Friday, November 1, 2013

የግንቦት ሰባት ፖለቲካና የዛሬው የለውጥ ትግል – ክፍል ሁለት (ተስፋዬ ደምመላሽ)

ግንቦት ሰባት አገር ቤትና ከአገር ውጭ ካሉ ብዙ ተቃዋሚ ወገኖች በተለየ መልክና መጠን መንቀሳቀሻ መንገዶች፣ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችና ሌሎች የትግል አቅሞች ያፈራ ታታሪና ዘዴኛ ድርጅት ነው። ይህን መቸም አጥብቀው የሚቃወሙት ወገኖች እንኳን ሊክዱት የማይችሉት ነገር ነው። ምንም ያህል አከራካሪ አይደለም። በኢትዮጵያዊያን ዘንድ አጠያያቂና አወያይ የሆነው የድርጅቱ ፖለቲካ ስምሪትና ሥራ ነው። የግንቦት ሰባት ፖለቲካ አከራካሪ ከመሆን አልፎ በሌሎች ተቃዋሚ ወገኖች ዘንድ ድርጅቱን በጥርጣሬ አይን እንዲታይ አድርጐታል። ምንም እንኳን የጥርጣሬውን መነሾ ከራሱ የፖለቲካ አስተሳሰባና አሠራር ውጭ አድርጐ ቢያይም ድርጅቱ ችግሩን አይክድም። እንዲያውም መወጣት ያለበት ጣጣ መሆኑን የተቀበለ ይመስለኛል። በዚህ ያለፈ መጣጥፍ ተከታይ ጽሑፍ ግንቦት ሰባት የገጠመውን የአመኔታ ኪሳራ ወይም ጉድለት ከድርጅቱ ማንነት ወይም ምንነት ጋር በማያያዝ ጀምሬ የድርጅቱን እንቅስቃሴ በመቃኘት የዛሬውን የኢትዮጵያ የለውጥ ትግል ችግሮች ትንሽ ሰፋ አድርጌ በሶስት ረድፎች እመለከታለሁ። እነዚህም የዲሞክራሲ ጉዳይ፣ የጐሳ ፖለቲካ ችግርና የአገርና የፖለቲካ ግንኙነት ዝንፈት ናቸው። ጉዳዮቹን የምመለከተው ፈታሽ፣ ተቺ ጥያቄዎችን በሚያካትት ትንተና እንጅ በቀላሉ በደጋፊ ወይም በተቃዋሚ ተከራካሪነት ተነሳስቼ አይደለም። ወገንተኛ የፖለቲካ አቋም ሳልይዝ አግባብ ያላቸውን ጉዳዮች የማየው ከሁለት አንጻር ነው። አንደኛውና ዋናው ከተቆርቋሪ የኢትዮጵያ ዜጋ እይታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከምሁራዊ የማወቅ ፍላጐት ነው። የግንቦት ሰባት ምንነትና ተልዕኮ ግንቦት ሰባት ማን ወይም ምንድን ነው? “እንቅስቃሴ” እንጅ ፓርቲ አይደለም ማለት በቅጩ ምን ማለት ነው? ከጽንሱና ከጅምሩ ፓርቲ ወይም ህዝባዊ ግንባር ከመሆን ይልቅ በእንቅስቃሴነት የተቋቋመውስ በምን ስሌት ይሆን? እነዚህ የግንቦት ሰባትን የፖለቲካ ህልውና የሚመለከቱ ጉዳዮች እኔ እስከማውቀው ድረስ በድርጅቱ አጥጋቢ ማብራሪያ አልተሰጣቸውም። ጉዳዮቹ ሌሎች ዝርዝር ጥያቄዎችም ያሰከትላሉ። ከነዚህ እስቲ ጥቂቶቹን እናንሳ። ድርጅቱ በውስጡ የተካተቱ የተለያዩ የፖለቲካና የጐሳ ወገኖች መካከል አንድነት የፈጠረ የሃሳብ፣ የእምነትና የስልት አስኳል አለው ወይስ ዝምብሎ የነዚህ ወገኖች የየቅል አስተሳሰቦች ድምር ነው? ግንቦት ሰባት የጐሳ ፖለቲካ አራማጆችን ከኢትዮጵያ አንድነት ሃይሎች ጋር ለማቀራረበ፣ ለማግባባትና ለማስማማት የሚያስችለው ብሔራዊ ራዕይ አለው ወይስ ባመዛኙ አንደኛውን ወገን አስጠግቶ ሌላውን በሚያገል ፖለቲካ ብቻ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው? በፖለቲካና በዘር ካልወገኑ የለውጥ ትግል ደጋፊ ከሆኑ የአገሪቱ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የሰባአዊ መብቶች ተከራካሪዎች፣ የስቪክ ማህበራት አባላትና መንፈሳዊ መሪዎች ጋር ግንቦት ሰባት መደበኛ ክፍትና ነፃ ውይይቶች፣ የሃሳብ ልውውጦች ያደርጋል ወይስ የነዚህን ማህበረሰቦች የለውጥ ትግል ተሳትፎ በራሱ ቀዳሚ ድርጅታዊ አጀንዳ ለማጣጣት ወይም ለመያዝ ይሞክራል? እነዚህ ጥርጣሬዎች በቂ መልስ ይጠብቃሉ። የድርጅቱ ተልዕኮ ወይም የትግል ዘዴስ ምን ይመሰላል? የወያኔን አምባገነናዊ አገዛዝ ለማስወገድና በኢትዮጵያ የተሻለ ብሔራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታን ለማገዝ የሚፈልገው በቀዳሚ “ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሂደት” ነው ወይስ በትጥቅ ትግል? ድርጅቱ ዛሬ በፊተኛው የትግል መንገድ ተስፋ ቆርጦ የኋለኛውን አማራጭ በይበልጥ የያዘ ይመስላል። ግን እዚህም ላይ ግልጽነት የራቀው አሻሚ ነገር አለ። በቅርቡ ተፈጠረ የተባለው የግንቦት ሰባትን ስም የያዘው ለትጥቅ ትግል የተነሳ “ህዝባዊ ሃይል” የግንቦት ሰባትን ስም ይያዝ እንጂ የግንቦት ሰባት ታጣቂ ክንፍ አይደለም ተብሏል። ታዲያ እውነታው የቱ ነው? ግንቦት ሰባት በትጥቅ ትግል አስፈላጊነት አምኖ ተፈላጊውን ሃይል ግንባታና እንቅስቃሴ ጀምሯል ወይስ አልጀመረም? በምን ምክንያት እንደሆነ ባይታወቅም ጉዳዩ የተድበሰበሰ ነው። በርዕዩተ ዓለም ወይም የፖለቲካ አስተሳሰባና እምነት አኳያም እንዲሁ አጠራጣሪ ሁኔታዎች አሉ። የግንቦት ሰባት መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ ያወጣው ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ የተባለ መጽሐፉ መታሰቢያነቱ በከፊል የተሰውለት “ርዕዩተ አለም የተሳሳተ እንኳን ቢሆን…በ1960ዎቹ የተሻለ ሥርዓት ለማምጣት” ብለው ሕይወታቸውን ለሰጡ ወገኖቹ ሁሉ መሆኑን ይገልጻል። ይሁን እንጂ የርዕዩተ ዓለሙ ስህተት ምን ያህልና እንዴት እንደሆነ፣ ዛሬም ቢሆን ከሞላ ጐደል ያለውን ተጽዕኖ እንዴት እንደምንወጣ ዶ/ር ብርሃኑ ምንም ያህል አይመለከትም፣ እትንተና ውስጥ አያስገባም። እንዲያውም ባለፈው ሰሞን ግንቦት ሰባት ባደረገው የህዝብ ስብሰባ ለአንድ ታዳሚ ሲመልስ ስለ ርዕዩተ ዓለሙ ትክክል መሆን አለመሆን ብይን ወይም ውሳኔ የለኝም ብሏል። እንደገና፣ ቀጥተኛው ሃቅ የቱ ነው? ርዕዩተ ዓለሙ የተሳሳተ ነበር ወይስ አልነበረም? ይህ ጥያቄ ያዘለው ቁም ነገር ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን ዛሬ ካለንበት የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ይያያዛል። ለዛሬው የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ትግል መነሻችን የሆነውንና በመሠረቱ መቀየርና ማሻሻል ያለብንን፣ በተዘዋዋሪም ቢሆን የጐሳ ፖለቲካ ያካተተ፣ “ተራማጅ” የአስተሳሰብ ባህላችንን ይመለከታል። ከባህሉ ጋር ያለንን የርዕዩተ ዓለምና የፖለቲካ ሂሳብ በግልጽ ዘግተን፣ የምንጥለውን ጥለን የምንይዘውን ይዘን በአዲስ የአንድነትና የዲሞክራሲ መንፈስ እንደ አገር ወደ ፊት የምንሄደው እንዴት ነው? ጥያቄው ይህ ነው። የዶ/ር ብርሃኑ መጽሐፍ ይህን ጥያቄ በመጠኑም እንኳን ቢሆን እትንተና ውስጥ ቢያስገባው መልካም ነበር። እንግዲህ ማንነቱን፣ ተልዕኮውንና የትግል ዘዴውን በሚመለከት ግንቦት ሰባት ከኋላው በይፋ እንዲታወቅ የማይፈለግ ሌላ አንቀሳቃሽ ሃይል ወይም አጀንዳ ያለው የሚያስመስሉ ጠመዝማዛና አሻሚ አቋሞች መውሰድ ለምን እንዳስፈለገው አይታወቅም። ይሁን እንጂ አንድ ነገር ግልጽ ይመስለኛል። ይኸውም ድርጅቱ ሃሳቦቹንና እንቅስቃሴዎቹን ግልጽ ኢትዮጵያዊ አገባብ ወይም ቅንብር የሚሰጡ አጠቃላይ አገራዊ መመዘኛዎችና መስፍርቶች ከመቅረጽ ወደኋላ ይላል። በኔ ግምት ግንቦት ሰባት በዜጐችና በሌሎች ተቃዋሚ ወገኖች በጥርጣሬ የመታየቱ ዋና ምክንያት ይኸው ወደኋላ ማለቱና በፖለቲካና በአገር ጉዳዮች ላይ ወላዋይ የተጠማዘዙ ክርክሮች ማቅረቡ እንጂ ድርጅቱ ራሱ እንደሚለው ገና ለገና ወያኔ ከገዥነት ከተወገደ በኋላ ሸውዶ ሥልጣን ሊይዝ አስቧል ተብሎ በመጠርጠሩ አይደለም። እንዲያውም የወያኔን አምባገነን መንግሥት ታግዬ እጥላለሁ ግን ሥልጣን የመያዝ እቅድ የለኝም የሚል የትም ያልታየና ያልተለመደ የፖለቲካ አቋሙ ነው አወዛጋቢ የሆነው። ዲሞክራሲያዊ ለውጥና አገር እንደ ግንቦት ሰባት የወደፊት ሁኔታዎች አፈጣጠር ወይም አመጣጥ እይታ ወያኔዎች በሃይል ተገደው ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ነፃ ምርጫ ተኪያሂዶ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ይቋቋማል። ዲሞክራሲ የግንቦት ሰባት ተልዕኮ እንደሚለው የትግሉ ሂደት ሳይሆን ውጤቱ ይሆናል ማለት ነው። ይህ የሄደትና የውጤት አለመያያዝ የምንፈልገውን መሰረታዊ የዲሞክሪያሳዊ ለውጥ ከማምጣት አኳያ አንዳንድ ጉድለቶች አሉት። ዋናው ችግሩ ዲሞክራሲያዊ ለውጥን በሃሳብም ሆነ በእውን ብዙ ጥረት፣ ትምህርትና ተግባራዊ ልምምድ የማይጠይቅ፣ ከብሔራዊ ህልውናችን ጋር መጣጣም የማያስፈልገው ቀላል ክንውን አስመስሎ ማቅረቡ ነው። በሂደት ባዶነት የተገኘ “ዲሞክራሲያዊ” ውጤት ምንም ያህል ተጨባጭ ይዘት እንደማይኖረውና አስተማማኝ እንደማይሆን ከወዲሁ መገመት አያዳግትም። በተለየ የትግል አነሳስና ሁኔታም ቢሆን ወያኔ በትጥቅ ትግል ደርግን ገልብጦ እንዳቋቋመው “ዲሞክራሲ” ማለት ነው። እርግጥ ግንቦት ሰባት ለግለሰብ ነፃነትና መብቶች ቅድሚያ የሚሰጠውን የምዕራቡ ከበርቴን መንግሥት ሥርዓት ተከትሎ ይህንኑ ቅድሚያ የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቡ መሰረት አድርጓል። ሆኖም በተወሳሰቡ ታሪካዊ፣ ህብረተሰባዊና ባህላዊ ሀኔታዎች ከምራቡ የመነጨ የግለሰብነት ጽንሰሃሳብንና ተጨባጭ እውነታን ኢትዮጵያ ውስጥ ከፖለቲካ እምነት ብቻ ተነስቶ ትርጉም ለመስጠትና እውን ለማድረግ መሞከርም የራሱ ችግር አለው። ማድረግ ቢቻልም በቀላሉ የሚሆን ነገር አይደለም። ከጠቅላላ ታሪካዊ ሁኔታዎች አስቸጋሪነት ባሻገር የጐሳ ማህበረሰቦችን ማንነት ወይም ራስነት አወድሎ የግለሰብና የዜግነት መብቶችን ያቀጨጨውን የገዥንም የተቃዋሚንም የጐሳ ፖለቲካ በሚገባ መቋቋም ይጠይቃል። አያይዞም የአማራጭ ዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና አስተዳደርን ልምድ በለውጡ ትግል በተሰማራው የፖለቲካ መደብ ዘንድና በጠቅላላ በኢትዮጵያ ዜጐችና ማህበረሰቦች መካከል ካሁኑ ቀስ በቀስ ማስፋፋትና ማጐልብት መጀመር ያስፈልጋል። እንግዲህ ዲሞክራሲ በቀጥታና በአንድ አፍታ የድህረ ወያኔ መንግሥት ማቋቋሚያ መሣሪያ ወይም መርሃዊና ተግባራዊ አካል ይሆናል ብሎ መጠበቅ የጋራ ብሔራዊ ህይወታችን ያለበትን ውጥረትና አስቸጋሪ ሁኔታ በሚገባ አለመገመት ነው። ጥበቃው የግንቦት ሰባትን እንቅስቃሴ በሚመለከት አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ይጋብዛል። በዛሬው የለውጥ ትግል ውስጥ ድርጅቱ የፖለቲካና የአገር አመራር ግዴታን ምን ያህል በቅጡ ተገንዝቦ ለመወጣት ተዘጋጅቷል ወይም እየተዘጋጀ ነው? በርግጥ ይህ ዋና ጥያቄ ሌሎች የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ተንቀሳቃሽ ሃይሎችንም ይመለከታል። የዲሞክራሲ ሥርዓት ለአገርና ለህዝብ ያለውን ጠቃሚነት በነዚህ አይነት ገደቦች ማየት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ ባሳተመው መጽሐፉ ያቀረበውን ሥርዓቱ “ለሁሉም አይነት የማህበረሰባችን ችግሮች መፍትሔ ነው” የሚል ዋና ክርክር በተመሳሳይ መንገድ መመልከት ያስችለናል። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ዲሞክራሲ ሥር ሰዶ የተቋቋመና የዳበረ ከሆነ የዚያን ህብረተሰብ ጉዳዮች በሚገባ ሊያስተዳድርና ህብረተሰቡ የሚገጥሙትን ችግሮች በሥርዓት ሊፈታ ወይም ውል ሊያስይዝ እንደሚችል እውቅ ነው። ግን እንደ ኢትዮጵያ ላለ ከአምባገነን አገዛዝ ባህል ተላቆ ለማያውቅ ህብረተሰብ አስመሳይ ሳይሆን በእውነት የሚሠራ ዲሞክራሲ ራሱን የቻለ ችግሩ ወይም እጦቱ እንጅ በቀላሉ እንደ መፍትሔ የሚቀርብለት አይደለም። ሥርዓቱን በእምነትም ሆነ በሃሳብ ደረጃ ብንመኘውና ብንፈልገውም ዝግጁ የሆነ ሕያው አማራጫችን አይደለም። ይህንኑ ነጥብ በምሳሌ ለማስቀመጥ፣ የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ችግሮች ሁሉ የሚፈታው ዲሞክራሲ ነው ማለት የሚበላው አጥቶ በጣም የተራበ አንድ የአገራችንን ሰው ከረሃቡ የሚያላቅቀው ምግብ ነው እንደማለት ነው። የሰውዬው ችግር ምግብ ማግኘት ነው! የግንቦት ሰባት አመራር የዲሞክራሲ አቀራረብ ሌላው ዋና እንከን ከአገራዊ ህልውናችን ጋር ያለው ግንኙነት ነው። እዚህ ላይ የሚታየው ችግር አገር ከፖለቲካ የሚቀድምና የሚተልቅ መሆኑ ተረስቶ በአመዛኙ በፖለቲካ አይን ብቻ የሚታይና የሚመዘን፣ ፖለቲካ የሚያነሳውና የሚጥለው ነገር ሆኖ መታየቱ ነው። ዶ/ር ብርሃኑ በዚህ ለተቺ ጥያቄ ክፍት በሆነ አቀራረብ ኢትዮጵያ “የጥሩ ዲሞክራሲ ሥርዓት” ረቂቅ መስፍርቶችን ስለ “አለማሟላቷ” ይናገራል። ይህ አነጋገር በተወሰነ ደረጃ ነጥብ ቢኖረውም የፊቱን (ቀዳሚውን፣ አገርን) ወደኋላ የኋላውን (ፖለቲካን) ወደ ፊት ያደረገ ስለሆነ መቀልበስ አለበት። ጉዳዩ ኢትዮጵያ የሆነ ረቂቅ ርዕዩተ ዓለም ትምሳሌ ወይም የዲሞክራሲ ሞዴል ማሟላቷ አለማሟለቷ ሳይሆን ዲሞክራሲ ከመነሻው ከአገሪቱ ህልውና ጋር መጣጣም አለመጣጣሙ ነውና። ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ከተረሳ ወይም ችላ ከተባለ ዲሞክራሲ ከአገር ምድርና ባህል በላይ የሚንሳፈፍ የትም ያለ ርዕዩተ ዓለም ከመሆን በቀር አገራችን መሬት ውስጥ ገብቶ ሥር አይሰድም፣ አያድግም፣ አያብብም። በዲሞክራሲ ውስጥ የተካተቱ ጽንሰሃሳቦችና መርሆች፣ ለምሳሌ “የግለሰብ መብቶች”፣ “የሕግ የበላይነት” እና ዶ/ር ብርሃኑ የሥርዓቱ ጥሩነት መስፍርቶች ብሎ ያሰቀመጣቸው ሌሎችም በረቂቁ ዓለም አቀፍ የሆኑ የቃል በቃል ትርጉሞች የያዙ ቢሆንም በኢትዮጵያ አገባባቸው እውን የሆነ ግብታዊ ትርጉምና ይዘት ይኖራቸዋል ማለት አይደለም። ፖለቲካችንን የሚመሩት የመንገድ ካርታ ወይም ጂፒኤስ የአውራጐዳና ጉዟችንን አቅጣጫዎች በቀላሉና በቀጥታ በሚያመላክተን መልክ አይደለም። የለውጥ መዳረሻ የሚሆነንን ፍሬ ነገራቸውን፣ ተጨባጭ መረጃቸውንና ትርጉማቸውን የሚለቁት ታሪካውና ዘመናዊ ሁኔታዎች ጋር አዛምደን በሃሳብም በተግባርም ስናዳብራቸው ብቻ ነው። ጉዳዩ የትናንቶቹም ሆኑ የዛሬዎቹ የአገሪቱ የለውጥ ሃይሎች፣ ግንቦት ሰባትንም አክሎ፣ በሚገባ ያሰቡበትና የተረዱት አይደለም። የኢትዮጵያ አብዮት የደረሰበት ታላቅ ውድቀትም እዚሁ ጉዳይ ላይ የተማከለ ነው። ትናንትም ዛሬም ከሞላ ጐደል የምናየው አዝማሚያ አገርን ከነችግሮቹ የዲሞክራሲያዊ ሃሳብና ፖለቲካ መነሻ ከማድረግ ይልቅ በቅድሚያ የአገር ችግሮን ያለምንም ቀሪ ወደ ፖለቲካ ጥያቄዎችና ጣጣዎች ማውረድ ወይም መቀነስ ነው። ለምሳሌ “የብሔሮች ጥያቄ” በኢትዮጵያ አገራዊ አገባቡ ምንም ያህል ያልታየ፣የአገሪቱን የጐሳ ማህበረሰቦች እውን ማንነት ሳይቀር በረቂቅ ዓለም አቀፈ የርዕዩተ ዓለም ፈርጆች የተካ ፍጹም የፖለቲካ “ጥያቄ” ነበር። ሌላ የተለየ ምሳሌ ለመጠቆም፣ የግንቦት ሰባት ንግግር ኢትዮጵያዊነትን ብዙውን ጊዜ ወደ “ፖለቲካ ማህበረሰብነት” ዝቅ ያደርጋል። ከዚህ የቆየ ግራ ክንፈኛ የአገር ጉዳዮችን ያለምንም ቀሪ ወደ ፖለቲካ ችግሮችና መፍትሔዎች ቅንሳ ባህል ጀርባ አንድ ጠቅላላ የአስተሳሰብና የእምነት ዝንባሌ አለ። ይኸውም ውስብስብ የሆነ አገር የመለወጥና የማሻሻል ትግል በቀላሉ የርዕዩተ ዓለም ፎርሙላ ተከትሎ (ትናንት “ህብረተሰባዊነት” ዛሬ “ዲሞክራሲ”) ማከናወን ይቻላል የሚል እምነት ነው። የዚህን አስተሳሰብ ፈለግ እስከተከተለ ድረስ ዛሬ በኢትዮጵያ ለለውጥ ታጋይ ማንኛውም ወገን ካለፈው የፖለቲካ ታሪካችን በሚገባ አልተማረም ማለት ነው። ካለፈው ስህተት ካልተማረ ደግሞ እንደሚባለው ታሪክን ደጋሚ ነው የሚሆነው። ትምህርቱ ምንድን ነው? በኔ ግምት አንዱ ዋና ትምህርት በኢትዮጵያ መሠረታዊ ለውጥና እድገት ለማምጣት የጋራ ብሔራዊ ሁነታችንን ወይም ህይወታችንን መሠረትና መነሻ ከማድረግ ይልቅ በንጹህ ፖለቲካዊ ተነሳሽነት መሠረታችንን ሲያንስ ችላ ማለት ሲበዛ ደግሞ መቃወምና አለመቀበል መጨረሻው የከፋ ነው የሚሆነው። ሁለገብ የፖለቲካ፣ የህብረተሰብ፣ የኢኮኖሚና የባህል ለውጥ ለማምጣት ቃል መግባት፣ ቆራጥነትና ተሰዊነት ያልጐደለው የትናንቱ የአገሪቱ ተራማጅ ሃይሎች ትግል ታላቅ ውድቀት የደረሰበት ከጥንስሱ ትግሉ የአገር ህልውናንና መንፈስ መራቁ ብቻ ሳይሆን መጠናወቱም ነበር። የለውጥ ትግል ፖለቲካውን ከአገር ታሪክ ውጭ ወይም በላይ ሆኖ፣ ከብሔራዊ ሥር መሠረቱ ራሱን ነቅሎ ለማራመድ በመሞከሩ ነበር። ዛሬ ግንቦት ሰባትም ሆነ ሌሎች ያሉ ወይም ወጤ ለለውጥ ታጋይ የአገሪቱ ሃይሎች ይህን ትምህርት በሃሳብ ጠለቅ ብለው መጨበጥና ትምህርቱን ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋቸዋል። ከአገር ህልውና ጋር በግልጽ ካልታረቁ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ በሰፊው ካልሳቡ፣ ከፖለቲካና ከጦር መሣሪያዎቻቸው በተጨማሪ አነሳሽና አስተዋይ አገራዊ ራዕይ ካልታጠቁ የትግል ጉዟቸው አደገኛ ነው የሚሆነው። መጨረሻው አያምርም። ኢሕአፓ እና ደርግ የተለያዩ ሌሎች የሽንፈት ሁኔታዎች ያጋጠሟቸው መሆኑ ባይካድም እነዝህን የውድቀት ምክንያቶች ከሞላ ጐደል ተጋርተዋል። ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጋር የተጻረረውና የተጣላው ወያኔም የሚጠብቀው ዕጣ ፈንታ ይዋል ይደር እንጅ እንዲሁ ውድቀት ነው። የጐሳ ፖለቲካ ችግርና መወጫው በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ ስለ ዘር ፖለቲካ ብዙ ይባላል። ግን ብዙውን ጊዜ ጉዳዩን በቀጥታና በሃቀኛነት ከመመልከትና ከመተቸት ወደኋላ እንላለን። የአገሪቱ የተለያዩ የጐሳ ማህበረሰቦች እንደየሁኔታቸው ያላቸውን የራስ ማንነት በራስ እይታ በማክበርም ሆነ በጉዳዩ ለእውነተኛ አስተያየት ምቹ አለመሆን ምክንያት የዘር ወገንተኛነትን ተገቢውን ፍተሻና ግምገማ እምብዛም አንሰጠውም። ይህ ደግሞ በማንነት ፖለቲካና በአገር አንድነት መካከል ያለን የተንዛዛ መቃቃር በሚገባ ለመገንዘብና ችግሩን ለማስወገድ አይረዳንም። ችግሩን በይበልጥ ለትንተናና ለትችት ለማመቻቸት በኢትዮጵያ የሚገኙ ጠቅላላ የጐሳ ማህበረሰቦች ያላቸውን ግብታዊ የዘወትር ራስ እይታ ወይም የማንነት መለያ ባህሎች፣ ሥራዓቶች፣ እሴቶችና ልምዶች በመሃበረሰቦቹ ስም ራሳቸውን የወከሉ ብቸኛ ወገኖችና ድርጅቶች ሆን ብለውና አስልተው ከፈጠሩት የፖለቲካ ዘረኝነት መለየት ይጠቅማል። በዚህ መንገድ የጠቅላላ ማህበረሰቦችን ጉዳዮችና ችግሮች ራሳቸውን የጐሳ ፖለቲከኞችና ሊህቃን ከሚሰጧቸው የተወሰኑ እይታዎችና ትርጉሞች ጋር ማምታታት እናቆማለን። ብለንም፣ በአንድ በኩል ዘር ላይ የቆመ ጠባብና ብቸኛ ወገንተኛነትን ለተቺ ጥያቄችዎች፣ ለድርድርና ለለውጥ በሚገባ መክፈት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጠቅላላ ማህበረሰቦችን ጉዳዮች፣ ችግሮች፣ ጥቅሞችና ፍላጐቶች በዛሬው አገራዊ የለውጥ ትግል ውስጥ በተሻሉ አማራጭ መንገዶች ማስተናገድና ማካተት እንችላለን ማለት ነው። ችግሩ ግንቦት ሰባትና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጐሳ ፖለቲካን በዚህ መልክ ለይተው ስለማያስቀምጡና እንዲያውም ከአራማጆቹ ጋር “መቀናጀትን” ሁነኛ የትግል ዘዴ አድርገው ስለሚያዩ ፖለቲካውን በሃቀኝነትና በድፍረት መግጠም ይሳናቸዋል። የዘር ፖለቲካን መሠረታዊ ችግሮች ለማስወገድ ማድረግ ካለባቸው የሃሳብና አመለካከት ተሃድሶ ይቆጠባሉ። ወይም የአዲስ ሃሳቦችና እይታዎች ፈጠራ አስፈላጊነት አይታያቸውም። እርግጥ የግንቦት ሰባት መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የፖለቲካውን አንዳንድ እንከኖች በመገንዘብ እነዚህን ለማረም ምሀራዊ ጥረት ያደርጋል። በቅርቡ ባወጣው መጽሐፍ ችግሮቹን በሚመለከት አስተያየቶች ሰጥቷል። ሆኖም አስተያየቶቹ በአመዛኙ ግንቦት ሰባት የሚያደርገው የቅንጅት ፖለቲካ ሥራ አፈጻጸም ላይ ያተኮሩና በቅድሚያ ከድርጅቱ ተልዕኮና የትግል ዘዴ ጋር የተያያዙ ስለሆኑ ጉዳዩን በሚመለከት ያላቸው የሃሳብና የትንተና ይዘት ውስን ነው። ከድርጅታዊ ቅደም ተከተሎች ጋር አያይዘውም በወያኔ አገዛዝ በአገሪቱ የተስፋፋውን የዘር ፖለቲካ ለምርመር፣ ለውይይትና ለለውጥ ምንም ያህል ክፍት ያልሆነ “እውነታ” አድርገው የሚነሱ አስትያየቶች ናቸው። ግንቦት ሰባት ከዚህ ኢሂሳዊ “ነገሮችን እንዳሉ ከማየት” አዝምሚያ ጋር የተሳሰረ ሌላ ችግር አለው። ችግሩ የድርጅቱን ወደ ጐሳ ፖለቲካ አድራጊ ፈጣሪዎች አቀራረብ የሚመለከት ነው። አቀራረቡ የዘር ፖለቲከኞንችና ሊህቃንን በሃሳብና በውይይት ከመፈታተንና የአንድ አገራዊ ለውጥ ትግል አመራር ወይም አካል ለማድረግ ከመጣር ይልቅ እነዚህን ግለሰቦችና ወገኖች ከነጐሳ ፖለቲካቸው መሳብና በነሱ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት ማግኘት ላይ ማተኮር፣ “ለቅንጅት” ማባበል ነው። ለምሳሌ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የዘር ብሔርተኞችን ሃሳቦች በተገቢ ትንተና ከመፈተሽ ይልቅ የነዚህን ታሪክ በድሎናል ባይ ወገኖች “ጭንቀቶች” በውይይት “ማረጋጋት” እና “ማለሳለስ” አስፈላጊነትን ያጐላል። ብሔርተኝነታቸው የታነጸበትንና የተማከለበትን ስታልናዊ ቀኖና የኢትዮጵያ “ታሪክ ትንተና” መሣሪያቸው አድርጐ አይቶ ያልፈዋል። ከዛሬው የኢትዮጵያ ለውጥ ትግል አንጻር ሲታይ ይህ መቸም የምሁራዊና ፖለቲካዊ አመራር ግዴታን በቅጡ አለመገንዘብና ለመወጣት አስፈላጊውን ጥረት ከማድረገ ወደኋላ ማለት ነው። በድርጂታዊ እንቅስቃሴ ረድፍም ባይሆን በሃሳብ መስክ ታታሪነት ማጓደል ነው። በኔ ግምት የዘር ፖለቲካ አራማጆችን ጉዳዮች ተገቢ እውቅና የምንለግሰው የአራማጆቹን አስተሳሰብና እምነት ክብደት ሰጥተን በትህትና ስንቋቋማቸው፣ በቀጥታ ሃቀኛ ለሆነ የሃሳብ ልውውጥ፣ ድርድርና ስምምነት ስንጋብዝቸውና ስናበረታታቸው ነው። በቀላሉና በድብስብሱ የጭንቀታቸው ተንከባካቢ መሆን ወይም የጐሳ ፖለቲካቸውን ከሞላ ጐደል እንደያዙ እለውጥ ትግሉ ውስጥ እንዲሳተፉ “በአድልዎ” መለማመጥ ጥቅማቸውን መጠበቅ ቢመስልም እነሱንም ሆነ የፖለቲካ ሃሳባቸውን ተገቢ ክብደት መስጠት አይመስለኝም። እርግጥ የግንቦት ሰባት መሪ ዶ/ር ብርሃኑ የሚናገረው እንደ አንዳዶቻችን በጐሳ ፖለቲካ ተመልካችነት ብቻ ሳይሆን የድርጅት አመራር ሃላፊነት ይዞ ስለሆነ ስለ ዘር ፖለቲካ ችግሮች የተሻለ ቢያውቅም አስተያየቱን “ዲፕሎማሲያዊ” አድርጐ ማቅረብ ይገደድ ይሆናል። ይሁን እንጂ አስተያየቱ በሰፊው የግንቦት ሰባት እንቅስቃሴን ውስንነት የሚያመለክት ይመስለኛል። እንቅስቃሴው ወያኔን አስገድዶ ከሥልጣን ማውረድ ግቡና እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ብሎ ከያዛቸው የተወሰኑ አጭርና መካከለኛ የትግል ጉዞ አጀንዳዎችና መላዎች ባሻገር ይህ ነው የሚባል አገር አዳኝ ብሔራዊና ስልታዊ ራዕይ አላዳበረም። ይህ አይነት ራዕይ ለአገር ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ ምንም ቦታ የሌለው፣ ለጐሳ ማህበረሰቦች መብቶችና አካባባዊ ጉዳዮች ግልጽና ቆራጥ አገራዊ መመዘኛዎች ወይም አገባቦች የሚቀርጽና የኢትዮጵያን ህልውና ከተለያዩ የአገሪቱ የፖለቲካና የጐሳ ወገኖች ድምር አልቆ የሚያሳይ ነው። ግንቦት ሰባት የዛሬውን የለውጥ ትግል በመጠነኛ ፀረ ወያኔ የፖለቲካ ስሌት አይን አይቶ፣ የጐሳ ድርጅቶችንና ሌሎች ተንቀሳቃሽ ወገኖችን አሰባስቦና አሰማርቶ፣ በዚህም ጥረት ትግሉን በሚመለከት የራሱ አጀንዳ ባለው በኤርትራ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ተደግፎ የተወሰኑ የፖለቲካ ግቦች፣ ምናልባት ገዢውን ፓርቲ ከሥልጣን ማውረድንም ጨምሮ፣ መምታት ይችል ይሆናል። ግን ይምንፈልገው መሠረታዊ የፖለቲካና የአገር ለውጥ በዚህ መንገድ የሚከናወን አይደለም። አወዛጋቢ የሆነውን የኤርትራን ድጋፍ ጉዳይ ወደ ጐን እንተውና ለምሳሌ በትጥቅ ትግሉ መስክ አንድ ዋና እምቅ ችግር አለ። በዘር የተደራጁ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የአማራና የሌሎች ጐሳዎች ታጣቂ ወገኖችን ማከማቸት ወይም ማቀናጀት ማለት አንድ አገር አዳኝና ጠባቂ የጦር ሃይል መገንባት ማለት አይደለም። እንዲያውም የአገርን አንድነት ከባሰ አደገኛ ሁኔታ ላይ መጣል ነው የሚሆነው። እንግዲህ የምንፈልገው የአገር ተሃድሶ ያሉ ህዝብ ከፋፋይ የጐሳ ፖለቲካ አስተሳሰቦችን፣ እንቅስቃሴዎችንና ሁኔታዎችን “የሚያሻሽል” ወይም የተለየ ቅርጽና መልክ የሚሰጥ ሳይሆን እነዚህን ከመሠረታቸው የሚለውጥ ነው። ለዚህ ዓላማ የሚካሄድ የለውጥ ትግል ደግሞ በተለያዩ ደረጃዎች፣ መስኮችና አገባቦች የተቀናበሩ ምሁራዊ፣ ፖለቲካዊና ህብረተሰባዊ ጥረቶች የጠይቃል። አወያዩ ጉዳይ የግንቦት ሰባት ፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ተልዕኮና እንቅስቃሴ ድርጅቱን የዚህ አይነት የለውጥ ትግል መምራት የሚያስችሉ ናቸው ወይ ነው። ጥያቄው አገር ቤትና ከአገር ውጭ ያሉ ሌሎች ተቃዋሚ ወገኖችንም ይመለከታል። ታሪክ፣ አገርና ፖለቲካ እንደ ብዙዎቻችን የአብዮቱ ትውልድ አባላት አስተሳሰብ የግንቦት ሰባት መሪዎችም ርዕዩተ ዓለም ከሞላ ጐደል የታነጸው በተማሪዎች እንቅስቃሴ በተጀመረው የኢትዮጵያ ተራማጅነት ልምድ ውስጥ ነው። ልምዱ ታሪክን፣ በተለይ የአገርን ታሪክ ወይም ታሪካዊነት በፖለቲካ እይታና ስሌት ያጥለቀለቀ፣ ታሪክ በኢትዮጵያ ህልውና ያለውን መሠረታዊ አገባብና ቦታ አመዛዝኖ ያልተረዳ መሆኑን ማወቅ ለዛሬው የለውጥ ትግል ጥቅም አለው። ለምሳሌ የዘር ብሔርተኞች የኢትዮጵያ ታሪክ ሲሠራ የተለያዩ የጐሳ ማህበረሰቦች “ፈቃደኛነት” እየተጠየቀ አልነበረም ለሚለው ቅሬታቸው አግባብ ያለው፣ ምናልባት ይልቅ አርኪ የሆነ መልስ መስጠት ያስችለናል። በይበልጥ ጠቃሚነት፣ በአገርና በፖለቲካ መካከል ያለን የቆየና ዛሬም (በወያኔ ዘረኛ አገዛዝ) ተባብሶ የቀጠለ በጣም የተዛባ ግንኙነት ለመለወጥና አሻሽሎ ለመገንባት ይበጃል። በነዚህ ታሪክንና ፖለቲካን የሚመለከቱ ጥቅል ነጥቦች ላይ በይበልጥ ትኩረት ለመሄድ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ ባሳተመው መጽሐፍ ካቀረበው ሃሳብ መነሳት ይቻላል። ሃሳቡ የጋራ (ብሔራዊ) ህይወታችንን መቅረጽ የምንችለው ታሪክ ላይ ተመሥርተን እንዳልሆነና በታሪክ መረጃ ለመስማማት በመሞከር እንዳይደለ የሚገልጽ ነው። ለዚህ የተሰጠው ምክንያትም የታሪክ እውነታ በተመራማሪዎችም ሆነ በፖለቲካ ወገኖች ዘንድ ያለማቋረጥ የሚያከራክር እንጂ እስምምነት ላይ የሚያደርስ አይደለም የሚል ነው። በዶ/ር ብርሃኑ እምነት፣ የጋራ ህይወታችን የገጠመው የፖለቲካ ችግር ስለሆነ የሚጠይቀውም የፖለቲካ መፍትሔ ነው። ከመነጨበት ከኢትዮጵያ ግራ ክንፈኛነት ልምድ አንጻር ሲታይ የዚህ አስተሳሰብ ታሪክ እና ፖለቲካ እይታዎች ችግር አላቸው። ታሪክን በሚመለከት እይታው ያለውን መሠረታዊ እንከን መጀመሪያ እንቃኝ። የሰው ልጆች እርግጥ ታሪክ ይሠራሉ፣ የሚሠሩት ግን ከዜሮ ተነስተው በንጹህ የፖለቲካ መንገድ ራሳቸውንና ዕድላቸውን በመፍጠር ሳይሆን ሊወስኗቸው ከማይችሉ በቅድሚያ የተሰጡ ታሪካዊ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ነው። ግለሰቦችና የተወሰኑ ድርጅቶች (ተመራማሪዎች፣ ፓርቲዎች፣ የጐሳ ፖለቲከኞች ወ.ዘ.ተ) ሆን ብለው የሚይዟቸው አከራካሪ የታሪክ አመለካክትና አተረጓጐም አቋሞች በአንድ በኩል የሚታዩ ሲሆኑ፣ ታሪክ በተጨባጭ ሂደት አገር ህልውና ውስጥ ያለው አገባብ ደግሞ ራሱን ችሎ የሚስተዋል ነገር ነው። የዶ/ር ብርሃኑ ሃሳብ እነዚህን ሀለት የታሪክ እይታ ደረጃዎች ያምታታል። የታሪክ ትንተና፣ ትችትና ክርክር ፈርጆችን ወይም አቋሞችን በእውን የታሪክ ሂድት ከተቀረጹና ከዳበሩ ተቋማዊና ባህላዊ የአገር ህልውና አካላት ጋር፣ ከብሔራዊ ልምድና ምግባር ጋር ይደባልቃል። እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን የጋራ ብሔራዊ ህይወታችን ዝምብለን በፖለቲካ አይን ብቻ አይተን “እውነት” ነው አይደለም፣ ታሪኩ የተሠራው ፈቃዳችን ተጠይቆ ነበር አልነበረም ብለን የምንስማማበት ወይም የማንስማማበት ጉዳይ አይደለም። ሰዎች ታሪክ ውስጥ የራሳቸው ተንቀሳቃሽነትና አድራጊ ፈጣሪነት ቢኖራቸውም የታሪክ ሂደት ራሱ በሰዎች ፈቃደኛነትና ስምምነት አይወሰንም። ይህ ማለት በአገር ጉዳዮች ስምምነት አያስፈልግም ወይም አገር ሲቋቋምና ሲያድግ የተሠሩ በደሎችንና ስህተቶችን ማስተካከል አንችልም ማለት አይደም። ብዙ አገሮች ሲመሠረቱና ሲስፋፉ በጣም አስከፊ ጭቆናዎች (ለምሳሌ የጥቁሮች ባርነት በአሜሪካ፣ የጥቁሮች ዘረኛ ጭቆና በደቡብ አፍሪካ) ተፈጽመው በኋላ በሂደት ከሞላ ጐደል ተስተካክለዋል። በዚህ መጠን ባይሆንም በኛይቱም አገር በደሎች ተሠርተዋል፣ ብዙዎች ችግሮችም በኢትዮጵያ አብዮት አማካኝነት ተወግደዋል። የአገር ስህተቶችን ማረም ማለት ግን በታሪክ ሂድትና አጋጣሚ የተቋቋመና የዳበረ አገርን ራሱን (ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካን ወይም ኢትዮጵያን) ማፈራረስ ወይም በዘር መከፋፈል ማለት ሊሆን አይችልም። በኢትዮጵያ ታሪክ አመለካከት ወይም ፖለቲካዊ አተረጓጐም ተስማማንም አልተስማማንም ኢትዮጵያ ሊለወጥና ሊሻሻል የሚችል ግን የማይካድ ተጨባጭ ታሪካዊ ህልውና አላት። ይህን ህልውና መቀበልና ማረጋገጥ ራሱ የጋራ ብሔራዊ ህይወታችንን የግድ አከራካሪ አያደርገውም። ባጭሩ እንግዲህ ታሪክ ከውጫችን ያለ መረጃ ወይም እውነታ፣ የምንተነትነው፣ የምንተቸውና የምንከራከርበት ነገር ብቻ ሳይሆን የጋራ ብሔራዊ ህይወታችን መሠረታዊ አካል ነው። ከግል ዜግነት አንጻርም ሆነ በማህበረሰቦችና በአገር ደረጃ ታሪክ እውስጣችን ነው። በዛሬው ትግል ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት ስንታገል ከአገራዊ ህልውናችን በጽናት ተነስተን እንጂ የቆምንበትን ብሔራዊ መሬት፣ ማንነታችንን እየሸረሸርን አይደለም። የታሪክና የባህል ባለጸጋ የሆነውን ኢትዮጵያዊነትን አደህይተን “በፖለቲካ ማህበረሰብነት” ለውጠን አይደለም። በሌላ በኩል ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ያለው ፖለቲካን ለሁሉም የአገር ችግር መፍትሄ የሚያደርግ እይታ ራሱ ከመሠረቱ እንከናማ ነው። በሰፊው ሲታይ እንከኑ ከተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን ጀምሮ እስከዛሬ ያልተለየን በአገር ገዳዮች ውስጥና ከጉዳዮቹ በላይ የተንሰራፈፈ፣ ብሔራዊ እሴቶቻችንን ያጥለቀለቀና ያመነመነ የፖለቲካ ግሽበት ችግርን የሚያመለክት ነው። ተራማጅ ነን ያልን የአብዮቱ ትውልድ አባላት ሁሉ የነበረን የአገር ገዳዮች እይታ ለእንከኑ አስተዋጽዎ አድርጓል። ችግሩን በእንቆቅልሽ መልክ ለማስቀመጥ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በድህረ አብዮቱ ዘመን እርስ በርስ ተጻራሪ የሚመስሉ ገጽታዎች ወይም ባህሪያት ያሉት፣ ተስፋፍቶ በሁሉም ሥፍራ የሚገኝ ግን በተለየ ወይም በተወሰነ መልክ የትም የሌለ፣ ረቂቅ ሃሳቦችን እንደ ጣኦት የሚያመልክና ቃል በቃል የሚያንደረድር ግን ተጨባጭ ይዘታቸውንና ትርጉማቸውን ከራሱ የከላ ምንድን ነው? ፖለቲካ! አዎ፣ “አብዮታዊ” ፖለቲካ ነው። ችግሩን በዚህ ጥቅል መልክ ስናስቀምጥ በአብዮቱ ጊዜም ሆነ በድህረ አብዮቱ ዘመን የተለያዩ ፓርቲዎችና ወገኖች የተለያዩ የፖለቲካ ግቦች ለመምታት ይጣጣሩ እንደነበር በመዘንጋት አይደለም። ወይም ደግሞ ዛሬ ግንቦት ሰባት ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከሌሎች ተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ያሉትን የአስተሳሰብና የእንቅስቃሴ ልዩነቶች ከቁጥር ባለማስገባት አይደለም። ይልቅስ የተለያዩ የአገሪቱ “ተራማጅ” እንቅስቃሴዎች፣ ፓርቲዎችና ድርጅቶች በፉክክርም ሆነ በትብብር የፈጠሩት ፖለቲካ በጠቅላላ የነበረውንና ያለውን ጥልቅ ጉድለት ለማጉላት ነው። ማለትም የአገር ችግሮች ሁሉ የሚፈቱት በፖለቲካ መንገድ ነው፣ በፖለቲካ አይን ሲታዩና የፖለቲካ ቁጥጥር ሲደረግባቸው ነው የሚል የተለያዩ ወገኖች ከሞላ ጐደል የተጋሩት እንከናማ እምነት ላይ መሠረታው ጥያቄ ለማንሳት ነው። ይህ እምነት ወይም አስተሳሰብ ፖለቲካን ከመጠን በላይ አስፋፍቶ የማህበረሰባዊና ብሔራዊ ህይወታችን ቅርጽ፣ ይዘትና አድማስ ያደርጋል። ይህን ሲያደርግ ተጻራሪ የሚመስሉ ግን የአንድ ሳንቲም ሁለት ጐኖች ሊባሉ የሚችሉ ባህርያት ያሳያል። በአንድ በኩል ፖለቲካን ፍጹም እሴት ወይም ከፍተኛ ግምት ሰጥቶ በአገር የበላይነት ይቀርጻል፣ ያዋቅራል። አክሎም በግልጽና ውስጥ ለውስጥ ስቪል ህብረተሰብን ያጥለቀልቃል፣ ያፍናል፣ ይጫናል። በሌላ በኩል እምነቱ ፖለቲካ ራሱን ችሎ፣ አንጻራዊ ነፃነቱን ወይም ልዩነቱን ጠብቆ ለአገርና ለህብረተሰብ አገልጋይ መሣሪያ እንዳይሆን ያደርጋል። ማለትም፣ ፖለቲካ ሁሉ ቦታ ስለሚገባ ይህ ነው የሚባል የራሱ ቅርጽ፣ ይዘትና አገልጋይነት ሊኖረው አይችልም። ወይም ራሱን በገደብ የሃሳቦች፣ የመርሆዎች፣ የተቋማትና የምግባር ምንጭ ሊያደርግ አይችልም። ይህ ሁኔታ እስከቀጠለ ድረስ ደግሞ በመላ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኝ መርሃዊና መዋቅራዊ ሃቀኝነት ያለው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አዳጋች ነው የሚሆነው። በተጨማሪ የአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወይም የጐሳና የባህል ማህበረሰቦች እውነተኛ ራስ ገዝነትም ቢሆን በተለመደው ከመጠን በላይ ተስፋፊና አምባገነናዊ ፖለቲካ አማካኝነት የሚገኝ አይደለም። ለምሳሌ የትግሬ ወይም የኤርትራ ህዝብ በነፃነት ራሱን በራሱ ያስተዳድራል ማለት ዘበት ነው። እንግድህ በኢትዮጵያ የቆየና ዛሬም ተባብሶ የቀጠለ በጣም የተዛነፈ የአገርና ፖለቲካ ግንኙነት እንዳለ ብዙ አከራካሪ አይደለም። ወያኔ የራሱ የሆነ ዘረኛ ዘዬ ይጨምርበትና ያባብሰው እንጂ የዝንፈቱ አመንጪ ወይም ብቸኛ ተጠያቂ አይደለም። ለተለያዩ የትናንት እና የዛሬ ፓርቲዎች፣ ወገኖችና ታጋዮች፣ የግንቦት ሰባት መሪዎችንም ጨምሮ፣ በጠቅላላ ለብዙዎቻችን የሚዳረስ ተጠያቂነት አለ። በኔ እምነት ይህን ተረድተን በዛሬው የለውጥ ትግል አገራችንን ለሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ዙር የፖለቲካ “መፍትሔ” ሙከራ ከመዳረጋችን በፊት ፖለቲካችንን ራሱን በሃሳብና በተግባር ከመሠረቱ ለማስተካከልና ለዘለቄታው ተገቢ ቦታውን ለማስያዝ መንቀሳቀስ አለብን። ይህ እርምጃ ኢትዮጵያን ከተጠናወታት የፖለቲካ ባርነት ለማላቀቅ መወሰድ ያለበት ነው። የኢትዮጵያ ተሃድሶ ከዚህ ያላነሰ ጥረት ይጠብቃል። ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com

No comments:

Post a Comment