Wednesday, October 9, 2013

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአራት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሥራ ዝውውር በዚህ ሳምንት ውስጥ ሊያደርግ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

መነሻ ገጽ – ዜና – የአራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሥልጣን ዝውውር ሊደረግ ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የአራት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሥራ ዝውውር በዚህ ሳምንት ውስጥ ሊያደርግ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ዝውውሩን የሚያደርገው በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፋሰስ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ጃርሶ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ቤኔሉክስ (ቤልጂየም፣ ኔዘርላንድና ሉግዘንበርግ) አገሮች አምባሳደር ዶ/ር ካሱ ኢላላና በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር በሆኑት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ላይ መሆኑን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ በሚደረገው ዝውውር መሠረት አቶ ዓባይ ፀሐዬ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና ምርምር አማካሪ ሚኒስትር፣ በአቶ ዓባይ ቦታ ደግሞ አቶ ሽፈራው ጃርሶ በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር፣
ዶ/ር ካሱ ኢላላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና ምርምር አማካሪ ሚኒስትር ሲሆኑ፣ ዶ/ር ካሱን በመተካት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የአውሮፓ ኅብረትና ቤኔሉክስ አገሮች አምባሳደር ሆነው ወደ ብራሰልስ እንደሚዛወሩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ አምባሳደር ተሾመ ቶጋን በመተካት በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው የሚሾሙት ደግሞ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ነጋ ፀጋዬ መሆናቸውን ምንጮች አክለዋል፡፡ አቶ ዓባይ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት ይገነባሉ የተባሉትን አሥር የስኳር ፋብሪካዎችንና የሸንኮራ አገዳ ልማት በሚመለከት፣ ከተለያዩ የቻይና ኩባንያዎችና ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመነጋገርና በመስማማት ሥራውን ለማስጀመር ጫፍ ላይ መድረሳቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ የሽንኮራ አገዳ ልማቱ በመስኖ መካሄድ ስላለበትና ለዚህ ደግሞ ባላቸው ዕውቀትና ልምድ ለሥራው ቅርብ ናቸው የሚባሉት የቀድሞው ውኃ ሀብት ልማት ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ጃርሶ በመሆናቸው፣ በአቶ ዓባይ ምትክ እንዲሾሙ ውሳኔ ላይ መደረሱን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱን በተባለው ፍጥነት በማቀላጠፍ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት በመዘግየቱ፣ አቶ ሽፈራው ያላቸውን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም ሊያሳኩት ይችላሉ የሚል ግምት መያዙን ምንጮች አክለዋል፡፡ የባለሥልጣናት የሥራ ዝውውርና ሽግሽግ ሊቀጥል እንደሚችል ምንጮች ጠቁመው፣ የአራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የሚኒስቴር ዴኤታው ምደባ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይፋ ሊደረግ ይችላል ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ኩማ ደመቅሳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና ምርምር አማካሪ ሲደረጉ፣ አሁን ደግሞ አቶ ዓባይ ፀሐዬና ዶ/ር ካሱ ኢላላ ተጨምረዋል፡፡ source,,http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/3569-የአራት-ከፍተኛ-ባለሥልጣናት-የሥልጣን-ዝውውር-ሊደረግ-ነው

No comments:

Post a Comment