Thursday, November 7, 2013

ኢትዮጵያ፣ የቦምብ ፍንዳታ እና ማስጠንቀቂያው


ኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር ጥቃቶች ሊደርሱ ይችላሉ በሚል የጸጥታ ኃይሎች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ በታዘዙበት በኣሁኑ ወቅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኣንድ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በፈነዳ ቦምብ አራት ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ።
ከሶስት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አዲስ ኣበባ ላይ ከናይጄሪያው ቡድን ጋር በሚጫወትበት ዕለት ጥቃት ለማድረስ ሲዘጋጁ ነበር የተባሉ ሁለት የሶማሊያ ኣጥፍቶ ጠፊዎች በራሳቸው ቦምብ መሞታቸው ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡም ጥንቃቄ እንዲያደርግ መንግስት እያሳሰበ ሲሆን የጥንቃቄ ማስጠንቀቂያውን ተከትሎም በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ቁጥጥሩ መጠናከሩም ተሰምቷል።
የዛሬ ሶስት ሳምንታት ገደማ መሆኑ ነው የኢትዮጵያ የእግር ኩዋስ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አዲስ ኣበባ ላይ ከናይጄሪያው ብ/ቡድን ጋር በሚጫወትበት ዕለት ጥቃት ለማድረስ ሲሞክሩ ነበር የተባሉ ሁለት የሶማሊያ ኣጥፍቶ ጠፊዎች የራሳቸው ቦምብ ፈንድቶባቸው ከቤታቸው ሳይወጡ መሞታቸውን የኢትዮጵያ ፖሊስ ኣስታውቆ ነበር። ይኽንኑ ተከትሎ የኢትዮጵያ የደህንነትና ጸጥታ ባለስልጣናት ኣልሸባብ በአዲስ ኣበባ እና በተለያዩ የኣገሪቱ አካባቢዎች ጥቃት ለማድረስ እየተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ የፖሊስ እና ጸጥታ ኃይሎች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ማዘዛቸውን ገልጿል።
ባለፈው ማክሰኞ ደግሞ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰኞ ገበያ በተባለ ስፍራ በህዝብ ማማላለሻ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ላይ የፈነዳ ቦምብ አራት ሰዎችን መግደሉ ተዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግስት ከኣልሸባብ በተጨማሪም በኤርትራ መንግስት ይደገፋሉ የሚላቸውን ሌሎች በኣገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎችን ከሽብር ጥቃት ጋር ኣያይዞ ሲወነጅል መቆየቱም ኣይዘነጋም።
የፊታችን ህዳር 29 ቀን በጅጅጋ ከተማ ይከበራል ተብሎ ከሚጠበቀው ዓመታዊ የብ/ብ/ ቀን ጋር በተያያዘ ዓማጺው የኦጋዴን ነጻ ኣውጪ ግንባር ጥቃት ሊያደርስ ይችላል በሚል በጅጅጋ ከተማ እና በአካባቢው የጸጥታ ቁጥጥሩ እጅግ መጠናከሩ ሲታወቅ በጅጅጋ ጎዳናዎች ላይ በየ 50 ሜትሩ ሰዎች በፍተሻ እንደሚዋከቡና ካለፉት ጥቂት ቀናት ወዲህ ደግሞ በጅጅጋ ከተማ የቤት ለቤት ፍተሻም እየተካሄደ መሆኑ ተሰምቷል።
በተቀሩት የኣገሪቱ ኣካባቢዎችም ህዝቡ የጸጉረ ልውጥ ሰዎች እንቅስቃሴን እየተከታተለ ለመንግስት እንዲጠቁም እና በተለይ የሆቴሎች አልጋ ኣከራዮችና በየመንደሩ ያሉ ቤት ኣከራዮችም ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ የተለየ ነገር ሲያጋጥም ወዲያውኑ ለመንግስት እንዲያሳውቁ መንግስት ኣሳስቧል።
ስለዚሁ ጉዳይ እንዲያብራሩልን የኢትዮጵያው የኮሞኒኬሺን ጉዳዮች ሚኒስትር ዲዔታ አቶ ሽመልስ ከማል ዘንድ ስልክ ደውለን ነበር። ፈቃደኛ ግን ኣልነበሩም። የኮሚኒኬሺን ጉዳዮች ሞኒስትሩ አቶ ሪድዋን ሁሴን ግን ለመንግስታዊው የኢትዮጵያ ቴሌቪዢን እንደገለጹት መንግስታቸው የሽብር ጥቃት መታቀዱን መረጃ ማግኘቱን ኣውስተው ህዝቡ ጥንቃቄ በማድረግ እና ለመንግስት ጥቆማ በማቅረብ እንዲተባበራቸው ጥሪ ኣድርጘል።ሆኖም ግን ከጥንቃቄ ያለፈ ህብረተሰቡ ተሸብሮ የዕለት ተለት እንቅስቃሴውን እንዲያቆም የሚያስገድድ ነገር ኣለመኖሩንም አቶ ርድዋን ኣስረድቷል።
በኣልሸባብ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ፍጥጫ መኖሩ ኣይካድም የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ጀዋር መሃመድ የኣሁኑ የኢትዮጵያ መንግስት ማስጠንቀቂያና መግለጫ አዲስ ነገር የለውም ይላሉ። እንደ አቶ ጀዋር ይህ የኢትዮጵያ መንግስት ተቀናቃኞቹን ለማሰር እና የፖለቲካ ትርፍ ለመሸመት የሚጠቀምበት የተለመደ የፕሮፓጋንዳ ስልት ነው።
በዩኤስ አሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ጥናት በማድረግ ላይ የሚገኙት አቲ ጀዋር መሐመድ ከወዲሁ ማስተካከያ ካልተበጀለት የዚህ ኣይነቱ ኣካሄድ አደጋም ኣለው ባይ ናቸው። ምክኒያቱም አቶ ጀዋር እንደሚሉት ተጨባጭ ነገር ሳይኖር ጥቃት ሊፈጸም ነው እየተባለ ህዝቡ የተለመደ የመንግስት ፕሮፓጋንዳ ነው እያለ በተዘናጋበት ኣጋጣሚ እውነተኛው የሽብር ጥቃት በተቃጣ ጊዜ መንግስት ከጎኑ የሚቆምለት ህዝብ ያጣል። አደጋውም የከፋ ይሆናል።
ባሳለፍነው ወር የአልሸባብ ታጣቂዎች በኬኒያ ናይሮቢ በሚገኘው የዌስት ጌት የበያ ማዕከል ላይ በጣሉት ጥቃት 67 ንጹኃን ዜጎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን እ ኣ ዘ ኣ በ 2010 በጎረቤት ኡጋንዳ የዓለም ዋንጫ ጫወታን ለመከታተል በታደሙ ዜጎች ላይ በደረሰ የቢምብ ፍንዳታም እንዲሁ 74 ያህል ሰዎች መሞታቸው ኣይዘነጋም።
ጃፈር ዓሊ

No comments:

Post a Comment