To breathe Democracy in Ethiopia , lets us fight together for our Freedom and Justice !!!!!
Wednesday, August 21, 2013
Wednesday, August 21, 2013 ከአዲስ አበባ ያልተነገሩ የሙስና ገመናዎች
ለዚህ ጽሑፍ መንደርደርያ እንዲሆን የቅርብ ጊዜ ጎረቤት አገሯን ታሪክ ላንሳ፡፡ ደቡብ ሱዳን ከእልህ አስጨራሽ ወጊያ ተካሂዶ ነፃነቷን ከተቀዳጀች ከወራት ዕድሜ በኋላ የሙስና ወሬ በጣም ጎልቶ ተሰማ፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ‹‹ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ ተወጋን፡፡ ነገር ግን ሥልጣን ላይ ስንወጣ ዓላማችንን ስተን የሕዝብን ገንዘብ መዝረፍ ጀመርን፡፡ በመሆኑም በአገራችን በተስፋፋው ሙስና የተነሳ ዛሬ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለድንጋጤ ተዳርጓል፡፡ የሕዝብና የመንግሥትን ገንዘብ መዝረፍ ብዙዎች የተሰውለትን ዓላማ እንደመክዳት የሚቆጠር በመሆኑ በሙስና ገንዘብ የዘረፋችሁ ሁሉ ልትመልሱ ይገባል፤›› ሲሉ ደብዳቤ በተኑ፡፡
በእርግጥም ፕሬዚዳንቱ በጻፉት ደብዳቤ ገንዘቡን ለሚመልሱ ባለሥልጣናት ሙሉ ምሕረት እንደሚደረግ ካስታወቁ በኋላ 60 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ተመላሽ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን አገሪቱ ከሰሜን ሱዳን ጋር ሁለገብ የሰላም ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ባለው አንድ ዓመት ብቻ 1.5 ቢሊዮን ዶላር እንደተመዘበረ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ. ሰኔ 2012 የአገሪቱ ፓርላማ 75 የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከሙስና ጋር በተያያዘ ከሥልጣን አስወግዶ መክሰሱም ይታወቃል፡፡ ከሰሞኑም ቢሆን ምንም እንኳ ከሥልጣን ሽኩቻ ጋር የተያያዘ ነው ቢባልም፣ በሙስና መዘዝ ምክትል ፕሬዚዳንቱና በርካታ የካቢኔ አባላት ተባረዋል፡፡ ለሙስና መራራት የሚያስከፍለው መስዋዕትነት ብዙ መሆኑን ሳልቫ ኪር የተረዱ ይመስላሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገና ‹‹ፊርማው ያልደረቀ›› (ይቅርታ የከንቲባ ለውጥ ብቻ ነው) ቢባልም ሙስና በአንድ ጀንበር ብዙ የሚሠራበት ነው፡፡ ለነገሩ የዚህ ጽሑፍ ትችት የሚያተኩረው በተለይ ‹‹ባለፈው አስተዳደር›› በሚባለው የአምስት ዓመታት ቆይታ ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ስለተከናወኑ ስኬታማ ሥራዎች ብዙ እየተነገረ መሆኑ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የውጤቶቹን ጭብጥ ያለመመርመርና አጋኖ ማቅረብ በአስተዳደሩ ውስጥ የኖረውን በሽታ ለማከም ያስቸግራል፡፡ ‹‹በሽታውን ያልተናገረ መድኃኒት የለውም›› እንደተባለው፡፡
የተዘረፈው የመሬት ሀብት ብዛት
የአዲስ አበባ መሬት ዝርፊያ ጣሪያ ነክቶ የነበረው በባለአደራ አስተዳደሩ ወቅት እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባደረጋቸው ልዩ ልዩ ጥናቶች እስከ 2003 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ሦስት ሚሊዮን ካሬ ሜትር የሚደርስ የአዲስ አበባ የሕዝብ መሬት በሕገወጥ ወረራ፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር ላልተገባ ጥቅም ውሏል፡፡ ይኼም በወቅቱ ባለው ዝቅተኛ ግምት እስከ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡
ይኼ ችግር ጫፍ የመድረሱ ማሳያ አንድ የማዘጋጃ ቤት ባለሙያ የከተማዋን ካርታ (ማስተር ፕላን) አውጥቶ በኮልፌ ቀራኒዮ ለ26 ማኅበራት ከ600 ለማያንሱ ሰዎች የቸበቸበበት ድርጊት ነው፡፡ ግለሰቡና ግብረ አበሮቹ ከ100 ሚሊዮን ብር በማያንስ በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረስ ከፍተኛ ወንጀል ተከሰው ቅጣታቸውን ያገኙ ቢሆንም፣ በአስተዳደሩ ከላይ እስከ ታች በችግሩ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሠራተኞችና ኃላፊዎች እንዳልተነኩ የሚያስረዱ አሉ፡፡ በወቅቱ የዞን አመራር የነበሩት ዛሬ ድረስ ሹመት በሹመት ላይ የተደረበላቸው ንፁህ ስለሆኑ ነው ወይ በማለት ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ፡፡
የከንቲባ ኩማ አስተዳደር ችግሩ ጫፍ በመድረሱ በ2003 ዓ.ም. የመጨረሻው ሩብ ዓመት ላይ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች አሉ፡፡ ወደ 1.8 ሚሊዮን ካሬ ሜትር የሚደርስ መሬት ከሕገወጥ የሪል ስቴት አልሚዎችና ተስፋፊዎች እጅ ቀምቶ ወደ መሬት ባንክ አስገብቷል፡፡ አንዳንዶች እስከ ስድስት ቢሊዮን ብር እንደሚገመት የሚያስረዱት ይህ የመሬት ሀብት ገቢ መደረጉ አንድ ዕርምጃ ቢሆንም፣ በተለይ ገንዘብ ከፍለው የገዙ ግለሰቦች ደግሞ ቀልጠው ቀርተዋል፡፡ በችግሩ ውስጥ በእግርጥ በእጃቸው ገብተው የተጨማለቁ ሙሰኞች ግን በስፋት ሲጋለጡ አልታየም፡፡
የአንዳንድ የለየላቸው ሙሰኞች ገመና ነካነካ ተደርጎ ታለፈ እንጂ፣ ከመሬት ዝርፊያው ጋር እስከ ላይ መፈተሽ ያለበት ብልሹ የድርድርና ከሊዝ ውጭ የኢንቨስትመንት ቦታ አሰጣጥ እንደነበር አዋቂዎች በሚገባ ይናገራሉ፡፡ በየደረጃው ያለው አመራር ሳይገማገም እያድበሰበሰ እንጂ፣ ሕዝቡ ውስጥ በአቋራጭ ካልሆነ መሬት እንደማይገኝ ተደጋግሞ ሲነገር መክረሙንም ያስረዳሉ፡፡
አስተዳደሩ በልደታ ክፍለ ከተማ ሙሉ ካቢኔ ሲያባርር፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚውን ጨምሮ በሙስና ሲያስከስስ፣ በሌሎች ክፍላተ ከተሞች ችግር ያለባቸውን አመራሮች ቦታ ከማዘዋወር አላለፈም የሚሉት ውስጥ አዋቂዎች፣ ብዙዎቹ ክፍላተ ከተሞች በመልሶ ማልማትም ሆነ በማስፋፊያ ሥራዎች ከፍተኛ የመሬት ዝርፊያ የተፈጸመባቸው ናቸው በማለት ይሞግታሉ፡፡ ለምን ችላ ተባሉ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ የኔትወርክና የመነካካት ጉዳይ እንዳይሆንም ይሰጋሉ፡፡
በከንቲባ ኩማ አስተዳደርም ሆነ በባለአደራ አስተዳደሩ የነበሩ አብዛኛዎቹ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ‹‹ሀብት ምዝገባን›› ከቦታ (መሬት) አንፃር የሚጠራጠሩ አስተያየት ሰጪዎችም አጋጥመውኛል፡፡ በኦሮሚያ የአዲስ አበባ ልዩ ዞን ሁለትና ሦስት ቦታ ይዘው በአዲስ አበባም ሕንፃ ገንብተው ወይም ቪላ ሠርተው፣ በመንግሥት ቤት የሚኖሩ የሉም? ይህንን ሁሉ ይዞታ ከምንና እንዴት እንዳገኙ ይታወቃል? የሙስና ትግሉን ቀፍድዶ የያዘው እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ሕዝቡ ውስጥ በይፋ የሚታወቅ ሀቅ መሆኑን በአንክሮ ይገልጻሉ፡፡ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ይሏል ይኼንን ነው፡፡
መሬት በተለይ ለሕዝብ ጥቅም ሊውል የሚችልን ሰፊ መሬት ‹‹ካለ ከልካይ›› ይዘው የተቀመጡ ዜጎችም የመሬት ሙስና ማሳያ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ለኢንቨስትመንት ከተወሰዱት ሌላ በየሥርቻው በጉልበተኛ የተወረሩ የሕዝብ ሱቅ ግቢዎች፣ ወፍጮ ቤቶችና መሰል ንብረቶች ማን ጠይቋቸው ያውቃል? ወንዝና የከተማ ተፋሰስ በሚባሉ ዳርቻዎች ከገጠር የመጡ የጨረቃ ቤት እየሠሩና እያከራዩ ከመኖር አልፈው ‹‹በጥቁር ገበያ›› እንደሚሸጥ ይታወቃልን? ከእንዲህ ዓይነቱ ወንጀል ሠሪዎች ጋር እየተባበረ (በሐሰት ፈቅደናል አይዟችሁ እያሉ!) በየጊዜው የድርሻቸውን የሚወስዱ የበታች ኃላፊዎች እንዳሉም ሕዝቡ ውስጥ በስፋት ይነገራል፡፡ ያልተነካ ጉዳይ!!
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የግዥ ሙስና
አስተዳደሩ እንደ ስኬት ከሚያነሳቸው ጉዳዮች አንዱ ተዳክመው የነበሩ የሙያ ትምህርት ቤቶችንና አንዳንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት ማድረጉ ነው፡፡ በእነዚህ ተቋማት የሚሠለጥኑ ሙያተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር ራሳቸውን ከድህነት ማውጣታቸውንም ይገልጻል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ግን በከተማዋ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የግዥ ሥርዓት ላይ ጥናት አድርጎ አስገራሚ ውጤት አግኝቷል፡፡
ተቋማቱ በአንድ ላይ አጠቃልለው ሊገዟቸው ለሚችሏቸው የሥልጠና ዕቃዎች ዓመቱን ሙሉ ግዥዎችን ሲያከናውኑ እንደነበር በጥናቱ ማየት ተችሏል፡፡ ይህም ተቋማቱ ሥልጠናቸውን በታቀደላቸው ጊዜ እንዳያከናውኑ፣ ሠልጣኞችም በወቅቱ ሊያገኙ የሚገባቸውን ግንዛቤዎች ሳያገኙ ወደሚቀጥለው ሥልጠና እንዲሸጋገሩ በመደረጉ፣ ትምህርታቸውን እንደሚረሱና በዚህም ብቃታቸው ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ ለዚህ የጥናት ድምዳሜ ማሳያ የሚሆነው ባለፉት አራት ዓመታት የብቃት ማረጋገጫ ከወሰዱ ሠልጣኞች መካከል ከ30 በመቶ የበለጡ ተፈታኞች አለማለፋቸው ነው፡፡ አስተዳደሩ ግን ‹‹ይኼን ያህል ሺሕ ሠለጠኑ›› እንጂ ‹‹ወደቁ›› የሚለውን ሊናገር አይፈልግም፡፡ ወይም ከተሞክሮ መማር ሳይሆን ውድቀት ይመስለዋል፡፡
ጥናቱ በዚህ ብቻ አይቆምም፡፡ ለሚገዙት ዕቃዎች የቴክኒክ ፍላጎት መግለጫ ሳይዘጋጅ መፈጸሙ፣ በግዥ አፈጻጸም መመርያ መሠረት የቴክኒክ ፍላጎት መግለጫ አለመዘጋጀቱ፣ የጨረታ ሥርዓትን ባለመከተል፣ ከጨረታ ኮሚቴ ውጪ በ‹ፕሮሰስ ካውንስል› ውሳኔ በመግዛት፣ በቋሚ ንብረቶች ገቢና ወጪ ሰነዶች ላይ ሴሪያል ቁጥራቸው ሳይመዘገብ ተድበስብሶ ማለፍ፣ ወዘተ ተዘርዝረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በአሥር ሚሊዮኖች የሚገመት የሕዝብ ሀብት ከመዘረፉም በላይ ጥራት በሌላቸው ዕቃዎች ተቋማቱ የመሞላት ዕድላቸው ሰፊ እንደነበር ተነስቷል፡፡ ለዚህም ነው ፀረ ኮሚሽን፣ ‹‹በአስተዳደሩ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኮሌጆች ውስጥ እየታዩ ያሉት የግዥና ንብረት አያያዝ ችግሮች በውስብስብና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኙት፤›› ሲል በአንክሮ የገለጸው፡፡ ይህን ችግር ያጋለጡ ባለሙያዎችና አንዳንድ አመራሮች ከሥራቸው ሲባረሩ በሙስና የተዘፈቁት ሹመት እንደተጨመረላቸው ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡
ስፖንሰርሽፕና ማስታወቂያ እንደ ሙስና ምንጭ
ስፖንሰርሽፕ በማድረግ የሚካሄድ ሥራ ፕሮሞሽን ሲባል ሌሎች ድርጅቶች የሚያዘጋጇቸውን ፕሮግራሞች፣ ሴሚናሮች፣ ዓውደ ጥናቶች፣ የልማት ሥራዎች፣ ስፖርታዊ ክንውኖች፣ የንግድ ትርዒቶች፣ የባዛር ዝግጅቶች፣ ወዘተ ድጋፍ በማድረግ ሥራን ማስተዋወቅ ነው፡፡ ‹‹ይህ በቂ አሠራርና መመርያ የሌለው በልማት ድርጅቶች (ሲቪክ ማኅበራት ድጋፍ የሚደረግባቸው መሥሪያ ቤቶች ጭምር) የግዢ አፈጻጸም መመርያ 001/96 ድንጋጌ የሌለውና ለሙስና የሚያጋልጥ ክፍተት አለው፤›› ይላል ፀረ ሙስና በሌላ ጥናቱ፡፡ በዚህ መሠረት እስከ 40 በመቶ የሚደርሰው የስፖንሰር የማስታወቂያ አሠራር በድርድርና በሙስና የሚፈጸም መሆኑን አረጋግጧል፡፡
በአዲስ አበባ አስተዳደር 26 ሺሕ የሚደርሱ በኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት እንዳሉ ይገመታል፡፡ በዚሁ ችግር ጧሪ ቀባሪ ያጡ አረጋውያንና ለችግር የተጋለጡ ዜጎችም ቁጥራቸው ከዚህ በላይ ነው፡፡ አሁንም ግን በስማቸው የሚመጣ ከፍተኛ ሀብት በስፖንሰርሽፕና ማስታወቂያ ሥራ ይባክናል፡፡
የዘርፉ አንድ ባለሙያ እንደሚያስረዱት፣ የኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ተጠሪነቱ ለአስተዳደሩ በመሆኑ ያለው በጀትና የፋይናንስ ስፋቱ የመንግሥት አሠራር ሊመስል ይችላል፡፡ ይሁንና በዚህ ተቋም በቀጥታ የድጋፍ ደብዳቤ የሚጠይቁ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሁንም በሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ ካለበቂ ጨረታና ውድድር ለስንፖንሰርሽፕ ይከፍላሉ፡፡ የመጽሔትና የሬዲዮ ፕሮግራም አየር ሰዓት ስፖንሰር ከማድረግ አልፎ ለእግር ኳስና ለስፖርት ውድድሮች ሳይቀር ‹‹ኤችአይቪ/ኤድስ ገዳይ በሽታ ነው›› የሚል የተለመደና አሰልቺ ማስታወቂያ ይደበደባል፡፡ በድሆች ስም የገባ ገንዘብ ይወጣል፡፡ ለጥቂቶች ይከፋፈላል ሲል አንዳንድ ማስረጃዎችን ይመዛል፡፡ (ጸሐፊዎች ስሞቹ ለጊዜው አቆይቷቸዋል)፡፡
የአስተዳደሩ ዋና ኦዲተር የሚባል መሥሪያ ቤትን የሚተቹ አንዳንድ ወገኖች የሚያነሱት ቅሬታ ወጣ ባለ መንገድ እንዲህ ዓይነት ክፍያዎችን አለመፈተሹን ነው፡፡ የከተማዋ ሚሊኒየም ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ እስከሚፈርስ የአዲስ አበባ 125ኛ ዓመት አከባበር ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ እስከሚፈርስ የፕሮጀክቱ ማስተባበሪያ በሚሊዮን የሚገመት ሀብት አንቀሳቅሷል፡፡ በሚሊዮን የሚገመት የስፖንሰርና የመስተንግዶ ወጪ ወጥቶ ኦዲት አለመደረጉን ውስጥ አዋቂዎች ያስረዳሉ፡፡ እዚህ ላይ ችግሮች እንደነበሩ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ሳይቀር ጥቆማ የሰጡ ሰዎች ምላሽ ሳያገኙ፣ በነበረው ሁኔታ የተሰላቹ ባለሙያዎች ለአንድ ጋዜጣ የሰጡት አስተያየት ይታወሳል፡፡
‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› ዓይነት የሚዲያ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም
የአዲስ አበባ አስተዳደር የራሱ መገናኛ ብዙኃንና የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ ሲኖሩት በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ የወጣባቸው ግዢ ይፈጽማሉ፡፡ ለምሳሌ የትራንስሚተር አንቴናዎች፣ የኦዲዮ ቪዲዮ ስቱዲዮ ኤዲቲንግ ማሽኖች (ከዝግጅት ክፍሉ አቅም በላይ አለው)፣ የሰርቨርና ግዙፍ የስርጭት ማሽኖች ይጠቀሳሉ፡፡ ኮምፒዩተርና የሬዲዮ ስቱዲዮ ዕቃዎችም ከፍተኛ ገንዘብ የሚወጣባቸው ናቸው፡፡
ግዣቸውም ሆነ የንብረት አያያዙ ግን እጅግ ኋላ ቀርና ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ያስረዳሉ፡፡ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ አንድ የተቋሙ ባለሙያ በባለአደራው አስተዳደር የነበሩ የኤጀንሲው ኃላፊዎች ያዝረከረኩት የንብረት አያያዝ አሁንም ቀጥሏል፡፡ በስፖንሰር የሚገኝ ኮምፒዩተርና ላፕቶፕ እንዲሁም ውድ ቴፖች በመንግሥት ደንብ መሠረት ገቢና ወጪ ሳይደረጉ በግለሰብ እጅ ቀርተዋል፡፡ አንድ የኢንጂነሪንግ መምርያ ኃላፊ ውጭ አገር ከድተው ሲቀሩ በስማቸው የነበረ በርካታ ሀብት የት እንደገባ አይታወቅም፡፡ በእጃቸው የነበሩ በርካታ ፔናክሎችና ኮምፒዩተሮች ሁሉ የጥቂቶች ሲሳይ ሆነዋል በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይህን ችግር ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥቆማ ደርሶት ‹‹ይጣራ!›› ብሎ ለቦርዱ ቢጽፍም ተደባብሶ መቅረቱ ባለሙያውን ያበሳጨዋል፡፡
በመንግሥት ውድ ንብረቶች ግለሰቦች የግል ሥራቸውን እንደሚሠሩም ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና የኦሮሚያ ቲቪ እንኳን የሌሉዋቸው ውድ የኤዲቲንግ ማሽኖችና ካሜራዎች በጥቂት ስግብግብ ባለመያዎች የጨረታ ዶክመንተሪ መሥሪያ፣ ተከታታይ ድራማና ፊልም ማዘጋጃ ሆነዋል ይላሉ፡፡ ችግሩን ተቋሙ ያውቃል፡፡ ቁርጠኛ ሆኖ ዕርምጃ ለመውሰድም ሆነ ሕገወጦችን ለማስቆም ያልቻለው በአስተዳደሩ ያለው በኔትወርክ የተሳሰረ ብልሹ አሠራር ውጤት እንደሆነ በመግለጽ፣ የዶክመንት አያያዙም ቢሆን የተዝረከረከ በመሆኑ ጋዜጠኞች በቀላሉ ምስል የሚያወጡበት፣ በብዙ ድካም የተሠሩ ካሴቶች እየወጡ ግለሰቦች እጅ የሚያድሩበት አሠራር ተመልካች አላገኘም የሚሉ ባለሙያዎች፣ በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ አስተዳደር የተዘጋጁ የቴሌቪዥን ድራማዎች መካከለኛው ምሥራቅ ተሽጠዋል የሚል መረጃ መስማታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በድምሩ ሲታይ የአስተዳድሩ አንዳንድ ቴክኖሎጂ ነክ ጥቆማዎች ብልሹ አሠራርና ሙስና እየቦረቦራቸው ብቻ ሳይሆን ‹‹ከሞኝ ደጃፍ...›› እየሆኑ ነው፡፡
ምን ይደረግ?
አስተዳደሩ የነቀዙ ግንዶችን ሳይቆርጥ አዲስ ‹‹ዛፍ›› ሊያፀድቅ አይቻለውም፡፡ በየቦታው የተዝረከረኩና ጥቂቶችን የሚያደልቡ አሠራሮችና ንብረቶች ካልታረሙ ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ›› የትም አይደርስም፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ሥርዓት በሙስና ላይ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ከአዲስ አበባ የተሻለ ቅርብ አውድማ የለውም፡፡ ነገር ግን ‹‹አለባብሶ›› በማረስ ሕዝቡ ችግር አለበት ያለውን ሁሉ በጅምላ መልሶ በመሾም፣ ሀቀኛና ለሕዝብ የቆሙ አመራሮችን በጥገኞች ‹‹እያስቆረጡ›› መዝለቅ አይቻልም፡፡ ፈተናውም መክበዱ አይቀርም፡፡ ቀሪውን በቀጣዩ ሳምንት እንዳስሰዋለን፡፡
ሙስና የጥፋት ክንዱን ሲሰነዝር ዓይነቱና መጠኑ ይለያይ እንጂ በሁሉም መንግሥታዊ መዋቅር ነው፡፡ ‹‹ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል›› እንዲሉ ሥነ ምግባር የጎደለው፣ ሞራሉ የነጠፈበትና እላፊ ፈላጊ የትም ቢያደርጉት መለቃቀሙ አይቀርም፡፡
በአንድ በኩል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ካለው የአቅም ውስንነት ሁሉም ዘንድ ደርሶ ችግሩን መከታተልና ማጋለጥ አይችልም፡፡ መሬት፣ ገቢና ግዥ ዋነኛ ትኩረቶች ናቸው ማለቱን ልብ ይሏል፡፡ በሌላ በኩል በየመሥሪያ ቤቱ ያሉት የዲስፕሊን ኮሚቴዎችና የሥነ ምግባር መኮንኖች የይስሙላ መሆናቸው ‹‹ተልከስካሹን›› እንዲበዛ አድርጎታል፡፡ የድርጅት መዋቅሩ ‹‹ጠንካራ›› የግምገማ ባህልም እንደ አዲስ አበባ ባሉት አካባቢዎች በኔትወርክና ‹‹በአትንካኝ አልነካህም›› ምክንያት አንድ ቦታ ቆሟል፡፡ በዚህ ረገድ ክልሎች ሳይሻሉ አይቀሩም፡፡
ለሁሉም ወዳነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ ልመለስ፡፡ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ በአዲስ አበባ አስተዳደር የታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ጥናት ተንተርሼ አቅርቤያለሁ፡፡ አንዳንድ የአስተዳደሩ ባለሙያዎችንና ምሁራንን ብቻ ሳይሆን ውስጥ አዋቂ የመረጃ ምንጮቼንም ተጠቅሜ ለመንግሥትና ለሕዝብ ይጠቅማል ያልኩትን አስነብቤያለሁ፡፡ በእርግጥ ‹‹አዲስ ወይን በአሮጌ አቁማዳ›› እንደሚባለው ባይሆንም የአስተዳደሩ አሮጌ ካቢኔ በሽታዎች ከሙስና ባህሪያቸው አኳያ ተንትኛለሁ፡፡ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ሌሎች ምልከታዎችንም እንዳቀርብ ብዙዎች እየጠቆሙኝ ስለሆነ በቀጣይም የምቀጥልበት ይሆናል፡፡
የፊልም ኢንዱስትሪው ‹‹የሙስና ቅርጫት›› መሆን
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም የሚመራቸው አራት ቴአትር ቤቶች (ሀገር ፍቅር፣ ባህል አዳራሽ፣ ወጣቶችና ሕፃናት ቴአትር፣ ራስ ቴአትር) በከተማዋ ቴአትርና ፊልም ያሳያሉ፡፡ በዚህ ላይ በአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ሥር ሦስት ሲኒማ ቤቶች (ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሲኒማ ኢምፔርና አምባሳደር ሲኒማ) ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የሕዝብ ሲኒማ ቤቶች በከተማዋ በየዕለቱ ፊልም፣ በሳምንት እስከ ሦስት ቀናት ቴአትር የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ ታዲያ አንዳንድ የፊልም ፕሮዲዩሰሮች ‹‹አነስተኛ ሙስና መደበኛ ሥራ የሆነባቸው›› ይሏቸዋል መንግሥታዊ ተቋማቱን፡፡ በቅርቡ አስተያየቷን የሰጠችው አርቲስት ሰብለ (እማማ ጨቤ) እንኳን፣ የፊልም ሥራው በየቴአትር ቤቱ ባሉ ግልጽ ሙስና ጠያቂዎች የከፋ ችግር ተደንቅሮበታል ማለቷ አይዘነጋም፡፡
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከወራት በፊት ቴአትር ቤቶችን ያማከለ ግምገማ አካሂዶ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውሱ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ ‹‹የቴአትርና ፊልም ባለሙያዎች በዘመድ ይቀጠራሉ፡፡ ከተቀጠሩም በኋላ በቴአትር ለመሳተፍ ጉቦ ይጠየቃሉ፡፡ ወይም በፆታና ሌላ ጥቅማ ጥቅም አስተዋጽኦ እንዳያደርጉ ይጠበቃል፡፡ አንዳንድ የቴአትር ቤት ኃላፊዎች ከመንግሥታዊ ሥራ ይልቅ በግል ሥራ ተጠምደዋል፡፡ ትልልቅ ኃላፊዎችን ጨምሮ በግል ስቱዲዮዋቸው እየተሯሯጡ የሚሠሩ ሲሆን፣ ከሚሠሯቸው ‘ልማታዊ ዜማዎች’ አኳያ ድርጊታቸው ተጋርዶ ሥራውን ጥለውታል፡፡ ፊልም ለማሳየት ፕሮዲዩሰሮች በጉቦና ኃላፊዎችን ካስት በማድረግ ቅድሚያ ያገኛሉ…›› ዓይነት የግምገማ ጭብጦች ተመዘዋል፡፡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም የየድርሻቸውን ወስደዋል ትላለች አንድ ውስጥ አዋቂ የመረጃ ምንጭ፡፡ አስቂኙ ነገር ግን በተጨባጭ መረጃ ተተንትኖ ብዙዎችን ተስፋ ያስቆረጠው ድርጊታቸው ተጋልጦ ያለምንም ዕርምጃ መሸፋፈኑ ነው፡፡ የራስ መተማመን የሌላቸውና የአቅም ችግር ያለባቸው የቢሮው ኃላፊዎች ችግሩ እንዳለ አምነው፣ ኃላፊዎችን ቴአትር ቤት በማቀያየር ብቻ አዳፍነውት መቅረታቸው ብዙዎችን አስቆጭቷል፡፡
ከሲኒማ ቤቶች ጋር በተያያዘ በከፋ ሁኔታ ተነስቶ የነበረው ችግር የሲኒማ ኢትዮጵያ ወንበር አቀያየር ጉዳይ ነው፡፡ በጨረታ ያሸነፈው ድርጅት ታውቆ ‹‹ዕቃው መናኛ ነው›› በሚል በዋና ሥራ አስኪያጁ የቀጥታ ትዕዛዝ በ700 ሺሕ ብር ልዩነት ከሌላ አቅራቢ ተገዝቷል ይላሉ አንዳንድ ሠራተኞች፡፡
‹‹ይኼ ችግር ትክክል እንዳልሆነና የሙስና ሽታ እንዳለበት ለአስተዳደሩ፣ ለቢሮው እንዲሁም ለሥራ አመራር ቦርዱ ነግረን ፍንጭ ስናጣ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ጠቆምን፤›› የሚሉ የመረጃ ምንጮች፣ ይሁንና እስካሁን ምንም የተገኘ ውጤት ካለመኖሩም በላይ አስተዳደሩ የሴክተሩን ችግር እንደሌለ ቆጥሮ አመራሩን አስቀጥሎታል ሲሉ በቅሬታ ያስረዳሉ፡፡ ሥራ አመራሩ ቦርዱም ቢሆን ችግሩን እያወቀ ዝም ያለው የበሽታው አካል በመሆኑ ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡
በዚህ ሴክተር ያለው የኪራይ ሰብሳቢነት ዝንባሌ ሁለት የከፉ ጉዳዮችን ያስከትላል፡፡ አንደኛው በንፅህና ሠርተው የሚኖሩ ሠራተኞችንና ተገልጋዮችን ተስፋ በማስቆረጥ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሠራርን ያሰፍናል፡፡ ሁለተኛውና ዋነኛው ግን የጥበቡን ዘርፍ አዘቅት የሚከት ነው፡፡ እነሆ ዛሬ ብዙ የተወራለት ፊልም በጥቂት ፕሮዲዩሰሮች፣ በአንድ ዓይነት ገፀ ባህርያትና በሳሎን ታሪክ ተቀራራቢ ጭብጥ በመያዝ እንዳይሆኑ ሆኖ ወድቋል፡፡ በነፀጋዬ ገብረ መድኅንና ወጋየሁ ንጋቱ (ኧረ የቅርቦቹም አሉ) ትልቅ ደረጃ ደርሶ የነበረው የአገራችን ቴአትርም ከባድ ጋኔን ለክፎት ይታያል፡፡ ሙስና የትም ቢሆን አጥፊ ነው ማለት ይህንኑ ነው፡፡ ስለሆነም የሴክተሩ አመራር በማይመለከተው ጉዳይ ሁሉ እየበዘነ ቤቱን የጅብ መንጋ የሚውልበት ከማድረግ ሊጠነቀቅ ይገባል፡፡
የመረጃ ስታንዳርዳይዜሽን ‹‹ካለአቅሙ የተንጠራራ ከተማ››
የአዲስ አበባ አስተዳደር የመረጃ ስታንዳርዳይዜሽን የሚባል መሥሪያ ቤት አቋቁሞ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 590 ለማስተግበር ሲሞክር ብዙዎች ‹‹ጥሩ ጅምር›› ብለውት ነበር፡፡ በተለይ የአስተዳደሩ አንዳንድ ተቋማት ለግሉ ሚዲያ መረጃ በመከልከል የሕዝብን መብት የሚጋፉ በመሆናቸው ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ሥራም ነበር፡፡
ያም ሆኖ መሥሪያ ቤቱ በሙስናና በብልሹ አሠራር ከመዘፈቅ አልዳነም፡፡ መረጃዎች እንደሚያስረዱት በየጊዜው በሚያሳትማቸው ልዩ ልዩ የከተማዋ የሕትመት ውጤቶችን ከማተሚያ ቤት ጋር በመመሳጠር ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎቹ ተባረዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመሥሪያ ቤቱ ያላግባብ ደመወዝ ሲከፈላቸው የነበሩ የሌላ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ተገኝተው ደመወዝ እንዲመልሱ እየተደረገ መሆኑ ይነገራል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች በተቋሙ ውስጥ በተፈጠረው ቡድንተኝነትና አለመግባባት ሥራው የተበታተነው ይህ መሥሪያ ቤት፣ በሚሊዮን የሚገመት የአስተዳደሩ ሀብት ቢመደብለትም እዚህ ግባ የሚባል ተግባር ሊፈጽም አልቻለም፡፡
ትናንት ተመረቁ የተባሉ መጽሔቶች፣ የመረጃ መስጫ ተቋሞችና ቤተ መጻሕፍት የት እንደደረሱ አይታወቅም፡፡ የአዲስ አበባ መረጃ አሰጣጥም ያመጣው ለውጥ የለም የሚሉት ውስጥ አዋቂዎች ኔትወርክና ብልሹ አሠራር እስካለ ድረስ ውጤት ማምጣት አዳጋች መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ የዚሁ መሥሪያ ቤት የኮሙኒኬሽን ቢሮ የውስጥ ኦዲት ኃላፊ የነበረው ባለሙያ እንዴት ተባረረ? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
የትምህርት ሴክተሩ ልክፍቶች
በከተማው በተለያዩ ገጽታዎች የሚንፀባረቁ ቡድነኝነትና ኔትወርክ የብልሹ አሠራር መገለጫዎች ናቸው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ምልክቶችን መጠቃቀስ የችግሩን ውስብስብ ባህሪ ለማሳየት ይረዳል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በዚህ ልክፍት ከሚታወቁ ተቋማት ቀዳሚው ነው፡፡ ኃላፊዎች በሽሚያ መልክ የአካባቢ ሰዎችን መሰብሰብና ለግል ኔትወርክ ምቹ የማድረግ ሥራ ላይ ይጠመዳሉ፡፡ በእርግጥ በዚህ ችግር የአንድ ሌላ ቢሮ ኃላፊም ክፉኛ ሲወቀሱ ከርመው አሁን ጠንካራ አመራር ተብለው በዚያው መቀጠላቸው፣ እውን ድርጅቱ የቀድሞዋ መርሁን ጠብቆ እየተጓዘ ነውን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
ወደተነሳሁበት የትምህርት ቢሮ የሙስና ‹‹ገበያዎች›› ላምራ፡፡ የመሥሪያ ቤቱ አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት አንዱ የሴክተሩ መደራደሪያ የአዲስ አበባ የትምህርት ኢንቨስትመንት መስጫና የሱፐርቪዥን መከታተያ ነው፡፡
በከተማዋ እንደ ድንችና ሽንኩርት መሸጫ ጉልት በየመንደሩ የሚኮለኮሉ መዋዕለ ሕፃናት የወጣላቸው ስታንዳርድ ውኃ በልቶታል፡፡ እንደፈለጉ ክፍያ እየቆለሉ ሕዝቡን በማስመረር ገንዘብ የሚሰበስቡት በምን ይመስላችኋል? የሚሉ ባለሙያዎች፣ በአንዳንድ አመራሮችና ይኼን ሥራ የሚያከናውኑ ባለሙያዎች በሙስና መደለል (አንዳንዶች ቆብ የሚጣልላቸው እንዳሉም ይነገራል) የሕዝቡን ጥቅም አሳልፈው እየሰጡ ነው ይላሉ፡፡
‹‹ትምህርት ቾክ እንጂ ሙስና የለበትም›› በሚል የአንዳንዶች ማሳሳቻ የተሸፈነው ይህ ሴክተር፣ በከተማዋ ከብቃት ምዘና ጋር ያለው የጎላ ሙስና የሚስተናገድበት ነው፡፡ በቢሮው ሥር የሚገኘው የብቃትና ምዘና ኤጀንሲ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር የምሩቃንን ምዘና ይሠራል፡፡ ይሁንና ፈተናውን ተፈትኖ ለማለፍ የምዘና ኮሚቴው፣ የኤጀንሲው አንዳንድ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ባለሙያዎች በእጅ መንሻና በጉቦ የሥነ ምግባር ጥሰት ይፈጸማል፡፡
አንድ አስተያየት ሰጪ እንደገለጹልኝ ለምሳሌ በነርሲንግ ወይም በላብራቶሪ የሲኦሲ ምዘናን ለማለፍ ከኤጀንሲው ወይም ይህን ፈተና ከሚመሩ ከጤና ቢሮ ሰዎች ጋር መተዋወቅና መዛመድ ያስፈልጋል፡፡ ወይም ይህን ጉዳይ በሚያስፈጽሙ ጉቦ አቀባባዮች በኩል እስከ ሁለት ሺሕ ብር ክፍያ መፈጸምና የፈተናውን ሚስጥር ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ይህ እውነት በሌሎች ታዛቢዎች በኩልም ተረጋግጧል፡፡
በአንድ ወቅት ይኼ ችግር እየተባባሰ መምጣቱን በጥያቄ መልክ የቀረበላቸው የኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ የምዘና ሥርዓቱ በአገራችን አዲስ እንደመሆኑ አንዳንድ ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ጠንካራ አሠራር ይዘረጋለታል ነበር ያሉት፡፡ ይሁንና የአነስተኛ ሙስና ባህሪ የያዘው ይህ ጉዳይ አድማሱን እያሰፋ የብዙዎችን እምነት ያጣ ‹‹የዘመድ ቤት›› አድርጎታል ተቋሙን፡፡ ይኼ አንድና ሁለት ሰዎች የሚሉት ሳይሆን ብዙዎች የሚጋሩት ነው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በከፍተኛ ትኩረት እያስገነባቸው ያሉ የትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ ግንባታዎችንም ‹‹ኦዲት የማያውቃቸው የሩጫ ተግባራት›› የሚሉ አልታጡም፡፡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በውስጥ ገቢና ከደጋፊ አካላት በሚገኝ ገንዘብ፣ አንዳንዶች ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ በሚመድበው በጀት አነስተኛና ከፍተኛ ግንባታና የትምህርት ሴክተር ልማቶች ይከናወናሉ፡፡ ይኼ በጎና ውጤት ያስገኘ ሥራ ቢሆንም፣ የሕዝቡ የገንዘብና የጉልበት መዋጮ የታከለበት ነው፡፡ ነገር ግን ትምህርት ቢሮው ያለውን ሀብት ለይቶ፣ የወጣና የገባውን በመከታተል ረገድ ክፍተት እንዳለበት ይነገራል፡፡ የከተማው የፋይናንስ ቢሮ የኦዲትና የክትትል ሥርዓትም አነስተኛ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ እንጂ ከፍ ያሉ ፕሮጀክቶችን በጎን የሚያልፍ ነው ሲሉ ባለሙያዎች ይተቻሉ፡፡
‹‹አንዳንድ የትምህርት ቢሮው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ንግድን ጨምሮ በግል ሥራ የመጠመዳቸው ሚስጥርስ ምን ይሆን?›› የሚሉት ተቺዎች ጠንካራ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለበት አሠራር የመንግሥትንና የሕዝብን ኃላፊነት መቀበል ‹‹የማይነጥፍ ላም ማለብ›› እንዳይሆን ነው የሚጠረጥሩት፡፡ ሴክተሩ በየዓመቱ የሚያከብራቸው ትልልቅ ፌስቲቫሎችንና ዓመታዊ በዓሎችን፣ የውጭ ጉዞዎችንና ውጤት አልባ ምልልሶችን በአግባቡ በመፈተሽ ተቋሙ የተንጋደደ ጉዞው ይቃና ዘንድ መሥራት እንደሚገባው ነው የሚገለጸው፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ትምህርት የተዳረሰባት ከተማ ብትሆንም፣ ጥራቱ አደጋ ላይ የወደቀ መሆኑን ያላጤነ መዋቅር መሆኑንም በማንሳት፡፡
አዲስ አበባን የሚቆጣጠረው ማን ነው?
ባለፉት ሁለት ጽሑፎች በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች የሚታየውን ችግሮች ለማመልከት ተሞክሯል፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ በአስተዳደሩ ጭምር የሚታወቁና የድርጅት ጽሕፈት ቤቱም በየጊዜው ግምገማ ሲቀመጥ የሚያነሳቸው ናቸው ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ ግን ከዓመት ዓመት ለምን ለውጥ አይመጣም? ሲባባስ እንጂ ሲሻሻል የማይታየውስ ለምንድን ነው? ከተማዋ በጀመረችው ፈጣን ልማት እየተሸፈነ፣ የጥቂቶች ሕገወጥ የመበልፀጊያ መንገድ የማይዘጋውስ ምክንያቱ ምንድነው? ሲሉ የሚጠይቁ ብዙ ናቸው፡፡
ለዚህ ችግር መባባስ ዋነኛው ተጠያቂ ‹‹የትግል መታጣትና የቁርጠኝነት መጓደል›› እንደሆነ ይነገራል፡፡ አብዛኛው የሥራ ኃላፊ በጥቅምና በልዩ ልዩ የትስስር ገጽታዎች የተያያዘ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም የሙስና ገበያውን ገለጥለጥ አድርጎ ንፋስ እንዲመታው ከማድረግ ይልቅ እየተድበሰበሰና እየታከከ እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ነው አዲሱ የድሪባ ኩማ አስተዳደር፣ የቀድሞውን አመራር እንዳለ ተሸክሞ ሊሄድ የቻለው የሚሉም አሉ፡፡
በአዲስ አበባ ሥር ነቀል ለውጥና የሕዝቡን ሙሉ እምነት ያገኘ አመራር ለመፍጠር አሁንም ጊዜው አይመሽም፡፡ አስተዳደሩ ችግሮቹን ይፈትሽ፣ የድርጅት ጽሕፈት ቤቱም ውስጡን ይመልከት፡፡ ‹‹ያወራ ሁሉ ሀቀኛ አይደለም›› የሚለውን የቻይና አባባል ያስታውስ፡፡ ደጋፊዎቹ በሚገኙበት ስብሰባ የሚባለውን አድምጦ የሕዝብ አስተያየት አድርጎ መውሰዱን ይተው፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ነችና፡፡
በአማኑኤል ነጋ ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው amanualN@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment