Tuesday, October 15, 2013

ለኢሕአዴግ ካድሬዎች ማሠልጠኛ ማዕከል አራት ምክትል ዳይሬክተሮች በሚኒስትር ኤዴታ ማዕረግ ተሾሙ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢሕአዴግ ካድሬዎች ለሚሠለጥኑበት ማዕከል በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ አራት ምክትል ዳይሬክተሮች ተሾሙ፡፡ የኢሕአዴግ ማሠልጠኛ ማዕከል በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ ናቸው፡፡ ከአቶ አዲሱ ሥር አራት ክንፎችን ይዘው እንዲመሩ የተሾሙት ከኢሕአዴግ መሥራች ድርጅቶች የተወከሉ አመራሮች ናቸው፡፡ ከብአዴን አቶ ለገሰ ቱሉ፣ ከደሕዴን አቶ ወንድሙ ገዛኸኝ፣ ከሕወሓት አቶ ነጋ በርሄ ሲሆኑ፣ ከኦሕዴድ የተወከለው አመራር እስካሁን አልታወቀም፡፡ ማሠልጠኛ ማዕከሉ እስካሁን በስድስት ዙሮች በርካታ ካድሬዎችን አሠልጥኗል፡፡ እነዚህ ካድሬዎች ከሥልጠና በኋላ በመንግሥትና በፓርቲ መዋቅሮች ውስጥ በተለያዩ የአመራር ደረጃዎች ላይ ይመደባሉ፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ ሥልጠና ማዕከሉ ከሚያተኩርባቸው የሥልጠና ዘርፎች መካከል የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ የኢትዮጵያ ህዳሴና የኢሕአዴግ ታሪክ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ምንጮች ኢሕአዴግ በ2007 ዓ.ም ለሚካሄደው ምርጫና መንግሥት የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች እንዲሁም መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍኑና ሙስናን የሚዋጉ አመራሮችን ለማፍራት ዕቅድ ነድፏል ይላሉ፡፡ ይህንን ለማሳካት በአቶ አዲሱ ለገሰ በሚመራው የኢሕአዴግ ማሠልጠኛ ተቋም ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሏል፡፡ በዚህ ማሠልጠኛ ውስጥ የሚያልፉ ካድሬዎች የፓርቲያቸውን ዕቅድ የማሳካት ብቃት ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት የካድሬዎች ሥልጠናን አጠናክሮ ለመቀጠል የማሠልጠኛ ማዕከል ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ የሥልጠና ማዕከል በተጨማሪ አራት ኪሎ አካባቢ ለሚገነባው የኢሕአዴግ ዋና የፖለቲካ ማዘዣ ጣቢያ ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ግንባታ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን በርካታ የፓርቲው ደጋፊ ባለሀብቶች የገንዘብ መዋጮ ማካሄዳቸው ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment