To breathe Democracy in Ethiopia , lets us fight together for our Freedom and Justice !!!!!
Wednesday, October 2, 2013
አንድነት በመንግስት ዛቻ አንደናገጥም አለ
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ከ33ቱ ፓርቲዎች ጋር በመሆን መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም በቀበና አካባቢ በተወሰነው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በሽብርተኝነት ጥፋተኛ ተብለው የታሰሩ ሰዎችን ይፈቱ ማለቱ፣ እንዲሁም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያለን የሙስሊም ኮሚቴ አባላት እንዲፈቱ መጠየቁና ባልተፈቀደ ቦታ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል በሚለውን የመንግስት ምላሽ ማዘኑንና በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ዛቻ እንደማይደናገጥም አስታወቀ።
የፓርቲው ምክትል ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ጉዳዩን በማስመልከት በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት በመንግስት በኩል ሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎ ፈጣን ምላሽ በአቶ ሽመልስ ከማል በኩል መገለፁን ፓርቲው መገንዘቡን ከገለፁ በኋላ በሚኒስትር ዲኤታው በኩል የተገለፀው ነገር የመንግስት አቋም ስለመሆኑ ቢያጠራጥርም ምላሹ ግን የህግ ትርጓሜን በማዛባት የቀረበ ነው ብለዋል።
“አቶ ሽመልስ ከመዛት ግላዊ ባህሪያቸው ተነስተው “ሕግ የሚያመጣውን መዘዝ ለመቀበል ይዘጋጁ” ማለታቸው ሁላችንንም ያሳዘነ አገላለፅ ነው። እኛ ሕግ አስተማሪና ቀጪ መሆኑን እንጂ መዘዝ መሆኑን አናውቅም። ካጠፋን ልንማር እንችላለን መንግስትም ካጠፋ ከስህተቱ ሊማር ይገባል ብለን እናምናለን። ስለዚህ የህግ መዘዝ አለው ማለት ለእኛ ከዛቻ የተሻለ ትርጉም የለውም” ብለዋል። አቶ ሀብታሙ ጨምረው እንደገለፁት የሚኒስትር ዲኤታው ንግግር በፖለቲካ ይዘትም ሆነ ከህግ አንፃር መሰረት የሌለው ነገር ከመሆን በዘለለ ይሄንን ሀገር በተሻለ ብቃት የመምራት አቅም ማጣታቸውን ማሳያ ነው ብለዋል።
አቶ ሽመልስ ከማል ካነሱዋቸው ነጥቦች መካከል “ሰልፉ ባልተፈቀደ ቦታ ተካሂዷል” የሚለው ወቀሳ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ “በእርግጠኝነት የአዲስ አበባ አስተዳደር ለአንድነት ፓርቲ በፃፈው ደብዳቤ የሰላማዊ ሰልፉ መነሻ ከፓርቲው ጽ/ቤት ተነስቶ በቀበና አደባባይ አድርጎ፣ ወደ ጃንሜዳ አምርቶ፣ ሰልፉ እዛው ጃንሜዳ እንዲጠናቀቅ የሚል ነው። ይህ ውሳኔ የደረሰንም የእኛን ሰልፍ ለማደናቀፍ፣ ያቀረብናቸውን ዘጠኝ አማራጮችንም በመቀልበስ፣ ባልፈለግነውና ባልመረጥነው ቦታ እንዲፈፀም ነው የተደረገው። ይህ ነገር ከሞራልም ከህግም አንፃር ተቀባይነት ባይኖረውም ለህግ ተገዢ በመሆን ወደ መስቀል አደባባይ የምናደርገውን ጉዞ በፖሊስ በከፍተኛ ኃይል መጥቶ መንገድ በመዘጋቱ፤ ከፖሊስ ጋር ግብግብ መፍጠሩን በመተው ወደቀበና አደባባይ በመዞር ቀበና አደባባይ ላይ ሰልፉን ለማጠናቀቅ ተገደናል። ወደጃንሜዳ ያልሄድንበት ምክንያት ኢህአዴግ ህግ እንድንጥስ በር ሲከፍትልን ህግ ላለመጣስ ብለን ወደጃንሜዳ አልሄደንም። ጃንሜዳ ያልሄድነው ቦታው ከጦር ካምፕ በ20 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የሀገሪቷ ህግ ደግሞ ማናቸውም ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከጦር ካምፕ ካለበት ቢያንስ 500 ሜትር ርቆ መካሄድ አለበት ስለሚል ነው” ብለዋል። ይህም ባልተፈቀደ ቦታ ሰልፍ ማካሄድ ሳይሆን ለሀገሪቱ ህግ ያለንን ተገዢነት ያሳየንበት ስለሆነ ሁኔታው የእኛን ሕጋዊነት ያሳየ ሲሆን በአንፃሩ እነ አቶ ሽመልስ የሚመሩት መንግስት ሕገ-ወጥነት ማረጋገጫ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በሕግ አግባብ ሲታይ ሃያ ሜትር የጦር ካምፕ ስር ሄዶ መሰለፍ ነው ወይስ እንዲሰለፉ ፈቃድ የሰጠው አካል የሚጠየቀው? ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል።
“ሌላው በነፃ ፍርድ ቤት አሸባሪ የተባሉትን ሰዎች እንደ ሰማዕት አስመስለው “መልዕክቶቻቸውን አንብበዋል” የሚለው የአቶ ሽመልስ ማስፈራሪያ ከሀገሪቱ ሕገ-መንግስት ጋር ይጋጫል የሚሉት አቶ ሀብታሙ የሀገሪቱ ሕገ-መንግስት በግልፅ እንዳስቀመጠው ማንኛውም የፍርድ ቤት ውሳኔ ከፍርድ ውሳኔ በኋላ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መቃወም ወንጀል ሳይሆን መብት ነው ብለዋል። እንኳንስ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ቀርቶ አንድ ግለሰብ ከፍርድ ውሳኔ በኋላ ውሳኔውን መቃወም መብት ሆኖ ሳለ አቶ ሽመልስ ግን ነፃ በሚሉት ፍርድ ቤት የተወሰነውን ውሳኔ ጥሳችኋል ማለታቸው ተገቢም ተቀባይነትም የለውም ብለዋል።
“አቶ ሽመልስ የሚመሩት ድርጅት በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ነፃ ናቸው ብሎ ያምናል። በአንፃሩ የእኛ ፓርቲ ደግሞ ነፃ ፍርድ ቤት የለም ብሎ ያምናል። በዚህ ረገድ የአቋም ልዩነት አለን። ነፃ ፍርድ ቤት የለም ብለን አቋም መያዝ የፖለቲካ መብታችን ነው። አቶ ሽመልስ ይሄ የፖለቲካ መብት መሆኑ ካልገባቸው በቀር ነፃ ፍርድ ቤት የለም ብለን ስናበቃ፤ ነፃ ያልሆነ ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ አንቀበልም ማለት በእኛ እምንት ተገቢ ነው። ህግ መጣስ የሚመጣው ያ ነፃ አይደለም ያልነው ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ በኃይል ለመቀበልስ ከሄድን ብቻ ነው። እኛ ግን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሰላማዊ መንገድ ነው የተቃወምነው። ይሄ ደግሞ መብት ነው እንጂ ወንጀል አይደለም” ሲሉ አቶ ሀብታሙ መልሰዋል።
