To breathe Democracy in Ethiopia , lets us fight together for our Freedom and Justice !!!!!
Saturday, August 24, 2013
Saturday, August 24, 2013 የአቶ መለስ ሞት እና ጥቅማጥቅሞቹ፤ ስላቅ እና ሀቅ
Saturday, August 24, 2013
የአቶ መለስ ሞት እና ጥቅማጥቅሞቹ፤ ስላቅ እና ሀቅ
ከአቤ ቶክቻው
የአቶ መለስ ሞት እና ጥቅማጥቅሞቹ፤ ስላቅ እና ሀቅ
2012-03-02t171851z_319859376_gm1e83303nh01_rtrmadp_3_kenyaሰላም ወዳጄ… ተጠፋፍተናል ግዴለም እቅ….ፍ አድርጌ ሰላም ልበልዎት… እንዴት አሉልኝ.. እኔ የምለው አቶ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሞቱ እንደዋዛ አንድ አመት ሞላቸው አይደለም እንዴ… ወይ ጉድ ጊዜው እንዴት ይሮጣል ጃል… ምን እንደሚያመጣልን እንጃለቱ፤ አሯሯጡ ግን ወርቅ በወርቅ እንደሚያንበሻብሽ አትሌት ነው፡፡ ይሁና እኛ እንደሆነ “በርታ ግፋ” እያልን ከመደገፍ ወደ ኋላ አንልም… አረ እንደውም ጊዜ ሆይ፤ …ሩጥልኝ ልጄ አምልጠልኝ ልጄ ቁጭ ብሎ መጠበቅ ለኔውም አልበጄ… ብለን እንደ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ እንቀኛለን፤
እናልዎ ወዳጄ ዛሬ የመጣው ይምጣ ብዬ ሙት ወቃሽ አታድርገኝም ሳልል የአቶ መለስ መሞት ለሰፊው ህዝብም፣ ሰፊ መሆን ለተሳነው ኢህአዴግም፣ መጠን አልባ ለሆኑት ተቃዋሚዎችም በጣም ስንሳለቅ ደግሞ ለወይዘሮ ሀዜብ ሳይቀር በርካታ ጥቅማጥቅሞች አሉት ብዬ ልሟገትልዎ ነው…!
በ22 ዓመት ውስጥ ያየናቸው አቶ መለስ እንደው ዝም ብለው የእነ ስምሃል አባት እንደው ዝም ብለው የነ ወይዘሮ አዜብ ባለቤት እንደው ዝም ብለው የአቶ ዜናዊ አስረስ ልጅ ብቻ አልነበሩም፡፡ አቶ መለስ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ኢህአዴግ ሊቀመንበር ከዛም ውስጥ ደግሞ እጅግ አደገኛ የሚባለው ህውሃት አባወራ የሀገሪቱ ጦር ሃይሎቹ አዛዥ (አሃ ለካስ ጦር ሃይሎች የድሮው ነው… እንደው የድሮ ስርዓት ናፋቂ የሆንኩ ሰውዬ… አሁን መከላከያ ነው ማለት ያለብን… በመከላከያው ውስጥ ጦር አለ ከተባለ እንኳ ጦሩ አቶ መለስ ነበሩ… ስለዚህ የጦር ሃይሎች አዛዥ ሳይሆኑ በመከላከያ ውስጥ ጦር የሆኑ ሰውዬ ነበሩ ብሎ አለመመስከር ጡር ነው… ) በጥቅሉ ሰውዬው የመላዋ ኢትዮጵያ ፈላጭ ቆራጭ ነበሩ፡፡
አሁን እኒህ ሰውዬ ሞተዋል… እስቲ ከተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ጋር አያይዘን የሞታቸውን ጥቅማ ጥቅሞች እንዘርዝር…
ለአባይ ግድብ ሲሉ አቶ መለስ እንኳን ሞቱ!
አባይን አቶ መለስ እንዴት እንዴት ይገደብ ብለ
ው እንደጀመሩት ተነጋግረን ተነጋግረን መቼም ከስምምነት ላይ የደረስን መስለኛል፡፡ አባይዬ ድንገት ያለ ዕቅድ… ያቺ እነ ሙባረክን እንደ ሾላ ፍሬ ርግፍ ርግፍ ያደረገች አብዮት ወደ እኛም ትመጣ ይሆናል… በሚል ስጋት ነው ለማስቀየሻ ተብላ ነው የተጀመረችው፡፡
ለዚህ ዋና ማስረጃ በአምስት አመቱ ትራስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ አለመፃፏ ሲሆን ሌላው ደግሞ የፕሮጀክቷ ስም አሁንም አሁንም መቀያየሩ ድሮውንም ቃሚዎች “በምርቃና” እንደሚሉት አይነት የታሰበች ድንገቴ ስራ መሆኗን ያሳብቃል፡፡ በነገራችን ላይ አሁንም ጭምር በተለይ ውጪ ሀገር የሚኖሩ “የኢህአዴግ ወጣት ክንፎች” የአባይን ግድብ “ሚሊንየም ዳም” ነው የሚሏት…! ህዳሴ መባሏን ከነጭርሹም አለሰሙም!
የሆነው ሆኖ አባይን አቶ መለስ ድንገት እንደጀመሯት ሁሉ ድነገት ያቋርጧታል የሚል ስጋት ሰቅዞ የያዛቸው ብዙዎች ነበሩ… (ብዙዎች ያልኩት አካብዶ ለማውራት እንዲመቸኝ ብዬ እንጂ… እንዲህ የሚያስቡት ምን ያህል ብዙ እንደሆኑ ስታስቲክስ አልሰራሁም፡፡ ነገር ግን ያናገርኳቸው ሁሉ የሰጡኝ ማብራሪያ አሳማኝ ነበር፡፡) እንደሚታወቀው አባይን ለመገደብ የሚጠይቀው የገንዘብ አቅም ቀላል አይደለም፡፡ በየመስሪያቤቱ በጥፊም በርግጫም የሚደረገው መዋጮ አስከምን ድረስ እንደሚያስኬድ የሚያውቁት እርሳቸው ብቻ ነበሩ… እናም የሆነ ቀን የሆነ ቀን ማጣፊያው ያጠራቸው ቀን መለኛው መሌ በሆነ መላ ግንባታው እንዲቋረጥ ያደርጉ ነበር የሚለው ነገር ውሃ የሚያነሳ ሆኖ አግኝቼዋለሁ… ይህንን እያንሰላሰልን ታድያ ምን ይበጃል እያልን ስንጨነቅ አቶ መለስ ሞቱ… ለአባይ ሲባልስ እንኳን ሞቱ! ልክ እርሳቸው ሲሞቱ ሌጋሲን ማስቀጠል በሚለው መርህ ከዋናዎቹ አንዱ አባይ ግድብ አይቋረጥም የሚለው ሆነ፡፡ እሰይ እንኳንም አልተቋረጠ፡፡ እንኳንም ሞቱልን…!
ለተቃዋሚዎች ሲባል አቶ መለስ እንኳን ሞቱ!
ተቃዋሚዎች በተለያየ ጊዜ ኢህአዴግን ሲቃወሙ ከሁሉ በላይ የሚበረታባቸው የአቶ መለስ ግልምጫ ሽሙጥ እና እርምጃ ነበር፡፡ ሲያሻቸው ጣት እንቆርጣለን እያሉ ሲያሰኛቸው ሰብስበው እስርቤት እየላኩ አቶ መለስ ተቃዋሚዎች ላይ እንደሚጨክኑት ኢህአዴግ አይጨክንባቸውም፡፡ እውነቱን እንበለው ካልን ደግሞ መጨከን ብቻም ሳይሆን በፖለቲካው ቼዝም አቶ መለስን ተቃዋሚዎቹ አይችሏቸውም ነበር፡፡ ተቃዋሚዎቹ ፈረሳቸውን ቆስቁሰው ገና “ቼ…” ብለው ሮጥ ሮጥ ማለት ሲጀምሩ መለስ በወታደሮቻቸው ፈረሶቻቸውን እየሰነከሉ፤ ንግስታቸውን “ቼዝ” እያሉ ተቃዋሚዎቹን መላወሻ አሳጥተዋቸው ነበር፡፡
አሁን አቶ መለስ ሞተውላቸዋል፡፡ ተቃዋሚዎች መቼም ጨካኞች እንዳይባሉ ሰግተው በአቶ መለስ ሞት ሀዘናቸውን ሲገልፁ ቢሰማም ውስጥ ውስጡን ግን እሰይ ግልግል እንደሚሉ ማወቅ አያቅተንም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ተቃዋሚዎቹ ትንሽ ጠንከር ካሉ ኢህአዴግ ውስጥ ክፉኛ የሚገዳደራቸው አለ ብሎ ማመን ይቸግራል፡፡ ስለዚህም ለተቃዋሚዎች ሲባል አቶ መለስ እንኳን ሞቱ!
ለራሱ ለኢህአዴግ ሲባል አቶ መለስ እንኳን ሞቱ!
በተለይ ከሆነ ጊዜ በኋላ ይመስለኛል ህውሃት ለሁለት ቃቃቃ…ቃ ብሎ ከተሰነጠቀ ጊዜ በኋላ የኢህአዴግ ስብዕና ኮስምኖ የአቶ መለስ ዜናዊ ስብዕና ደግሞ እጅግ በጣም የጎላበት ወቅት ነበር፡፡ አረ ከነጭርሹ መለስ ከልለውን ኢህአዴግን ማየት ተስኖን ነበር…! በዛ አያያዙ ጥቂት አመታት ቢገፉ ኖሮ ኢህአዴግዬ መለስ በተባለ ቅብ ተሸፍና እሰከመፈጠሯም እንረሳት ነበር፡፡
አሁን ግን መለስ ሞቱ ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲም ምን አይነት ቅርጽ እና መልክ እንዳለው ሊታወቅ በቃ፡፡ ታድያ ለኢህአዴግ ሲባል ቅርፀ ግንባሯ እንዲታይ ሲባል፤ ያለ መለስ መኖር እንደምትችል ለማሳየት ሲባል፣ እንኳን መለስ ሞቱላት ብንል ምን ግፍ ተናገርን ይባላል፡፡
ወላ ለወይዘሮ አዜብ ሲባል አቶ መለስ እንኳን ሞቱ!
መጣች ስላቋ… ወይዘሮ አዜብ ቀላል ክብሮ ሆኑ እንዴ…! ክብሮ ማለት አራዶቹ ከበረ ከሚለው አማርኛ ቃል የወሰዷት ስትሆን የተከበረ ለሚባል ሰው የሚሰጥ ማዕረግ ነው፡፡ አዎ ወሮ አዜብ ክብሮ ሆነዋል፡፡ የመለስ ፋውንዴሽን ፕረዘዳንትነት አቶ መለስ ባይሞቱ ኖሮ ከየት ይመጣ ነበር… አረ እንኳን ሞቱላቸው… (እዝችጋ እንኳ ጨክኛለሁ ይቅር ይበለኝ!) የምር ግን ወይዘሮ አዜብ እንደልቸው መልካም ገፅታቸውን እንዲገነቡ የአቶ መለስ ሞት ትልቅ እድል ሰጥቷቸዋል ብዬ አምናለሁ… ዝም ብለን ከመረመርን ወይዘሮ አዜብ በአቶ መለስ ሞት ጉዳት እንደገጠማቸው ሁላ በርካታ ትቅማጥቅሞችንም እንዳገኙ ግን መጠርጠር አያቅተንም!
ለችግኝ ተከላ ሲባል አቶ መለስ እንኳን ሞቱ!
አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት ዘመናቸው እና በበትረ ስልጣናቸው ጊዜ ሰዎች አጥብቀው የሚያማርሯቸው በችግር ተከላ ነበር፡፡ አሁን ግን ሞቱ፣ አመትም ሞላቸው በስማቸውም በርካታ ችግኞች እየተተከሉላቸው ነው፡፡ በእውኑ ለእነዚህ ችግኞች ሲባል አቶ መለስ እንኳን ሞቱ ብንል ማነው እርኩስ የሚለን…! ማንም!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment