Friday, September 20, 2013

ግልጽ ደብዳቤ ለኮሎኔል መንግሥቱ ሃይለማሪያም

Mengistu Haile Mariam 3.jpg በቅድሚያ እርስዎንም ሆነ አንባቢውን ይቅርታ እየጠየቅሁ፤ የሚከተለውን ለማለት እፈልጋለሁ። ይህም እርስዎ ኮሎኔሉ በሕይወት እስካሉ ድረስ በታሪክ አጋጣሚነት የኢትዮጵያ መሪ በነበሩበት ወቅት ስላደረጕትም ሆነ ስላላደረጉት የመፃፍና የማስረዳት መብት የእርስዎ ወይንም እርስዎ የሚወክሉት ሰው ብቻ ነው። ምክንያቱም በሥልጣን ላይ በነበሩ ወቅት ያደረጉት የወሰኑት የጻፉትና የተናገሩት ሁሉ የኢትዮጵያ ታሪክ ስለሆነ። ስለዚህም ማንም ሰው ያለእርስዎ ፈቃድ በንዝህላልነት በግብዝነትና በትምክህተኝነት ተነሳስቶ የእዚህን የግልጽ ደብዳቤ ዋናና አንገብጋቢ ዓላማ ለመረዳት ባለመቻል ሊናገር ሊመልስ ሊጽፍ ሊበርዝ ሊጠግንና ሊያስተካክል መብት የለውም። ሊደመጥም አይገባም። ታሪክን ለታሪክ ሠሪው መተው ተገቢ ይመስለኛል። በክፍል አንድ ላይ እንዳቀረብኩት፦ በንጉሥ ኅይለሥላሴ ላይ እንዲያዝኑና ቂም እንዲይዙባቸው ካደረገዎት አንዱ ምክንያት በመጽሐፍዎት ገጽ 259 ላይ ያሰፈሩት ነው። እርስዎ ሲገልጹትም “….በታሪክ http://www.ethiomedia.com/

ከሚታሰቡ አሳዛኝ ጉዳዮች አንዱ ደግሞ የቀዳማዊ ኅይለሥላሴ መሠደድ ነው። በጊዜው የኢትዮጵያ የነቁ መንፈሳዊ አባቶች፡ አረጋዊ የየህብረተሰቡ መሪዎች፡ ለነፃነት የታገሉ አርበኞችና በአገሪቱ ምሁራን ዘንድ የቀዳማዊ ኅይለሥላሴ ለአምስት ዓመታት አውሮፓ በተለይም እንግሊዝ መቆየት ሁለት ገጽታ ነበረው። አንደኛ ያለጥርጥር ከፍ ያለ የመንፈስ ጉዳት የሚያደርስና ቅስም የሚሰብር የኅዘንና የፈተና ጊዜ ሲሆን….” ይህ ምክንያት፦ በገጽ 271 እንደገለፁት፦ ንጉሡ እንደ ሌሎች አርበኞች አስከሬናቸው በቅዱስ ሥላሴ ፍትሀትም ሆነ ቀብር እንዲነፈጋቸው አድርጓል። እርስዎ የንጉሡን መሰደድ ከፍርሀት የመጣ ስለሆነ ሽሽት እንጅ ለስራ ወይንም የኢትዮጵያን ሕዝብ አቤቱታንና እሮሮን ለማሰማት እንዳልሆነ ወስነዋል። ሽሽት ለመሆኑ ያቀረቡት ማስረጅያ ግን የለም። መንግሥቱ ኅይለማሪያም ስለሆንኩኝ እመኑኝ የሚሉ ይመስላል። የኢትዮጵያ ታሪክ ስለሆነ በዘፈቃድ የሚሆን አይመስለኝም። የኢትዮጵያ ታሪክ ፅሐፊዎችና ምሁራን ስለጉዳዩ ምን ይላሉ? አምባሳደር ዘውዴ ረታ “የቀዳማዊ ኀይለሥላሴ መንግስት” በሚል አርዕስት እአአ በ 2012 ዓም ታትሞ በወጣው መጽሐፋቸው ምዕራፍ አስር የሚከተለውን ያሳስቡናል። “መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሠራዊት “መሐን” ከተባለው ስፍራ ተነስቶ ማይጨው ሰፍሮ የነበረውን የጠላት ሠራዊት ለመግጠም ወደ ስፍራው ሲቃረብ፦ ጦሩ ከበባ ሳያደርግና የጦር አዛዡን ትዕዛዝ ሳይጠብቅ አንዱ ስለተኮሰ ጦርነቱን ለመጀመር ታቅዶ ከነበረው ከአንድ ቀን በፊት ተጀመረ። ከዝያም ጦርነቱ እንዲቀጥል ንገሠ ነገሥቱ ትእዛዙን ሰጡ። “ ይሁን እንጂ ማርሻል ባዶግሊዮ ገና ከመነሻው የአድዋ ታሪክ እንዳይደገምበት ካለው ሦስት የተሟላ ዲቪዚዮን የምድር ጦር ይልቅ፤ በአየር ኅይሉ በመተማመን ከፍ ያለ ዝግጅት አድርጎ ስለነበረ፤ መርዝ የሚረጩትና ቦንብ የሚጥሉት በአንድ ጊዜ ቁጥራቸው ከአንድ መቶ ሃምሳ በላይ የሆኑ አውሮፕላኖች፤ በአሥር መንታ እያንዣበቡ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ እሳቱን እንደ ዝናብ እንዲያወርዱት አስደረገ። ኢትዮጵያውያኖቹም በአንድ በኩል ከሰማይ የሚወርድባቸውን መርዝና ቦንብ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከምድር የሚተኮስባቸውን መድፍና መትረየስ በድፍረት እየተጋፈጡ፤ በዚያ በያዙት በጥንታዊ የሰናድር ጠምንጃና ወጨፎ ውጊያቸውን ቀጠሉ። በዚህ አኳኋን፤ ጦርነቱ በተጀመረ አምስት ሰዓቶች ባልፈጀ ጊዜ ውስጥ፤ በማይጨው ላይ ጠላት የሰፈረባቸውን አምስት ምሽጎች በጀግንነት ለማስለቀቅና የጠላትን ወታደሮች ብዙዎቹን ገድለው ብዙዏቹንም ለማባረር ችለው ነበር። ይሁን እንጂ፤ የኢትዮጵያ ተዋጊ ኀይል እየቀናው መሄዱ ንጉሠ ነገሥቱን ቢያስደስታቸውም፤ በጠላት በኩል በተለይ በአየር ኀይል የተጣለው መርዝና ቦምብ ብርቱ ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ፤ ከሞት የተረፈው ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጥቂት እንዲያርፍና የሞተውም ሬሳው እየተነሣ እንዲቀበር፤ መጋቢት 23 ቀን ሮብ መሐን ላይ የአንድ ቀን ውሎ ይደረግ ሲሉ፤ የጦሩ ዋና አዛዥ ለየአዝማቹ ትዕዛዝ አስተላለፉ።…. ለዳግማዊ ምኒሊክ አድዋ ላይ ድልን ያስገኘው የየካቲቱ ጊዮርጊስ ለቀዳማዊ ኅይለሥላሴ ደግሞ የመጋቢቱ ፈረሰኛው ጊዮርጊስ የጉልበት ማጠናከሪያ ዕድል የሚሰጥ እንዲሆን ተስፋ በማድረግ፤ በማግስቱ ሐሙስ መጋቢት 24 ቀን ከጠላት ጦርነቱን እገጥማለሁ ብለው ንጉሠ ነገሥቱ ወስነው ነበር። ነገር ግን፤ በአራት ግንባር የተመደቡት ዋና ዋናዎቹ የጦር አዝማቾችና ከሞት የተረፉት የጦር አለቆች በሙሉ ተሰብስበው ይህን ንጉሠ ነገሥቱ ያቀዱትን ውጊያ ለመፈጸም የሚቻል አለመሆኑን አስረዱ። በተለይም ልዑል ራስ ካሣና ልዑል ራስ ሥዩም በገለጹት አስተያየት፤ “….ሠራዊቱ መድከም ብቻ ሳይሆን አልቋል ማለት ይቻላል። ቢቆጠር ሕይወቱ ከተረፈው ይልቅ በመርዝ የተቃጠለውና በመድፍ ተመትቶ የሞተው ይበልጣል። ….እግዚአብሔር ፈቃዱ ባይሆን ነው እንጂ፤ በትናንቱ ዕለት ጠላትን ደህና አድርገን አድቅቀነው ነበር። ጠላታችን እኛን የበለጠን በምድሩ ውጊያ ሳይሆን፤ በማናውቀውና መሣሪያው በሌለን በሰማዩ ጦርነት ነው። አሁንም ዛሬ ተነሥተን እንግጠመው ብንል፤ የሚያጠቃን ያው በተለመደው የፈሪ በትሩ ከሰማይ በሚያዘንብብን እሳትና መርዝ ነው እንጂ፤ እንደ ወንዶቹ ፊት ለፊት ቢመጣብን አንበገርም ነበር። ስለዚህ፤ የሚሻለው ወደ ኋላ ተመልሰን ከሞት የተረፈው ሠራዊታችን የሚያገግምበት ዕድል እንዲያገኝ ማድረግና፤ ሌላም ተጨማሪ ጦር ለማዘጋጀት የሚቻልበትን መንገድ ማጥናት ይሻላል….” አሉ። (ገጽ 246) ንጉሠ ነገሥቱ ለዚህ የሚሰጡትን መልስ አንባቢው በተለይም እርስዎ ኮሎኔል መንግሥቱ በአንክሮ፤ በንጹህ ልቦናና በጥሞና እንዲያነቡና እንዲገነዘቡ አሳስባለሁ። ምክንያቱም እርስዎ የንጉሡን ወደ አውሮፓ ስደት ከታሪክ መዝገብ ሳይጠቅሱ እንደ ሽሽት እንጅ በሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል አገራት በተቀነባበረ ሴራ በተለይም በፋሽስት ኢጣሊያ ጦር በአገራቸውና በሕዝባቸው ላይ እየደረሰ የነበረውን ስቃይና በደል ለማሰማትና ዕርዳታ ለመጠየቅ የስራ ስደት እንደነበር ለመቀበል ፈጽሞ ስለማይፈልጉ ነው። ታሪኩ የኢትዮጵ ሕዝብ ስለሆነ ማንም ሊለውጠው፤ ሊያስተባብለው ወይንም እኔ ከማስበውና ከማምንበት የተለየ ስለሆነ አልቀበለውም ሊል አይችልም። እኔም ይህንን የምጽፈው አስተሳሰብዎትን አስለውጣለሁ ብዬ ሳይሆን፤ የአገሪቷና የንጉሡ ታሪክ የሁላችን ቅርስ ስለሆነ ሲገደፍ ዝም ብዬ ባልፈው ሕሊናዬ ሊወቅሰኝ እንደሚችል ስለተገነዘብኩ ነው። ወደ ቁም ነገሩ እንመለስ። አምባሳደር ዘውዴ ረታ የንጉሡን መልስ እንደሚከተለው አስቀመጠዋል። “ እኛ ከዚህ ካለንበት ቦታ ለቅቀን ወደ ኋላ ብናፈገፍግ፤ ድሉን ለጠላታችን አረጋግጥንለት ማለት ነው። እኔ እዚህ ጦር ሜዳ የመጣሁት ለኢትዮጵያ ነፃነት ደሜን ለማፍሰስ ቆርጬ ነው። ስለዚህ፤ ከዚህ በፊት ዓለሜን ከሕዝቤ ጋር እንደተካፈልኩት መከራውንም ከሕዝቤ ሳልለይ እካፈላሁ እንጂ፤ አገሬን ለጠላት አስረክቤ ወደኋላ በመመለስ ሕይወቴን ለማዳን አልሞክርም። ቀድሞውን እኔ እዚህ የመጣሁት፤ ድል አደርጋለሁ ብዬ አይደለም። ድል ብሆንም፤ ሕይወቴ እስኪያልፍ ድረስ ተዋግቼ ተግባሬን ፈጽሜ ሞትን ለመቀበል ነው። ሁላችሁም እንደምታውቁት አሁን ያለነው በሁለት ዓይነት ሞት መካከል ነው። አንደኛው ሞት፤ ከጠላት ጋር ተዋግቶ መሞት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሲሸሹ በጠላት እጅ ወድቆ መሞት ነው። ከእነዚህ ከሁለቱ ይመረጥ ቢባል፤ ያለጥርጥር በጀግንነት ሲዋጉ መሞት ከሁሉም የበለጠ ክብር ነው። እኔ ዓላማዬ ይኽ ስለሆነ፤ የፈቀደ ከእኔ ጋር ይሙት። እኔ ግን ወደ ኋላ አልመለስም አሉ።” (ገጽ 246) ከዚያም መኳንንቱና ሹማምንቱ በአቡነ ጴጥሮስ፤ በእጨጌ ገብረጊዮርጊስ እና በልዑል ራስ ካሳ ኅይሉ አማካኝነት ሽሽት ሳይሆን የእስትራተጅ ለውጥ ይደረግ ማለታቸውን አስረዱ። ከዚያም ንጉሡ የሚከተለውን አሉ። “ አሁን ሁላችሁም ጦሩ ወደ ኋላ ተመልሶ ሌላ ዝግጅት ቢደረግ ይሻላል ብላችሁ የተናገራችሁት፤ እኔን ለመደለል ሳይሆን ቁርጥ ሐሳባችሁ መሆኑን በመንፈስ አባቶቻችን ፊት በመሐላ አረጋግጣችሁልኛል። እንግዲህ፤ የሁላችሁም ሐሳብ እንደዚህ አንድ ከሆነ፤ እኔም ያቀረባችሁት እንዲፈጸም ይሁን እላለሁ።” አምባሳደር ዘውዴ ረታ በጫካ እንዋጋ ? ወይስ በዤኔቭ እንሟገት በሚለው አርስተ ጉዳይ ላይ፤ ንጉሠ ነገሥቱ እንደ ኢ/አቆ ሚያዝያ 22 ቀን 1928 ከዘመቻ ተመልሰው አዲስ አበባ በገቡበት ዕለት የትግሉን ሂደት ለመገምገምና አማራጩን መንገድ ለመምረጥ በታላቁ ቤተመንግሥት ከፍተኛ ጉባኤ ተደርጎ ስለነበር፤ ሂደቱን እንደሚከተለው አስቀምጠዋል። ስብሰባውን የመሩት ንጉሠ ነገሥቱ ነበሩ። በስብሰባው የተካፈሉት በልዑል ራስ ካሣ አማካይነት ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ፤ ከሚኒስትሮቹና ከጦር አልቆቹ መካከል የተመረጡት ነበሩ። አምባሳደር ዘውዴ በገጽ 252 እንዳስቀመጧቸው ለውይይት ቀርበው የነበሩት ዐርስተ ጉዳዮች የሚከተሉት ነበሩ። ሀ) ከእንግዲህ ወዲህ ጦር አሰባስቦ ጠላትን ፊት ለፊት ለመግጠም የሚያስችል መሣሪያም ሆነ በቂ ሠራዊት ስለሌለ ለነፃነት የሚደረገው ትግል በጫካ የሽምቅ ውጊያ በአርበኝነት ከማድረግ ሌላ አማራጭ መንገድ አለመኖሩን ሁሉም ተስማምተውበት በሙሉ ድምፅ ተወሰነ። ለ) ጠላት ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተቃረበ ስለሆነ፤ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት መምሪያ ሳይውል ሳያድር ወደ ይልባቦር ጠቅላይ ግዛት ጎሬ ከተማ እንዲዛወር ተወሰነ። በዚህም ጊዜ ጎሬ ላይ ለሚካሄደው የመንግሥት አስተዳደር ቢትወደድ ወልደጻድቅ ጎሹ፤ የቀዳማዊ ኀይለሥላሴ እንደራሴ ሆነው ተሾሙ። ሐ) በመጨረሻው ብዙ የሐሳብ ልውውጥ የተደረገበት ትልቁ ጉዳይ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው ዤኔቭ ሄደው የዓለም መንግሥታትን እርዳታ ቢጠይቁ፤ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም በሚለው ሐሳብ ላይ ነው። በዚህ ጉዳይ ሦስት ሰዎች በየተራ የገለጿቸው አስተያየቶች የሁሉንም ሐሳብ ለውሳኔ ያመቻቸ ሆኖ ተገኘ። ሶስቱ ሰዎች የሚከተሉት ነበሩ፤ ልዑል ራስ ካሣ ኅይሉ፤ ብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደሥላሴ እና አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ። የሶስቱም አመለካከትና አቋም ተመሳሳይ ስለሆነ የብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደሥላሴን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ አስተያየት እነሆ። “ልዑል ራስ ደህና አድርገው ገልጸውታል። የአገርን ጠላት ለሚያህል ትልቅ ጉዳይ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልገው፤ በሁሉም አቅጣጫ ነው። በጦር ሜዳውም፤ በፖለቲካውም፤ በፕሮፓጋንዳውም የሚከናወኑ ብዙ ነገሮች አሉ። ንጉሠ ነገሥታችን በጦር ሜዳ በሠራዊታቸው መካከል ሆነው ተዋግተዋል። መከራውንም በቆራጥነት ተቀብለዋል። አሁን ደግሞ በፖለቲካው ሜዳ ላይ ለመታገል፤ ዤኔቭ ሄደው ለመንግሥታት ማህበር የሚያቀርቡት አቤቱታ፤ ምን አልባት በእግዚአብሔር እርዳታ፤ የታላላቆቹ አገሮች ህሊና ተቀስቅሶ ለዚች በስቃይ ላይ ለምትገኝ አገራችን ይደርሱላት ይሆናል ብለን ተስፋችንን ማጽናት አለብን። ስለዚህ፤ ልዑል ራስ እንደተናገሩት የግርማዊነታቸው ወደ ዤኔቭ መሔድ ከልብ የምደግፍ መሆኔን በታላቅ ትሕትና እገልጻለሁ።” (ግጽ 253) እንግዲህ እዚህ ላይ ኮሎኔሉንና አንባቢውን ማሳሰብ የምፈልገው፤ ከላይ ግልጽ እንደሆነውና ታሪክ እንደመሰከረው፤ ንጉሡ ወደ እንግሊዝና ዤኔቭ የተጓዙት የአገራቸውን ችግርንና የሕዝባቸውን ሰቆቃ ለድርጅቱ አባላትና ለሚመለከታቸው መሪዎች ለማሰማትና እርዳታ ለመጠየቅ ሲሆን፤ የኮሎኔሉ ክስ ታሪክን መሰረት ያላደረገ አሳዛኝ አሉባልታ መሆኑን ነው። አምባሳደር ዘውዴ በገጽ 255 እና 256 የንጉሡን መልስ አስቀምጠዋል። “ ሁላችሁም ለአገራችን ነፃነት የምትሰቃዩና መሥዋዕት ለመሆን ወደ ኋላ የማትሉ ናችሁ። በዚህም አኳኋን የምታቀርቡልን ምክር ሁሏ እውነተኛውንና በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ዘንድ የሚከበረውን ስለሆነ፤ ሙሉ ዕምነት እናሳድርበታለን። ራስ ካሣ በተናገርካቸው ብዙዎች በሆኑት ፍሬ ነገሮች ውስጥ፤ ዤኔቭ ሄደን የምናቀርበው አቤቱታ አዳማጭ ካጣ፤ በአንደኛው ጠረፍ በኩል ወደ አገራችን ተሻግረን የአርበኝነት ተግባር ለመፈጸም ይቻላል ያልከው፤ ከሐሳባችን ጋር የተገጣጠመ ሆኖ ስላገኘነው ደስ ብሎናል። ሕሩይ በተናገርከው ውስጥ፤ ለነፃነት መዋጋት በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን፤ በፖለቲካውም፤ በፕሮፓጋንዳውም በኩል መሆን አለበት ያልከው፤ የምንስማማበት መልካም አስተያየት ነው። መኮንን ሀብተወልድ የተናገርከው ከጠበቅነው በላይ ነው። ዤኔቭ ሄደን አቤቱታችንን የምናቀርብለት የመንግሥታት ማሕበር፤ጠላታችንን ከአገራችን ለማስወጣት በጦር ሠራዊት ሆነ በመሣሪያ ምንም ዓይነት እርዳታ እንደማይሰጠን ተስፋህን ቆርጠሀል። እንዳልከው፤ እኛም ይህን ያህል እናገኛለን ብለን ተስፋ አላሳደርንም። ተክለ ሐዋርያት በዤኔቭ በመጨረሻ ቀኑ ስለተናገረው የጠቀስከው ማለፊያ ነው። መቸም እሱ በጠባዩ ጥሩ ነገር ሲሰራ አይናገርም። እኛም የሰማነው እሱ ነግሮን አይደለም። የሚያሳዝነው ይህን የመሰለ ንግግር አድርጎ ከአዳራሹ ሲወጣ፤ ከጓደኞቹ የመንግሥታት እንደራሴዎች መካከል ያመሰገነውም ያደነቀውም አለመኖሩ ነው። ከዚህ ሌላ በተናገረው ውስጥ፤ ፈረንሣይ በሙሴ ላቫል መንግሥት ጉዳት ቢያደርስብንም፤ እንግሊዝም ፊት ለፊት ተጋፍጦ ጠቃሚ እርዳታ ባይሰጠንም፤ ከአሜሪካም የጠበቅነውን ባናገኝም የወደፊቷ ኢትዮጵያን በማሰብ፤ ተስፋ መቁረጥ የለብንም። እነዚህ አገሮች ሁሉ ለዛሬው ባይሆኑን ነገ ተመልሰው አገራችንን ሊጠቅሙ ይችሉ ይሆናል ብለን ማሰብ ይሻለናል። ዛሬ ያለንበት ሁኔታ፤ በሞትና በሕይወት መካከል የሚያጣጥር ነው። የጦር መሣሪያ ባጠረን ጊዜ፤ ሠራዊታችንም ተዳክሞ በተበተነበት ሰዓት፤ ጥቂት ተዋጊዎች ይዘን ጠላትን እንመክታለን ብለን ብንነሣ፤ በመጀመሪያ ሰላማዊውን የአዲስ አበባን ሕዝብ እናስጨርሳለን። እኛም እናልቃለን። ስለዚህ፤ መንግሥታችን ወደ ጎሬ (ይልባቦር) ተዛውሮ በቢትወደድ ወልደጻድቅ ጎሹ እየተመራ እንዲቆይና፤ እኛም አቤቱታችንን ለዓለም መንግሥታት ማሕበር ለማቅረብ ወደ ዤኔቭ እንድንሄድ ያቀረባችሁልን ን ሐሳብ ተቀብለናል። በዚህ መሠረት፤ ቤተመንግሥታችንን ለቅቀን እንደወጣን፤ ጠላት የአዲስ አበባን ሕዝብ በመርዝና በጋዝ እንዳይፈጀው፤ ከተማው “ነፃ ከተማ” ተብሎ ይታወጅ።” አንባቢው ከንጉሡ መልስ መገንዘብ የሚችለው፤ በቀውጢ ጊዜ ማሰብ መቻላቸውን ብቻ ሳይሆን አርቆ አስተዋይነታቸውንም ጭምር ነው። ምክንያቱም እንግሊዝን ፈረንሳይንና አሜሪካንን በችግራችን ወቅት ስላልደረሳችሁልን ወዳጅነታችሁን አንፈልግም ከማለት ይልቅ የወደፊቷን ኢትዮጵያን ብናስብ ጥሩ ነው ምክንያቱም ሊጠቅሙን ይችላሉና ! እንግዲህ የንጉሡ የትግል ታሪካቸው እንዲህ ሆኖ ሳለ፤ ኮሎኔሉ አዲስ እና ሊያውም አሳፋሪ የሆነ ለመፃፍ መነሳታቸው በጣም የሚገርምና የሚያሳዝንም ነው። የ ሰማኒያ አምስት/85 ዓመት ሽማግሌን ሕይወታቸው በእርስዎ በኮሎኔሉ ትዕዛዝ እንዲወሰድ ያደረጉት አንስዎት፤ ታሪካቸውንም ለማጥፋት አቅደው መነሳትዎ በጣም አሳፋሪና አሳዛኝም መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ። የእርስዎ አስራሰባት ዓመታት አገዛዝ ኢትዮጵያን በወጣት ልጆችዋ፤ በተማሪዎችዋ፤ በመሪዎችዋና በመኮንን ሰራዊቶችዋ ደም ያጠበ ሕዝቡ ሰላም አጥቶ በሁሉም ክፍለ ዓለም እንዲሰደድና እንዲበተን የሆነበት በአገሪቷዋ ታሪክ አሳፋሪ ምዕራፍ ሆኖ ለዘላም የሚኖር ይሆናል። እዚህ ላይ አንባቢው ትንፋሹን ዋጥ በማድረግ “ሕይወታቸው በኮሎኔሉ ትእዛዝ ተወሰደ” ለሚለው ማስረጂያ የሚጠይቅ እንደሚሆን ይሰማኛል። ከመጽሐፍ ደራሲ ሻምበል ተስፋዬ ርስቴ ጋር ተዋወቁ። ኮሎኔሉ ሸሽተው አዲስ አበባን ከለቀቁ በኋላ፤ ወያኔ አዲስ አበባ ሲገባና ሲይዝ፤ ሻምበሉ ከኮሎኔሉ ባለሥልጣናት ጋር የመታሰር ዕጣ ከደረሰባቸው አንዱ ናቸው። አምባሳደር ሞገስ ሀብተማሪያም ሻምበሉን ሲያስተዋውቁና ለመጽሐፋቸው ማሳሰቢያና ምስክርኑት ሲሰጡ (blurb)፤ የሚከተለውን ይላሉ። “የመጽሐፉ ደራሲ ሻምበል ተስፋዬ ርስቴን በአንድ መሥሪያ ቤት ስንሰራ ዐውቀዋለሁ። በትምህርት ከተገነባው ዕውቀቱ ባሻገር፤ የግል ታታሪነት ባህሪውን አደንቃለሁ። ይህ ተሰጦው አብሮት ወህኒ ቤትም ገብቷል። የደርግ አባሎችንና በጊዜው የነበሩ ባለሥልጣናትን በአንድ ጣራ ሥር ስላገኛቸው ያልተጻፈውን የደርግ መንግሥት ታሪክ ለመክተብ በየትኛውም ቦታ ቢሆን የማይገኘውን ዕድል ተጠቅሞበታል። በተጨማሪም የተለያዩ መጽሐፍትን አንብቦ በዋቢነት አጣቅሷል። በሦስተኛ ደረጃ በሥራ ምክንያት የተለያዪ ሁኔታዎችን ለመገንዘብ ስለቻለ የተሟላ ዝግጅት ሆኖለታል። እናም ይህ ታሪክ ተዝቆ የማያልቅን የወርቅ ማዕድን ይመስላል።” ሻምበሉ “ምስክርንት በባለሥልጣናቱ አንደበት” በሚለው መጽሐፋቸው፤ ምዕራፍ አንድ ከገጽ 47-51 ስለንጉሡ አሟሟት የጻፉ ስለሆነ፤ አንኳሩን አቀርባለሁ። በረጋ መንፈስ ያነብቡ። “ለውጡ የንጉሡን እና የመኳንቶቻቸውን ሥልጣን ብቻ ነጥቆ አላበቃም ሕይወታቸውን ጭምር ጠይቋል። ንጉሡ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ለአንድ ሙሉ ዓመት በሕይወት ለመቆየት አልታደሉም። በሻ/ መንግሥቱ ኅ/ማርያም ውሳኔ ኮትኩተውና ቀልበው በአዘጋጁት ጦር አባላት ታፍነው ተገደሉ። አሟሟታቸውን አስመልክቶ በምኒሊክ ቤተመንግሥት ውስጥ የመንግሥቱ ኅይለማርያም ጠባቂ የነበረው ልዩ ጦር የመቶ አዛዥ የነበሩት የመቶ አለቃ ወንድሙ አበበ “ ንጉሡ የተገደሉት በነሐሴ 20 ቀን 1967 ሲሆን የተቀበሩት በተከታዩ 21 ቀን ነበር። ግድያው የተፈጸመው ከደብረብርሃን በመጡ ልዩ ጦር አማካይነት በሻ/ዳንኤል አስፋው ነው። ንጉሡ የተገደሉት ሰመመን ሰጭ መድሐኒት በአፍንጫቸው እንዲያሸቱ ከተደረገ በኋላ በተንተራሱት ትራስ በማፈን ነበር። እንዲያፍን የተላከው ወ/ር ህሊናው እምቢ ብሎት እየተርበተበተ በመቸገሩ ራሱ ዳንኤል አስፋው አፈናውን ፈጽሞታል በማለት ገልጽዋል።” መኮንኑ አክለውም “በዚያን ወቅት ቤተ መንግሥቱ ግቢ ውስጥ የተቀራረቡ ግን የተለያዩ ጥልቅ ጉድጓዶች ጦሩ መቆፈሩን አስታውሳለሁ። ምሽግ ለማድረግ እንዳይባል አጭር ነው የውሃ ማጠራቀሚያ እንዳይባል ደግሞ ሞላላ ነው ጥልቅ የሆኑ አራት ወይም አምስት ጉድጓዶች ተቆፍረው ውለው ሳያድሩ ደግሞ በስሚንቶ ተዘጉ በመለት የጉድጓዶቹን አቆፋፈርና መዘጋት ይገልፃሉ። ከላይ የተገለፅውን ሀሳብ ሻ/ል መንግሥቱ ገመቹ እውነት መሆኑን ገልጸዋል።” (እዚህ ላይ አንባቢውን ማሳሰብ የምፈልገው ሻ/ል መንግሥቱ ገመቹ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ድረስ የኮሎኔል መንግሥቱ ልዩ ፀሐፊ ሁነው ያገለገሉ ናቸው) ሻምበል ተስፋዬ በመቀጠል “ በተለይ የታላቁ ቤተመንግሥት የጥገና ክፍል ኅላፊ ነበርኩ ጉድጓዶቹንም በወታደርች ያስቆፈርኩ እኔ ነኝ የሚሉት መሐንዲስ ጥላሁን ኪዳኔ” ሲገልጹ “ግርማዊ ቀዳማዊ ኅይለሥላሴ እንደሞቱ ዐውቃለሁ የሞቱት ነሐሴ 20 ቀን 1967 ነበር። በነሐሴ 21 ቀን 1967 ከጧቱ 2:30 በመርዕድ ንጉሤ ተጠርቼ የከፈን ጨርቅና የሬሳ ሳጥን እንዳቀርብ ተጠይቄ ሰጥቻለሁ። መሐንዲሱ በመቀጠልም በሰባት ሰዓት ላይ ሦስት ጉድጓዶች 3 x 3 ሜትር አስቆፈርኩ። አራተኛ ጉድጓድም ተቆፍሯል። ቦታው በኋላ የፕሬዝዳንት ቢሮ ተሰራበት። አራት ጉድጓድ መቆፈሩ እኛ እንዳናውቅ መሰለኝ ጉድጓዶችን በዳንኤል አስፋው ትዕዛዝ በኮንክሪት ዘጋኋቸው፤ በአጭር ጊዜም በጉድጓዶቹ ላይ ቤት ተሠራ። ኢሕአዴግ ሲገባ ኮ/ል ስለሺ መኩሪያ ቦታውን ካሳየ በኋላ ስምንት ሜትር ተቆፍሮ ሦስት ሜትር ቱቦ ተገኘ፤ በኮ/ሉ መሪነትእንደገና ወደ ውስጥ ሦስት ሜትር ሲቆፈር የንጉሡ አጽም ተገኘ እና በሙሉ ወጣ በማለት ሰኔ 4 ቀን 1988 ለዋለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የምስክርነት ቃል ሰጥተዋል።” ( 47-48) አንባቢው፤ ኮሎኔሉ ስለ ንጉሡ አሟሟት የሚሰጡትን መረጂያ እንደሚሻና መስጠቱም አግባብ ስለሆነ እነሆ። “….ከታሰሩት ባለሥልጣኖች ብዙዎቹ የጤና ችግር እንደነበራቸው ሁሉ በሰኔ ወር 1967 ዓ.ም ንጉሡም በፊኛና በሽንት መሽኛቸው የጤና መታወክ ደርሶባቸዋል የሚል ሪፖርት ስለቀረብልን ሐኪማቸውን ፕሮፌሰር አሥራትን ጠርተን በማነጋገር ስለ ሁኔታቸው ከተረዳን በኋላ ከማረፊያቸው ወደ ሆስፒታል ሄደው አስፈላጊው ህክምና ይደረግላቸው ዘንድ በሙያው የላቁ ሐኪሞች ከውጭ እንዲመጡ በተጠየቀው መሠረት ታዝዞ መታከማቸውን ጤንነታቸው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደነበር አስተውለናል። በነሐሴ ወር ከዚህ በፊት የታወቀው የጤና ችግራቸው ያገርሽ ወይም ሌላ ዛሬ የማላስታውሰው እንደገና ስለመታመማቸው ተነግሮን እንደተለመደው ተገቢው እንክብካቤ እንዲደረገላቸው ከታዘዘ በኋላ ማረፋቸው ስለተነገረን በብዙሃን ማሰራጫ ሕዝቡ እንዲያውቅ ተደረገ።” (270-271) ከዚያም የሚከተለውን ስለወያኔ በመፃፍ ስለጉዳዩ ያላቸውን አስተያየት ያበቃሉ። “ አብዮታዊው መንግሥት ከፈረሰና ኢትዮጵያ የወያኔ ቅኝ ከሆነች በኋላ፤ ወያኔ በሃገር ላይ የፈፀመውን ክህደት፤ የባዕድ ምንደኝነት፤ ፀረ አንድነት፤ የመገንጠልና የማስገንጠል ወንጀሉን የከለለና ከወንጀለኛነቱ የሚያፀዳው እየመሰለው አብዮታዊያንንና አብዮትን ለመኮነን ብሎ አውርቶ ያስወራቸውን ብዙ ወሬዎች ሰምተናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ ያለበት እውነት፤ ደርግ በቀዳማዊ ኅይለሥላሴ ሕይወት ላይ ምንም አይነት ውሳኔ ያልሰጠ መሆኑን ነው።” (271) አንባቢውን አንድ የማሳስበው ዜና አለ። ይኸውም ኮሎኔሉ የንጉሡን ሐኪም ፕሮፌሰር አሥራትን ጠርተን አነጋግረን ነበር የሚለው ፍጹም መሠረት የሌለው አባባል እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ለፕርፌሰር ጆን ስፔንሰር፤ የቀድሞው የንጉሡ የፖለቲካና የውጭ ጉዳይ አማካሪ የነበሩት፤ በሰጡት ቃለ ልውውጥ አስታውቀዋል። ፕሮፌሰር ጆን ስፔንሰር Ethiopia At Bay: A Personal Account of Haile Selassie’s Years መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተለውን አስፍረዋል “ The Dergue announced that Haile Selassie had been found dead in bed and that it had immediately summoned the former emperor’s physician Dr. Asrat Woldeyes. With considerable courage, the doctor publicly denied any such summons. He had been at home all day and no such call had ever reached him.” ኮሎኔል፤ ከእርስዎ ጋር ይህንን የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ የስገደደኝ ዋናው ነገር፤ ንጉሡ ንጉሥ ተብለው ዘውድ ከጫኑበት ከመስከረም 27/1921 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ደርግ ከሥልጣናቸው እስካወረዳቸው ድረስ የንጉሡን አስተዳደር በታሪክ ትምህርት የሰለጠኑ ብዙ ምሁራኖች መረጃዎችን (data) በመሰብሰና በወቅቱ ከነበሩ ታሪካዊ ሂደቶች ጋር በማገናዘብ፤ ከእነርሱ ፍላጎትና ምርጫ ነፃ በሆነ መንፈስ መረጃዎችን ብቻ መሠረት ያደረገ ጥናተና ትንትና አድርገዋል። ማንኛውም ታሪክ ፀሐፊ ይህ ይጠበቅበታል። ንጉሡ በ ዤኔቭ በድርጅቱ አባል መንግሥታት መሪዎች ጉባኤ ተገኝተው አገራቸው ኢትዮጵያና ሕዝባቸው በፋሽስት ጣሊያን የወራሪ አውሮፕላኖች በሚዘንብባቸው የመስታርድ ጋዝ እየተቃጠሉና እየታፈኑ በስቃይ እየሞቱ ስለመሆናቸው እሮሮና አቤቱታ ማቅረባቸውን ማቃለልዎትና የሚገባውን ትኩረት አለመስጠትዎት፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት የሲሪያ መንግሥት በሕዝቡ ላይ የተጠቀመውን የመርዝ ጋዝ በማውገዝ በአሜሪካና በረሽያ እንዲሁም በሌሎች መንግሥታት መካከል ከሚታየው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ትግል አንፃር ሲታይ፤ የእርስዎ አመለካከት የቱን ያህል ኋላ ቀር እንደሆነ ያሳያል። ኮሎኔል የሚከተለውን ጥያቄ በማቅረብ ከእርስዎ ጋር ያለኝን ውይይት አበቃለሁ፤ በመጽሐፍዎት ምዕራፍ አስር ገጽ 258 የኮሎኔል አጥናፉ አባተ ግድያ ለምን አስፈለገ ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ የሚከተለውን የደርግ መሠረታዊ መርሕን principle አስቀምጠዋል። “ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምናልባትም ዓለም ጭምር ስለደርግ ማወቅ ያለበት አንድ ነገር አለ። ለምንወዳት አገራችን ለኢትዮጵያ መሠረታዊ ለውጥ በመታገል ሕይወታችንን እንሰጣለን ብለን ለራሳችን ቃል ኪዳን ስንገባ፤ ከገባነው አብዮታዊ ቃል ኪዳን ዝንፍ ብንል፤ የኢትዮጵያ ትቅደም አብዮታዊ ሠይፍ ይረፍብን በማለት ምለን ነው።” ጥያቄው እንግዲህ እርስዎ በዚያ ማለዳ ጥዋት ብላቴን የወታደር ሥልጠና በማግኘት ላይ የነበሩትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ለማነጋገርና ለመጎብኘት በሚል ሰበብ ከአዲስ አበባ ተነስተው፤ የአውሮፕላኑን አብራሪ መንገዱን አስለውጠው፤ ጓዶችዎን ሳይሰናበቱ፤ ወደ ናይሮቢ ከዚያም አሁን መኖሪያዎ ወደ ሆነችው ወደ ሐራሬ መሄድዎን፤ ከደርጉ መሠረታዊ መርህ ጋር እንዴት ያስታርቁታል? ጤና ይስጥልኝ ! ፕሮፌሰር ሰለሞን ተርፋ በ st2151@bellsouth.net አድራሻ ይገኛሉ

2 comments:

  1. bhewenyu betam aszghe tarike new tadya yhane sew tarike yefaredewalhe weynse endzhe yeqere yhune ferdune lethiopia ezbe metew new..........

    ReplyDelete
  2. This comment has been removed by the author.

    ReplyDelete