Saturday, August 3, 2013

“ሰማያዊ ፓርቲ፣ግንቦት ሰባት እና አክራሪዎች ጋብቻ ፈፅመዋል” Posted: August 3, 2013 in Amharic News 0 qq ሙሉጌታ ውለታው፤ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ሰማያዊ ፓርቲ፤ ግንቦት ሰባት እና አክራሪዎች ህገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጪ ሀይማኖትና ፖለቲካን በማደባለቅ ለመስራት ጋብቻ ፈፅመዋል ሲሉ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው ተቹ፡፡ ከነሐሴ 21-23 ቀን 2005 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የሀይማኖት ኮንፈረንስ በማስመልከት በአዳማ ከተማ ለሚዲያ እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች እየተሰጠ ባለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ገባ ማለት በእሳት ተጫወተ ማለት ነው፤ አሁንም ሆነ ወደፊት ጣልቃ አይገባም” ብለዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሙስሊሙ ህብረተሰብ የሀይማኖት ነፃነት አልተከበረም በሚል ተቃውሞ ማሰማታቸው እንዴት ይታያል? በሚል የተጠየቁት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “በክርስቲያንም ሆነ በሙስሊሙ ያልተመለሰ የሀይማኖት ጥያቄ የለም፤ ያልተመለሰም ካለ የሰማያዊ ፓርቲ እና የግንቦት ሰባት ጥያቄ ነው” ያሉት ሚንስትር ዴኤታው፤ የነዚህ አካላት ጥያቄም ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ የፖለቲካ ጥያቄ እንጂ የሀይማኖት አለመሆኑ ግልፅ ነው ብለዋል፡፡ “በዚህ ጉዳይ ላይ አጥፊና አፍራሽ ጉዳዮችን አብሮ ለመፈፀም ሰማያዊ ፓርቲ፣ ግንቦት ሰባት እና አክራሪዎች ጋብቻ ፈጽመዋል፤ ጋብቻቸውም ግልጽ ያልሆነ እና “ኦድ ኬሚስትሪ” (ያልተለመደ ቁርኝት) ነው” ብለዋል፡፡ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ እየገባ ነው በሚል የሚነሳውን ወቀሳ በተመለከተ ሲናገሩም፤ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ገባ ማለት በእሳት ተጫወተ ማለት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፤ አክራሪዎች በሚያነሱት ረብሻ ሰላማዊ ህዝብ እንዳይበጠበጥ መንግስት ሠላም የማስከበሩን ሃላፊነትን ሲወጣ ጣልቃ ገባ ማለት አግባብ አለመሆኑንና አንዲትም ኢንች ጣልቃ እንዳልገባና ወደፊትም እንደማይገባ ገልፀዋል፡፡ አክራሪዎች ጥቂት ናቸው ከተባለ ለምን ጉዳዩ እንዲህ አንገብጋቢ ሆነ ተብሎ ለተነሳው ጥያቄም “ጉዳዩ አለምአቀፍ ስጋት ነው፤ ችላ ከተባለ የዕንቁላሉ ስርቆት ወደ በሬ ስርቆትነት ስለሚሸጋገር በእንጭጩ መቀጨት አለበት”ያሉት ሚንስትር ዴኤታው፤ መንግስት እየሰራ ያለው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ አይነት እርምጃ እንደሆነም አስምረውበታል፡፡ የሼሁን ግድያ በተመለከተ፤ ተጠርጣሪዎች ፍ/ቤት ቀርበው ሳይፈረድባቸው በመንግስት መገናኛ ብዙሃን አሸባሪ መባላቸውን በተመለከተ ሲመልሱ፤ “መገናኛ ብዙሃኑ ተጠርጣሪ እንጂ አሸባሪ አላሉም” ሲሉ በማለት አስተባብለዋል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙት “የሙስሊሞች ችግር መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላት ቀደም ሲል ከመንግስት ጋር ሲደራደሩ የነበሩ ከመሆኑ አንፃር፣ እነሱን “አሸባሪ” ብሎ ማሰሩ ጉዳዩን አክርሮታል ይባላል በሚል ስለ ጉዳይ የተጠየቁት ሚኒስትር ዴኤታው፤ “የሀይማኖት ጥያቄ አንስቶ የታሰረ የለም፤ ያጠፉትም ቢሆኑ ሁሉም አልታሰሩም” ካሉ በኋላ በተመረጠ አካኋን ከሀይማኖት ውጪ ችግር ሲፈጥሩ በፖሊስ የተያዙ ጥቂት ሰዎች ብቻ መታሰራቸውን እና ስለጥፋተኝነታቸውም ፖሊስ ተጨባጭ ማስረጃ እንዳለው አብራርተዋል፡፡ “የሀይማኖቶች በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን በማጎልበት እና ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር የሀገራችንን ህዳሴ ጉዞ ለማሳካት እንረባረባለን” በሚል መሪ ቃል ከነሀሴ 21-23 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ለሚደረገው አገር አቀፍ የሀይማኖት ኮንፈረንስ፣ ጋዜጠኞች ሊኖራቸው በሚችለው ሚና ዙሪያ የተሰጠው ስልጠና ትላንት አመሻሽ ላይ ተጠናቋል፡፡

No comments:

Post a Comment