Thursday, October 10, 2013

ትንሽ ስለ ተስፋዬ ገብረአብ – አብርሃ ደስታ ከመቀሌ

‘የተስፋዬ ገብረአብ ማንነት አጋለጠ’ የተባለውን ፅሑፍ አነበብኩት። ገረመኝም። ረዥም ነው። የአንድ ሰው ማንነት ለማጋለጥ አርባ ምናምን ገፅ? ተስፋዬ ገብረአብን ‘ያጋለጠ ‘ ፅሑፍ ለኔ ምንም ዓይነት ተጨማሪ መረጃ አልሰጠኝም። ስለ ተስፋዬ ገብረአብ ትንሽ ለመፃፍ የተገደድኩት ምክንያት አንዳንድ የህወሓት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ‘የተስፋዬን መጋለጥ’ ምክንያት በማድረግ እኔ አንድ ነገር እንድልላቸው ስለወተወቱኝ ነው። አንዳንዴ’ኮ ጎበዞች ናቸው። ተፎካካሪያቸውን ማኖ ማስነካት ይችላሉ። እኔ ደግሞ ማኖ መንካት እወዳለሁ፤ (ማኖ ካልነካንላቸው ከስድብ ዉጭ ሌላ የሚያውቁት ነገር የላቸው)። ተስፋዬ ገብረአብ ጎበዝ የስነ ፅሑፍ ሰው ነው። ፅሑፉን ለመገምገም ማንነቱና ስራው አያገባንም። የፅሑፉ ይዘትና መልእክት መገምገም በቂ ነው። እንደ የስነፅሑፍ ሰው ጥሩም መጥፎም ስራዎች ይኖሩታል።
ለምሳሌ ‘የቡርቃ ዝምታ’ ፅሑፉ መጥፎ ዓላማ ያለው መሆኑ የሚያሳይ ነው። አሁን ‘የተስፋዬ ገብረአብ ማንነት ተጋለጠ’ እያላችሁኝ ነው። የሻዕቢያ ቅጥረኛና ሰላይ መሆኑ እየነገራችሁኝ ነው። ለዚህ ማስረጃችሁም በኤርትራ መንግስት የተሰጠው ግዝያዊ መታወቅያና በማስታወሻ ደብተሩ ላይ በፃፈው መሰረት ነው። ጥሩ ነው። ግን ተስፋዬ ገብረአብ የኤርትራ ግዝያዊ መታወቅያ ማግኘቱና የሻዕቢያ ሰላይ መሆኑ ምን ይደንቃል? እንዳውም ሲያንሰው ነው። በመጀመርያ የተስፋዬ ስራዎች የምናነበው ኤርትራዊ ስለሆነ ወይ ስላልሆነ አይደለም። የሻዕቢያ ሰላይ ስለሆነ ወይ ስላልሆነም አይደለም። ‘ኢትዮዽያዊ ነኝ’ ብሎ ስለነገረንና ስላመነውም አይደለም። ፀሓፊ ስለሆነ ነው። የፕሮፌሰር ክላምፓም፣ ፕሮፌሰር ለቪና ሌሎች ስለ ኢትዮዽያ የሚፅፉና የምናነብላቸው የኢትዮዽያ ደም ስላላቸው አይደለም። ስለ ኢትዮዽያ ለመፃፍ የግድ ኢትዮዽያዊ መሆን አይጠበቅብህም። የተፃፈ ለማንበብም የፀሓፊው ማንነት ማወቅ ግድ አይደለም። ግድ የሚለን የፅሑፍ ይዘት መገምገም ነው። ተስፋዬ ገብረአብ የሻዕብያ ሰላይ ነው እንበል። ይሄ አይደንቅም። እንዳዉም የሚደንቀው ሰላይ ባይሆን ኑሮ ነው። የኤርትራ መንግስት በሰጠው ግዝያዊ መታወቅያ ላይ የትውልድ ሀገር ደብረዘይት ይላል። መኖርያውም ናይሮቢ። ተስፋዬ ደብረዘይት ተወልዶ እንዳደገና ኢትዮዽያዊ መሆኑ ነግሮናል። ከኤርትራውያን ቤተሰብ እንደተወለደ ግን ይታወቃል። ተስፋዬ ይህም ቢሆን ክዶ አያውቅም። ከኤርትራውያን ቤተሰብ ቢወለድም (ተስፋዬ ሲወለድ ኢትዮዽያና ኤርትራ አንድ ሀገር እንደነበሩ ይታወቃል) ኢትዮዽያ ዉስጥ ተወልዶ በማደጉ ብቻ የኢትዮዽያ ዜግነት የማግኘት ሕጋዊ መብት አለው። የኢትዮዽያ ዜግነት ተሰጥቶም የኢትዮዽያ ሬድዮና ምናምን ሓላፊ ሁኖ ሰርቷል (ዜግነት ሳይኖረው ስልጣን ተሰጥቶት ከሆነ የራሳቹ ጉዳይ)። ሌላ ነጥብ ደግሞ ተስፋዬ ከኢትዮዽያ ባለስልጣናት ከተጣላ በኋላ ወደ ኬንያ መሄዱና የኢህአዴግ ባለስልጣናት የኢትዮዽያ ፓስፖርቱ እንደነጠቁት ተናግሮ ነበር። እንዴት ነው ነገሩ? ፓስፖርት መንጠቅ?! ወይስ ከኢህአዴግ ባለስልጣናት ከተጣላ በኋላ ነው ኢትዮዽያዊ አለመሆኑ ያወቁ? ይህ የሚያሳየው ነገር ቢኖር የሻዕቢያ መንግስት ግዝያዊ መታወቅያ የሰጠው ከኢትይዽያ ተጣልቶ ከወጣና ናይሮቢ ከገባ በኋላ መሆኑ ነው። አንድ ሰው ፓስፖርቱ ከተነጠቀ ዜግነቱ ተነጠቀ ማለት ነው። በሌላ ሀገር (ለምሳሌ ኬንያ) እየኖሩ ዜግነት አልባ (Stateless) መሆን እንዴት እንደሚከብድ አስቡት። ፓስፖርት ሳይኖርህ እንዴት በሌላ ሀገር መንቀሳቀስ ይቻላል? ኬንያ እያለ ፓስፖርቱ ከተነጠቀ እንዴት ብሎ ወደ ደቡብ አፍሪካ መሻገር ይችላል? (ሻዕቢያ ሌላ ፓስፖርት ሰጥቶት ይሆናል)። ለምንድነው የኢትዮዽያ ፓስፖርቱ የተነጠቀው? የኤርትራ ደም ስላለው ነው? እንዲህማ ከሆነ የኤርትራ መንግስት መታወቅያ መስጠቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ብዙ ከኢትዮዽያ የተፈናቀሉ ኤርትራውያን በሻዕቢያ መታወቅያ ይሰጣቸዋል። ትክክልም ነው። ከኤርትራ የተፈናቀሉ (የተባረሩ) ኢትዮዽያውን የኢትዮዽያ መታወቅያ እንሰጥ የለም እንዴ?! የማንሰጥ ከሆነም መስጠት አለብን። ስለዚህ ተስፋዬ የኤርትራ መታወቅያ ማግኘቱ አይደንቅም። እንዳውም ተገቢ ነው። የኢትዮዽያ ፓስፖርቱ ከተነጠቀና በናይሮቢ የኤርትራ ግዝያዊ መታወቅያ ከተሰጠው በኋላ ኤርትራዊ ሁነዋል። አሁን ‘ኢትዮዽያዊ ነኝ’ ካለ ተቀባይነት የለውም። የኤርትራ ዜግነት ካገኘ ታድያ ለሀገሩ መስራቱ ምን ይደንቃል? የሻዕቢያ ሰላይ መሆኑ ምን ይደንቃል? ኤርትራዊ አይደለምን? አዎ! ለሀገሩ መስራት አለበት፤ በሚፈልገው ዘርፍ። ስለዚህ ተስፋዬ የሻዕቢያ ሰላይ ነው መባሉ አልገረመኝም። መርሳት የሌለብን ነገር አለ። በፖለቲካ ብዙ ዉጣ ዉረዶች አሉ። ብዙ የተጠላለፉ ስለያዎች አሉ። ብዙ ታዋቂ ሰዎች የታላላቅ የስለላ ድርጅቶች ቅጥረኞች የሆኑ አሉ።። በተስፋዬ ‘መጋለጥ’ የተደነቀ ሰው በነዚህ ሰዎች ስራማ ጨርቁ ሊጥል ነው። የሻዕቢያ መንግስት እንኳንስ ተስፋዬ ገብረአብን የመሰለ የህወሓት/ኢህአዴግ የዉስጥ አዋቂ፣ ታማኝ ሊሆን የሚችልና የኤርትራ ደም ያለው ምርጥ ፀሓፊ አግኝቶ ኢትዮዽያን ለመበታተን ያለው መሰሪ ተልእኮ ለማሳካት ለኢትዮዽያውያንምኮ በገንዘብና በጦር መሳርያ ይደልላል። ሻዕቢያ እንኳንስ ተስፋዬ ምርጥ የሀገሩ ልጅ ለአልሸባብም ኮ ያግዛል፤ መታወቅያ እየሰጠ እንዲሰልሉና እንዲያሸብሩ ይተባበራል። ታድያ ይሄ ምን ይደንቃል? ተስፋዬ ገብረአብ በሻዕቢያ የተላከ የሻዕብያ ቅጥረኛ ነው አላችሁኝ። በተመሳሳይ መንገድ የተላከ ስንት የሻዕቢያ ቅጥረኛ ባለስልጣን ይኖረን ይሆን? ህወሓት በራሱ ኮ የሻዕቢያ ተልእኮ ለማስፈፀም በሻዕቢያ የተቋቋመ ድርጅት ነው። ህወሓት የመሰረተው ማነው? ሻዕቢያ ነው። ሻዕቢያ መሓሪ ተኽለ (ሙሴ) የተባለ ኤርትራዊ የሻዕቢያ አባል በትግራይ ለሻዕቢያ ሊያግዝ የሚችል ድርጅት እንዲያቋቁም ወደ ኢትዮዽያ ላከ። እነዚህ ህወሓት የመሰረቱ የሚባሉ ሰባት ሰዎች አሰባስቦ እንዲደራጁ አደረገ። ስለዚህ በተስፋዬ ስራ መደነቅ የሻዕቢያ ተግባር አለማወቅ ነው። ተስፋዬ ገብረአብ ኤርትራዊ ከሆነ ከድሮ ጀምሮ ኤርትራዊ መሆን ነበረበት። መንግስት ሲፈልግ ዜግነትና ሓላፊነት የሚሰጥ ሲፈልግ (ከባለስልጣናት ሲጣላ) ደግሞ መንጠቅ የሚችል መሆን የለበትም። አሁን ‘ተጋለጠ’ የተባለውን ትክክል ከሆነ ተስፋዬ ኤርትራዊና የሻዕቢያ ሰላይ መሆኑ ግንዛቤ እንያዝ። ምክንያቱም መረጃ ጥሩ ነው። ሰላይ ስለሆነ መፃሕፍቶቹን አናነብም ግን አልልም። ምክንያቱም አንድ የሻዕቢያ ሰላይ የፃፈው ይቅርና የሲአይኤ (CIA) ስራ አስከያጅ የፃፈውም አነባለሁ። ሰይጣን የፃፈውም ካገኘሁ አነባለሁ። ጉዳዩ መሆን ያለበት አረዳዳችን ላይ ነው። ተስፋዬ ስለ ፃፈው ጥሩ ወይ መጥፎ ነገር መነጋገር እንችላለን። የተስፋዬ ሁኔታ በማጋለጥ የተስፋዬን ፅሑፍና ሓሳብ ማጥቃት ግን አይቻልም። እንዳውም ህፀፅ ነው (Ad hominem Circumstantial Fallacy)። ተስፋዬ ብዙ ግዜ የሚወቀስባት መፅሓፍ ‘የቡርቃ ዝምታ’ ነች። እኔም አልወደድኳትም። አካኪ ዘራፍ ግን አላልኩም። ምክንያቱም ተስፋዬ ሓሳብ አንስተዋል። ስህተት ከሆነ ስህተት መሆኑ በፅሑፍ ማስረዳት አለብኝ እንጂ ወደ ተስፋዬ ማንነት አልሯሯጥም። ምክንያቱም ተስፋዬ ፀሓፊ እንጂ ባለስልጣን አይደለም። ፅሑፍ ሓሳብ ነው። ስልጣን ግን ተግባር አለው። ሓሳብ ሰለማዊ ነው። ስልጣን የማስገደድ ባህሪ አለው። ሓሳብ የማሳመን ስራ እስከሆነ ድረስ የጭንቅላት ጨዋታ ነው። ስልጣን ግን በሃይል የማስፈራራት እርምጃም አለው። በሓሳብ ያለመቀበል መብታችን የተጠበቀ ነው። በስልጣን ግን ያለመቀበል መብታችን ሊጣስ ይችላል። ስለዚህ ማንኛውያም የሓሳብ ክርክር ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። ማንኛውም የስልጣን (የሃይል) እርምጃ ለመቀበል ግን አልተነሳሁም። ተስፋዬ ፀሓፊ እስከሆነ ድረስ (ኤርትራዊ ሰላይ ጭምር) አያስፈራኝም፤ ማንነቱ ስለተጋለጠም ትኩረት የምሰጠው ጉዳይ አልሆነም። ባለስልጣን ቢሆን ኑሮ ግን (አስቡት ሰላይ ሁኖ ባለስልጣን) እቃወመው ነበር። ማንነቱ በመጋለጡም ደስ ይለኝ ነበር። ለመረጃ እንዲሆን ግን ተስፋዬ ‘የቡርቃ ዝምታ’ የፃፈው የኢህአዴግ ባለስልጣንና የኢትዮዽያ ዜግነት ጨብጦ በነበረበት ግዜ ነው። መፅሓፉም ገዢዎቻችን እያጨበጨቡ አስመርቀውለታል። ስለዚህ ኢትዮዽያዊ እያለ የፃፈው ነው። ከድሮ ጀምሮ ሰላይ ነበር ካልን ሌላ ጉዳይ ነው። እኔ ደግሞ ለምን የሻዕቢያ ሰላይ የሚድያ ባለስልጣን አድርገን ሾምን? ብዬ እጠይቃለሁ። እንደሚድያ ሰዎች የተስፋዬ ማንነት ማጋለጣቸው ግን ጥሩ ነው። ምክንያቱም ግዴታቸው ተወጥቷል። በዚህ መሰረት ለተስፋዬም (ላልታወቁ ሌሎችም) ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። በፌስቡክም ቢሆን ስንት ያልተደረሰባቸው ሰላዮች ይኖራሉ። http://www.zehabesha.com/

No comments:

Post a Comment