Friday, November 8, 2013

ኢህአዴግንና ተቋማቱን ለምን ማመን ተሳነን?


በእኛ አገር መንግስትና ፓርቲን መነጠል አይቻልም፡፡ ህገ መንግስቱ ሳይቀር በብዙ አንቀጾቹ  የገዢው ፓርቲ ፕሮግራም ግልባጭ መሆኑ ትስስሩን ላቅ ያደርገዋል፡፡ስለዚህ መንግስት ሲለወጥ ባንዲራ፣ህገ መንግስት፣ብሄራዊ መዝሙር እንቀይራለን፡፡የመንግስት ስርዓት መዘርጋት አለመቻላችን ያመጣብን ጣጣ ልንለው እንችላለን፡፡
ህዝቡ በፓርቲው እምነቱን አጣ ማለት መንግስትንም አያምነውም ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ኢህአዴግ በኢትዮጵያ የመንገስታት ታሪክ አመኔታ በማጣት ረገድ ግምባር ቀደሙ ይመስለኛል፡፡እምነት የጠፋበት አጋጣሚም ከኢህአዴግ የትጥቅ ትግል ቆይታ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ደርግ የያኔዎቹን አማጺያን ወንበዴ፣አገር አስገንጣይ በማለት ይፈርጃቸው ነበር፡፡ከተሜው የደርግን ፕሮፓጋንዳ ሲጋት በመቆየቱ ተጋዳላዮቹ ወደ ከተማ ሲገቡ የተቀበላቸው በፍርሃት ድባብ ታስሮ ነበር፡፡
ትግራይን ነጻ ለማውጣት በረሃ የገቡት የትግራይ ልጆች የህዝቡን አመኔታ ለማግኘት የሐውዜንን ድብደባ ለደርግ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የቪዲዮ ካሜራ በማዘጋጀት የተዋጣለት ፊልም መቅረጻቸውና ለጊዜውም ቢሆን በዚህ ምክንያት የትግራይ ህዝብን ድጋፍ ለማግኘት ቢበቁም እያደር ግን የሐውዜን ምስጢር አፈትልኮ መውጣቱ ተአማኒነታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሯል፡፡በግሌ እምነት የሰጧቸው ዋና ዋና ተግባሮቻቸው የሚከተሉት ናቸው
—- በትግራይ መንግስት የወረሳቸውን ቤቶች በመመለስ ለሌሎቹም ይህንን እንደሚያደርጉ ቃል ቢገቡም ቃላቸውን መጠበቅ አለመቻላቸው
—- የአልባንያን ሶሻሊዝም ተጋዳላዮቹን ይግት የነበረው ኢህአዴግ አዲስ አበባን ለመቆጣጠር ከጫፍ በደረሰበት ወቅት የምዕራባዊያንን ድጋፍ ለማግኘት ራሱን ነጭ ካፒታሊስት በማድረግ መጥራት መጀመሩ ርዕዮት አልባ አድርጎታል፡፡ይህም በሚከተለው የፖለቲካ ፍልስፍና አቋመ ቢስ ስላደረገው የገዛ ታጋዮቹን እምነት አሳጥቶታል፡፡
—–በበደኖ፣በአርባጉጉና በአሰቦት  በተፈጸሙ አንድ ብሄር ላይ ያነጣጠሩ ጭፍጨፋዎች  ኦህዴድና/ኦነግ ሃላፊነት በመውሰድ መጠየቅ ይገባቸው የነበረ ቢሆንም ኢህአዴግ የኦህዴድን እጅ እንደ ጲላጦስ በማጠብ የደሙን ዋጋ ኦነግ ላይ መጣሉ በኦሮሚያ አማኝ አሳጥቶታል፡፡
—– የመምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት የነበሩትን መምህር ዶክተር ታዬ ወ/ሰማያትን የ17 ዓመት እስራት ሲያከናንብ በዜና ያስደመጠው ‹‹ታጣቂ ቡድን እያደራጁ ነው››ብሎ የነበረ ቢሆንም በፍርድ ቤት ይህንን ማስመስከር አልቻለም፡፡
—–እነ ርዕዮት አለሙ በታሰረበት ቅጽበት ምሽቱን በኢቴቪ የተደመጠው ዜና ‹‹በመንግስት መሰረተ ልማቶች ላይ አደጋ ለማድረስ ሲያሴሩ ተገኝተዋል፡፡››ተብሏል፡፡ፍርድ ቤት ጋዜጠኞቹ በቀረቡበት ወቅት ግን በኢቴቪ የቀረበው በክሳቸው ውስጥ አልተካተተም፡፡ይህም አመኔታን የሚያሳጣ ድርጊት ሆኖበታል፡፡
—-የ1997 ምርጫን ነጻና ፍትሃዊ አደርጋለሁ በማለት ቃል የገባው ኢህአዴግ ለ200 ሰዎች ዕልቂት መንስኤ የሆነን ኮሮጆ ግልበጣ ፈጽሟል፡፡
—-የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቢሮን ለአመታት ተቆጣጥረውት የነበሩት አቶ ስዮም መስፍን የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ፍርድን ለኢትዮጵያ ህዝብ ባስደመጡበት ወቅት ‹‹እንኳን ደስ አለን ብዙ ሺህ የህይወት ዋጋ የከፈልንባት ባድመ ለእኛ ተፈረደች››በማለት ህዝቡ ደስታውን በሰላማዊ ሰልፍ እንዲገልጽ ቢያደርጉም እውነታው ግን ባድመ ለኤርትራ መወሰኗ ነበር፡፡
—- በተለያዮ ቦታዎች ስለተፈጸሙ የቦንብ ፍንዳታዎች መንግስት ተቃዋሚዎችን ተጠያቂ ቢያደርግበትም ዊኪሊክስ በቅርቡ በለቀቀው መረጃ መንግስት ሆን ብሎ እንዲህ አይነት ድራማዎችን እነደሚሰራ አጋልጧል፡፡እስከ እናንተ ለምን መንግስትን እንደማታምኑ ምክንያታችሁን አካፍሉን፡፡
source: dawitsolomon

No comments:

Post a Comment