Tuesday, August 27, 2013

ኢ/ር ተስፋሁን ጨመዳ በእስር ቤት ውስጥ ህይወቱ አለፈ

ኢ/ር ተስፋሁን ጨመዳ በእስር ቤት ውስጥ ህይወቱ አለፈ ነሃሴ ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለኦሮሞ ህዝብ መብት በመታገል ላይ የነበረው የ37 ዓመቱ ወጣት ኢ/ር ተስፋሁን ጨመዳ ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ እንዳለ መሞቱ ታውቋል። ኢ/ሩ በምን ምክንያት እንደሞተ ግን አልታወቀም። ከጓደኞቹ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢ/ር ተስፋሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ከነበረበት ጌዜ ጀምሮ ገዢውን ፓርቲ ይቃወም ነበር። ኢ/ር ተስፋሁን ኬንያ በነበረበት ወቅት ምንም እንኳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና ቢኖረውም በኬንያ የደህንነት ሰራተኞች ታፍኖ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ በመሰጠቱ በመንግስት ግልበጣ ወንጀልና ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለው በሚል ተከሶ ያለፉትን 6 አመታት በቃሊቲ እስር ቤት ካሳለፈ በሁዋላ በመጨረሻም ህይወቱ አልፎአል። ገና በልጅነቱ እናቱን ያጣው ተስፋሁን ከደሀ ቤተሰቦች ቢወለድም አላማውን በማስቀደም ለነጻነቱ አስፈላጊውን መስዋት ይከፍል እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ይናገራሉ። የተስፋሁን አስከሬን በምስራቅ ወለጋ ዞን ጉድሩ ወረዳ ሀርቡ ቀበሌ መላኩን ለማወቅ ተችሎአል። ኢሳት ለኢ/ር ተስፋሁን ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል።

No comments:

Post a Comment