Saturday, August 31, 2013

የሃገራችንን ህልውና የሕዝባችንን ነፃነት እናስመልስ!!!

የሃገራችንን ህልውና የሕዝባችንን ነፃነት እናስመልስ!!! – ከኤደን መስፍን(ኖርዌይ) August 29th, 2013 ለአንድ ህዝብ ሃገር ማለት የመኖር ዋስትናው ተጠብቆ ሳይሸማቀቅ፣ ሳይበደል፣ ፍትህ ሳዩጓደል፣ የዜግነት መብቱ ተጠብቆ የህግ ከለላ አግኝቶ በነፃነት የሚኖርብት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን ሃገር መሆን ከተሳናት እንሆ ሃያ ሁለት አመት ተቆጠረ፡፡ የደርግ ስርዓትን ተክቶ በትጥቅ ትግል መንበሩን የተቆናጠጠው የወያኔ ዘረኛ ቡድን ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ የፖለቲካ ስልጣኑንም ሆነ የኤኮኖሚ አውታሩን በአንድ ብሄር ብቻ አደራጅቶ የተቀረውን ኢትዮጵያዊ እንደ ዜጋ የመኖር መብቱን ገፎ በግዞት ያኖረዋል፡፡ ይህ ፈላጭ ቆራጭ ግፈኛ ብድን ሰብአዊ መብት አለማክብሩ ብቻ ሳይሆን ሃገርን የማፍረስ ጭምር አላማና ተልኮ ስላለው የሚፈልገውን ለማድረግ ማንም ምንም ተቃውሞና ትችት እንዲያቀርብለት አይፈልግም፡፡ ስለሆነም በሃገሪቱ ባለው ህገ -መንግስት፣ ያውም እራሱ ባፀደቀው መሰረት የሚንቅሳቅሱ ኢትዮጵያዊያን የሲቪክ ማህበራት፣ የነፃው መገናኛ ብዙሃን አባላት፣ የዴሞክራሲ ተሟጋቾችን፣ የሰብአዊ መብት ታጋዮችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እነዚህንና ሌላውን ንጹሃን ዜጎችን ሳይቀር እያዋከበና እያሳደደ ገሚሱን ስም እያወጣ ወህኒ ሲያጉር ከፊሉን ደግሞ በሃገራቸው የመኖር መብት ነስቶ እንዲስደዱ ያደርጋል፡፡ 1997 ዓ.ም በጭላንጭል የታየውን የመደራጀት መብት ተጠቅመው ህዝብን ያደራጁና በኋላም በምርጫው የህዝብ ይሁንታ አግኝተው በካርድ የተመረጡ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይህው ፈላጭ ቆራጭ ቡድን በማን አለብኝነት አለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚያውቀውን ውጤት ለውጦ እስካሁን ድረስ ባልመረጠው ህዝብ ጫንቃ ላይ ተፈናጧል፡፡ በወቅቱም ሽንፈቱን ላለመበቀል በመቶዎች የሚቆጠሩትን በጠራራ ፀሃይ ሲገድል፣ አስር ሺዎችን ወደ ማጎሪያ ማጋዛቸው፣ መደብደባቸው፣የተቀሩት ማሳደዳቸው አለም የሚያቀው እውነታ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ያየውን መከራና ፍዳ ቅን የሆኑ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ምስክር ናቸው፡፡ይህ አምባገነን ቡድን ህዝቡን አፍኖ፣ አሸማቆና አንገት አስደፍቶ የሄደበት የአፈና መዋቅር 2005ዓ.ም ላደረገው የይስሙላ ምርጫ ጉልበት ሆኖት ዘርፎም፣ አታሎም፣አጭበርብሮም 99.6% አሸነፍኩ ሲል መደመጡ ብዙዎችን ያስገረም ጉዳይ ነበር፡፡ የህዝብን የነፃነት ጥያቄን ለማፈን በተለይም በሰሜን አፍሪካ ከአረቡ አብዮት ጋር በተያያዘ ህዝብ ይነሳብኛል ብሎ የሰጋው የወያኔ ቡድን የተለያዩ አፋኝ ህጎች ሲያወጣ ከርሟል፡፡ ከዚህም አንዱ የፀረ-አሸባሪ ህግ ነው፡፡በዚህ ህግ ብዙሃን የነፃነት ታጋዮች ከሞት እስከ እድሜ ይፍታህ ተፈዶባቸዋል ፡ይተቀሩትም የህሊና እስረኞች አሁን ባለንበት ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በየቀኑ የሚገደሉባት፣የሚደበደቡባት ቶርች የሚደረጉባት ስብእናቸው እየተዋረደ በዘራቸው የሚሰደቡበት በተለያዩ ቦታዎች ታጉረውና ያለፍርድ ተረስተው የሚገኙባት በአጠቃላይ ለፍትህ እና ለነፃነት ለሚታገሉ ንፁሃን ዜጎች የምድር ሲኦል የሆነች ሃገር አርገዋታል፡፡ ገዥው ብድን የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ የህዝብን የማወቅ መብት መገደብና እሱ ከሚለው ውጪ ምንም እንዳይሰማ፣ እንዳያይ አማራጭ የመገናኛ ብዙሃንን ማፈን ትልቅ ስራ አድርጎታል፡፡ ስለዚህም ለአገዛዙ እንዲመቸው ለ90 ሚሊዮን ህዝብ አንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ አንድ ሬድዮና፣ አንድ በሁለት ቋንቋ የሚታተም ጋዜጣ ብቻ በዚህ ዘመን አለም በመረጃ መረብ በተጥለቀለቀችበት ጊዜ ከራሱ ውጪ ለህዝብና ለሃገር ደንታ የሌለው አምባገነን መንግስት ሌሎች አማራጮችን ዘግቷል፡፡ ከዚህ ሁሉ የወያኔ አፈናና ግፍ በኋላ ቢዘገይም(ቢረፍድም) በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከተደራጁ ለቁጥር ከሚታክቱ ድርጅቶች ውስጥ የሃገሪቱ ህገ-መንግስት በሚፈቅደው መብታቸውን ተጠቅመው ህዝብን በንቃት በማደራጀት ትግላቸውን እያፋፋሙ ያሉት ሰማያዊ ፓርቲና አንድነት የወያኔ የእግር እሳት እየሆኑ በት እንዳለ ሰሞኑን በተለያዩ የሃገራችን ክልሎች እየሆነ ያለውን እልህ አስጨራሽ ትግል እያየን ነው፡፡ ይህ ሲጀመር በሰማያዊ ቀጥሎም በአንድነት ፓርቲ የተጀመረው ፍርሃትን የሰበረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ዘርኛውን የወያኔ ስርዓት ምን ያህል እርቃኑን እንዳስቀረውና ኢትዮጲያን እየመራ ያለው ስርዓት ለህግ ተገዢ እንዳልሆነ ፍንትው አርጎ ያሳየን አጋጣሚ ነው፡፡ የመንግስት ስልጣን ብቻ ሳይሆን በዘረፋ ያካበቱትን ሃብትና ንብረት ለማስጠበቅ ፍጹም ስርዓት በጎደለው መልኩ የእውር ድንብራቸውን የሚወራጩት የወያኔ ካድሬዎች ላለቆቻቸው ለመታመን ንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሱ ያሉት ወከባና እንግልት የስርዓቱን ሃላፊነት የጎደለው ተራ የውንብድና ተግባር ያሳያል፡፡ ስለሆነም ሁል ጊዜ ስለበደላችን፣ በሃገራችን ህልውና ላይ እያንዣበበ ስላለው አደጋ ስንተርክና ስንቆዝም አንድም ጠብ የሚል ነገር ሳይገኝ ሁለት አስር አመታት ተቆጠረ፡፡ ጊዜው የተግባር ነው አሁን ያለውን የህዝባችንን ለነፃነቱ፣ ለመብቱ ለትግል መነቃቃት፣ የወያኔና መዝረክረክና በእቅድ ሳየሆን በግምት መዳከርን ከግምት በማስገባት ልዩነታችንን አቻችለን በአንድነት በኢትዮጲያዊ ጥላ ስር ተከልለን ለለውጥ እንነሳ፡፡ ከፍርሃት ድባብ ወጥተን በውስጥም በውጪም ካሉት ጠንካራ ድርጅቶች ጎን በምቆም የሃገራችንን ህልውና የህዝባችንን ነፃንት እናስመልስ፡፡ ኢትዮጲያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

1 comment:

  1. አሳስባለው https://www.penpaland.com ቋንቋ ልውውጥ ላይ የተመሠረተ ድር ጣቢያ
    Android:http://app.appsgeyser.com/Penpaland

    ReplyDelete