Saturday, February 8, 2014

የአንዷለም አራጌ የውሳኔ አሁንም ቀጠሮ ተራዘመ፤ ኢሕአዴግ 4 የአንድነት አመራሮችን ሊያስር መሆኑ ተሰማ


ዘ-ሐበሻ) በኢትዮጵያውያን ዘንድ የዓመቱ ምርጥ ሰው በሚል የተሰየመው ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ በካንጋሮው ፍርድ ቤት ዕድሜ ልክ ዕስራት እየተፈርደበት መሆኑ ይታወሳል። ወጣቱ ፖለቲከኛ ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን ለውሳኔ ከተቀጠረ በኋላ አሁንም እንደዚህ ቀደሙ ቀጠሮው መራዘሙን የዜና ምንጮች ለዘ-ሐበሻ ጠቁመዋል።

አቶ አንዷለም አራጌ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ወህኒ እየተሰቃየ ቢሆንም “የእኔን መታሰር ተቃዋሚዎች ሊጠቀሙበት አልቻሉም” ሲል መናገሩ አይዘነጋም። ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረብ የነበረበት አንዷለም በዳኞች የተለመደ ምክንያት ቀጠሮው ለመጋቢት 8 ቀን 2006 እንዲተላለፍ ተወስኗል። ዛሬ አንዷለም ላይ ምን ይወሰን ይሆን የሚለውን ለማየት በርካታ ሰዎች ስድስት ኪሎ በሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታድመው እንደነበርም የደረሰን መረጃ ያመልከታል።

የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዘጋቢ ነብዩ ሃይሉ እንደዘገበው ኢህአዴግ አቶ ዳንኤል ተፈራን ጨምሮ አራት የአንድነት አመራሮችን ለማሰር መዘጋጀቱ ተጋለጠ። በዘገባው መሠረት ወጣቱ ፖለቲከኛና ደራሲ ዳንኤል ተፈራን ጨምሮ 4 አመራሮችና አባላት እንዲታሰሩ ኢህአዴግ ወስኗል፤ የክስ ቅድመሁኔታዎች በፍርድ ቤት መጠናቀቃቸውን ታውቋል፡፡


የፍትህ ሚ/ር ምንጮች እንዳስታወቁት በኢህአዴግ ጽ/ቤት ትዕዛዝ ክስ እንዲከፈትባቸውና እንዲታሰሩ የተወሰኑት የአንድነት አባላት በርካታ ናቸው፡፡ ሆኖም የመጀመሪያው ዙር ክስና እስር በ4 አመራሮችና አባላት ላይ ያነጣጠረ ነው ይላል የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዘገባ።

No comments:

Post a Comment