Friday, October 18, 2013

ኤርትራን ለነጻነት ትግሉ በመጠቀሙ ላይ ትንሽ የግል ኣስተያየት

ገለታው ዘለቀginbot7-popular-force በዚህች ኣጭር ጽሁፍ ውስጥ ኤርትራን ለነጻነት ትግሉ በመጠቀሙ ዙሪያ በሚነሱ ክርክሮች ላይ የግል ኣስተያየት ለማከል እፈልጋለሁ። እንደሚታወቀው ኣመጸኛው ህወሃት ያስመረራቸው እና ለለውጥ የሚታገሉ ሃይሎች በሰላማዊ መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ዘበት ነው ብለው ኣምርረው በማመናቸው ነፍጥ ማንገባቸው ከታወቀ ውሎ ኣድሯል።Ginbot 7 Popular Force – GPF formed
እነዚህ ሃይሎች ኤርትራን እንጠቀማለን ኤርትራ የኢትዮጵያን ህዝብ ትግል ለማገዝ ከፍተኛ ፍላጎት ኣሳይታለች እያሉ ነው። ታዲያ ይሁን እንጂ ኣንዳንድ ዜጎችና የተደራጁ ሃይላት በዚህ ላይ ስጋት ኣለን በማለታቸው ሁለት ክንፍ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። በመጀመሪያ እነዚህ “በኤርትራ በኩል የሚደረግ እንቃስቃሴ ለውጥ ኣያመጣም” የሚሉ ወገኖች ከሚያነሷቸው ጉዳዩች መካከል ቀዳሚው ነገር ሻእቢያ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራት የሆኑ ድርጅቶች እንዲያብቡና ኢትዮጵያ ዴሞክራት ኣገር እንድትሆን የሚፈልግ ልብ ከየት ሊያመጣ ይችላል? ዛሬ ኤርትራና ኢትዮጵያ መጣላታቸው ብቻውን ኤርትራ የኢትዮጵያን እውነተኛ ተቃዋሚዎች ዴሞክራትና የኣንድነት ሃይሎች ለመደገፍ ሊያበቃት ይችላል ወይ? ኤርትራ ወያኔን የምር ከጠላችም ልትደግፍ የምትችለው በብሄር ላይ የተመሰረቱትን የመገንጠል ኣላማ ያላቸውን እንጂ የኢትዮጵያን ኣንድነት የሚፈልጉትን ወይም ለዚህ የሚታገሉትን ኣይሆንም:: ደሞ ሁሉም ይቅርና ኣሁን ያለው የኤርትራ ሁኔት ተቀይሩዋል ከተባለ እየታገልን እያለ መሃል ላይ ድንገት ሃሳቧን ብትቀይርስ? ወይም ከወያኔ ጋር ቢታረቁስ? በትግል ላይ እያለን ሳንዱች መሆናችን ኣይደለም ወይ? ሪስኩ በዛ:: ሌላው ቀርቶ ኣሁን በቅርቡ እንኳን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ከኢትዮጵያ መብራት ልንገዛ እንችላለን ኣሉ ሲባል በቃ ታረቁ ማለት ነው? ብሎ የደነገጠ ኣለ። እነዚህን የመሳሰሉ ስጋቶች ባንድ ጎራ ሰፍሯል። በሌላ ጎራ ያለው ወገን ደግሞ መሬት ላይ ያለው ነገር ተቀይሯል:: ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ ኣይታደርም:: ሪስክ መውሰድ ኣለብን:: ኤርትራ እኛን ልትደግፍ የሚያስችላት መሰረታዊ ነገር ብዙ ኣለ። ከነዚህም ውስጥ ለራሷ ሪጂናል ሰኪዩሪቲ የኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ ነው። የኣሰብ ጉዳይም ቢሆን ወያኔ በፈጠረው ችግር ምክንያት የግመል ማጠጫ ነው የሆነው። ከዚህም በላይ እነዚህ ህዝቦች ከጊዜው ፖለቲካ በላይ የሆነ ትስስር ያላቸው ህዝቦች በመሆናቸው ኢትዮጵያ የኤርትራን ፈጽሞ መጥፋት ኤርትራ የኢትዮጵያን ፈጽሞ መጥፋት የሚመኛኙ ኣይደሉም። ሌላው ደግሞ የኛ የተቃዋሚዎች በዚህ ኣካባቢ መኖር ከወያኔ መጥፋት በሁዋላ ለሚኖረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ከፍተኛ የሆነ ኣዎንታዊ ሚና ይጫወታል የሚሉት ዋና ዋናዎቹ መከራከሪያዎች ናቸው። እነዚህ ወገኖች ከሌላው ጎራ የሚቀርብባቸውን ፍርሃትም የሚከላከሉበት ኣንዱ ነገር ደሞ እስከዛሬ ድረስ በኤርትራ በኩል የነበሩ ተቃዋሚዎች ፍሬ ያላፈሩት በራሳቸው ችግር እንጂ በኤርትራ በኩል ባለ ችግር ኣይደለም ይላሉ። ኤርትራ ተቃዋሚዎችን እያስጠጋች እዚያው እንዲያረጁ ታደርጋለች እንጂ ለውጤት እንድንበቃ ኣትፈልግም የሚሉትን ወገኖች ለማሳመን። ኣስተያየት በሃገራችን ውስጥ ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ኣለ ብየ ኣላምንም። በርግጥ ግን ፖለቲካዊ ጽንፈኝነት ኣለ። ይህ ፖለቲካዊ ጽንፈኝነት ደሞ ያለው በገዢው መንግስትና በተቃዋሚው መካከል ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚውና በተቃዋሚው መካከልም ይታያል። ከጽንፈኝነታችን መሰረቶች ኣብዛኞቹ በግልጽ ተነጋግሮ መረዳዳትን (understanding each other) ካለማስቀደም የመጡ ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ኤርትራን ለነጻነት ትግል መጠቀም ለምን የሬዲዮና የቴሌቪዥን ዜና እንደሆነ ኣልገባኝም። በመሰረቱ የማሰልጠኛ ቦታና እርዳታ የምናገኝባቸውን ምንጮች በነጻነት ትግል ጊዜ በሚስጥር የምንይዛቸው ጉዳዮች ይመስሉኝ ነበር። ወያኔ ኣፍጦ እያየ በኤርትራ በኩል ገባን የለም ኣትግቡ መባባሉ መርሆዎቹን የጣሰ ነው ባይ ነኝ።ዋናው ነገር ግን እነዚህ ኤርትራን መጠቀም የለብንም የሚሉ ወገኖች ኤርትራን መጠቀም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ኣይተነዋል ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይልም ይሁን ሌሎች ከኤርትራ ድጋፍ እያገኘን ነው የሚሉ ወገኖች ኤርትራን እንጠቀማለን ሲሉ ከኤርትራ መንግስት የሎጂስቲክስ ድጋፍና የማሰልጠኛ ስፍራ ተሰጠን ማለታቸው ይመስለኛል።ኤርትራን መጠቀም የሚባለውም ነገር በዚህ ታጥሮ መታየት ያለበት ይመስለኛል።ይሄ ደሞ በራሱ ፍጻሜ ሆኖ ለክርክር የሚበቃ ኣሳብ ኣይመስለኝም። በመጀመሪያ ደረጃ ግንቦት ሰባትም ሆነ ሌሎቹ ድርጅቶች እንደ ድርጅት ይህንን ርዳታ የመቀበል መብት ኣላቸው። ያስፈልጋቸውማል። ምናልባት በሌላው ወገን ዘንድ ስጋት የፈጠረው የኤርትራን መንግስት የድጋፍ ኣይነት በደንብ ለይቶ ካለማጤን ጋር ተደበላልቆ የመጣ ችግር ሊሆን ይችላል። በመሰረቱ ግንቦት ሰባትም ሆነ ሌላው ኣካል ኤርትራን እጠቀማለሁ ሲል በነጻነት ትግሉ ጊዜ ጦርነት ሲጀምር ግንቦት ሰባት ከወዲህ ማዶ ሆኖ የ ኤርትራን ድንበር ይዞ ወዲያ ማዶ ዛላምበሳ ካለ የወያኔ ሰራዊት ጋር ኣይደለም የሚዋጋው። ኤርትራም ሉኣላዊት ኣገር በመሆኗ እንዲህ ኣይነት ስምምነት ውስጥ ከተቃዋሚዎች ጋር ኣትገባም። ተቃዋሚዎች ያኔ ለባድመ ጦርነት ጊዜ ሻእቢያ የቆፈረውን ምሽግ ይዘው ኤርትራ ድንበር ላይ ሆነው ኣይደለም የሚዋጉት። እነዚህ ተቃዋሚዎች ስልጠናና ሎጂስቲክስ ያግኙ እንጂ ወታደራዊ ንቅናቄውን የሚያደርጉት በኢትዮጵያ መሬት ላይ ሰርገው ገብተው ነጻ በሚያደርጉት ኣካባቢ ነው። ጎንደር ውስጥ ሊሆን ይችላል፣ ትግራይ ውስጥ ሊሆን ይችላል፣ ወይ ካንድ በላይ የሆኑ ቦታዎች ሊሆን ይችላል ኣሁን ኣናውቅም። ትግሉን የሚመሩትም ራሳቸው የድርጅቱ መሪዎች እንጂ ኤርትራዊያን ጀነራሎች ሊሆኑ ኣይችልም። ኤርትራ ድጋፍ ሰጠች ማለት ድንበሩዋን ተዋጉበት ፈንጩበት ለወታደራዊ ስልት ወደሁዋላ ማፈግፈግ ስትፈልጉ በ ኤርትራ መሬት ላይ ተዋጉ ቀጥሉ ማለት ኣይደለም። በዚያ ቀጣና ጦርነት ከተጀመረ ወያኔ የድንበር ውጊያ ኣድርጎት እንደባለፈው ወደ ኤርትራ ግዛት ሁሉ ዘልቆ ሊገባም ኤርትራ ኣትፈልግም። ምን ኣልባት ኤርትራ ራሱዋ ወያኔን መውጋት ከፈለገች ተቃዋሚዎች ኣብረው በዚያ ሊሰለፉ ይችላሉ። ይህ ካልሆነ ግን የተቃዋሚዎች ድጋፍ በኤርትራ ሊተረጎም የሚችለው የሎጂስቲክስና የስልጠና ቦታዎችን በመፍቀድ የታጠረ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ተቃዋሚዎችን እዚያ ኣትሰልጥኑ የሚለው ነገር ለክርክርም የማይበቃ ነው ብለናል። ተቃዋሚዎች የሚያሰለጥኑትን እያሰለጠኑ ወደ ነጻ መሬታቸው ይልካሉ እንጂ ዝም ብለው ሲደምሩ ኣይኖሩም። እንዴውም ትንሽ ውሎ ሲያድር ተራ ወታደሮች የሚሰለጥኑት ከመንግስት እይታ ውጭ በሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ በረሃዎች ውስጥ ነው። ራሱ ሻእቢያ የመሸገው ኣልጀሪያ ወይም ሊቢያ ሳይሆን ናቅፋ ላይ ነበር። ናቅፋ ሸሽቶ ማምለጫው፣ ናቅፋ ሊሞትላት የቆረጠባት ነጻ ምድሩ ነበረች። ወያኔዎችም ቢሆኑ ሰባት ሆነው ደደቢት በረሃ ነው የገቡት። ስልጠናው የትም ይሁን የት ግንቦት ሰባትም ሆነ ሌላ ተቃዋሚ ሃይል ሊጠየቅ የሚገባው ከኤርትራ ርዳታ ትቀበላለህ ኣትቀበልም ሳይሆን “ናቅፋ” መስርተሃል ወይ? “ደደቢት” ገብተሃል ወይ? ነው። በዚህ ደረጃ ደጋፊዎች ይህንን ኣጥብቀው ቢጠይቁ ፍሬ ያለው ሲሆን ከዚያ ውጭ ግን ውሃ ኣይቋጥርም። ኣሁን ያሉት ማሰልጠኛ ተቋማቱ ደግሞ የግድ ኣንድ ሃገር ብቻ መሆን የለባቸውም። ጎረቤት ኣዋሳኝ ኣገር ባይሆኑም ችግር የለም። በተለያዩ ኣገሮች የስልጠና ጣቢያ መኖሩና በኢትዮጵያ መሬት ላይ ነጻ መሬት መኖሩ ሪስኮችን ይቀንሳል። ለምሳሌ የዚምባብዌው የነጻነት ታግይ ድርጅት (Zimbabwe African National Union – Patriotic Front (ZANU–PF) ) በነጻነት ትግሉ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስቱ ሃይለማርያም የሎጂስቲክስና የስልጠናዎችን ድጋፍ ይሰጠው ነበር። ኣዋሳኝ ኣገር ባትሆንም ንቅናቄው ዳረሰላም ታንዛንያ ውስጥ ብዙ ነገር ይሰራ ነበር። በመሆኑም ግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይልም ይሁን ሌሎቹ ሃይላት እንዲሁ የኣካባቢ ኣገሮችን በማሳመን በምስጢር የማሰልጠኛ ጣቢያዎችን መክፈት፣ ድጋፎችን ከሁሉም ኣቅጣጫ መቀበል ተገቢ ነው። የለም እኛ ከኤርትራ ውጭ ሌላ ሃገር ኣካባቢ እንቅስቃሴ ኣናደርግም ካልን ከፖለቲካው ነባራዊ ኣለም ልንወጣ ስለምንችል በደጋፊዎች ዘንድ ጥርጣሬን ያሰፋል።ሪስክ የሌለው የፖለቲክ እንቅስቃሴ ስለሌለና በዚህ ደረጃ ሪስክ መውሰድ በተለይ ከትግሉ ክብደትም ኣንጻር ተገቢ ኣይደለም። ለተቃዋሚ ሃይላት ኢትዮጵያ ውስጥ የምትገኝ “ናቅፋን” ለመቆጣጠር በጣም ብዙ መሆን ላይኖርባቸው ይችላል።እንዳጋጣሚ ሆኖ ተውልጄ ያደኩበት ኣካባቢ ብዙ ጊዜ ጦርነት የተካሄደበት ኣካባቢ ነበር። ኣጼ ሃይለ ስለሴ ከስልጣን ከወረዱና ደርግ ስልጣኑን ከያዘ በሁዋላ የራስ ብሩ ወልደገብርኤል ልጆች መርዕድ ብሩና መስፍን ብሩ ደርግን ይቃወሙና እምቢኝ ብለው ወደ ኣባታቸው የትውልድ ቦታ ወደ መንዝ ልዩ ስሟ ባዶጌ ቀበሌ ይመጣሉ። በዚያም የባዶጌን፣ የላምበርን፣ የሾላንና ሌሎች ኣጎራባች ቀበሌ ገበሬዎች ኣሳምነው ነፍጥ ኣነሱ። ብዙ ህዝብም ተቀብሏቸው ነበር። በወቅቱ ግን ገበሬዎቹ የነበራቸው መሳሪያ እናት ኣልቤን፣ ምንሽር፣ ቤልጂግ፣ ዲሞትፌርና ሰነኔ ነበር። ደርግ ይህን ያመጸ ህዝብ “ሽፍቶች” ብሎ ይጠራቸው የነበረ ሲሆን እነዚህ ኣማጽያን እንደ ናቅፋ የተቆናጠጡዋቸው ቦታዎች ባዶጌ ርጎጎ ቆላንና ኣፍቀራ ቆላን ነበር። ደርግ እነዚህን ኣማጽያን ለመደምሰስ ከኣንስተኛ ሰራዊት እስከ ብርጌዶች ኣስልፎ ብዙ ጊዜ ተሸነፈ። ገበሬዎቹም የያዙት ስትራተጂካዊ ቦታ እያገዛቸው ተዋግተው የማረኩዋቸው ብዙ መሳሪያዎች የመትረየስ፣ የቦንብ፣ የክላሽና የመሳሰሉት መሳሪያዎች ባለቤት ኣደረጋቸው። ሁዋላ ላይ መርዕድና መስፍን ብዙም ሳይቆዩ ኣፍቀራ ላይ ቢሞቱም ኣጠቃላይ ኣመጹ ግን ኣምስት ኣመት ቆየ። በየጊዜው ደርግ ሰራዊቱን ያመጣል ባዶ መኪና ይመለሳል። እንዲህ ተብሎ ተዘፈነ “የደርጉ መኪና ሸራ የለበሰው ያን ሁሉ ወታደር ወዴት ኣደረሰው” ሁዋላ ላይ ግን ደርጉ በተዋጊ ጀቶችም ታግዞ ብዙ ወታደር ካለቀ በሁዋላ ኣማጽያኑ ተደመሰሱ። እርጎጎ ቆላን “ናቅፋቸውን” ማለቴ ነው የጠቆመውና እነ ኣስፋው እሸቴን ያስገደለው የራሳቸው ኣሸከር የነበረ ነው። ምን ኣልባትም እሱ ባይመራና ባያስገድላቸው ትግሉ ይቀጥል ነበር። እነዚህን ገበሬዎች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚመራቸው፣ ጥያቄያቸውን ወግ ኣስይዞ የሚያደራጃቸው ኣጥተው እንጂ የቆረጡ እንደነበር ሁዋላ ላይ ደርግ ይዙዋቸው ለብዙ ኣመታት ናዝሬትና ኣዲስ ኣበባ ኣለም በቃኝ ታስረው በምህረት ከተለቀቁት ጥቂት ሰዎችን ኣነጋግሬ ታሪካቸውን መማር ችያለሁ። ። ሲያጫውቱኝ ኣስደምመውኛል።ከውጭ ርዳታ ሊመጣልን ይችላል ብለው ሁሉ ተስፋ ኣድርገው ነበር። ነገር ግን ትግላቸው ከዚያ ኣካባቢ እንዲያልፍ የሚረዳቸው የተማረ ሰው ባለመኖሩ ኣምስት ኣመት ሙሉ ብቻቸውን ደከሙ። ይህን ያመጣሁበት ዋና ነገር በነጻነት ትግል ጊዜ ኣንድ ነጻ ኣውጪ ሊጠየቅና ሊገመገም የሚገባው የት እየሰለጠንክ ነው? ምናምን ሳይሆን የተቆናጠጥቃት መሬት ኣለች ወይ? ነው።ኣገርቤት ለሚደረገውም ትግል ደጀን የሚሆነው ሮጦ ማምለጫ ነጻ መሬት ሲኖር ነው። በዚህ ደረጃ ነው መወያየትና መከራከር ያለብን እንጂ በድጋፍ ዙሪያ ኣይመስለኝም። እንዲህ ኣይነቱ ውይይት የሚመጣው ራሱ ከጥገኝነት ስሜት ነው። ኤርትራ እንዳስጠጋችን የነጻነት ትግሉ በሱዋ ርዳታ ላይ ተንጠልጥሎ መታየት የለበትም። በዙሪያው ባሉ ሃገራትም ላይ የተጠጋ ኣይደለም ትግሉ። እዚያው ሃገር ቤት የሚቆናጠጠውን መሬት የሚያስፋፋ ነው መሆን ያለበት። ኤርትራን ኣማራጭ የሌለው የትጥቅ ትግል ማድረግ ኣስፈላጊም ኣይደለም:: ኤርትራም ከኔ ውጭ ሌላ ቦታ ርዳታ ከፈለጋችሁ ኣልረዳም ካለች ችግር ኣለ ማለት ነው። ነገር ግን ይህ ኣልሆነም። በኣሁኑ ሰዓት የምንሰማው ኤርትራ እህት ኣገሩዋን ኢትዮጵያን ነጻ ለሚያወጡ ሃይላት ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት ቆርጣለች።ለማናቸውም ኣሁን ኣሁን ኣገር ቤት ያለው ህዝባዊ ኣመጽም እየበረታ ስለሆነ ለውጦች በኣጭር ጊዜ መጥተው ሊያሳርፉን እንደሚችሉ ተስፋ እናደርጋለን። እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

No comments:

Post a Comment