Saturday, August 3, 2013

በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች አለመረጋጋት እየታየ ነው

ሐምሌ ፳፮(ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌደራል ፖሊስ አባላት በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች በብዛት መታየታቸውን ተከትሎ በከተሞች የሚታየው አለመረጋጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ዘጋቢዎቻችን ገልጸዋል። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘወትር አርብ የሚደረገውን የጁመአ ስግደት አስታኮ የተቃውሞ ድምጹን የሚያሰማ ከሆነ እርምጃ እንደሚወስድ መዛቱ ይታወቃል። የፖሊስን መግለጫ ተከትሎ የድምጻችን ይሰማ አመራሮች ሌሊቱን የተቃውሞ መርሀግብሩን መሰረዛቸውን አስታውቀዋል። ይህም ሆኖ የፌደራል ፖሊስ አባላት ዛሬ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በብዛት በመሰማራት የስነልቦና ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይተዋል። በአዲስ አበባ ፍልውሀ አካባቢ የተወሰኑ ሙስሊም ወጣቶች በፖሊሶች ተደብድበው የታሰሩ ሲሆን፣ ከሮመዳን ጾም ፍቺ በፊት ተቃውሞውን ያስተባብራሉ የተባሉትን ወጣቶች በብዛት የማሰር እንቅስቃሴ እንደሚጀመር የደረሰን ዜና ያመለክታል። ከሙስሊሙ እንቅስቃሴ በተጨማሪ አንድነት ፓርቲ በባህርዳር፣ አርባምንጭ፣ ጅንካና መቀሌ ከተሞች የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ እንዲሁም በወላይታ ሶዶ የተጠራው የቤት ውስጥ ስብሰባ ውጥረቱን ጨምሮታል። በባህርዳር፣ በመቀሌና በጅንካ የአንድነት አመራሮች የሚደረስባቸው እንግልት፣ በባህርዳር የኢህአዴግ ካድሬዎች ሰፈር ለሰፈር እየዞሩ በሰልፉ ላይ የሚገኙትን በካሜራ ይቀረጻል የሚል መልእክት ማስተላለፍ መጀመራቸው እንዲሁም በጅንካ የዞኑና የወረዳው አመራሮች የሚፈጥሩት ጫና ውጥረቱን እንዳባባሰው በስፍራው የተገኙ ዘጋቢዎች ከሚልኩት ዘገባ ለመረዳት ይቻላል። በመቀሌ ታስረው የነበሩ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ዛሬ ሲለቀቁ፣ በባህርዳር ደግሞ ከኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት ፈቃድ ካላመታችሁ በስተቀር ቅስቀሳ አታደርጉም የተባሉ የፓርቲው አመራሮች ዛሬ ጧት ፈቃድ ለማግኘት በስፍራው ተገኝተዋል። ከባህርዳር የደረሰን መረጃ እንዳመለከተው ፓርቲው በከተማዋ በርካታ ወረቀቶችን በትኖአል።

No comments:

Post a Comment