተባለ እና ከ 78000 በላይ ወጣት ኢትዮጵያዊያን እንዲፈጁ ተደረገ ይህም ጠንካራ የነበረውን የኢትዮጵያ ወጣት እሳት ውስጥ የማገደ ብሎም የቀረው ጠንካራ ወጣት እንዲሰደድ ምክንያት የፈጠረ ሴራ ነበር በጦርነቱ መሀል መሪዎቻችን ምን ያደርጉ እንደነበር በቅርቡ ዊኪሊክስ ላይ ካየነው በኋላ ጦርነቱ የድንበር ሳይሆን ወጣት የማስፈጃ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡
በአንድ ወቅት መሳሳት ልማዱ የሆነው ስብሀት ነጋ አዳልጦት በብሄራዊ ቲያትር የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ህዝቦች እጅግ የሚዋደዱ እና ወንድማማች ህዝቦች ናቸው ካለ በኋላ ኤርትራን የሚወር አንድ ሀገር ቢመጣ ቀድመን ጦራችንን ከኤርትራ ወንድሞቻችን ጋር እናሰልፋለን በማለት መናገሩን ለሚያስታውስ ግለሰብ ግን ህወሀት እና ሻአቢያ ተጣልተዋል የሚለው ብሂል እውነታነቱ ለኢቲቪ ተመልካች እንጂ ማሰብ ለሚችል ሰው መራር ቀልድ ነው የሚሆነው፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ በኤርትራ የሚገኙ የት.ብ.ዴ.ን አባላት ነጻ እናወጣዋለን ያሉትን የትግራይ ህዝብ ነጻ ከማውጣት ይልቅ ወታደሮቻቸው አስመራ ውስጥ ኬላ ጠባቂ እንደሆነ በማህበራዊ ድህረ ገጾች አነበብኩ የተጠበኩት ነገር ስለሆነ ባይገርመኝም የወያኔን እድሜ እያራዘመን እንደሆነ ሲገባኝ ግን አዘንኩኝ በነገራችን ላይ የኤርትራ ተቃዋሚዎችንም ሰብስቦ በመያዝ ረድፍ ህወሀትም ለሻዐቢያ ውለታ እየሰራ እንደሆነ ጠጋ ብሎ የሻዐቢያ ተቃዋሚዎችን ያነጋገረ ግለሰብ የሚረዳው ሀቅ ነው፡፡
ስለ ሻአቢያ ደህንነት ከህወሀት በላይ የሚጨነቅ ሊኖር ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ሻዐቢያ ማለት ለህወሀት ዘብ ነው ህወሀት ለሻዐቢያም እንደዛው እናም ከሻዐቢያ ጋር በመወዳጀት ወያኔን እንጥላለን ሀገራችንንም ነፃ እናወጣለን ማለት ሞኝነት ስለሆነ ቆም ብለን አካሄዳችንን ማሳመር ይኖርብናል፡፡
ሁኔ አቢሲኒያዊ
ከፒተርቦሮው ዩ.ኬ

No comments:

Post a Comment