Wednesday, October 23, 2013

ህወሓት ኢህአዴግ ለምን ግን በልጆቼ ላይ ዘመተ?

October 23, 2013 የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ልጄ ክብሮም አስገደ እንደ ወንድሞቹ የእስር ሰለባ ሆነ፡፡ እኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ፉጹም ወዳጅ እንጂ ጠላት አይደለሁም። መጀመርያ ደርግን 17 ኣመት በመታገል ፋሽሽታዊ ሥርዓትን በማስውግድ ኣስተዋፅኦ ነበረኝ። ህውሃት ኢህኣደግ ስልጣን ከያዘ በኋላም ለኑሮየ፣ ለደሞወዝ ሳላስብ 17 ኣመት ሙሉ የታገልኩለት ኣላማ ስለተቀለበሰ በተጨማሪ የህውሓት መሪዎች ለኢትዮጵያ ሉኣላዊነትና ኣንድነት ታማኝነት ስላጎደሉ የኢትዮጵያ ሕገመንግስት በሚፈቅደው መሰረት በግልም በፓርቲ ተደራጅቼ እየታገልኩ ቆይቼ ኣሁንም እታገላለሁ። ታድያ እኔ በሃገራችን ህገመንግስት በሚፈቅድልኝ መሰረት መታገሌ እንደ ሃጠያት ተቆጥሮ የቂም በቀል ፖለቲካ ሰለባነቱ ከኔ አልፎ ወደ ልጆቼ ወርዷል። የማነ ኣስገደ ልጄ ምንም ሳይፈፅም በገጠር ቤተሰብ ለመጠየቅ ሄዶ ታስሮ ብዙ ግፍ ተፈፅሞበታል። በተፈፀመበት ግፍ ጠንቅ ታሞ እናቱ የመከላክያ ኣባል ስለሆነች በመከላክያ ሚኒስተር ሆስፒታል ብዙ ጥረት ተደርጎ ሊያድኑት ስላልቻሉ ወደ መቀሌ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ከስልጣን በላይ ብለዉት ሂወቱ ተርፎ ኣሁንም በቤቱ የኣልጋ ቁራኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ በተማረው መሰረት ለሃገሩ እንዳያገለግልም እንደማይሰራ ኣካል ጉዳተኛ ኣድርገዉታል። ወደ ውጪ ወስድን እንዳናሳክመው ኣቅም የለም፡፡ ኣሕፈሮም ኣስገደ ልጄም ከስራ ገብታው ኣፍነው ወስደው እነሆ በፖሊስ ጣብያ አስረውት ክስ ሳይመሰረትበት ከ6ወር በኋላ በቀዳማይ ወያኔ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎት ከ 15 ጊዜ በላይ ቀጠሮ ጊዜ እየተባለ ሲመላለስ ከርሞ በመጨረሻ ክሱ የዋስ መብት የሚከልክለው የፀረ ሙስና ኣንቀፅን ይመለከታል አሉ። በሙስና የተከሰሰ የዋስ መብት ኣይፈቅድም በሚል ሽፋን ልጄን ከእስር ቤት ነፃ ላለመልቀቅ ክሱ ወደ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በማዞር፤ የፀረ ሙስና ጉዳይ ደግሞ በወረዳ ስለማይታይ 6 ወር ሙሉ ሲያንገላቱት ከርመው ክሱ በመቀሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደ ኣዲስ ተመስርቶ በ 28/1/2006 ዓ.ም በዞኑ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ደግሞ ሌላ ተጠርጣሪ ስላለና ስለታጣ በጋዜጣ ኣሳውጀን እስከ ምንፈልግ ኣሕፈሮም በወህኒ ቤት ይግባ በማለቱ ልጄ ያለ ፍርድ በወህኒ ቤት ተወርውሮ ይገኛል የጊዜ ቀጠሮ እየተባለ 7 ወሩ በስቃይ ይገኛል፡፡ ሌላ ያሁኑ ይባስ። ክብሮም ኣስገደ የሚባል የ10ኛ ክፍል ተማሪ የስብእና መሳት ስነ ኣእምሮ ችግር ያለው ይህም በሃኪም ክትትል ላይ ያለ በፍርድ ቤትም ታይቶ ያደረ አስረውቷል። ኳስ ሜዳ እየተጫወተ እንዳለ ፖሊሶች መጥተው ወሰዱት። በኣንድ ጨለማ ቤት ለብቻው ኣስረው ከወላጆቹ ከሃይማኖት ኣባት፣ ከህግ ኣማካሪ እንዳይገናኝ ኣድርገው ኣፍነዉት ይገኛሉ። የምንሰጠው ምግብ ለማን እንደሚሰጥ ኣናውቅም። ለፍትህ ቢሮ ፖሊስ ኣዛዞች ኣመለከትን ፍትህ ኣልተገኘም። ዳኛ እንድያገናኙን በስልክ ነግሮዋቸው ፖሊሶች ኣልተቀበሉትም። ኣሁን ከ80 ሰኣት በላይ ታስሮ ቤተሰብ ልናገኘው ኣልቻልንም። ይህ ዘመቻ በእኔ የጀመረው ልጆቼም የግፍ ሰለባ ሆነዋል። የኔ ጉዳይም የህወሓት የ17 ኣመት ታሪክ በመፃፌ፣ ከኣንድ ዜግነቱ ኣሜሪካዊ ትውልድ ኢትዮጵያዊ በሰዎች የተቀናበረ ሴራ ተከስሼ 3 ኣመት ባስቆጠረ ክስ ላይ ነኝ ገና መቋጫ ኣላገኘም፡፡ ይህ ጉዳይ የእኔና የልጆቼ ብቻ ችግር ኣይደለም ብዙ የሚናገርላቸው ያጡ ዜጎች በስቃይ ላይ ይገኛሉ ስለሆነ ሁሉም ዜጎችና ለፍትህና ለዲሞክራሲ ለሰብኣዊ መብት የምትታገሉ ያላችሁ ተቃዋሚ ሃይሎችም ዝምታ ከመምረጥ ብትነጋገሩበትና ብትቃወሙት ጥሪየን ኣቀርባለው፡፡ በተለይ በኣሁኑ ጊዜ ኣንዳንድ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች የታሰረው ልጄ ኣሕፈሮም ኣስገደ ከታሰረበት ድረስ በመሄድ ・ኣባትህ ኣስገደ ተው ኣርፈህ ተቀመጥ፣ ትእግስት ኣድርግ በለው!・ እያሉ እስከማስፈራራት ድረስ ሄደዋል። ለዚሁ አንደ ምሳሌ ኮማንደር ገ/ሂወት ካሕሳይ የመቀሌ ከተማ ፖሊስ ዋና ኣዛዠ ይጠቀሳል። በዛ በሰጠው ማስፈራርያ ታድያ ልጄ ኣሕፈሮም በትልቅ ስጋት ላይ ይገኛል ታድያ ከዝሂች ኣገር ኣገሬ የት ልሂድ ንፁህ ዜጋ ነኝ እና በዚህች ኣገር የዳኝነት እና የህግ የበላይነት መረጋገጥ ኣለበት ወተደራዊ ኣገዛዝ እንዳይደገም እንጠንቀቅ ፡፡ እባካችሁ የቂም በቀል ፖለቲካ ለልጆቻችን ኣናውርሳቸው ሰላም ፍትህን ዲሞክራሲን እናውርሳቸው፡፡

No comments:

Post a Comment