Wednesday, October 23, 2013

‹‹ፈሪ›› መንግሥት ,,

‹‹መንግሥት ፈርቷል ብላችሁ ራሳችሁን አታሞኙ፡፡ መንግሥታችን አይፈራም፡፡ የሕዝብ መንግሥት ነው፤›› ይህንን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ፈሪ አይደለም›› በሚለው በዚሁ ዓረፍተ ነገር የቋጩት ንግግራቸው፣ በፓርላማ ብቸኛው ተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ላቀረቡት የሞሽን ሐሳብ የተቃውሞ ምላሽ ሲሰጡ ነበር፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ለ12 ዓመታት ከቆዩበት ሥልጣን ለቀው በአዲስ ፕሬዚዳንት ተተክተዋል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አምባሳደር ሙላቱ ተሾመ ለረዥም ጊዜ ዲፕሎማት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ከመሆናቸውም በላይ፣ መንግሥት የተለየ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቁርኝነት ካለው ከቻይና መንግሥት ጋር የጠበቀ ቅርበት ያላቸው ናቸው፡፡ የቻይንኛ ቋንቋ ሳይቀር መናገራቸው ለዚህ በምሳሌነት እያቀረበ ነው፡፡ ምናልባትም ከቀድሞው ፕሬዚዳንት በተለየ ሁኔታ ሕገ መንግሥቱ ለዚሁ ቦታ ከሰጠው እዚህ ግባ የማይባል ሥልጣን ውጪ ‹‹በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ›› ሥራ እንዲያገለግሉ በመንግሥት እየተጠበቁ ነው፡፡ በበዓለ ሲመታቸው የመንግሥትን የዘንድሮን አቅጣጫ ጠቋሚ የሆነ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ያደረጉት ንግግር በቀጥታ በመንግሥት ሚዲያ የተላለፈ ሲሆን፣ አድማጩ ሕዝብ አንድ ለየት የለ ነገር ጠብቆ የነበረ ይመስላል፡፡ ራሱን አውራ ፓርቲ ብሎ እስከመጥራት ያደረሰው ኢሕአዴግ፣ 99.6 በመቶ የተቆጣጠረው ፓርላማ በመጠኑም ቢሆን ሚዛን ሊያስጠብቅ ይችላል ያለውን ገለልተኛ የሆነ ሰው ቦታው ላይ ይቀመጣል የሚል ተስፋ ነበር፡፡ ዳሩ ግን አልሆነም፡፡ ፍርኃት አንድ – ገለልተኛ ፕሬዚዳንት የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የአቶ ግርማ ሰይፉ ምልልስ መነሻው የሆነው የአዲሱ ፕሬዚዳንት የዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ንግግር ነው፡፡ መንግሥት ለውጥን ይፈራል ወይስ አይፈራም የሚለውን ከማየት በፊት አንድ ጉዳይ መነሳት አለበት፡፡ በአዲሱ ፕሬዚዳንት አመራረጥና ምንነት ዙሪያ ከጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያ ጋር በቅርቡ ቃለ ምልልስ ያደረጉት የሕግ ባለሙያው ዶ/ር ለማ ይፍራሸዋ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሚመሳሰል የመንግሥት መዋቅር ያላቸው አገሮች ፕሬዚዳንት የሚመርጡት አሳታፊ በሆነና ግልጽነት ባለው መንገድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ቦታ የሚመጥኑት በአገሪቱ በማስታረቅ የታወቁ፣ የአባታዊነት ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ፣ በፓርቲዎች መካከልም ሆነ በብሔረሰቦች ወይም ደግሞ በሃይማኖቶች መካከል አንድ ግጭት ቢፈጠር የማስታረቅ ሚና የሚኖራቸው ሉዓላዊ የሆነ የአገር ክብር ተምሳሌት ናቸው ብለዋል፡፡ በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፣ በዚሁ የሥልጣን ዘመናቸው አንድም ቀን ተገቢውን ሚና መጫወት የሚችሉበት ነፃነት እንዳልነበራቸው አምነዋል፡፡ የሚሠሩትም ሥራ ሙሉ በሙሉ የገዢው ፓርቲ ፖለቲካ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶም ሆኑ ዶ/ር ለማ በአንድ ጉዳይ ላይ ተማምነዋል፡፡ ላለፉት 12 ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስም፣ ሕዝብንና አገርን ከፓርቲ አስተሳሰብ ውጪና ሉዓላዊ ሆነው የአባታዊነት ሚና የተጫወቱበት ጊዜ የለም የሚለው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ግልጽ የሆነ የምርጫ አሸናፊነት የሚያስገኝ የሕዝብ ድምፅ ባላገኙበት ወቅት ፓርቲዎች ፓርላማውን የመበተን፣ ጥምር መንግሥት የመፍጠር ወይም ዳግሞ ምርጫ እንዲካሄድ የማወጅ ሥልጣን ተጠቅመው አያውቁም፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ግልጽ አሸናፊ ሆኖ ባልታየበት ወቅት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሚናቸውን አልተጫወቱም በማለት አስረድተዋል፡፡ በኦርቶዶክስ ሃይማኖትና በእስልምና እምነት አማኞች መካከል ግጭትና ቀውስ በተከሰተ ወቅትም አንድም የማስታረቅ ሚና አልሞከሩም፡፡ ይልቁንም በሁለቱም አጋጣሚዎች መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ችግሩን አወሳስቦታል የሚል በስፋት የሚቀርብ ትችት አለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተለየ አቅጣጫ እየተከተሉ ይመስላሉ፡፡ በተለይ ደግሞ አዳዲስ የሥልጣን ማዕከላትን በመፍጠርና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን የማካፈል ሥራ እየሠሩ ነው ተብሎ ይታመንባቸዋል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ቀደም ሲል የተጠቀሱ የአባታዊነትና የአስታራቂነት ሥራ እንዲሠራ የሚያስችል ገለልተኛ አካል ያመጣሉ ተብለው በብዙዎች ሲጠበቁ፣ ኢሕአዴግ ላለፉት በርካታ ዓመታት የኢሕአዴግን አስተሳሰብ ሲያራምዱ የቆዩ ፖለቲከኛ ወይም ዲፕሎማት ወደ ፕሬዚዳንትነት አምጥቷል፡፡ ኢሕአዴግ በፓርላማ ያልተሳካለት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የመገንባት ጉዳይ ሚዛን ሊጠበቅለት ይችል የነበረው ይኼው የፕሬዚዳንትነት ቦታ ብቻ እንደነበር ይነገራል፡፡ ኃላፊነት ከሚሰማው ተቃዋሚ መሪ አለበለዚያም በሕዝብ ተቀባይነት ያተረፈ የመሸምገልና የማስታረቅ ሥራ ሊሠራ የሚችል የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ ታዋቂ ግለሰብ የማስቀመጥ ዕድል አምልጧል የሚሉም አሉ፡፡ ይህም ብዙዎች የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ በኢሕአዴግ በካድሬነት ያላገለገለን ሰው ያለማመንና መጠራጠር የፈጠረው ሥጋትና ፍርኃት መነሻ ይመስላል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ የአገር መሪነታቸው ምናልባት አዲሱ ፕሬዚዳንት በመሰየሙ ላይ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው፣ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚለይ በገለልተኝነትና በአገር አባትነት ርዕሰ ብሔር የሚመራ አገር የመፍጠር ዕድል አልተጠቀሙበትም የሚሉም አሉ፡፡ ይህ ብዙዎች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የአገር ሽማግሌዎች የማይሳተፉበት ግልጽነት የጎደለው ምንም ዓይነት የዕጩዎች ውድድር የማይታይበት ድንገተኛ ሹመት ምክንያት፣ ሕዝቡ ከጠረጠራቸው ሰዎች ውጪ አዲስ ሰው ሊያስቀምጥ ችሏል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለፕሬዚዳንትነት በቂ ሥልጣን አለመስጠቱ ተደምሮ፣ አሰያየሙና የኢሕአዴግ ብቸኛ ሹመት መምሰሉ በሕዝብ ዘንድ ብዙም ቀልብ የማይስብ ሹመት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ የኢሕአዴግ ‹‹ገለልተኛ›› ፕሬዚዳንትን ከመፍራት የመነጨ አያስብልም? የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ሌሎች አገሮች ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ብቃት ያላቸው መርጠው ሚኒስትር አድርገው ሲሾሙ፣ ኢሕአዴግ ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ ርዕሰ ብሔር ለመሰየም ድፍረት ያጣ ይመስላል በማለት ትችቶች ይቀርባሉ፡፡ ፍርኃት ሁለት – ድርድርና ጥምር መንግሥት ኢሕአዴግ ከወታደራዊ መንግሥት በኃይል ሥልጣን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ፣ አራት አገር አቀፍ ምርጫዎች አካሂዷል፡፡ በተለይ የ1997ቱ ምርጫ ጥንካሬው የተፈተሸበት ሲሆን፣ በገዢው ፓርቲ ግትርነትና በተቃዋሚዎች አለመብሰል ምክንያት አገሪቱ ወደማያባራ ብሔራዊ ቀውስ በመግባት ላይ ነበረች፡፡ በወቅቱ ከተለያዩ የፖለቲካ ጠበብቶችና ከዓለም አቀፍ መንግሥታት የቀረበው ሐሳብ የጥምር መንሥት የመመሥረት ወይም የሥልጣን መከፋፈል ጥያቄ ሲሆን፣ ኢሕአዴግ የመደራደር መንፈስ አላሳየም፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ የሕዝብ ተሰሚነት አግኝተው የማይናቅ ቁጥር ያለው የፓርላማ ወንበር ያገኙ ተቃዋሚዎች መንግሥትን ለመመሥረት የሚያስችል ቁጥር ባያገኙም የሚሊዮኖች ድምፅ ድጋፍ ያገኙ ነበሩ፡፡ ያም ሆኖ በሁለቱ ወገኖች መካከል የነበረው ግንኙነት የተበላሸ በመሆኑ ችግሩ መፍትሔ አላገኘም፡፡ እንደ ኬንያና እንደ ዙምባቡዌ በሕዝቦች መካከል ደም መፋሰስ ባያጋጥምም፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ከእነሱ ጋር ተመሳሳይነት ነበረው፡፡ በኬንያ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙአይ ኪባኪ ፓርቲና የኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ከሆኑት ከራይላ ኦዲንጋ ጋር በተደረገው ድርድር ጥምር መንግሥት መፍጠር ችለዋል፡፡ ቀጥለውም ሕገ መንግሥታቸውን በሕዝብ ውሳኔ ማሻሻል ችለዋል፡፡ በተለይ በፕሬዚዳንቱና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል የነበረውን ሥልጣን ማጥበብ ተችሏል፡፡ ይህ በአገሪቱ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭትና መቃቃር በወሳኝ ሁኔታ ማስቀረቱን የሚነገር ሲሆን፣ በዚሁም መልካም መገለጫ ባለፈው ምርጫ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ፉክክር የታየበትና የኬንያውያን የዲሞክራሲ ፍላጎት በዘላቂነት የቀጠለ ሆኖ አልፏል፡፡ ሁለተኛ በዚምባብዌ በፕሬዚዳንት ሙጋቤና በተቃዋሚው መሪ ሞርጋን ሻንጋራይ መካከል በተፈጠረው ቀውስ በድርድር ጥምር መንግሥት ፈጥረው አገሪቱ በዲሞክራሲ ወደኋላ እንዳትመለስ አድርጓል፡፡ በኬንያ ፕሬዚዳንት ሙአይ ኪባኪ ራሳቸውን ከምርጫው በማግለላቸው ምክንያት፣ ተቃዋሚ የነበሩትን ኡሁሩ ኬንያታ ሕዝቡ አዲስ ፕሬዚዳንት አድርጎ ሲመርጥ በዚምባብዌ ፕሬዚዳንቱ አሁንም አሸናፊ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በሁለቱም አገሮች የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ በምርጫ የተነሳ ሆኖ ከኢትዮጵያው ጋር ተመሳሳይ መልክ የነበረው ነው፡፡ ምርጫውን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሆነው ግን በሁለቱም አገሮች ከሆነው በተቃራኒ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የተቃዋሚ አመራሮች ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ቆይተው በይቅርታ ሲወጡ (……. አንዳንዶቹ የካዱት ቢሆንም) ፓርላማ ሳይገቡ በመቅረትቸው ፓርላማው የብዙኃን ድምፅ የሚንሸራሸርበት አልሆነም፡፡ ቀጥሎ በ2002 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫም ተቃዋሚዎች እጅግ በመዳከማቸው አሊያም ሕዝቡ ተስፋ በመቁረጡ ምክንያት ኢሕአዴግ መጀመርያ ሥልጣን ከያዘባቸው ዓመታትም በባሰ 99.6 በመቶ ፓርላማውን ሊቆጣጠር በቅቷል፡፡ ተቃዋሚዎች የተዳከሙት በመሪዎቹ የትግል ፅናት ማነስ ምክንያት ብቻ እንዳልሆነ ብዙ ጊዜ ተነግሯል፡፡ መንግሥት ለተቃዋሚዎች ክፍተት ፈጥረዋል ያላቸው የዳያስፖራ፣ የግል ሚዲያና የሲቪክ ማኅበረሰቦች ድጋፍ እንዳያገኙ በማድረግ ፖለቲካውን በሕግ የማያፈናፍን በማድረጉ መሆኑም ብዙ ተብሎበታል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተቃዋሚዎች ደጋፊ ወጣቶችም በመንግሥት ሀብት ጥቅማ ጥቅም ደልሎ፣ አባል በማድረግና ለተቃዋሚዎች ቦታ በመስጠት ነው ብለው ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ስለዚህም መንግሥት ድርድርና ጥምር መንግሥትን እንደ ጦር ይፈራል ተብሎ ይታመናል፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እንዳሉት የሕዝብ መንግሥት በመሆኑ ኢሕአዴግ የሕዝብ ይሉኝታ አግኝቻለሁ የሚል ዕምነት ያለው ቢሆንም፣ ተቀባይነት ያለው ውድድር ሳያደርግ የሕዝብ አመኔታ አገኘሁ ማለት አይቻልም ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡ ፍርኃት ሦስት – ብሔራዊ ዕርቅ በኢትዮጵያ ላይ ሥልጣን ላይ ያለው አካል ላለፉት በርካታ ዓመታት የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነት አሸናፊ ሆኖ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በተደጋጋሚ በማሸነፍ ሥልጣን መያዙን ቢናገርም፣ በዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የተኮራረፈና የተቀያየመ የኅብረተሰብ ክፍል የለም ማለት አይቻልም፡፡ በደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ምክንያት በነጭና በጥቁሮች መካከል የተፈጠረው ቁስል የዳነው፣ ብሔራዊ ዕርቅ በመፍጠር ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እዚያ ደረጃ የደረሰ ችግር ባይኖርም፣ ቢያንስ በልሂቃኖች መካከል ያስከተለው የጥላቻ ፖለቲካ መኖሩ መንግሥትም ራሱ አይክድም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ራሳቸው በዚሁ ንግግራቸው ተቃዋሚዎች ‹‹ከጥላቻ ፖለቲካ ይውጡ›› ማለታቸውም ራሱን የቻለ አስረጂ ነው፡፡ በአንዳንድ ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር ብሔራዊ ዕርቅ እንደሚያስፈልግ የፖለቲካ ተንታኞች ይመክራሉ፡፡ አለበለዚያ ግን ምርጫ በመጣ ቁጥር የመሸናነፍ መንፈስ ብቅ ጥልቅ እያለ የጥላቻ ፖለቲካ ይደርቃል ማለት አይቻልም፡፡ ይህ በተለይ በዳያስፖራ ፖለቲከኞች ዘንድ እጅግ ገኖ የሚታየውን የጥላቻ ፖለቲካ ማድረቅ የሚቻለው በሰፊ ብሔራዊ ዕርቅና መነጋገር ብቻ ነው የሚለው የብዙዎች አቋም ነው፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹ማንና ማን ተጣልተው ነው ብሔራዊ ዕርቅ የሚፈጥሩት?›› የሚል ማከራከሪያ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ቢያንስ በሕገ መንግሥቱና በአዲሱ ፌደራል ሥርዓትም ሙሉ መስማማት እንደሌለ ግን ያምናል፡፡ ፍርኃት አራት – የዲሞክራሲ ተቋማት የአንድ አገር ዲሞክራሲ የተደላደለ እንዲሆንና የብዙኃን ፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖር ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ነፃ የፍትሕ ተቋምና ገለልተኛ የፀጥታ ኃይሎች ተኪ የሌለው ሚና አላቸው፡፡ የአንድ አገር ዲሞክራሲ የዳበረ ስለመሆኑና አለመሆኑ አመላካች ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት (በተለይ ከገዢው ፓርቲ) ነፃ የሆኑት የዲሞክራሲ የቋማት የመኖራቸው ጥያቄ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ በአንድ የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንት የተመራችው ግብፅም፣ ነፃ የፍትሕ ተቋምና ገልተኛ መከላከያ እንደነበራት አረጋግጣለች፡፡ ሕዝቡ በመሪዎቹ ላይ ሲያምፅ፣ ለሕዝብ ፍላጎት የሚቆም ተቋም መሆኑን አስመስክሯል፡፡ የቆሙት ሥልጣን ላይ ያለውን አካል ሊጠብቁ ሳይሆን ሕዝቡን፣ የአገሪቱን ደኅንነትና የመንግሥት ተቋማትን ለመጠበቅ መሆኑን አስመስክረዋል፡፡ በኢትዮጵያ እነዚህ ገለልተኛ ተቋማት ለመመሥረት መንግሥት የተሳካለት አይመስልም፡፡ ጠንካራ፣ በራሱ የሚተማመን የፀጥታ ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት ቢኖራትም፣ የፖለቲካ ችግር በተፈጠረበት ወቅት ገለልተኛ አቋም ይያዛል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ የለም፡፡ በተለይ በተቃዋሚዎች በኩል ምንም ዓይነት መተማመን አይታይም፡፡ በተለይ ደግሞ ገለልተኛ የፍትሕና የምርጫ ተቋም በሌለበት አገር ፍትሐዊና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ ማሰብ ዘበት መሆኑ ዘወትር የሚወሳ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ የእነዚህ ተቋማት ገለልተኝነት ሁሌም ጥያቄ ውስጥ እንደገባ ነው፡፡ በእነዚህ ተቋማት ላይ መተማመን ባልተፈጠረበት አኳኋን፣ በአንድ አገር የዲሞክራሲ ምሰሶ የሆነውን የሕግ የበላይነትና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የመገንባት ህልም ደግሞ ዕውን ሊሆን እንደማይችል የብዙዎች ዕምነት ነው፡፡ ፍርኃት አምስት – ሰላማዊ ሠልፍ ለዚሁ ጽሑፍ መነሻ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አቶ ግርማ ላነሱዋቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹መንግሥት አይፍራም›› የሚል ነው፡፡ ጥያቄው በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቂ የመጫወቻ ሜዳ እንዲኖር፣ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረሩ አዋጆች እንዲሰረዙና በተቃዋሚዎችና በገዢው ፓርቲ መካከል መግባባት እንዲፈጠር የሚል ሐሳብ በፕሬዚዳንቱ የመንግሥት አቅጣጫ ጠቋሚ ንግግር እንዲካተት የሚል ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ምላሽ፣ ‹‹ሌት ተቀን የጎዳና ላይ ነውጥ አምጥቼ ገዢውን ፓርቲ እቀይራለሁ ብሎ አቅዶ ከሚሠራ ፓርቲ ምን እንነጋገራለን? የጎዳና ላይ ነውጥ አቁም ብለን ነው የምንነጋገረው?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ቀጠል አድርገውም፣ ‹‹አሁን በጋራ ለመሥራት የሚያስችለው መንገድ በከፍተኛ ደረጃ እየጠበበ መጥቷል፤›› ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውም ተቃዋሚዎች የጎዳና ላይ ነውጥን እየገመገሙና የዓረብ አብዮት በኢትዮጵያ ለማከናወን ከውጭ አካላት ጋር እየመከሩ ነው የሚል ነው፡፡ ከ1997 ምርጫ በኋላ ‹‹በዚህ አገር ምርጫ ብሎ ነገር የለም›› ብለው ተስፋ በመቁረጥ ነውጥ አንስተናል የሚሉ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህም ኃይሎች ከኤርትራም ከግብፅም ሆነ ከአልሸባብ ጋር እየመከሩ ነው የሚል ስሞታ ቢቀርብ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ አስቸጋሪ ይሆናል እንጂ ከእነዚህም ኃይሎች ጋር መደራደር ለምን አይቻልም የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ለዚህም መንግሥት ከኦነግና ከኦብነግ ጋር በተለያዩ ጊዜያቶች መደራደር ችሏል፡፡ ስምምነቶችም ተፈራርሟል የሚሉ ምሳሌዎች ይነሳሉ፡፡ በአገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ለውጥ ይመጣል ብለው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ሰላማዊ ሠልፍ ቢወጡ፣ ‹‹የጎዳና ላይ ነውጥ›› ሊሰኝ አይችልም የሚሉ መከራከሪያዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄያቸውን ከሃይማኖታዊ ችግር ጋር መቀላቀላቸው በብዙዎች የሚተች ቢሆንም፣ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደ ሰላማዊ የመቃወም መብት መሆኑ ለምን ይዘነጋል ተብሎ ጥያቄ ይቀርባል፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻ ተከታታይ ሰላማዊ ሠልፍ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ መጠየቅ ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው ከማን ጋር ነው የምንደራደረው የሚያስብል እንዳልሆነ ይተቻል፡፡ ኢሕአዴግ ከምርጫ 2002 ጋር በተያያዘ ከተቃዋሚዎች ጋር የጀመረው ድርድር መድረክን ከድርድሩ ውጪ እንዲሆን ካደረገ በኋላ፣ በወቅቱ የተቋቋመ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ኮሚቴ ምን እንደፈየደ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ለጥያቄው የሰጡት ምላሽ ይዘትም ሆነ አመላለሳቸው፣ ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር አብሮ ለመሥራት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሌለው አመላካች ይመስላል፡፡ እሳቸው ‹‹የጎዳና ላይ ነውጥ›› ያስነሳሉ ካሉዋቸው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ካልተደራደሩ ከማን ጋር ድርድር ያደርጋሉ በማለት የሚጠይቁ አሉ፡፡ ‹‹ድርድር የሚደረገው ወደ ጦርነት ደረጃ ሊያመራ የሚችል የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታትና ለማስታረቅ መሆኑን የዘነጉት ይመስላል፤›› የሚሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ናቸው፡፡ ጠቅላላ ፍርኃት ሰላማዊ ትግል ከላይ የተጠቀሱት አንዳንድ አገባቦች የሰላማዊ ትግል መገለጫዎች ናቸው፡፡ ገለልተኛ የዲሞክራሲ ተቋማት እንዲፈጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትግል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከሌሎች የሚለዩት እዚህ አገር ምንም ዓይነት የፖለቲካ ችግር የለም የሚል አቋም ይዘው አይደለም፡፡ ነገር ግን ሰላማዊ የሆነ ትግል በማካሄድ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል አቋም ያላቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ እንደሚሉት፣ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ተቃዋሚዎች የሚያሠራ የፖለቲካ ምኅዳር ማጣታቸው በነውጥ ለተነሱ ኃይሎች ትክክለኛ የትግል ስልት መሆኑን ማረጋገጫ እንደ መስጠት ነው፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጊዜም ሆነ በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ ትግልን ይፈራል የሚለው ዕውን እየሆነ ነው በማለት ትችት የሚያቀርቡ አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃይለ ማርያም በዚሁ መንግሥት አይፈራም በሚለው ንግግራቸው ያስቀመጡት፣ ‹‹ኳሱ እናንተ ዘንድ ነው ያለው›› የሚል አባባል አለ፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የተለያዩ ሰዎች ግን ተቃዋሚዎች ውስጣቸውን ማፅዳት አለባቸው፣ እውነተኛ የዲሞክራሲ ታጋዮች መሆናችሁን ማስመስከር አለባቸው፣ ከጥላቻ መውጣት አለባቸው የሚል ምላሽ ቢሰጡም፣ ‹‹ኳሱ ግን ያለው ሥልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ ዘንድ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ በእጁ ላይ መሆኑን በምክንያትነት በማስቀመጥ፡፡ ethiopianreporter

No comments:

Post a Comment