በተጨማሪ አቶ ሽመልስ “በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ሽብርተኝነት አበረታተዋል” ሲሉ ከሰውናል ያሉት አቶ ሀብታሙ በመጀመሪያ ደረጃ እኛ የታሰሩት ሰዎች ሽብርተኛ ናቸው ብለን አናምንም። አለማመን ደግሞ መብት ነው። ፍርድ ቤቱ የሰጠውንም ውሳኔ ተገቢ ነው ብለን አናምንም። እንደ ፓርቲም መቃወማችንን እንቀጥላለን። እነሱ ሽብርተኛ ያሉዋቸው ሰዎች ቀደም ሲል እስር ቤት ሆነው ኀሳባቸውን በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶች ሲገልፁ ቆይተዋል። ነገር ግን ለኢህአዴግ ህመም የፈጠረበት በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ሲገለፅ ነው። ይሄ ደግሞ የሰልፉ ውጤት ኢህአዴግን ስላስከፋው እንጂ ህግ መጣስ አይደለም። በተጨማሪም አንድ ሰው በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ኃይሉ ዜሮ በሆነበት ሁኔታ “አበረታታችኋል” ማለቱ ትርጉም የለውም። ስለዚህ ሽብርተኝነትን የምናበረታታበት ምንም ዕድል የለም ብለዋል።
የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን በተመለከተም በትክክልም በፍርድ ሂደት ላይ ያለ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሀብታሙ በፍርድ ሂደት ላይ ያለን ነገር መቃወም ተገቢ አይደለም ብለዋል።
“ነገርግን አቶ ሽመልስ የተረዱን አይመስለኝም” ያሉት አቶ ሀብታሙ እኛ እየተቃወምን ያልነው ፍ/ቤቱን ሳይሆን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን “ጀሀዳዊ ሀረካት” የሚል ዘጋቢ ፊልም ሰርቶ ተጠርጣሪዎቹን “አሸባሪ” ብሎ ከፍርድ ቤቱ በፊት መወሰኑን ነው። ይሄንን ደግሞ በአደባባይ መቃወም አሸባሪን መደገፍ አይደለም። ፍርድ ቤቱ የሚወስነውን ከወሰነ በኋላ ደግሞ የምንይዘውን አቋም እንይዛለን። ነገር ግን አሁን ፍርድ ቤቱ “ተጠርጣሪ” እያላቸው ኢቲቪ ግን “አሸባሪ” ብሏቸዋል። እኛ ደግሞ “የለም እነዚህ ሰዎች ተጠርጣሪ እንጂ አሸባሪ አይደሉም” ብለን ተሟግተናል። የምንቃወም ይሄንኑ ነው በማለት አስረድተዋል።
“ሌላው በሽብርተኝነት የታሰሩ ይፈቱ ብላችኋል” የሚለው የአቶ ሽመልስ ከማል ክስ በተመለከተም ፍ/ቤት በነፃነት የመወሰን መብቱ ኢቲቪ ባስተላለፈው ፊልም ነፃነቱን በመጋፋቱ በተያዙት ሰዎች ላይ ነፃ ፍርድ ይሰጣል ብለን አናምንም። ስለዚህም ሰዎች በነፃ ይለቀቁ ብለን መጠየቃችንን የሕግ መዘዝ ያመጣል ማለት የመንግስት ስልጣናቸውን ከመመካት የሚመነጭ እንጂ የሕግ መሰረት የለውም ብለዋል። በአጠቃላይ የአቶ ሽመልስ ምላሽ በግብታዊነት ፓርቲው ላይ እርምጃ ለመውሰድና ሰላማዊ ትግሉን ለማዳፈን በመሆኑ መዘዙ የከፋ ነው ሲሉ በበኩላቸው መልሰዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል እሁድ ዕለት ማምሻውን ለኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት በሰጡት ማብራሪ አንድነት ፓርቲ ባልተፈቀደለት ቦታ ሰልፍ ማካሄዱን እንዲሁም በሰልፉ ላይ በሽብርተኝነት ጥፋተኛ ተብለው የታሰሩ ሰዎችን በማወደስና እንዲፈቱ በመጠየቅ ሽብርተኝነት ማበረታታቱን በመግለፅ ህገ ወጥ ተግባር መፈፀማቸውንና ፓርቲውም ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ መጠየቃቸው አይዘነጋም።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment